በአዲስ አበባ በየቦታው ቆሻሻ ለሚጥሉና በቅርቡ የተተከሉትን ዘንባባዎች ለሚገጩ የሚከፈለው ቅጣት ያነሰ መሆኑን በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ። ተግባሩን ለመከላከል የሌሎች አገራት ልምድ ተግባራዊ እንዲደረግና ጥፋቱን ለመቀነስ የቅጣት መጠኑ መጨመር እንዳለበት ነው ነዋሪዎች የተናገሩት።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለከተሞች የሚገኙ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር ባደረገው ኢመደበኛ ጥናት ሁሉም ተጠያቂዎች የሰጡት ምላሽ ጥፋቱን በሚፈጽሙ ላይ የተበየነው ቅጣት ከዚህ መጨመር እንዳለበት ነው። ሌላው የሰጡት ምላሽ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በማጥናት በአገራችን ላይ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ሲሆን፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንደ ጥንቃቄ የሰጡት ምላሽ ሁሉም ሰው አውቆ ዘንባባ ስለማይገጭ እንደ አገጫጩ ምክንያትና ዐውድ ቅጣቱም በዚያው መልኩ አጥፊዎችን ከአደጋ አድራሾች በመለየት የሚፈጸም ሊሆን እንደሚገባው ገልጸዋል።
ለምሳሌ በግዴለሽነትና ከተለመደው ፍጥነት በላይ ወይም ሌላውን ለመቅደም ወዘተ በሚደረግ መልኩ የሚገጭ ዘንባባ እና በሌላ አሽከርካሪ የተፈጸመን ስህተትና የሚያስከትለውን ከፍተኛ ጉዳት ለመታደግ ሲባል ሰውን ከመግጨት ይልቅ ዘንባባውን መግጨት የግድ የሚሆንበት ጊዜ የሚፈጸም ለይቶ መቅጣት ተገቢ ነው በማለት በምሳሌ ያስረዱም ነበሩ። ሌሎች ደግሞ ቆሻሻ መጣል ትክክል አለመሆኑ በዘመቻ መልክ ቢሠራበት እና ከታዋቂ ግለሰቦች ጀምሮ የኪነት ሰዎችን ያካተተ መርሃግብር ቢዘጋጅ፤ ተማሪዎችንም ብናስተምር ጥሩ ለውጥ ልናመጣ እንችላለን የሚል ጥቆማ ሰጥተዋል።
ጥናቱ ኢመደበኛና በሃብት ውሱንነት ምክንያት የተወሰደው ናሙናም በቂ ነው ባይባልም በተወሰነ መልኩ ጠቋሚ እንደሆነና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የተሻለ ጥናት እንዲያደርጉ የሚያመላክት እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።
በአዲስ አበባ ከተማ በኮሪደር ልማት የተሠሩ ሥራዎችን በአግባቡ ያልተጠቀሙ እና ጉዳት ያደረሱ አካላት መቅጣት መጀመሩን ኢዜአ በቅርቡ ዘግቦ ነበር። በዚህም 3 ተቋማት ከተፈቀደ ቦታ ውጪ ቆሻሻ በመጣል እንደየጥፋት ደረጃቸው 100 ሺሕ ፣ 50 ሺ እና 20 ሺሕ ብር የተቀጡ ሲሆን 5 አሽከርካሪዎች በመንገድ አካፋይ ላይ የተተከሉ ዘንባባ ዛፎችን ገጭተው በመጣላቸው እንደየጥፋት ደረጃቸው ከ150 እስከ 300 ሺሕ ብር እንዲሁም 11 ሰዎች ከተፈቀደው የእግረኞች መንገድ ውጪ በመሄዳቸው ከ150 እስከ 1000 ብር ተቀጥተዋል።
