አጠገብ ያሉ ሕንፃዎች ውስጥ የሚኖሩ እንዲለቁ ተነገራቸው
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ለማድረግ ስምምነት ሊያደርግ ነው
በግዙፉ የጀሞ የጋራ መኖሪያ ሕንፃዎች መንደር ውስጥ በአንድ በኩል በመስመጥ ላይ ከሚገኘው ኮንዶሚኒየም ሕንፃ ግራና ቀኝ የሚገኙ ሕንፃዎች ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች ከሕንፃው እንዲለቁ ተነገራቸው፡፡
በሁለቱ ሕንፃዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ከሕንፃዎቹ እንዲለቁ የተጠየቁት በክፍለ ከተማው የቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት አማካይነት መሆኑን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የውሳኔው መነሻ ወደ አንድ ጐን በማዘንበል ላይ የሚገኘው ሕንፃ አጠገብ ያሉት ሁለት ሕንፃዎች ተመሳሳይ ችግር አለባቸው በሚል ቢሆንም፣ በሕንፃዎቹ ላይ በዓይን የሚታይ ችግር መኖሩን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱ ሕንፃዎች ተመሳሳይ መሰነጣጠቅ በውስጥ አካላቸው ቢኖርም፣ መሰነጣጠቁ መቼ እንደተፈጠረ በእርግጠኝነት መናገር የሕንፃዎቹ ነዋሪዎች አይችሉም፡፡ በጉዳዩ ላይ መረጃ እንዲሰጡ የአዲስ አበባ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ካሣ ወንድሙ ተጠይቀው፣ ስለተጠቀሱት ሕንፃ ነዋሪዎች የሰሙት ነገር እንደሌለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ነዋሪዎቹ በክፍለ ከተማው እንዲለቁና ተለዋጭ መኖሪያ ቤት እንዲወስዱ እንደተነገራቸው ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
ችግር በታየበት ሕንፃ ላይ ይኖሩ የነበሩ ሁሉም ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት ተለዋጭ ቤት እንደተሰጣቸው ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በሕንፃው ላይ የተፈጠረው ችግር እንዲጠና በዚህ ሳምንት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ውል እንደሚፈረም ያስረዱት አቶ ካሣ፣ ጥናቱ የጂኦ ቴክኒካል፣ የኮንትራክሽንና ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን እንደሚያካትት አረጋግጠዋል፡፡
ጥናቱ ችግር ባለበት አንድ ሕንፃ ላይ ብቻ የሚከናወን ሳይሆን በጠቅላላ የጋራ መንደሩ ላይ እንደሚሆንም አስረድተዋል፡፡ (ሪፖርተር)
Leave a Reply