የጎልጉል ጥብቅ ማሳሰቢያ!
ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ዋናው ዓላማ የሕዝብ እንደመሆኑ በጨዋነት የሚላኩልንን ጽሁፎች የምናትም መሆናችንን ስንገልጽ ቆይተናል፡፡ ሆኖ ግን አልፎ አልፎ የሚላኩልን ጽሁፎች በግለሰብ ዙሪያ ያጠነጠኑ ከመሆናቸው ባሻገር ምንም እንኳን ጸያፍ ቃላትን በግልጽ የሚታይባቸው ባይሆንም የሚሰነዘሩት ሃሳቦች ግን የግለሰቦችን ሰብዕና የሚነካ ከመሆኑ ባሻገር በስራችን ላይ ከፍተኛ ውስብስብ ነገር የሚፈጥርና ወደ አልተፈለገ እንካሰላንቲያ የሚመራ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በመሆኑም በእንደዚህና መሰል ጽሁፎች ላይ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ለየት ያለ የኤዲቶሪያ ፖሊሲ በመጠቀም ጽሁፎችን እንደሁኔታው እያየን የምናትም መሆናችንን እንገልጻለን፡፡
በተለይ ከዚህ በታች በተጠቀሰው አስተያየት ዙሪያ የሚላክልንን ማንኛውንም ጽሁፍ የማንቀበል መሆናችንን እንገልጻለን፡፡ በጉዳዩ ለመነጋገር የሚፈልጉ በግል በኢሜይልም ሆነ በሌላ መንገድ መገናኘት ይችላሉ፡፡
ከዚህ በታች ያለውን የአስተያየት ጽሁፍ ያተምነው ከዚህ በፊት በዚህ ዙሪያ ላይ ጽሁፍ በመለጠፋችን የተሰጠ የአስተያየት አጸፋ በመሆኑ ብቻ መሆኑ እንዲታወቅልን ይሁን፡፡
የዚህ ጽሁፍ ዓላማ አቶ መስፍን አብርሃ “መርዓዊና መንታ መንገዳቸው” በሚል ርዕስ የጻፈውና በኢትዮ.ሚድያ ላስነበበን ጽሁፍ በበኩሌ የማውቀውን ለማለት ነው። በቅድሚያ አሁን ካሉት የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች ለጥቂቶቹ ታናሽ ወንድም ለብዙዎቹ ወንድምና ታላቅ ወንድም የሆኑትን በምዕራብ አውሮፓ እንደ ሐዲስ ሐዋርያ የሚቆጠሩትን ካህንና ምሑር፤ ቄስ የሚለውን ማዕረግ እንኳን ነፍጎ መርዓዊ ብሎ መዘርጠጥ “አሳዳጊ የበደለው” ያሰኛል። ከዚህ አልፎ ጽሁፉም በዕውእነት ዙሪያ የሚያውጠነጥን አለመሆኑን ከአርስቱ ጀምሮ መረዳት ይቻላል። “መርዓዊና መንትያ መንገዶቻቸው” ልብ በሉ፤ ይህ መንታ መንገድ ከተፈጠረ 22 ዓመት አልፎታል። ነገሩን ግልጽ ለማድረግ ያህል፤ ቤተ ክርስቲያኗ በሁለት ሲኖዶሶችና በሁለት ፓትርያርኮች ከተከፈለች በኋላ መሆኑ ነው። ከዚህ ሌላ እኔም እንደ አቶ መስፍን እንዳለልዘረጥጥ ጥንቃቄ በማድረግ ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ ከ30 ዓመት በኋላ የኋላ ማርሽ አስገብተው መንትያ መንገድ ላይ ይቆማሉ ብሎ ማሰብ ለጤነኛ አእምሮ አይሆንም። ከዚህም ሌላ በፓትርያርኩ መልካም ፈቃድ ራሳቸው በመሰረቱት ሀገረ ስብከት ሊቀ ካህናት ሁነው የተሾሙትን፧ አሁንም በኃላፊነት ላይ ያሉትን አባት “የዛሬው የጽሑፌ ቅኝት በቀድሞው የጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን “ኃላፊ” እና የኮሎኝ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ፤ በጀርመን የኮሎኝ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ብቻ ስለሆኑት ቀሲስ ዶክተር መርዓዊ ተበጀ አመራር ላይ ያጠነጥናል።“ ስትል፤ ይህ መቸም ከዚያው ከግብር አባተህ ከ……የተማርከው ቅጥፈትና ውሸት ካልሆነ በስተቀር እኔ እስከማውቀው ድረስ አሁንም ያው በኃላፊነታቸው ላይ እንዳሉ ነው። ጉደዩ ምንም ምሰጢርነት ስለማይኖረው፤ ማስረጃው አስፈላጊ ነውና ሲቀርብ እኔም እቀበለዋለሁ። አቶ መስፍን “በእርግጥ ግለሰቡ በጀርመን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን መሥራች መሆናቸውን ማንም አይክድም።” ማለትህን እኔም እጋራዋለሁ። በልጃቸው አፍ “ግለሰብ” ተብሎ ሲነገር ግን መረን መልቀቅ ነው።
