ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ከትናንት በስቲያ አመሻሹን ከጋዜጠኞች ጋር ተገናኝተው ነበር። ሚዲያው በምርጫው ላደረገው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለማመስገን በተዘጋጀው በዚህ መርሀ ግብር ላይም ሚዲያውን ካመሰገኑ በኋላ ስለ ምርጫው እና ስለ ትግራይ ሁኔታ ለጋዜጠኞች አብራርተዋል። ካነሷቸው ነጥቦች መሀከልም የተወሰኑትን በግርድፍ እንዲህ አስታውሻቸዋለሁ
በምርጫው እኛም ሆነ ተቃዋሚዎች የተመኘነውን ያህል ቡራቡሬ ፓርላማ አላገኘንም!
ተቃዋሚዎች በምርጫው ውጤት ደስተኛ ባይሆኑም በምርጫ ቦርድ፥ በፍርድ ቤት እና በሚዲያ ላይ ቅሬታ እንደሌላቸው ተስማምተናል!
ሚዲያው የትርክት ለውጥ ላይ በደንብ መስራት አለበት። ኢትዮጵያዊ አንድነትን ከዚህም በላይ መስበክ አለበት!
በትግራይ ባካሄድነው ዘመቻ ተይዘውብን የነበሩትን መሳሪያዎች በሙሉ አስመልሰናል። ማስተካከል የምንፈልገውንም አስተካክለናል
መቀሌ ከዘመቻው በፊት የነበራትን የስበት ማእከልነት አጥታለች። ስለዚህ ከመቀሌ መውጣት ከሌሎች ቦታዎች ከመውጣት የተለየ ፋይዳ የለውም!
ከዘመቻው በፊት ጁንታው የነበረው ወታደራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ አቅም አሁን የለም።ከጦርነቱ በፊት በትግራይ ክልል እና በሌሎች ክልሎች መሀከል የነበረው ልዩነት ሰፊ ነበር። አሁን ግን እኩል ሆኗል ወይም ከዚያ በታች ወርዷል!
በዚህ ጦርነት ወደ 100 ቢሊየን ብር ገደማ አውጥተናል። ይህም ለትግራይ ከምንመድበው አመታዊ በጀት ከ13 እጥፍ በላይ ነው።ከአሁን በኋላ ግን እያወጣን ለመቀጠል ፍላጎት የለንም!
ጦሩ እየተጠቃ ያለው በህዝብ ነው።ራሳችን በምንቀልበው ህዝብ የምንጠቃ ከሆነ በእልህ አንዴ ገብተንበታል በሚል በዚያ መቆየት ፋይዳ የለውም!
ጦሩ በህዝብ ነው እየተገደለ ያለው።ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ጦሩ እንዲቆይ ካደረገን ጦሩ ወዳልተፈለገ እርምጃ ሊገባ ይችላል!
መጀመሪያ የገጠመን የተደራጀ ፥ የታጠቀ እና ዩኒፎርም የለበሰ ሀይል ነበር።እሱን በሁለት ሶስት ሳምንታት ውስጥ አስወግደናል። ከዚያም የተወሰነ የጎሬላ ውጊያ ነበር። አሁን ግን በየመንደሩ ስንሄድ የሚገጥመን ጦር የለም። የምናገኘው ህዝብ ነው።በቃ ሰላም ነው ብለን ስናልፍ ግን ከጀርባችን ህዝብ ነው ባልነው አካል እንጠቃለን!”
የትግራይ ህዝብ የጽሞና ጊዜ እንዲኖረው እና ነገሮችን በትክክል እንዲያገናዝብ እድል ሰጥተነዋል!
አሁን ፕራዮሪቲያችን ትግራይ ሳትሆን የህዳሴው ግድብ ነው። ስለዚህ ጦሩ ትኩረቱ ወደዚያ ነው!
እኛ ትግራይን ተቆጣጥሮ እንደ ቅኝ ገዢ የመቆየት አላማም አልነበረንም። የሚስተካከለውን አስተካክሎ ወደ ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች መመለስ ነበር አጀንዳችን!
የጁንታው አላማ ማሸነፍ፥ ስልጣን መያዝ፥ ወዘተ አይደለም። እኔ አመድ ስለሆንኩ ኑ አብራችሁኝ አመድ ሁኑ ነው። እኛ በተቀደደልን ቦይ አንፈስም። ነገሮችን ቆም ብሎ አይቶ የራስን አካሄድ መምረጥ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ቆም ብለን አይተን ነው የወሰንነው!
በሳውዲ የነበሩ 45ሺ ኢትዮጵያውያንን የማንገላታቱ እንቅስቃሴ ክህዳሴ ግድቡ ጋር የተያያዘ ጫና የማድረግ ሂደት ነው!!
አማራ ክልል ከሁለት አመት በፊት ያለበት ስጋት የለበትም።ተክዷል የሚሉ ሀይሎች ህዝቡን እየናቁ ነው።የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ አይደለም ዛሬ ለ30 አመታት ዱላ እየወረደበት እንኳን ከፍ ሲል ኢትዮጵያዊ ነው ዝቅ ሲል የበጌ ምድር ሰው ነው”
ጦሩ ከዚያ እንዲወጣ ከወሰንን በኋላ ትናንት እስከ እኩለ ሌሊት ብዙ የአለም መሪዎች ስልክ እየደወሉ ጦሩን ማውጣታችንን ሲቃወሙ ነበር!”