የሠለጠኑ በሚባሉ አገራት የሚታየው ንጽህና ዋጋ የተከፈለበት ነው። ለምሳሌ በአሜሪካ የኦሪጎን ጠቅላይ ግዛት ያልጠፋ የሲጋራ ቁራጭ መጣል እስከ 2,500 ዶላር የሚስቀጣና ለስድስት ወር የሚያሳስር ነው። ግዛቱ ለሰደድ እሣት የተጋለጠ በመሆኑ የቅጣቱ መጠንም ከበድ ይላል።
በአጠቃላይ በአሜሪካ ቆሻሻ መጣል የሚያስከትለው ቅጣት በየግዛቱ የተለያየ ነው። ቅጣቱን በተመለከተ ብያኔ የሚያስተላልፉ ፍርድ ቤቶች ከገንዘብ ቅጣት በተጨማሪ የተጣለውን ቆሻሻ ማንሳትን የጨመረ ቅጣት ይበይናሉ። በጣም ትንሹ የሚባለው ቅጣት የማሳቹሴትስ ግዛት የሚበይነው የ25 ዶላር ሲሆን ትልቁ ደግሞ የሜሪላንድ ግዛት የሚበይነው የ30,000 ዶላር ቅጣት ነው። ከዚህ ሌላ እንደየግዛቱ የጥፋቱ ፈጻሚዎች መንጃ ፈቃዳቸው ሊታገድ፤ ዘብጥያ ሊወርዱም ይችላሉ። የበለጠ መረጃ ለማግኘት እና በእያንዳንዱ ግዛት የተደነገገውን ቅጣት ለመረዳት እዚህ ላይ ይጫኑ (https://www.ncsl.org/environment-and-natural-resources/states-with-littering-penalties)።
የቆሻሻ መጣል ጉዳይ ካሳሰባቸው መካከል ለምሳሌ በአሜሪካ የቴክሳስ ጠቅላይ ግዛት “Don’t Mess With Texas” የሚለውን በርካታ ሽልማቶችን ያስገኘ የጸረ ቆሻሻ ዘመቻ ከመጀመሩ በፊት በ1980ዎቹ በቴክሳስ አገር አቋራጭ መንገዶች ላይ የሚጣለው ቆሻሻ ግዛቱን እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር ያስወጣው ነበር። ይህ ዘመቻ በተለያዩ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ዘፋኞች፣ የተለያዩ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ በትምህርት ቤቶች ወዘተ እንዲታወቅ በመደረጉ ቆሻሻ መጣል አሁንም እንደየቦታው ከፍተኛ ቅጣት የሚያስቀጣ ሆነ፤ አርባ ዓመት አካባቢ ያስቆጠረው ዘመቻ እስካሁንም ቀጥሏል።
በአውሮጳ የሚኖሩ ጎልጉል ያነጋገራቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊ እንዳሉት “አብዛኛው ዳያስፖራ በውጭ አገር ሲኖር ንጽሕናውን፣ ለዛፎች የሚደረገውን እንክብካቤ፤ አልፎ ተርፎ ያለ መንግሥት ፈቃድ በቤት ያለ ዛፍ እንኳን መቁረጥ እንደሚከለከል ያውቃል፤ ቅጣቱ የከፋ እንደሆነ አምኖ ተቀብሎ ሕጉን አክብሮ ይኖራል፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ላይ ተመሳሳይ ነገር ሲተገበር አቃቂር የሚያወጣውና በየማኅበራዊ ሚዲያ መሳለቂ የሚያደርገው ነገር አይገባኝም። እነዚህ የምናደንቃቸው አገራት ሕዝብ ካለው ዲሲፒሊን በተሻለ ያገራችን ሕዝብ በሕግ ለመመራትና ትክክል ያልሆነን ነገር ትቶ ለሕግ ለመገዛት የሚቀልለው ነው፤ ነገርግን ቆሻሻ ጥሩ ነገር ይመስል የኖርንበት የተበላሸ መስመር እንዲቀጥል፤ ለዛፎች ምንም ትኩረት ሳይሰጥ ሲገጩም ገጪዎች በነጻነት እንዲያልፉ ከተደረገ አውሮጳንና አሜሪካንን እያደነቅን መኖር ነው፤ ይህ ደግሞ በራስ ላይ መሳቅ ነው” ብለዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply