መግቢያ
በዚህ አርዕስት ላይ ለመጻፍ ከአሰብኩ ረዥም ጊዜ ሆነኝ። እንደሚታወቀው አንድ ጥናታዊ ጽሁፍ ለማቅረብ ቀላል አይደለም። የመንፈስ ርጋታን የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን፣ ለአንባቢ የሚቀርበው ጽሁፍ ከርስ በርስ ቅራኔዎች የተላቀቀና አሳማኝ እንዲሆን አድርጎ ለመጻፍና ለማስነበብ ረዥም ጊዜን ይፈጃል። ብዙ ዕውቀትንና ምርምርን ይጠይቃል። ተመራምሮና የተለያዩ አስተሳሰቦችን አወዳድሮና አመዛዝኖ ለአንባቢ አንድ የሚያረካና እንደመመሪያ ጥናት ለማቅረብ ረዥም ጊዜ ብቻ ሳይሆን ቢያንስ የሶስትና የአራት ሰዎችን የስራ ክፍፍል ይጠይቃል። አንድ ሰው ብቻ የሚጽፍ ከሆነ ደግሞ ቢያንስ የሶስት ወር ዝግጅት ማድረግ አለበት። በተጨማሪም በኢንስቲቱሽንና በገንዘብ የሚደገፍ መሆን አለበት። በተለይም ለአገር ዕድገትና ነፃነት ተብሎ የሚጻፍ ጽሁፍና የፖለቲካ ሀተታ በአቦ ሰጡኝ የሚቀርብ ሳይሆን ብዙ ጥንቃቄን ይጠይቃል። ለአንባቢው ትክክለኛ ዕውቀትና በመረጃ የተረጋገጠ ኢንፎርሜሽን ማቅረብ ያስፈልጋል። ኢንፎርሜሽኑ ወደ አንድ ወገን ብቻ የሚያደላ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ከዚህ ስነሳ ለተለያዩ የኢትዮጵያ ድህረ-ገጾች የሚቀርቡ ኢንፎርሜሽኖች ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል። በተለይም ዕውቀትን ያዘሉ ቢሆኑ ለትግላችን ያመቻሉ። ይህን ስል ግን እኔ የተሻልኩ እጽፋለሁ ለማለት ሳይሆን፣ ቢያንስ የኔን ብቻ እንኳ ከሌሎች ኤክስፐርቶች ጋር ሳወዳድረው በብዙ እጅ ያንሳል። ከዚህ በመነሳት ወደ ዋናው ቁምነገር ልግባ።
እንደሚታወቀው በአገራችንም ሆነ አብዛኛውን ጊዜ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ያለው ሁኔታ እያሳሰበንና እያስጨነቀን መጥቷል። ተስፋ የተደረገባቸውም የጥቢው አብዮት ተካሄደባቸው በሚባሉ አገሮች ውስጥ፣ ቱኔዚያ፣ ሊቢያና ግብጽ ያለው መተረማመስና መፋጠጥ፣ በተለይም ደግሞ የእስልምና ሃይማኖት አክራሪ ቡድኖች ዐይን ባወጣ መንገድ ሙሉ በሙሉ ስልጣንን በመቀዳጀትና፣ የእስልምናን ሃይማኖት እነሱ በፈለጉት መሰረት ተርጉመው ኢንስቲቱሽናላዊ ለማድረግና፣ ይህንን አካሄድ በሚቃወሙ ሊበራሎች በሚባሉት መሀከል የሚካሄደው ፍጥጫ አቅጣጫውን እየሳተ ነው። እንደቱኒዚያ በመሳሰሉት አገሮች ውስጥ በጠራራ ጸሀይ አክቲቢስቶችን መግደሉ የቀጠለ ሲሆን፣ ግብጽ ደግሞ በሚሊታሪውና በሙስሊም ብራዘር ሁድ መሀከል ያለው መፋጠጥና የርስ በርስ መተላለቅ ቀጥሏል። ይህ ሁኔታ በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ህይወት ላይ፣ በኢኮኖሚውና በህዝቡ የህሊና አወቃቀር ላይና፣ በየቤተሰቡ የኑሮ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እያመጣ ነው። በተለይም ዋና ገቢያቸውን በቱሪዝም ላይ የገነቡት ቱኒዜያና ግብጽ በጎብኝዎች ቁጥር ዝቅ እያለ መሄድ የተነሳ በዚያ የሚተዳደሩት ሆቴል ቤቶችና የቡና ቤቶች፣ እንዲሁም የመዋኛና ልዩ ልዩ የቱሪስት ትዕይንቶች ገቢያቸው በከፍተኛ ደረጃ እየቀነስ መጥቷል። የብዙ ቤተሰቦችም ኑሮ እየተቃወሰ በመምጣትና፣ በኑሮ ውድነትም አብዛኛው ህዝብ እየተሰቃየ ለመሆኑ ወደ ውጭ የሚመጡት ዜናዎች ያረጋግጣሉ።
ወደ አገራችን ስንመጣ ከሃያ አንድ ዐመት በላይ በምዕራቡ የኢምፔሪያሊስት ዓለም እየተደገፈ አገራችንን የሚቆጣጠረው የወያኔ አገዛዝ አገራችንን የባሰውኑ እያተረማመሳት እየመጣ ነው። የአገራችን ህዝብ፣ ከገበሬው እስከነጋዴውና፣ እንዲሁም እስከ ኢንዱስትሪ ባለቤት እስከሆነው ድርስ፣ በተጨማሪም በአስተማሪዎችና በልዩ ልዩ ሙያ ላይ ተሰማርተው በሚሰሩ ስዎች ላይ የሚደርሰው ጫናና ማሰፈራሪያ ህብረተሰቡ እየተዋከበ እንዲኖር እያደረገው ነው። ከፍተኛ አለመረጋጋት ተፈጥሯል። ራሱ አገዛዙ በፈጠረው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ የተነሳ በሃይማኖት መሪዎች ላይ የሚያደርገው ጫናና እስራት እንዲሁም ግድያ ወደ ፊት አገራችን ወዴት እንደምታመራ አስቸጋሪ ሁኔታ እየፈተጠረ ነው። አክራሪዎችና አሸባሪዎች የሚባሉ ካሉ ራሱ አገዛዙ በተከተለውና በሚከተለው የተበላሽ የኢኮኖሚና ፀረ-ዲሞክራስያዊ እርምጃ ሊወለዱና ሊዳብሩ የሚችሉ እንጂ ራሳቸው የሃይማኖት መሪዎች እንዳልፈጠሩት በግልጽ ይታወቃል። አገዛዙ ከአሜሪካን ኤምፔሪያሊዝም ጋር ያደረገው ያልተቀደሰ ጋብቻ አገራችንን የአክራሪዎችና የአሸባሪዎች መፈልፈያ ሊያደርጋት እንደሚችል ካሁኑ በግልጽና በተራ ሎጂክ ማረጋገጥ ይቻላል።