ጦራችን ተሸንፎ አይደለም የወጣው ነገር ግን ባለበት ቦታ ባእድ እንዲሆን ከተደረገ ደጀን ወደሚለው አካባቢ መሄዱ አግባብ ነው!
አሁንም ቢሆን ጦራችን መያዝ የሚገባው ቦታም ሆነ ሌላ ነገር ካለ ለመያዝ ከበቂ በላይ አቅም አለው!
እስከ ዛሬ እኩለ ቀን ድረስ መቀሌ የገባ አንድም የጁንታው ወታደር የለም!
አንጻንድ ነገሮችን መግዛት ፈልገን በገዛ ገንዘባችን እንዳንገዛ በአሜሪካ እና በጀርመን ያለን አካውንትን ዘግተውብናል!
ባለፉት ወራት ወጣቱ መከላከያን እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርበን ያገኘነው ሰው ብዛት ግን 5 ሺ ብቻ ነው!
የዚህ ጦሩን የማውጣት እርምጃን ውጤት በጥቂት ጊዜ ውስጥ እናየዋለን።ነገር ግን ዳግማዊ ድሉ የኢትዮጵያ እንደሆነች በእርግጠኝነት እነግራችኋለሁ!
(ንግግሮቹ ቃል በቃል የተወሰዱ ሳይሆኑ በግርድፍ የጻፍኳቸው ናቸው) በመቶዎች የሚቆጠሩ ከፌደራል እና ክልል ሚዲያዎች የተሰባሰቡ የሚዲያ ባለሙያዎች በተገኙበት በዚህ ፕሮግራም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው ሁኔታዎችን ባብራሩበት ወቅት አዳራሹ ውስጥ የነበረው ጋዜጠኛ ብቻ ሳይሆን የሸራተን ሆቴል የመስተንግዶ ባለሙያዎች እንኳን ስራ አቁመው በትኩረት አዳምጠዋል። ባላጋንነው ለብዙ ደቂቃዎች አዳራሹ ውስጥ ሰው ያለ እስከማይመስል ድረስ ጸጥታ እና ሙሉ ትኩረት ነበር። በተለይ ጦሩ ባለፉት ሳምንታት በህዝብ ደረጃ የደረሰበትን ክህደት በገለጹበት ወቅት ብዙዎች ሲናደዱ ይታይ ነበር።
“አንድ ቦታ ላይ ህዝቡ መከላከያ ገብቶ ይጠብቀን ብሎ ጥሪ አቅርቦ መከላከያ በቦታው ከገባ በኋላ ሁኔታውን ለማስተካከል የተወሰኑ ወታደሮችን በቦታው አስቀምጦ ወደሌላ ስፍራ ለዘመቻ ሄደ። ነገር ግን ማታ ላይ በቦታው የቀረውን ወታደር፥ ይጠብቀን ብሎ የጠራው ህዝብ መሳሪያም ገጀራም ይዞ ወጥቶ ጨፍጭፎታል” ብለው ሲናገሩ በተለይ ብዙ ሰው ስሜቱ በንዴት በጣም ግሎ ነበር። በጥቅሉ ጦሩን ያወጡበት ፖለቲካዊ፥ ዲፕሎማሲያዊ፥ ኢኮኖሚያዊ እና ስትራቴጂካዊ ምክንያት ለብዙዎች አሳማኝ ሆኗል ማለት እችላለሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእልህ ጦሩን መማገድ እንደማይፈልጉ እና ከዚህ ቀድም በነበሩ አገዛዞች የተሰራውን ስህተት መድገም እንደማይፈልጉ አስታውቀዋል። ከኢኮኖሚያዊ ፥ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካው ምክንያት ባሻገር የጦሩን የጦር ሜዳ ሰሙናዊ ቆይታ ሲያብራሩ የነበረው ሁኔታ ሳውዲ እና UAE በየመን ከነበራቸው ዘመቻ ጋር አመሳስለውታል። እኔ ደግሞ Black hawk down የተሰኘው ፊልም ጥሩ ምሳሌ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።
በጥቅሉ ግን ያለው ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደርግን ስህተት መድገም እንደማይፈልጉ፥ በተዘረጋላቸው ወጥመድ ውስጥ ሰተት ብለው መግባት እንደማይፈልጉ፥ ትኩረታቸውን ወደ ሌሎች አጣዳፊ ጉዳዮች ለማድረግ እንደመረጡ የገለጹበት ሲሆን በትግራይ ጉዳይ ይህ ውሳኔያቸው ውጤታማ እንደሚሆንም እርግጠኛ ሆነዋል።በንግግራቸው ውስጥ ስለ ድርድር ያነሱበት አጋጣሚ ግን አልነበረም። (Ab Bela)
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ከዚህ በታች ይገኛል
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply