እንደሚታወቀው ከቅርብ ቀናት በፊት ከመስከረም 4 ጀምሮ የሚሰጠውን የመምህራን ስልጠና በምን መልኩ ወደ ተቃውሞ መድረክ መቀየር እንደምንችል መምህራኖችን መጠየቃችን ይታወሳል። መምህራኖችም ግልፅ በሆነ ቋንቋ ሀሳባቸውን ገልፀውልናል። ለዚህም ልናመሰግናቸው እንወዳለን። እኛም ሀሳባቸውን ጨምቀን አቅርበናል። ከዛ በፊት ግን ይህንን ስብሰባ መቃወም ለምን እንደሚያስፈልግ መግለፁ ተገቢ ነው።
1) ይህ ስብሰባ መምህራን ሙያቸውን የሚያሻሽሉበት ሳይሆን ገዥው ፖርቲ የራሱን ፕሮፖጋንዳ የሚነዛበት የፖለቲካ መድረክ ነው። ይህንን ደግሞ ከዚህ በፊት ከነበረው ልምድና ለስልጠናው ከተዘጋጁት ማኑዋሎች መረዳት ይቻላል። ስለዚህ ከዚህ ስልጠና ለመማር ማስተማሩ ሂደት የሚጠቅም አንዳች ነገር አይኖርም።
2) ወያኔ የሀገሪቱን የፖለቲካ ቀዉስ በውይይት ሳይሆን በመሳሪያ ለመፍታት ወስኗል። ይህንን ምርጫም በ10 ወር ዉስጥ ከ1000 የሚበልጡ ንፁሀን ዜጎችን በመግደልና የወያኔ ቱባ ባለስልጣናት በሚያሰሙት ፉከራ አረጋግጠዋል። ስለዚህ ከዚህ የመምህራን ስብሰባ የሀገሪቱን የፖለቲካ ቀዉስ ለመፍታት የሚያስችል ነገር አይኖርም።
3) ይህ ስብሰባ የሚመራው በኦህዴድ መሪዎች ነው። እነሱም ሆኑ ድርጅታቸው በመምህራኑ ሊነሱ የሚችሉትን ጥያቄ የመመለስ ምንም አይነት ስልጣን የላቸውም። የኦህዴድ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ የገጠመውን ማስተር ፕላን ሰርዘናል ብሎ ለህዝቡ ቢነግሩም ሰሞኑን የወያኔ ቱባ ባለስልጣናት የሆኑት አባይ ፀሐዬና በረከት ስምዖን “ማስተር ፕላኑ ለጊዜው እንዲቆይ ተደረገ እንጂ አልተሰረዘም” ማለታቸው ኦህዴድም ሆነ የድርጅቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ምንም አይነት የመወሰን ስልጣን እንደሌላቸው የቅርብ ምሳሌ ነው።
ስለዚህ የታቀደውን የፕሮፖጋንዳ መድረክ መቃወም ይኖርብናል። ሆኖም ግን የሚደረገው ተቃዉሞ የጥቅምና ጉዳት ትንተና መሰረት ያደረገ መሆን ይኖርበታል። መምህራኖችን ማወያየት ያስፈለገበት ምክንያትም ይኸው ነበር። የቀረቡትን የተቃዉሞ አማራጮችን በዚህ መልኩ ገምግመውታል።
1) ከስብሰባው ሙሉ በሙሉ መቅረት (Boycott)። ይሄኛዉ እጅግ ተመራጭ ቢሀንም ሁሉም መምህራን ካልተሳተፉበት መምህራኑን ለደመወዝ ቅጣትና ከስራ ለመባረር አደጋ ያጋልጣል።
2) በስብሰባዉ ላይ መሳተፍና መድረኩን ሙሉ በሙሉ ወደ ተቃዉሞ መግለጫ መቀየር። ይህ የሰዎችን ቀልብ የሚገዛ ቢሆንም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። ችግሮችን ለመፍታት በኦሆዴድ በኩል አቅም ከማጣትና በህወሀት በኩል ፍላጎት ካለመኖሩ በስተቀር በእስካሁኑ ሂደት መንግስት ጋር ያልደረሰ ጥያቄም ሆነ የመፍትሄ ሀሳብም የለም።ይህኛው አካሄድ የሚቀርቡትን ጥያቄዎችና ሀሳቦችን ቆራራጦ በሚዲያ በማቅረብ ለፕሮፖጋንዳ እንዲጠቀሙበት እድል ይሰጣቸዋል። ከሁሉም በላይ በመድረኩ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ጠንካራ መምህራንን ለይቶ ለመጉዳትም ያስችላቸዋል። ይህ ደግሞ ከዚህ በፊትም በተግባር ያየነው ነገር ነዉ።
3) በስብሰባው ላይ መሳተፍና ምንም አይነት ሀሳብም ሆነ ጥያቄ አለማንሳት (Silent Protest)። ይህ ከሁሉም ተመራጭ የሆነ የተቃዉሞ ዘዴ ነዉ። መምህራንን ለምንም አይነት አደጋ አያጋልጥም (It has Zero Cost) ። በአብዛኛው ዝም በማለት የጠላትን ልቦና ለማዳከምና ለማሸበር (Psychological Terror) ይረዳል። በተጨማሪም በመምህራኑ ዉስጥ አስርገው የሚያስገቧቸው አስመሳዮችና የመንግስት ካድሬዎችን ለመለየትና ለወደፊቱም ለመጠንቀቅ ይረዳል።
በመሆኑም ከነገ ጧት ጀምሮ ሁሉም መምህራን በስብሰባው በመገኘት በአንድነትና በፅናት በዝምታ ተቃውሟቸውን እንዲገልፁ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። ከዚህ በፊት ስታነሷቸው የነበሩት ጥያቄዎችና እናንተ ያፈራችኋቸው ተማሪዎቻችሁ ይህንን ስርዓት እንዳናጋው ሁላ በዚህ ስብሰባም ድምፃቹን በጋራ መንፈጋችሁ ይበልጡኑ ስርዓቱን ግራ ያጋባዋል።
በአንድነት ዝምታን በመምረጥ
ጠላትን ግራ አጋቡት!
Leave a Reply