አቶ መስፍን አብርሃ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ወላፈን ተቀጣጥሎ አንድ የፖለቲካ አንጃ በወጣ ቁጥር ድጋፍ ለምትሰጠውና አቋሟን ለምትለዋውጠው ለጥላ መጽሄት ዋና አዘጋጅ መሆንህ ይታወቃል። ለዚህም ሙከራህ ልትበረታታ እንጅ ልትነቀፍ አይገባም። የሚያሰነቅፍህ ግን የፖለቲካው መንገድ አላዋጣ ሲል፤ ወደ ቤተ ክርስቲያን ዘወር ብሎ ጠለሸት ለመቀባት መሞከርህ ነው። እንዲያውም “የኢ.ኦ.ተ.ቤተክ. የምዕመናን ኅብረት” የሚል ህጋዊ ያልሆነ ማህበር አቋቁመህ ለሰላሳ አመት የተጠናከረ ህብረት ያላትን ታሪካዊቷን ቤተ ክርስቲያን በማመስ ላይ ትገኛለህ።
ከሁሉም የገረመኝ ግን የማታውቀውን የቤተክርስቲያኗን ታሪካዊ ሂደት ለመተቸት መነሳትህ ነው። ትችትህ ገንቢ ቢሆን ኖሮ ሃሳብሕን እጋራ ነበር። ነገርህ ሁሉ “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ሆነብኝ። እስቲ በመግቢያህ ላይ የጠቀስከውን ጥቅስ ልብ ብለህ ተመልከተው።
“መልካም መሥራትን ተማሩ፤ ፍርድን ፈልጉ፤ የተገፋውን አድኑ፤ ለድሃ አደጉ ፍረዱለት፤ ስለመበለቲቱም ተሟገቱ። ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር ፤ ኃጢያታችሁ እንደ አለላ ቢሆን እንደ በረዶ አነፃዋለሁ፤ እንደ ደምም ቢቀላ እንደ ባዘቶ አጠራዋለሁ። እሽ ብትሉና ብትሰሙኝ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እምቢ ብትሉና ባትሰሙኝ ግን ሰይፍ ትበላችሁዋለች፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሯልና።“ ትንቢተ ኢሳይያስ 1፣17-20
ወንድሜ! “ኑና እንወቃቀስ ይላል እግዚአብሔር፤ እምቢ ብትሉና ባትሰሙኝ ግን ሰይፍ ትበላችሁዋለች፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሯልና።” “ኑና እንወቃቀስ“ የሚለው የእግዚአብሔር ቃል በሊቀ ካህናቱ ዘንድ ሁል ጊዜ የሚጠቀስ፧ እንዲያውም ይህን እያሉ ለእርቅና ለሰላም እጃቸውን በመዘርጋታቸው “አስጠቃኸን” እየተባሉ የሚወቀሱ አባት ናቸው። “እምቢ ብትሉና ባትሰሙኝ ግን ሰይፍ ትበላችኋለች፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሯልና።” ብለህ ለጠቀስከው፤ አሁንም ሊቀ ካህናቱ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰውን የዕድሜ ጣራ የነኩ ስለሆነ አንተንና እኔን ይመለከት እንደሆን እንጂ እርሳቸውን አይመለከትም። ሁሉም በማስተዋል ቢሆን መልካም ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ያለቦታው መጠቀም ለቅስፈት እንጂ ለድኅነት አይሆንም። ወይስ እኛ የማናውቀው አንተና ግብረ አበሮችህ የምታዉቁት ሰይፍ ተስሎባቸዋል።?
