መሰላል
መሰላል ለመውጣት
አለው ትልቅ ብልሃት፡፡
የላዩን ጨብጦ፣
የታቹን ረግጦ፣
ወደላይ መመልከት፡፡
እጆችን ዘርግቶ በኃይል መንጠራራት፡፡
ጨብጦ መጎተት የላዩን!
ላዩ ታች እንዲሆን!
አንድ ባንድ እየረገጡ፣
መሰላል የወጡ፡፡
ብልሆች የማይጣደፉ፣
ሞልተዋል በያፋፉ!
ዘርግተው የጨበጡትን መርገጥ፣
የመውጣት ሕግ ነው የማይለወጥ
ሲወርዱ ግን ያስፈራል፤
የረገጡትን ያስጨብጣል፡፡
(መስፍን ወልደማርያም፣ እንጉርጉሮ፣ 1967)
yeKanadaw kebede “በሳቅ ፍርስ አሉ” በሚል ርዕስ ላቀረቡት የግጥም ጨዋታ ዱባለ፣ በለው እና dawit ለጨዋታው ምላሽ ስለሰጣችሁ ከልብ እናመሰግናችኋለን፡፡ የጨዋታውን ደራሲ yeKanadaw kebede እንዲሁ፡፡ ስለ “መሰላል”ስ ምን ትላላችሁ? እስቲ ጨዋታውን አምጡታ!?
በለው ! says
********************
መሰላልን የወጡ
እንዳይረሱ እንዴት እንደወጡ
ሲጀምሩ ጨብጠው እረግጠው
ግራ ቀኝ እጃቸውን ዘርግተው
የሚደርሱበትን እየማተሩ
አንገት ሳያዟዙሩ ይወጣሉ እንደፈሩ
ከጫፍ መድረስ አይቀር
ደግሞ ሲውርዱ ማቀርቀር
ከታች ደግፎ ያበረታታቸው
ይገረማል ይጨነቃል
ከላይ ወደታች ያዩታል
ቀስ ብላችሁ አይዟችሁ ውረዱ ይላቸዋል
እንደወጡ መቅረት የለ ተመልሶ ያገኛቸዋል
በእርግጥ ተጨብጦ የተረገጠው
ተረግጦ የተጨበጠው
የሁሉ መወጣጫ መሰላል የሆነው
በተራው ደስ አለው
ለካስ ይህ ሁሉ የተፈጥሮ ውጣ ውረድ ነው።
*************
ከሀገረ ካናዳ ከሰላምታና ምስጋና ጋር በለው!።
ዱባለ says
መስላል ነው መወጣጫ እላይ መስቀያ
ከጫፍ ሆኖ ሁሉን ማያ
እጅግ በጣም አርቆ ማስተዋያ
ለባለ እጅ ለአዋቂ ባለሙያ
ካላቆሙት አስተካክሎ በጠንካራ መደገፍያ
ለዝንጉ አይሆንም ለገልቱ ማረፊያ
ይስደዋል ወደ ታች ያወርደዋል ዘብጥያ
ለአላፊው ለአግዳሚው ለተረሳው መሳለቂያ::
አሥራደው (ከፈረንሳይ) says
አጉል መንጠላጠል በመሰላል መውጣት፤
ከሆነ ፈሊጡ ተሰቅሎ ለመቅረት፤
እንዲህ እንደዋዛ ሲቀናጡ የወጡት፤
ወደታች ሲጎትት የመሬቷ ስበት ፤
ሆኖ ያስቸግራል ቁልቁለቱ አቀበት ::
መሰላል የሚሉት መወጣጫ ነገር፤
ሲወጡ ይመቻል አያዳልጥ እግር፤
ግን !
ካልተስተካከለ እታች ካለው በምድር፤
መውረጃ ያሳጣል በድንገት ሲሰበር ::
yeKanadaw kebede says
መልካም መዳላድል ከተሠራላቸው
ምሣርና ሸክም ካላስመረራቸው
ሰውና መሰላል አንድ ባሕሪ አላቸው
መዶሻና ሚስማር የያዘውን ሁሉ
‘ምሁር ነው’
‘ጀግና ነው’
‘መላክ ነው’……እያሉ
ከዳመና በላይ ሰውን ይሰቅላሉ