ያም ሆነ ይህ፣ በደርግ ዘመንም ሆነ በዚህ አገዛዝ ከሃያ አንድ ዐመት ጀምሮ የሚካሄደው ፖለቲካ በርግጥም ፖለቲካ ነው ወይ? ፓለቲካስ በዚህ መልክ መካሄድ አለበት ወይ? ማለትም ግብ ግብ መፍጠሪያ፣ ስልጣንን የጨበጡ ጥቂት ስዎች ወይም ቡድኖች እንደፈለጉ አንድን ማህበረሰብና ህብረተሰብ እንደፈለጉ የሚበውዙበት? ፓለቲካ ሲባል በየጊዜው የሚለዋወጥ፣ ወይስ በፍልስፍና መርሆች ላይ የተመረኮዘና ስትራቴጂያዊ ዓላማ ያለው? ፓለቲካን ለማካሄድ ወይም አገርን ለመምራት የግዴታ በቡድን ቡድን እየተደራጁና ይኸኛውን ወይም ያኛውን ረዕዮተ-ዓለም እናራምዳለን እየተባለ ትርምስ የሚፈጠርበት ወይስ ፖለቲካ ሲባል ሳይንሳዊ ባህርይ ያለውና ታሪክን መስሪያ መሳርያና መመሪያ? በአገራችንም ሆነ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ተብለው በሚጠሩ፣ በተለይም በአፍሪካ ምድር የፖለቲካ ትርጉም ከፍልስፍናና ከሳይንስ አንፃር በሚገባ ስለማይተነተንና ስለማይጠና፣ እንዲሁም ደግሞ ለህዝቡ በትምህርት መልክ ስለማይቀርብ፣ አብዛኛው ፖለቲካን የሚረዳው የቁማር ዐይነት ጫዎታ፣ የዱርዬዎች ወይም ደግሞ የዚህ ወይም የዚያኛው ኃያል መንግስት ጥቅም አስጠባቂ ነን ባዮች የሚፈነጥዙበት መድረክና መሳሪያ ሆኗል ማለት ይቻላል። በጣም የሚያሳዝን ስራ እየተፈጸመ ነው። ወደ ሰፊው የፖለቲካ ትርጉም ሀተታ ከመግባቴ በፊት ይህንን በቅጡ ለመረዳት በደርግ ጊዜ የነበረውን የፖለቲካ ትርጉምና ድርጊት ግንዛቤ በመጠኑም ቢሆን እንመለከት።
በአብዮቱና በደርግ ዘመን የነበረው የፖለቲካ ግንዛቤ!
አብዮቱ ከመፈንዳቱ በፊት የተማሪው እንቅስቃሴ የሚመራበት አንድ ዋና መመሪያ ነበረው። ይኸውም ተማሪና አስተማሪ ተማር፣ ወደ ህዝብም በመሄድ ከነሱ በመማርም መልሰህ አስተምራቸው የሚል ብልህ መመሪያ ነበር። ይህንን መሰረት በማድረግ ህዝቡን በማደራጀትና የፖለቲካ ነቃቱን በማሳደግ አዲሲቱን ኢትዮጵያ መገንባት ይቻላል የሚል ግምት ነበር። በተለይም ፖለቲካዊ አደረጃጀትና፣ ሃሳብን መግለጽ ባልተለመደበትና የፍጹም ሞናሪኪ አገዛዝ በሰፈነበት እንደ ኢትዮጵያ በመሰለ አገር ይህ ዐይነቱ ቅስቀሳና እርምጃ ለአዲሲቱ ሪፑብሊክ መመስረት አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር የታወቀ ነበር። እንደዚህ ዐይነቱን በዚያን ወቅት በንጹህ አስተሳሰብ የተነደፈውንና እንደመምሪያ የተወሰደውን ትክክል አልነበረም፤ ሶሻሊስታዊ ወይም ከኮሙኒስታዊ አስተሳሰብ ጋር የተያያዘ ነው የሚል ካለ ወይ በጊዜው የነበረውን የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታንና፣ ከትውልድ ትውልድ ሲዋረድ የመጣውንና፣ ለአዲስ አስተሳሰብና ለጭንቅላት ተሃድሶ አስቸጋሪ የነበረውን የህብረተሰብአችን ልማዳዊ አወቃቀር አልገባውም፣ ወይም ዝም ብሎ ጥላቻን የሚያናፍስ ብቻ ነው ብሎ ከመናገር በስተቀር ሌላ ነገር ማለት አይቻልም።
እንደሚታወቀው ወፍ እንደ አገሩ ይጮሃል የሚባል ቁም ነገር አባባል አለ። በጊዜው የተማሪው እንቅስቃሴ የፖለቲካን ትርጉም በዓለም ላይ ከሚናፈሰውና ከአገራችንም ተጨባጭ ሁኔታና፣ የምሁር ንቅታ-ህሊና ሁኔታ ተነስቶ እንደመመሪያ የነደፈው ስለሆነ ብዙም ጭቅጭቅ ውስጥ ሊከተን አይችልም። ምክንያቱም ቀላል ነው። ቀደም ብሎም ሆነ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን በጊዜው አዲሱ ትውልድ ከልዩ ልዩ የፖለቲካ አስተሳሰቦችና ፍልስፍናዎች ጋር ለመተዋወቅና ለመማር ዕድል ማግኘት ስላልቻለ የግዴታ በጊዜው እጁ ውስጥ በወደቀውና ትክክል ነው ብሎ ያመነውን ብቻ ነበር እንደ ፖለቲካ ትግል መመሪያ መውሰድና ማስፋፋት የሚችለው። ችግሩ ግን እዚህ ላይ ሳይሆን አብዮታዊው እንቅስቃሴና ትምህርቱ ረጋና በሰከነ መልክ መሰጠቱ ቀርቶ፣ በተለይም ደግሞ ብሄራዊ ባህርይ እንዲኖረውና የሁሉም መመሪያ እንዲሆን ለማድረግ ያለመቻሉ ላይ ነበር። ይህም ቢሆን የተማሪው እንስቃሴ መሪዎች ድክመት ብቻ ሳይሆን የአገራችን የህብረተሰብ አወቃቀርና ትምህርቱ ብሄራዊ ባህርይ ስላልነበረውና፣ አገር የሚለው ፅንሰ-ሃሳብም በተለይም በኤሊቱ ዘንድ የታመነበትና ከጭንቅላት ጋር ተዋህዶ በጋራ ለመነሳትና አገርን ለመገንባት እንደመመሪያ ለማስተማር የማይቻል በመሆኑ ብዙ ነገሮች መስመራቸውን እየለቀቁ አንዲመጡ ከፍተኛ አስተዋዖ አድርጓል። ሂደቱን በአብዮተኛና በፀረ-አብዮተኛ በከመከለልና፣ የአብዮቱን መመሪያ ያለተቀበለ ደግሞ እንደ ፀረ-አብዮተኛ እየተፈረጀበት ወደ ማያስፈልግና ስራን ወደማያሰራ ግብ ግብ ውስጥ መግባቱ በአገራችን የሰፈነውን በጣም ደካማ መንፈሳዊ አስተሳሰብና የጭንቅላት ተሀድሶ ጉድለት የሚያሳይ ነው።
እጅ ላይ የወደቀውን ወርቅና አልማዝ እንዲባክን ወይም ደግሞ ብልጣ ብልጥ ነን የሚሉ እንዲሻሙት በማድረግ አብየታዊው ሀብት እንዲወድም የተደረገበት ሁኔታ በዓለም ታሪክ ውስጥ ተሰምቶ አይታወቅም። አብዮት ተካሂዶባቸዋል የሚባሉትን አገሮች የፖለቲካ ሁኔታ፣ ከቀድሞ ሰቭየት ህብረት እስከቻይናና እስከቬትናም ድረስ እንዲሁም የሌሎች አገሮችን ሁኔታ ስንመለከት እንደዚህ ዐይነት ሪፎርም ተደርጎ በህዝብና በአገር ላይ አምጾ ወደ ብጥብጥና አገርን ወደ ማፈራረስ የተደረሰበት እንደ ኢትዮጵያ የመሰለ አገር የለም። በሶቭየትም ሆነ በቻይና በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ቢያልቅም ብሄራዊ ነፃነታቸውን የሚያናጋና ለስራ እንቅፋት የሆነ ሁኔታ ሊፈጠርባቸው አልተቻልም። በነዚህ ሁለቱ አገሮች የአብዮትና የፖለቲካ ግንዛቤ እንደ ኢትዮጵያ ዐይነት ቢሆን ኖሮ ሁለቱም አገሮች የቴክኖሎጂና የኑዩክላር ቦንብ ባለቤት መሆን ባልቻሉ ነበር። ህዝቦቻቸውን መመገብ ባልቻሉ ነበር። ከህብረተሰብአቸው አወቃቀርና የባህል ተሀድሶ ጉድለት የተነሳ በሁለቱም አገሮች የደረሰውን ግፍ ወደ ጎን ትተን፣ ሁለቱም አገሮች አገራቸውን በመካድና በማፈራረስ ሊታሙ በፍጹም አይችሉም። ይህም የሚያሳየው በሁለቱም ትልቅ አገሮች የነበረው የፖለቲካ ንቃተ-ህሊናና ግንዛቤ፣ እንዲሁም የተከበረ አገር የመመስረቱ ጉዳይ ከኛው ጋር ሲወዳደር እጅግ ልቆ የሚገኝ ነበር ማለት ይቻላል። የአገራችንን ሁኔታ ስንመለከት የሚያሳፍረው ነገር ምሁርና ታጋይ ነኝ ባዩ አውቆም ሆነ ሳያውቅ ለስልጣን ሲል ብቻ ያለ የሌለውን ኃይል በማጣመርና በከፍተኛ ቁጣ በመነሳሳት በአገራችን ላይ መዝመቱና ሁኔታውን ማተረማመሱና ህዝቡም እንደገና እንዳይነሳና ለነጻነት እንዳይታገል ማድረጉ ነው።
የዚህ ሁሉ ትርምስ ምክንያቱ ምንድነው? የብዙዎችችን ችግር የአንድን ነገር ሁኔታ በጥቁርና በነጭ መመልከቱ፣ ወይም ደግሞ መተርጎሙ አንድን ነገር ከብዙ ሁኔታዎች አንጻር እንዳንመለከትና እንዳንገመግም አድርጎናል። እንደሚታውቀው በዕውቀት ውስጥ ፍልስፍና፣ የህብረተሰብ ሳይንስና ስነልቦና ወይም ሳይኮሎጂ የሚባል ነገር አለ። ሌሎችም አሉ። ለጊዜው በነሱ ላይ አናተኩርም። ያም ሆነ ይህ እነዚህ ነገሮች ዝም ብለው የፈለቁ ሳይሆኑ መመሪያዎች ብቻ ሳይሆኑ ከሰውነታችን ጋር በመዋሃድ አዳዲስ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ እንደመመራመሪያ መሳሪያ የሚያገለግሉን ናቸው። ይህም ማለት ምን ማለት ነው ? እያንዳንዱ ህብረተሰብ ወደ አንድ ዓላማ ወይም ድርጊት ከመምራቱ በፊት በህብረተሰብ ሳይንስ መገምገም አለበት። ይህንን በቀላሉ ለማስረዳት፣ ሺለር የሚባለው ታላቅ የድራማ ሰውና ደራሲ፣ ህብረተሰብአዊ ክንዋኔ ወይም ሶሻላይዜሽን ፕሮሴስ እያለ የሚናገረው ነገር አለ። በመሰረቱ የሰው ልጅ እንስሳ ነው። ከእንስሳ የተለየ ባህርይና የማሰብ ኃይልም ቢኖረውም አብዛኛውን ጊዜ ከእንስሳ የተለየ ነገር ሊሰራ የማይችልበት ሁኔታ አለ። እያሰበና ተፈጥሮን በሚገባ እየቃኘ ኑሮውን በስነስርዓት ለማደራጀት የማይችልበት ሁኔታ በመፍጠር አዕምሮው ይጋረዳል። ሺለር የሰውን ልጅ ታሪክ በሚገባ ካጠና በኋላ የሰው ልጅ ታሪክን ለመስራትና ለመሰልጠን የረዥም ጊዜ ሶሻላይዜሽን ፕሮሴስ እንደሚያስፈለገው ያስረዳል። አንድ ቦታ ላይ እንደዚህ ይላል። ከአርስቲቶለስ ጀምሮ ስለዲሞክራሲ ሰምተናል፣ አሁንም ቢሆን ከአረመኔያዊ ባህርያችን አልተላቀቅንም በማለት የነበረበትንና ዛሬም ያለውን ሁኔታ በሚገባ ይነግረናል።