በጽሁፍህ መጀመሪያ በዚህ ፳፻፮ ዓ.ም. ባለፉት ዓመታት በአለማዊውም ይሁን በመንፈሳዊው የነበሩ ግድፈቶችን ለማሻሽል የተነሳህ መሆንህን ጠቁመሃል። ምኞትህ የሚደገፍ ነው፥ ሸፍጥ የተሞላበት ባይሆን ኖሮ! “እውነት ከሆነ አንዱ በበቃ” ይላሉ አባቶች ሲናገሩ። በጣም ያብከነከነህ የሊቀ ካህናት ዶር መርዓዊ ተበጀ ለምስጋና መብቃት ነው። በምጸትም ከቅዱሱ ሙሴ ጋር አነጻጽረህ ተናግረሃል። ሳታውቀው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የትሁቱን የሙሴን ስም አንስተህ እንድትናገር አድርጎሃል። ዲክታተር እያልክ የምታብጠለጥላቸው ካህን በ30 ዓመት ውስጥ 10 አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አቋቁሞ፤ ለተወሰኑ ካህናት በጀት አሰገኝቶ፤ የሚያስተዳድር፧ በአገር አቀፍ ደረጃ ቤተ ክርስቲያኑን ወክሎ ለቤተ ክርስቲያኑ መልካም ገጽታን ያተረፈ ካህን ካለ ለምሳሌ ብትጠቅስልኝ አመሰግንሃለሁ። ከዚያም አልፎ ትችትህን እቀበላለሁ። ምነው አንተና ብጤዎችህ ከአራት ኪሎ ሃሳብ ተላቃችሁ፤ ያላችሁበትን ሀገር ኑሮ ብታጣጥሙ፧ ጀርመናውያን “ምስጋና ዋጋ አይከፈልበትም” ይላሉ። ከዚህ ላይ አዋሳ ከተማ ውስጥ ከአንድ ገበሬ ቄስ ጋር ስንነጋገር፤ ኗሪነቴ ጀርመን ሀገር መሆኑን ስነገራቸው “ያ ሻጭና ገዥ የሚመሰጋገንበት ደግ ሀገር“ ነው!? ያሉት ዛሬ ልብ ብየ ነገሩን (”Bitteschön! Dankeschön!”) ሳስበው እውነት ሆኖ አገኘሁት።
ሰዎችን ሥራቸው ያስከብራቸዋል። የሥራቸው ውጤት ምስክራቸው ነውና። ዛሬ እንተና ግብረ አበሮችህ የምታምሷት የቤተ ክርስቲያን መድረክ በማን የተደላደለ ይመስልሃል።? ዛሬ በጀርመንና በምዕራብ አውሮፓ የሚያገለግሉ ካህናት ሁሉ የእርሳቸው የሥራ ውጤት እንደሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ሃቅ ነው። ከትምህርት ቤት ገበታ ጀምሮ እርሳቸው የተቀበሉትን የመከራ ገፈት ሳይቀምሱ ጎዳናው ተስተካክሎላቸው በሰላም አገልግሎታቸውን ስለሚሰጡ ምኑም የማይሰማቸው እንዳሉ ለማጤን አይከብድም።
