አቶ ጀዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ በፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ኦሮሚያ ሚድያ ኔትወርክ ዘገበ። ኦሮሚያ ሚድያ ኔትወርክ ከደቂቃዎች በፊት በሰራው ዘገባ እንዳለው ጀዋርን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በተደረገው ጥረት የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ኃይሎች ከፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር።
በሁለቱ ኃይሎች መካከል በተፈጠረው ፍጥጫ ጉዳት ስለመድረሱ የዘገበው ኦኤምኤን ተጨማሪ ማብራሪያ ግን አልሰጠም። የፌዴራል የጸጥታ አስከባሪዎች ኃይል ጨምረው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራሮችን በቁጥጥር ሥር እንዳዋሉ የቴሌቭዥን ጣቢው ዘግቧል።
ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ጀዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ «ለጊዜው የታሰሩበት ቦታ አልታወቀም» ብሏል። በውጭ አገር የተመሠረተው እና አቶ ጀዋር መሐመድ በኃላፊነት ሲመሩት የነበሩት ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ የአዲስ አበባ ስቱዲዮ መዘጋቱ ተረጋግጧል።
የኦሮሚያ ሚድያ ኔትወርክ የአዲስ አበባ ስቱዲዮ ሰራተኞች በፌዴራል የጸጥታ አስከባሪዎች መያዛቸውን በኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገፁ ባሰራጨው መረጃ አስታውቆ ነበር። የቴሌቭዥን ጣቢያው ሰራተኞች የት እንደተወሰዱ እንደማይታወቅ ገልጿል።
የኦሮሚያ ሚድያ ኔትወርክ የድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ከተሰማበት ቅፅበት ጀምሮ በተከታታይ በኩነቱ ላይ አተኩሮ ሥርጭት ሲያከናውን ቆይቷል።
የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ
Leave a Reply