ወደ አገራችን ሁኔታ ስንመጣ የአገራችን ወደ ኋላ መቅረት፣ በሊትሬችር፣ በፍልስፍና፣ በከተማዎች ግንባታ፣ በዕደ-ጥበብ መስፋፋት፣ በቲያትር ወዘተ… የሚገለጹ ዕድገት ባለመታየቱና ባለመኖሩ የኛም ጭንቅላት በአርቆ አሳቢነት መመዘኛ ሊታነጽ አልቻለም። በተለይም በጥራዝ ነጠቅነት ትምህርት የሰለጠነው ኤሊት የሚባለው ዘመናዊነትን የተረዳው በአውቅሁኝ ባይነትና ከአመጽ ጋር በማያያዝ እንጂ ሰፋ ካለ የስልጣኔ ሂደት ጋር ባለመሆኑ የየካቲቱ አብዮት ሲፈነዳ አገራችንን ወደትርምስ ውስጥ ለመክተት ለእንደዚህ ዐይነቱ ኤሊት ቀላል ነበር። የሆሜርን ድርስት ወይም ኤፒክ የተረጎሙ ወይም የተነተነቱን በኢሊያስና በኦዴይሲዩስ መሀከል ያለውን ልዩነት ሲናገሩ፣ በኢሊያስ ዘመን የነበረው የሰው ልጅ አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ የሰውን ልጅ ባህርዮች (attributes) ያላዋሀደ፣ ማለትም ፍቅርን፣ ስሜትን፣ ለሌላው ማሰብን፣ መሳቀቅን፣ መጸጸትንና በተለይም ደግሞ ቆንጆ ቆንጆ ነገሮችን መመኘት ከጭንቅላት ወይም ከሰውነቱ ጋር ያላዋሃደ በመሆኑ ስራው ሁሉ በስሜት ላይ የተመረኮዘና ወደ አመጽ የሚያመራ ነበር የሚል ነው። ወደ ኦዴይስዩስ ስንመጣ ደግሞ ኦዴይስዩስ ከአስር ዐመት የብኩን ጉዞና ጦርነት በኋላ እንደገና ወደ ተወለደበትና ወደ አደገበት፣ እንዲሁም ወደቤተሰቡ ያደረገውን ጉዞና ቀስ በቀስም ሰው መሆኑን የተረዳበት፣ የወንድማማች ጦርነት ትርጉመ-ቢስ መሆኑን የተገነዘበበትና፣ የሰው ልጅም የኑሮ ትርጉም ይህ ዐይነቱ የመባከንና የጦርነት ኑሮ አለመሆኑን የተማረበት ሁኔታን እንመለከታለን።
አሁንም ወደ አገራችን የአብዮትና የዛሬው ሁኔታ ስንመጣ ይህ ዐይነቱ የአውሬነት ባህርይ፣ ከሰለጠንና አገርን ከሚያስገነባ መመሪያና ፍልስፍና ይልቅ ወደ ጦርነት ማምራቱና መተላለቁ ሆሜር በድርሰቱ ውስጥ ያስቀመጠውን የሞኞች ስራ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። ይህም ማለት በአብዮት ዘመን አገርን ለመገንባት አንድ ሆኖ በአዲስ አስተሳሰብ ከመነሳት ይልቅ ፖለቲካን መረዳትና መስበክ የተጀመረው በቡድን ቡድን እየተደራጁ አገርን ማመስና ማተረማመስ ነው። ተራማጅ የሚባለው ኃይል በዚህ ዐይነቱ ሆሜራያዊ የጅሎች ጫዎታ ከተላለቀ በኋላ ደርግና በሱ አካባቢ የተሰበሰቡ አድርባዮችና ካድሬዎች በሙሉ ፓለቲካንና አብዮትን የዱርዬዎችና የአረዳዎች መጫወቻ ነው ያደረጓቸው። አንዱን ማቅረብ ሌላውን ማራቅ፣ ለምሳ ለማድረግ ያሰቡንን ቁርስ አደርግናቸው የሚለውና የፍየል ወጠጤዎች ዝማሬ ከዚህ ዐይነቱ ፖለቲካን በተሳሳተ መልክ በመተርጎሙና ግንዛቤ ውስጥ በገባ አስተሳሰብ መመሪያ በመደረጉ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ስልጣን ለማግኘት ሲባል ጓደኛን እየጠቆሙ አሳልፎ መስጠትና እንዲገደል ማድረግ፣ ቀስ በቀስም ድርጅቶች እንዲፈራርሱ ማድረግ በጊዜው የነበረው የፖለቲካ ግንዛቤ የቱን ያህል የተበላሸ እንደነበር ነው የሚያረጋግጠው። በተጨማሪም በአጠቃላይ ሲታይ የኛ የኢትዮጵያኖች ጭንቅላት በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ ነው መገንዘብ የሚቻለው። ስለዚህም ፖለቲካ፣ አንድ ጊዜ የሚቻለውን ነገር ብቻ ማድረጊያ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከተጨባጩ ሁኔታ ጋር እየታየ የሚካሄድበት፣ ካሊያም ደግሞ ሙሉ በሙሉ የጮሌዎችና የዱርዬዎች መሳሪያ በመሆን ወደ አገር አፍራሽነት የተለወጠበትን ሁኔታ ስንመለከትና፣ ማንም እየገባ የጨፈረበትን ሁኔታ ስንመረምር ትላንትናም ሆነ ዛሬ የፖለቲካ ግንዛቤአችን የቱን ያህል ኮመን-ሴንስ የጎደለውና በዲያሌክቲክና በሳይንስ መነጽር እየተመረመረ አገርን ማስተዳደሪያ መሳሪያ መሆን ያለመቻሉን ነው። ስለሆነም ፓለቲካ ታክቲካዊና ስትራቴጂያው በሚባሉት ውስጥ እንደየሁኔታው የሚቀየስ እንጂ፣ ስትራቴጂያዊ ወይም ከረዥም ጊዜ ዓለማ በመነሳት የሚታቀድና ሳይንስ በመሆን ታሪክን መስሪያና አገርን መገንቢያ አይደለም ተብሎ ግንዛቤ ውስጥ ከተገባ ዘመን አልፎታል። ነገሩን ይበልጥ ለማብራራት፣ አንዳንድ ተራማጅ ድርጅቶች ውስጥ የነበረው ግንዛቤ ከሌላው ድርጅት ጋር አብሮ ለመስራት የሚቻለው የራስን ድርጅት ከማጠንከርና ሌላውን ከማዳከም ታክቲክ በመነሳት እንጂ በውይይት በማሰመንና በመተማመን ወደ አንድ ስትራቴጂያዊ ዓላማ ለማምራት አልነበረም። ይህ ሁኔታ ደግሞ ደርግን ለመጣል ሲባል ብቻ ተራማጅ ነኝ የሚለው ኃይል አድሃሪው ከሚባለው ወይም አብዮቱን ከሚቀናቀነው ጋር ጊዜያዊ ትብብር በማድረግ ራሱም የተዳከመበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ይህ ዐይነት በፕሪንሲፕልና በፍልስፍና እንዲሁም ደግሞ ሌላውን በጥሞና በማስተማር ላይ ያልተመረኮዘ ፖለቲካ የብዙዎችን ድርጅት ምንነት አረጋግጧል። ትግላቸው ሁሉ ከስልጣን አልፎ እንደማይሄድ አሳይቷል።
ከዚህ ስንነሳ ትላንትም ሆነ ዛሬ ፖለቲካ ትርጉም የተሰጠው ስልጣንን ከመጨበጥ ጋር ብቻ ነው። ሌኒን በተሳሳተ መልክ ያስፋፋው አጉል አባባል አለ። ይኸውም የማንኛውም አብዮት ዋና ዓላማ ስልጣን መያዝ ነው የሚል እጅግ አደገኛ አባባል አለ።በሌላ ወገን ደግሞ ሺለር እንደሚያስተምረን አብዮት የሚባል ነገር የለም። ይህንንም የሚያስቡም የተፈጥሮን ህግ ያልተረዱ ብቻ ናቸው ይላል። በእሱ አባባልም ተፈጥሮ መዝለልን አታውቀም። እንደዚሁም ህብረተሰቦች ከአንድ የህብረተሰብ አኗኗር ወደ ሌላኛው ከመቅጽበት ሊዘሉ አይችሉም። ተፈጥሮ የራሷ ህግ እንዳላት ሁሉ፣ ማንኛውም ህብረተሰብ ተፈጥሮን የሚምስል የራሱ ውስጣዊ ህግ አለው። ይህንን ሳያጤኑ በስሜት ወይም ደግሞ ካለበቂ ጥናትና ምርምር የሚወሰዱ እርምጃዎች የመጨረሻ መጨረሻ ወደጥፋት ነው የሚያመሩት። በሌላ አነጋገር ማንኛውም ተፈጥሮአዊ ነገር ከአንድ ሁኔታ ወደ ሌላ ለመለወጥም ሆነ ለማደግ የረዥም ጊዜ ክንውን እንደሚያስፈልገው ሁሉ የህብረተሰብም ዕድገት ረጅም ጊዜ የሚፈጅና ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው። በመፈክር ጋጋታና በቀረርቶ የሚካሄድና የሚተገበር አይደለም። ሁሉም ነገር ወደ ጦር ሜዳና ወደ አብዮቱ በሚል አጉል መፈክር ህብረተሰብአዊ ለውጥ ማምጣት አይቻልም። ወይም ደግሞ ሰውን ሁሉ በማግበስበስና በጠላትና በወዳጅ ሰፈር እንዲሰለፍና እንዲፋጠጥ በማድረግ አብዮትን መስራት አይቻልም። እንደሚታውቀው የየካቲቱ አብዮት የሚባለው ነገር በዕቅድ የመጣ አይደለም። ግብታዊ ነው። ሳይታሰብ የመጣ ነው። ከአገዛዙ ድክመትና ከህብረተሰቡ ድህነትና ረሃብ፣ እንዲሁም ሌሎች ነገሮች ጋር በመዳመር ከመቅጽበት የፈነዳ ነው። ስለዚህም ስልጣንን መጨበጥ ካልሆነ በስተቀር አንድን ሁኔታ ወዲያውኑ መቀየር አይቻልም።
ያም ሆነ ይህ የየካቲቱን አብዮት ትርምስና የርስበርስ መተላለቅና አገርን ማፈራረስና እየጣሉ መሸሽ ስንመለከት ፖለቲካችን ሁሉ በሰፊ ጥናትና በዕምነት ላይ ያልተመረኮዘ፣ ፕሪንሲፕልና ፍልስፍና የጎደለው፣ ሳይንሰ-አልባ የሆነ፣ ብሄራዊ ጥቅምንና አንድነትን ከማስቀደም ይልቅ የፓርቲን አጀንዳ ያስቀደመ፣ በጋራ ዓላማ ላይና ሁሉንም ሊያሰባስብ በሚችል አመለካከት ላይ ያልተገነባ፣ አገርን ከሀፍረት ለማውጣት የግዴታ ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ግንባታ ያስፈልጋል የሚለውን መመሪያ የትግሉና የመመሪያው ዓላማ ያላደረገ፣ ስልጣን ላይ ለመውጣት ሲል እንደ አስፈላጊነቱ ከውጭ ኃይልም ጋር በመተባበር አገርን የሚያፈራርስ አካሄድ ነበር ማለት ይቻላል። ትግል የሚባለውም ጽንሰ-ሃሳብ በዚህ ክልል ውስጥ የሚሽከረከር ሲሆን፣ የመንፈስን የበላይነት ያላስቀደመና፣ በጽሞናና በውይይት ወይም ደግሞ በሳይንሳዊ ክርክር ለማሳማን ሳይሆን ጎልበትን ወይም አመጽን ያስቀደመ ነው። የማንኛውም የሰው ልጅ ኑሮ ሁሉ ከትግል ጋር የተያያዘ ቢሆንም፣ ትግል የሚባለው የኑሮ ፍልስፍና ከሽወዳ፣ ከማጭበርብር፣ ከአመጽ፣ በአጭሩ አርቆ አሳቢነት ከጎደለው ድርጊት ጋር የሚያያዝ ከሆነና እንደመመሪያ ከተወሰደ አንድ ቀን አጥፊ ይሆናል።
ከሃያ አንድ ዐመት ጀምሮ በአገራችን የሚካሄደውን ፖለቲካ የሚባለው የእነ አቶ መለስና የሌሎችን ጮሌዎችንም ጫዎታ ስንመለከት ዕውነቱን ለመናገር ከፈለግን ድርጊታቸው በሙሉ ሆሜር ከሶስት ሺህ ዐመት በፊት ከደረሰው የኢሊያስ ሁኔታና፣ ወይም ደግሞ ጆን ሚልተን ዘ ፓራዳይስ ሎስት(Paradise Lost) በሚለው እጅግ ግሩም ትምህርታዊ ኤፒኩ ውስጥ ከደረሰው የሞንስተር ወይም የጭራቅ ስራ ተነጥሎ በፍጽም ሊታይ የሚችል አይደለም። በዚያም ጊዜ ቡድናዊና ጎሳዊ አስተሳሰብ ነበር። በማዕከለኛው ዘመን ደግሞ የሃይማኖት ጭፍን አስተሳሰብ ሰፍኖ ፈላስፋዎችንና ሳይንቲስቶችን የሚያቃጥልበትና የሚያሳድድበት ዘመን እንደነብር ይታወቃል። የሆሜርን ስራ በሚገባ ያነበበው ፕላቶ የደረሰበትም የፖለቲካ ትርጉም መደምደሚያ፣ ፖለቲካ ወደ ጎሳነት ወይም ወደቡድናዊ ስሜትንት የሚለወጥ ከሆነ አንድ ህዝብ ሊወጣ የማይችለው ሁኔታ ውስጥ እንደሚወድቅ ያሳስባል። ከላይብኔዝ እስከ ሺለረና ጎተ፣ እንዲሁም ካንት ድረስና፣ በተለይም ደግሞ ከአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በኢንላይተንሜንት ምሁሮች የተደረገውን የጭንቅላት ትግልን ስንመለከት፣ ትግሉ ዝም ብሎ ከፍጹም ሞናሪኮዎች አገዛዝ ለማላቀቅና ሪፑብሊክን ለመመስረት ብቻ ሳይሆን፣ ከጎሳና ከሃይማኖትም የጸዳ ፖለቲካ ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግና ህዝብም እንዲረዳው ማድረግ ነበር። ስለሆነም ይህ ሶስተኛው የሰብአዊነት እንቅስቃሴ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ የካፒታሊዝምን ወይም የከበርቴውን የበላይነት ያረጋገጠበትን ሁኔታ እንመለከታልን። ይህ ሁኔታ፣ በተለይም ኢኮኖሚው ቀስ በቀስ እያደገና እየተስፋፋ ሲመጣ፣ በአንድ አካባቢ መሆኑ ብቻ ቀርቶ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ሲስፋፋ የተለያዩ ፓርቲዎች ብቅ በማለት ለሲቪል ሶሳይቲ መመስረት መንገዱን ያዘጋጃሉ። የጎሳና የከረረ የኃይማኖት አስተሳሰቦች በሳይንሳና በሰፊ ምሁራዊ እንቅስቃሴና ክርክርና ሎጂካዊ አቀራረብ ይተካሉ። ተገፍተው ይወጣሉ። የካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ስልት ኃያልነትን በመቀዳጀት የሰው ልጅ አስተሳሰብ ሁሉ ከኢኮኖሚ ጋር እንዲያያዝ ያደርጋል። ገንዘብ የሚባለው ነገር ሲስፋፋ ደግሞ የሰው ልጅ ዕድሉ እየሰሩ ገንዘብን ከማግኘትና ፍጆታን ከመጠቀም ጋር ይያያዛል።
እዚህ ላይ ለማለት የምፈልገው ነገር ምንድነው? ሬናሳንስንና ኢንላይተንሜንትን የማያውቀው ህብረተሰባችን በተራ ካፒታሊዝም ከተዘጋጀለት የቁሳቁስ አጠቃቀም ጋር ሲጋጭና የሞነቴሪ ኢኮኖሚ ሲስፋፋ ሃሳቡ የተሰበሰባና የተገለጸለት ሰፋ ያለና የሰከነ ምሁራዊ አንቅስቃሴ ከማበቡ ይልቅ ሁኔታው የተዘበራረቀበትና ወደ አመጽ የሚያመራ ኃይል ብቅ ማለት ቻለ። የፊዩዳሊዝምና የተዘበራረቀ የካፒታሊዝም መግባት ከፍተኛ የሆነ ውዥንብር በመፍጠር አመጽን ጋባዥ ሆኑ። ተራው ንዑስ ከበርቴ ብቻ ሳይሆን ራሱ ፍልስፍና የተማረውና ዶክትሬት የጨበጠው እንኳ ሳይቀር፣ ጥበብንና አርቆ አስተዋይነትን ከማስቀደም ይልቅ ወደ ጦርነት አመራ። ይህም የሚያረጋግጠው ወደ አገራችን የገባው ትምህርት ጭንቅላታችንን የማደስና የማነጽ ኃይሉ እጅግ ዝቀተኛ ስለነበር የጭንቅላታችንን የማሰብ ኃይል ክፍል ሊያዳብረውና ወደ አርቆ አሳቢነትና ከወገን ወይም ቡድነ-አልባ የሆነ ትግል ለማራመድ አላስቻለንም። የተወሳሰበን አስተሳሰብ እንድናዳብር አላስቻለንም። የአገራችንን የህብረተሰብ አወቃቀርና የዓለምን የፖለቲካ ሁኔታ በሰፊው እንድናጤን የሚያስል ዕውቀት አላስካነንም። ይህ ሁኔታ አብዮቱ ከተቀለበሰ ከሰላሳ ዐመት በኋላም ጭንቅላታችንን ይዞ የምንፈልገውንና የምናስበውን እንኳ በግልጽ እንዳንወያይበት እየተከታተለን ነው። ልክ ዛሬ የአሜሪካን የስለላ ድርጅት ስልካችንን፣ ኢሜይላችንና ኤንተርኔታችንን እንደሚቆጣጠርና እንደሚከታተል ሁሉ፣ ድሮ ታጋይ ነን ይሉ የነበሩ ድርጅቶች የድሮውን አስቸጋሪና አደገኛ ድርጊት በገሃድ እየተየወያየን ወደፊት እንዳንራመድ እያደረገን ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን አዲስ መጤው ኃይልም ወይም ቡድን ፖለቲካን ከርብርቦሽና ግብ ግብ ወይም ከቡድናዊነት ጋር በማገናኘት ለሰከነና ለትችታዊ ውይይት መንገዱን ሁሉ እየዘጋ ነው። ዛሬም እንደትላንትናው ፊዩዳላዊ አስተሳሰብ ሰፍኖ ይታያል። እጅግ በጠባብ አስተሳሰብ ውስጥ እዚያው በዚያው የሚንደፋደፍና የፖለቲካን ትርጉም ሳይረዳ ፖለቲከኛ ነኝ የሚል መድረኩን ሁሉ በማጥበብ የኢትዮጵያን ህዝብ የነፃነት ጥማትና የስልጣኔ ፍላጎት እያረዘመው ነው። እንደሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮችም በዘለዓለማውዊ ጨለማ ውስጥ ሳያውቀው እንዲኖር እያስገደደ ነው። ከዚህ ስነሳ ፖለቲካ ሳይንስ ነው ወይ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ወይም ለማብራራት ልሞክር።
ለመሆኑ ፖለቲካ ሳይንስ ነው ወይ?
እንደሚታወቀው ብዙ የትምህርት ዐይነቶች ሳይንሳዊ ባህርይ እንዳላቸው ይነገራል፤ ወይም በራሳቸው ሳይንስ ናቸው። የተፈጥሮ ሳይንስ፣ የሜዲካል ሳይንስ፣ የህሊና ሳይንስ፣ የህብረተሰብ ሳይንስ፣ የህግ ሳይንስ፣ የአርት ሳይንስ፣ የኮምፒዩተር ሳይንስ፣ የኢኮኖሚክስ ሳይንስ፣ የፖለቲካ ሳይንስ፣ ወዘተ… እየተባለ ይዘረዘራል። ተማሪዎችም ዩኒቨርሲቲ ተመዝግበው ሲገቡ እንደዝንባሌያቸውና እንደ ሪከርዳቸው ይህኛውን ወይም ያኛውን የሳይንስ ዐይነት ይማራሉ። በሌላ አነጋገር ሁሉም የትምህርት ዐይነት ከሳይንስ አንፃር በመመርመር ችግርን ለመፍታት፣ ወይም አንድ አዲስ ነገር መፍጠሪያ ወይም ደግሞ መመራመሪያ መሆኑን ተማሪው እንዲረዳው ይደረጋል ማለት ነው።
ለምሳሌ የተፈጥሮን ሳይንስ ስንወስድ የተፈጥሮን ምንነትና ባህርይ ለመረዳት ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዱ ነገርስ ለምን እንደሚጠቅም ለማወቅና ወደ ተግባራዊነት ወይም ወደ ጠቀሜታ ለመለወጥ ነው። ከኤምፔሪሲስት የሳይንስ ምርምር ሁኔታ ስንነሳ ደግሞ የሳይንስ ዋናው ዓላማው አንድን ነገር በጥብቁ መመልከት፣ በሃይፖቴሲስ ወይም በሙከራ አንድ ውጤት ላይ ለመድረስ ነው። ይህም ሆነ ያ ተባለ፣ የሳይንስ ዋናው ዓላማው በተቻለ መጠን የተፈጥሮን ህግ በመረዳት የሰውን ልጅ ኑሮ ለማቃላል አዳዲስና የተሻሉ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው። የሰው ልጅ በተፈጥሮ ላይ ብቻ ጥገኛ ሳይሆን አንድን ነገር ከአንድ ሁኔታ ወደ ሌላ በመለወጥ ብቻ ሳይረካ፣ አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠር በአዲስና በተሻለ ዓለም ውስጥ እንዲኖር ማድረግ ነው። የሳይንስ ትርጉሙ ከዚህ ውጭ ሊሆን አይችልም።
ወደህብረተሰብና ወደ ፖለቲካ ሳይንስም ስንመጣ በመሰረቱ ከዚህ የሚለይበት ሁኔታ የለም። የህብረተሰብ ሳይንስ የአንድን ህብረተሰብ አወቃቀርና ውስጣዊ ህግ እንድንመራመርና እንድንረዳ የሚያደርገን ወይንም መንገዱን የሚያስጨብጠን ነው። ለምሳሌ አንድ ህብረተሰብ በኢኮኖሚ ካላደገ፣ የምርት ኃይሎች ቀጭጭው የቀሩና፣ የሰውም የቀን ተቀን ኑሮ በዘልማዳዊ አሰራርና አኗኗር ላይ የተመረኮዘ ከሆነና፣ ህብረተሰቡም በልዩ ለዩ የኢኮኖሚ የስራ-ክፍፍል መደራጀቱና መተሳሰሩ ቀርቶ በጠባብ የገበያ የኢኮኖሚ ክንዋኔ ውስጥ ብቻ የሚሽከረከር ከሆነ ይህንን ሁኔታ በህብረተሰብ ሳይንስና በባህል የምርምር መሳሪያ በመመርመርና በማጥናት ሁኔታውን ለማስተካከልና ወደተሻለ ሁኔታ ለማምራት ሙከራ ማድረግ በዚህ ሙያ የሰለጠነው ምሁር ተግባር ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የህብረተሰቡ የምርት ግኑኝነት፣ የፖለቲካውና የመንግስት አወቃቀር በህብረተሰብና በኢኮኖሚው ማደግና አለማደግ ላይ የሚኖራቸውን ተጽዕኖ ማጥናትና ማረሚያ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ የህብረተሰብ ሳይንስ አዋቂዎች ዋና ተግባር ነው። ይሁንና የህብረተሰብ ሳይንስ እንደ ተፈጥሮ ሳይንስ አይደለም። በተለይም ጥቅማቸው እንዲነካባቸው የማይፈልጉ ጥልቀት ያለው ጥናት ስለማይሹ ከመጀመሪያውኑ ዕገዳ ያደረጋሉ። ይህንን በሚመለከት በየዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከፍተኛ ትርምስና ክርክር ይደረጋል። ዕውቀቶቹ ከመሰበጣጠራቸው የተነሳ በነገሮች መሀከል ምንም ግኑኝነት የሌለ ይመስል ወጣቱን ትውልድ እያሳሳተና ችግር እንዳይፈታ እያደረገው ነው። ወደ ፖለቲካ ሳይንስ ስንመጣም ያለው ችግር የፖለቲካ ሳይንስን የተማረ ሁሉ ስለፖለቲካ፣ ወይም ስለዓለም ፖለቲካ ትክክለኛ ግንዛቤ ይኖረዋል ማለት አይደለም። እያንዳንዱ የፖለቲካ ተንታኝ ከአንዳንድ ዓለምን እንደፈለጋቸው ለመበወዝ ከሚፈልጉ ወይም ከተደራጁ ቡድኖች ወይም ኢንስቲቱሽኖች ጋር በጥቅም በመተሳሰር ከተጨባጭ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም ትንተና ይሰጣል። ይህም ማለት ፖለቲካል ሳይንስም ልክ እንደ ኢኮኖሚክስ በርዕዮተ-ዓለም የተሸፈነ ስለሆነ ችግር ፈቺ መሆኑ ቀርቶ ችግር ፈጣሪ እየሆነ መጥቷል። በዕውቀት ላይ የተመረኮዘ ከመሆን ይልቅ በኢንፎርሜሽን ላይ ብቻ በማድላት ወደ እንካስላንቲሃነት ሊለወጥ በቅቷል። ይህንን ችግር ለመገንዘብ የፖለቲካ ትርጉምንና የአሰራር ዘዴንና እንዲሁም ፖለቲካ የሚለውን ፅንሰ-ሃሳብ እንዴት እንደፈለቀ ትንሽ ጠጋ ብለን እንመልከት።