ስማ አቶ መስፍን! እንዲህ፤ እንደአንተ ገና ከዛሬ ሰላሳ ዓመት ጀምሮ የሊቀ ካህናቱን ስም በማጥፋት እስከዛሬ የዘለቁ አሉ። ነገር ግን እውነትን የሚቋቋማት የለምና እስከዛሬ እውነት ሳትበጠስ ሥራቸው በየእለቱ እያበበ እዚህ ደርሷል። ይህ ደግሞ በመልካም ነገር ለማይደሰቱ፧ እኛ ብንይዘው ብለው ለሚቋምጡ፣ ማጥፋትን እንጂ ማልማትን ለማይወዱ ምቀኞች የእግር እሳት እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ ባህላችን ባለው ላይ እንገንባ፤ እናስተካክል ሳይሆን ያለውን መሰረት አፍረሰን እንጀምር መሆኑ አሳዛኝ ነው።
አቶ መስፍን በሰላማ መጽሔት የወጣው የምስጋና ቃና ሊዋጥልህ እዳልቻለ ከጽሑፍህ መረዳት ይቻላል። አንተና ግብረ አበሮችህ አድማችሁ የቀራችሁበት የ30 ዓመት ክብረ በዓል ሲከበር፥ የተለያዩ የብዙ አብያተ ክርስቲያናት አባቶችና ኃላፊዎች የእንኳን አደረሳችሁ ንግግር ሲያደርጉ፥ በታላቋ ከተማ በኮለኝ ከንቲባ አንደበት ከንግሥተ ሳባ አንስቶ አስከ ዋልድባ ቅዱስ ገዳም ያለው ታሪክ ሲወሳ፧ ሙገሳው በዝቶ ሕዝበ ክርስቲያኑ በእልልታና በጭብጨባ ደስታውን ሲገልጥ፥ በውስጡ ያለፉበትም የደስታ እንባ ሲተናነቃቸው፣ ንዋያተ ቅድሳቱ በክብር ተይዘው፥ የእግር ጉዞ በሚደረግበት ጊዜ በጀርመን ያሉ የውጭ አገር አብያተ ክርስቲያናት አግኝተውት የማያውቁት ዕድል ለእኛ ተስጥቶ፧ አውራ ጎዳናው በፖሊስ ኃይል ተዘግቶ፥ ጀርመኖች በውጭና በመስኮት እያጨበጨቡ፧ ሕዝቡና መዘምራኑ “እኔስ አገሬን መሰለኝ፧ የኮለኙ ቅዱስ ሚካኤል” እያሉ ሲዘምሩ፥ ተደርጎ በማያውቅ መልኩ ለክብረ በዓሉ የተጋበዙ ጀርመናውያን ለቤተ ክርስቲያኗና ለሊቀ ካህናቱ ክብር ከምሳ በኋላ በአዳራሹ ሲዘምሩ፧ ሙገሳው ሲጎርፍ ሕዝብ በደስታ ሲፍለቀለቅ ብትኖሩ ኖሮ ያው የተለመደው የቅንዓት ዓይናችሁ ይቀላ ነበር ብል አልተሳሳትኩም ባይ ነኝ። ከተሳሳትኩም የአተንና የእኔን ጽሑፍ ያነበበ ሁሉ ይፍረድ። ባነበብከው ብቻ “ውዳሴ መርዓዊ ከነቤተሰቡ” በማለት ለመተቸት ሙክረሃል። በእለቱ ተገኝተህ የክበረ የበዓሉን ድምቀት በዓይንህ ብታይ፣ የቀረበውን ገጸ በረከት ብትመለከት፣ ሙገሳውን በጆሮህ ብትሰማ፥ ምን ትል ነበር?
ጋዜጠኛ አቶ መስፍን የጋዜጠኝነት ሙያ መርማሪነት ነው ብለሃል። እስቲ ልጠይቅህ፤ ይህንን ጽሁፍ ስታዘጋጅ እውነትን ለማግኘት ምን ያህል ጥረት አድርገሃል።? ስህተቶች ካልካቸው አንዱን ላንሳ ለምሳሌ፤ “አብረዋቸው የሚሠሩ ካህናት እንኳን በመጽሄቱ ዝግጅት አልተካተቱም” ብለሃል፤ አባቶች ያሉት ካጠገብህ ነው፤ እሩቅ ያሉትም ቢሆን በደቂቃ ታገኛቸዋለህ፧ እድሜ ለዘመኑ ስልጣኔ፤ ምነው ጠይቆ መረዳትና ማስረዳት ከበደህ።? የሙያውን ስነ ምግባር ያለማወቅ ይሏል ይህ ነው። እነዚህም አባቶች ይታዘቡሃል። ጽሑፍ እንዲያቀርቡ ከስድስት ወር በላይ ጊዜ ተሰጥቷቸው ሊያቀርቡ አልቻሉም። በዚህም ምክንያት ይቅርታ ጠይቀዋል።
አንባቢዎችን እንዳላሰለች ስጋቱ አለኝ፧ ይሁን እንጂ አንዳንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያናትን አስመልክተህ ስላነሳሃቸው ጉዳዮች ላንሳ፤ ስለ ካልስሩኼ የጽዋ ማሕበር ወደ ቤተ ክርስቲያንነት ከፍ ማለት ጠቅሰሃል። ለመሆኑ እውነትን ፈላጊ መርማሪ ጋዜጠኛ ከሆንክ ታዲያ ከጽዋ ማህበርነት ወደ ቤተክርስቲያንነት ከፍ ማለቱን ስትከታተል፤ ለምን ስለታቦቱ አመጣጥ አልገለጽክም? እስቲ እኔ የማውቀውን ላጫውትህ፤ አንድ ግለሰብ ጳጳስ ከሃገርቤት አስመጥቶ በማሳከሙ ስለውለታው ብቻ ሳይገባው፤ ሳይማር፤ የቅስና ማእርግ ተሰጠው፥ አሁንም እኝሁኑ ጳጳስ እቤቱ ያስተናገደ አንድ ግለሰብ፥ ለውለታው ታቦት ተላከለት። ያለምንም ጥናትና ጥያቄ፤ ቋሚ ካህን ሳይመደብ ታቦቱን ይዘው የመጡት ደግሞ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሆኜ ተሹሚያለሁ የሚሉት ብፁዕ አቡነ ሙሴ ናቸው። ይህ ሁሉ የተፈጸመው ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ካህናት ከዶ/ር መርዓዊ ተበጀ ተደብቆ ነው። ታዲያ ጋዜጠኛ መስፍን እንዲህ ዓይነቱን ሕገ ወጥ ተግባር፤ የቤተ ክርስቲያናችንን ታሪክ የሚያጎድፍ በመሆኑ ማጋለጥ ሲገባህ፤ ሊቀ ካህናቱን እጅና እግር በሌለው ውሽት ለመንቀፍ ግን ብዕርህን አሾልክ።
ስለቪስባደን ቤተ ክርስቲያን አንስተሃል። እንደአንድ ምእመን በንስሃ የማምን በመሆኑ የካህኑን ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው መመለስ የምደግፍ ቢሆንም፤ ውሳኔው የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አባቶች እንጂ እንዳንተና እንደ እኔ ያሉ ማሃይምናን ውሳኔ አለመሁኑን ላስገነዝብ እወዳለሁ። በቪስባደን ስለገንዘብ መባከን አንስተሃል፧ ከዚያ ያሉ ምዕመናን በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ካህኑም አገልግሎት የሚያበረክቱት ያለምንም ክፍያ መሆኑን ምስጢሩን ልንገርህ። መባከን የሚኖረው እኮ ገንዘብ ሲኖር ነው።
“የሙኒክ ቅዱስ ገብርኤል አስተዳዳሪ በፍራንክፈርት ቅድስት ማርያም በኮለኝ ሚካኤልና በሽቱትጋርት አቡነ አረጋዊ አብያተ ክርስቲያናት ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ብክነት ዝርፊያ ሙስናና የአስተዳደር ችግሮች፤” መከሰታቸውን ገልጸህልናል። አንድ ባንድ ስንቃኛቸው ግን ክስተቶቹ እንደዚህ ናቸው። የሙኒክ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ትጉሕና ብዙ የደካሙ ካህን መሆናቸውን እንኳን ወዳጅ ጠላት የሚመሰክረው ነው። ሆኖም ተፈተኑ፧ ከስህተትም ላይ ወደቁ። በዚህም ሊቀ ካህናቱ ከልብ ማዘናቸው የሚረሳ አይደለም። ሊቀ ካህናቱንም የጥፋቱ ተካፋይ ለማድረግ ብዙዎች ቢጥሩም አልተሳካላቸውም።
የፍራንክፎርት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪም እንደአንተ ድፍረትን ተላብሶ፥ ከአንተም በተሻለ መልኩ አንድ ግለሰብ ማስረጃ አለኝ ብሎ በተለያዩ መንግሥታውያን ድርጅቶች ላይ ክስ መሥርቶባቸው ነበር። አቃቤ ሕግም ቤታቸው በወንጀል መርማሪዎች እንዲፈተሽ አድርጓል። ምንም ጥፋት ባለመገኘቱ ነፃ ከወጡ በኋላ፧ በዚህም ቅሬታ ያላቸው ወገኖች ከሳሽና ምስክር ሁነው እንደገና ቢቀርቡም ክሱ ውድቅ ሁኗል።
የሽቱትጋርት ልደታ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ካህን ከራሳቸው የአስተደዳር ችግርና የግል ጠባይ የተነሣ የተሰበሰበውን ምእመን መበተናቸው አንሶ፤ አባት አለን ብለው የተከተሏቸውን ሁሉ የተለያየ ስም በመስጠት የነበረውን እንዳልነበር ማድረጋቸው የሚያሳዝን ነው። ሊቀ ካህናት በፍርድ ቤት ያስመለሱላቸው 28.000,00€ በሰበብ አስባብ ወጥቶ አልቋል። ይኸውም ካህኑ በአገልግሎት ጠንክረው ገንዘብ ስላልተጨመረበት እንጂ በብዝበዛ ያለቀ አይደልም።
በኮሎኝ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሰለገንዘብ መባከንና ስለሙስና ተናግረህ አንባቢዎችን ወደ አልተፈለገ ውዥብር ውስጥ እንዳይገቡ በቅርብ የማውቀውን ላስረዳህ። እንደ ፍራንክፈርቱ አባት ሁሉ ሊቀ ካህናትም ለአቃቤ ሕግ የቀረበ ክስ ተመሥርቶባቸው ነበር። የፍራንክፈርት ከሳሾች ደረታቸውን ነፍተው ማንነታቸውን አሳውቀው ነበር። በሊቀ ክህናቱ ላይ የቀረበው ክስ ግን በሽምቅ ወይም በስመ አልባ ነበር። የሊቀ ካህናቱ ከሳሾች ስማቸውን ባይገልጡም ለምስክርነት ይሆኑናል ያሏቸውን የ8 ሰዎችን ስም ሰጥተው ነበር። እጅግ የሚገርመው ደግሞ ለምስክርነት ከተጠሩት መካከል አንዷ የቱርክ ሴት ነበረች። ሌሎቹ ግን የሊቀ ካህናት የመንፈስ ቅዱስ ልጆችና ወዳጆች ነበሩ። ከ8 አንዱ ለወንጀል መርማሪ ፖሊስ ቃሉን ሲሰጥ ሁሉም “እራያና ቆቦ” በመሆኑ ምስክር ነኝ ብሎ የቀረበው ማስጠንቀቂያውን ተከናንቦ ፋይሉ ተዘግቷል። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ሊቀ ካህናት መርዓዊ ተበጀ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ሊያውቁ የቻሉት ቀርበው ሳይጠየቁ አቃቤ ሕግ ከጀርመን ወንጀለኛ መቅጫ ዐቢይ አንቀጽ 170 ንዑስ ቁጥር 2 ያለውን በመጥቀስ “ተከሰው ነበር” ብሎ በጻፈላቸው ደብዳቤ ነው። ነገሩ ይህ ሆኖ ሳለ አንተና ግብረ አበሮችህ “ተበላ፥ተበዘበዘ፣ተመዘበረ ሙስና” እንዳላችሁ እስካሁን አላችሁ። የሙኒኩን ካህን ጽዋ ላማስጎጨት በመቻኮልም ላይ ናችሁ። ክርስቲያን ከፈተና ሰውረው ብሎ ይጸልያል እንጂ የወገንን ጥፋት መመኘት ክርስቲያናዊ ተግባር አይደለም።
“በአዘጋጅነት የተሳተፉት የጀርመን ድምፆቹ ሁለት ሴት ጋዜጠኞችም ያሉትን ችግሮች መርማሪያዊ በሆነው የጋዜጠኝነት ስርዓት ለሌሎች የሚሰነዝሯቸውን ምላሶቻቸውን በመርዓዊ ላይ ማጠፋቸው አስተዛዝቦናል። የሙያዊ ስነምግባርም አይደለም።” ስትል በሰላ ምላሰህ ዘልፈሀቸዋል። ሊቀ ካህናቱ በመመስገናቸው “የሙያዊ ስነምግባርም አይደለም።” በማለት ለማስተማር ሞክረሃል።ምን ያህል የጥላቻ መንፈስ ቢያድርብህ ነው? እንዳንተ ያልተገራ ምላሳቸውን ካልመዘዙ ብልህ የምታንቋሽሻቸው? የአንተ የጋዜጠኛነት የሙያ ስነምግባር እስከ ዚህ ነው።
አቶ መስፍን አብርሃ፧ በኮለኝ ያለውን ሁኔታ ጥሩ አድርጌ ስለማውቀው በጋዜጠኛ ባለሙያነትህ ሁሉን አንጠርጥረህ እንድታውቀው ሊቀ ካህናት ይተባበሩሃለ ብዬ በአጽንኦት መናገር እችላለሁ። “መጠየቅ ያደርጋል ሊቅ” እንዲሉ፤ ጠይቅ! ተረዳ፤! ከዚያ እራስህን የአሉባልታ ቆሬ ከማድረግ ትድናለህ።
በተለይ የኮሎኙ ቤተ ክርስቲያን ግዢ እውነት መሆኑን የተጠራጠርክ ይመስላል ጋዜጠኛ እኮ ነህ! ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ጠይቀህና መርምረህ እውነቱን ለማውጣት ያልሞከርከው አንዴ አሉባልታ ስለተጠናወተህ ከሱ አልላለቅም ብለህ ነው?። “ለአፍ ዳገት” የለውም እንዲሉ። በርክክቡ ቀን ብትኖር ኑሮ ከሻጮች ወገን ካህኑ “ወንድማችን መርዓዊ፧ የተወደዳችሁ የዚህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን አባላት ቤተ ክርስቲያኑ የአምልኮ መፈጸሚያ ሆኖ በመቀጠሉ እጅግ ደስ ብሎናል። ብሎም በገንዘቡም ተጠቃሚዎች በመሆናችን በፀሐይ ኃይል መብራት የሚያመነጭ መሣሪያ ገዝተንበታል። ቀሪውም ለተመሳሳይ አገልግሎት ይውላል። እናመሰግናለን” ሲሉ ተናግረዋል።
ሰለ ሊቀ ካህናቱ የአስተዳደር ችሎታ ማነስ ስትገልጽ አማርኛው አላረካህ ብሎ ይሆን ወይም የእንግሊዘኛ ቋንቋ የተማርክ ምሁር መሆንህን ላማሳየት በwikipedia የተጻፈውን ገልብጠህ አስነብበኸናል። አንድ ነገር ልንገርህ፤ ለአንድ ሰው የጀመረው ሥራ ፍሬ አፍርቶና ተተኪ አገኝቶ ማየት ታላቅ እድል ከመሆኑም በላይ፤ የአስተዳደር ቾሎታም ነው። ለዚህ እድል የሚበቁ ጥቂቶች ናቸው። እኚህን አባት ብዙዎች እንደ አይን ብሌን ሲያዩአቸው አንዳንድ የሚነቅፏቸው የመልካም ሥራ ጠላቶች አልጠፉም። የተከሉት ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ አያፈራም። በመሆኑም እንተና መሰሎችህ ብትነቅፏቸው አያስደንቅም። ባሁኑ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ የትእግስታቸውንና የሥራ ፍሬአቸውን እያዩ ስለሆነ፤ የታደሉ ናቸው። ሊቀ ካህናት ዶር መርዓዊ ተበጀ እውነተኛ የክህነት ግዳጃቸውን ፈጽመዋል፤ የሚያሳዝናቸው ነገር ቢኖር እንደአንተና እንደ መሰሎችህ ያሉ አለማን ብለው ቤተ ክርስቲያንን ሲያደሟት ማየት ነው። ሆኖም መልካም ሥራ ባለበት ክፉ መኖሩ ግዴታ መሆኑ እንጂ፤ ቤተ ክርስቲያንማ “የገሃነም ደጆች ሊቋቋሟት አይችሉም” ተብሎ ተጽፎ የለ።? ለዚህም ነው የኢ.ተ.ኦ.ቤ.ክ በጀርመን ብሎም በአውሮፓ ፋናዋ የሚያበራው። ባይሆንማ ኖሮ የሰላሳ ዓመቱ ጉዞ በተሰናከለ ነበር።
አቶ መስፍን አብርሃ በመጨረሻ ወደዚያው ወደ ተነሳህበት ርእስ ተመልሰህ ለዝከረ ነገር በተዘጋጀው የሰላማ መጽሔት “በስደት ወይም በአገር ቤት ያሉትን ፓትሪያርክ ፎቶ ከፊት ይዘው መውጣት ሲገባቸው የሁለቱንም አላወጡም።” በማለት የማይሆን ሰብቅ ይዘህ ትዘባርቃለህ፤ – በነገራችን ላይ ለመሆኑ አንተ የማንኛቸው ፎቶ ቢወጣ ነበር አንጀትህ የሚርሰው? – ሰው ያልበላውን ሲያክ እጅግ ያስገርማል። እኔ እስከማውቀው ድረስ ሊቀ ካህናት ከአዲስ አበባው መንበረ ፓትርያርክ ጋር የጠነከረ ግንኙነት ስላላቸው ከነፍስ አድን ዘመቻ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ቤተ ክርስቲያናችንን፥ ገዳሞቻችንና መንፈሳውያን ትምህርት ቤቶቻችንን በጎአድራጊዎችን በማስተባበር እንደረዱ ናቸው። ስለ ፎቶ ግራፉም፧ የአዲሱ ፓትርያርክ ሐዋርያዊ ቡራኪያቸው በሰላማ መጽሔት እንዲወጣ ተጠይቀው መልስ ባለመገኘቱ ቀርቷል። እንዲያውም ከተቻለ በ30ኛው ዓመት ክብረ በዓል ቅዱስ ፓትርያርኩ እንዲገኙላቸው ጥሪ አስተላልፈውም ነበር።
ያም ሆነ ይህ፤ “ያላወቂ ሳሚ … “ እንደልኩት በማታውቀው ጉዳይ ገብተህ ስትዘባረቅ ትዝብት ላይ ወድቀሃል፤ በበኩሌ ግን ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሜ ለብዙ ዘመን ስለማውቃቸው ጽናት ያልተለያቸው ካሕንና ስለቤተክርስቲያኗም የማውቀውን አንዳንድ የተከደነ ሃቅ እንዲከፈትና ሕዝብ እንዲያውቀው ለማድረግ በመቻሌ ደስ ብሎኛል። የተረፈውን ደግሞ በቀጥታ ጉዳይ የሚመለከታቸው መልስ ይሰጡበታል ብዬ አምናለሁ። ብሎም፤
አቶ መስፍን፧ ከመነሻው ላይ እንደመግቢያ አድርገህ የጠቀስከውን የነቢዩ የኢሳይያን ጥቅስ እኔም ልመልሰው። “ኑና እንወቃቀስ ይላል እግዚአብሔር ……፣” የሊቀ ካህናት መርዓዊ መመሪያቸው ይህ መሆኑን የሚያውቋቸው ሁሉ ይመሰክራሉ ሰው በደለኝ ብለው ፊታቸውን የማያዞሩ፤ በውይይት የሚያምኑ፤ ትእግስተኛ ናቸው። ለአንተና ለመሰሎችህ የሚስማማችሁን ጥቅስ ከይሁዳ መልእክት ም. ፩ ከቁ. ፱ ላይ ያለውን በመጥቀስ እሰናበታለሁ። “የመላእክት አለቃ ሚካኤል ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር፧ ጌታ ይገስጽህ “ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም።”
በጊዜው የተከደነው ሁሉ ተገልጧል።
ቸር ያቆየን
ጽዮን አምባዬ
ጀርመን
E-Mail: zionambaye@gmail.com
koster says
tell us about the gift Merawi gave to DIABLOS