እንደሚታወቀው በመሰረቱ የሰው ልጁ ፖለቲካዊ ስለሆነ፣ እንደ ህብረተሰብ ወይም እንደማህበረሰብ መደራጀት ከጀመረ ጀምሮ በየጊዜው ብቅ ብቅ ያሉ የፖለቲካ ተመራማሪዎችና ሊቃውንት የፖለቲካን ትርጉም ፍልስፍናዊ መሰረት ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የትና መቼ እንደተጀመረ መቶ በመቶ አፍን ሞልቶ መናገር ባይቻልም፣ የመጀመሪያው ፖለቲካዊ የአጻጻፍ ዘዴ በሆሜር በሁለቱ ድርሰቶች ውስጥ፣ ኢሊያስና ኦዲይሶይስ በሚባለው ውስጥ በሚገባ እንደተቀመጠ የሚያስተምሩ ብዙ የሊትሬቸር ወይም የፖለቲካ ተመራማሪዎች አሉ። የፖለቲካ አደረጃጀትን በሚመለከት ደግሞ ግሪኮች ከግብጾች የአስተዳደር አወቃቀር እንደተማሩ ይናገራሉ። ለዚህ ደግሞ የሚሰጡት ምክንያት የግሪክ ስልጣኔ ብቅ ከማለቱ በፊት ብዙ የግሪክ ፈላስፋዎች ዕውቀታቸውን ወይም ደግሞ የዕውቀቶች ሁሉ አባት የሚባለውን ፍልስፍናና ሳይንስ ከግብጽ ቀሳውስት እንደተማሩና፣ ግብጽም በነበሩበት ወቅት አስተዳደሩን እንደተመለከቱና፣ ይህንንም ግሪክ አገር ውስጥ ማስፋፋት እንዳለባቸው ተናግረዋል። በተለይም ይህ አገላለጽ በማርቲን በርናል በተደረሰው ብላክ አቴና ተብሎ በሚጠራውና፣ ሼይክ አንታ ዲዮፕ፣ አፍሪካ የአውሮፓው ስልጣኔ እናት፣ በሚለው መጽሃፋቸው ውስጥ በሰፊው ተብራርቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የግብጽን ስልጣኔ በመረመሩ ሰዎች የመጀመሪያዊ አዋቂው ወደ እግዚአብሄር የሚጠጋው፣ ሁሉንም ዕውቀት፣ ማለትም ከፍልስፍና እስከ አስትሮሎጂና አስትሮኖሚ ደረስ እንዲሁም የመጀመሪያው የሳይንስ እናት ተብሎ የሚጠራው አልኬሚንና ሌሎችን ዕውቀቶች ያፈለቀው ግብጻዊ ቄስ እንደነበር የሚናገሩ አያሌ ምርምሮች አሉ። ይህም ሰው ሄርመስ ትሪስሜጊስቶስ(Hermes Trismegistos) በመባል ሲታወቅ፣ ከሞሰስ በፊት የነበረ ደራሲና፣ የሞሰስም ጽሁፍ ሆነ በኋላ የመጽሀፍ ቅዱስ ዋናው መሰረቱ የሄርመስ ትሪስሜጊስቶስ ስራዎች እንደሆኑ በሰፊው ያብራራሉ። የሄርመስ ትሪስሜጊስቶስም ዋናው መመሪያው ጥበብና ዕውቀትን ያጣመረ ነው። ይህም የሚያሳየን በመጀመሪያው ወቅት ፖለቲካ ከሌሎች ዕውቀቶች፣ በተለይም ከፍልስፍና ውጭ ተነጥሎ አይታይም ነበር። ዋናው ውስጣዊ ይዘቱም ሆነ ባህርይው ጥበባዊ ነበር ማለት ይቻላል። ችግርን መፍቻ እንጂ ችግር ፈጣሪ እንዳልነበረ እንገነዘባለን።
ዛሬ የፖለቲካል ሳይንስ እየተባለና ከፍልስፍና ተነጥሎ ወደ ሚታየው ስንመጣም፣ ዝም ብሎ በአቦ ሰጡኝ የተዘጋጀና እንደመመሪያ የቀረበ ነገር አይደለም። የፖለቲካል ሳይንስ ዋናው ዓላማው በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚኖረውን የኃይል አሰላለፍ የመመራመሪያ፣ የፓርቲዎችን አደረጃጀትና ርዕዮተ-ዓለምን ፕሮግራም መመርመሪያ ቢሆንም ከረዥሙ የታሪክ ግምገማ አንፃር ፖለቲካ ልዩ ዐይነት ትርጉም ነው ያለው። በተጨማሪም የዓለም ፖለቲካ እየተባለ ግንዛቤ እንዲኖር በየዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በትምህርት መልክ ይሰጣል። በሌላ በኩል በፖለቲካና በሌላው የህብረተሰብ ሳይንስ፣ ለምሳሌ ሶስዮሎጂ የሜቶዶሎጂካል አሰራር ጉዳይ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር እስከዚህም ድረስ የሚለዩበት ትልቅ ነገር የለም። ለማንኛውም ከነሶክራቶስና ከፕላቶንም ጽሁፎች የምንረዳው ፖለቲካ በፍልስፍና የተደገፈ፣ ወይም በፍልስፍና መነጽር የሚታይ ነው። በሌላ አነጋገር የፖለቲካና የፍልስፍና ዋናው ዓላማ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ አርቆ-ማሰብ የጎደለው ፖለቲካዊ ተግባር የሚፈጸም ከሆነ ይህ ዐይነቱ አርቆ አስተዋይነት የጎደለው ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር ቻለ ብሎ በመመራመር፣ የአንድን አገር አገዛዝ አስተሳሰብ ለማነጽና ህብረተሰብአዊ ባህርይ እንዲኖረው በማድረግ ታሪክን መስሪያ መመሪያ መንገድ ነው። ከዚህ ስንነሳ፣ በነፕላቶን ዲስኩርስ ውስጥ ጥሩ ሰው መሆን፣ ትክክለኛ ዕውቀትን መቅሰም፣ እኩልነትን መመሪያ ማድረግ፣ ስግብግብነትን አለማስቀደም፣ ለስጣልን አለመቻኮል፣ እነዚህ ሁሉ በፖለቲካ ዲስኩርስ ውስጥ ገብተው እንደዋና መመሪያ በመወሰድ አንድን ህብረተሰብ የመወዛገቢያ መድረክ ሳይሆን የታሪክ መስሪያ ሁኔታ እንዲሆን የሚያስተምር ነው። ስለሆነም የእነ ፕላቶን የፖለቲካ ፍልስፍና መሰረተ-ሃሳብ ሁሉን ያካተተና፣ የሰውን ልጅ ወደ ፈጠራና ወደ ተረጋጋ ሁኔታ እንዲያመራ የሚያደርገው ነው። የእነ ፕላቶን የፖለቲካ ፍልስፍና የጦር መመሪያና የውዝግብ መፍጠርያ፣ ወይም ደግሞ የከፋፍለህ-ግዛ ፖሊሲ ማውጫ ሳይሆን፣ የጦርነትንና የህብረተሰባዊ ውዝግብን ዋናውን ምክንያት መፈለጊያ ዘዴ ነው። በዚህም ምክንያት በሶሎን የአገዛዝ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ፖለቲካ የጥቂት ስዎች መሆኑ ቀርቶ በዲስኩርስ መልክ በትልቅ ሜዳ ላይ ህዝቡ የሚወያይበት ወይም የሚከራከርበት ሆነ። የእነ ፕላቶን የፖለቲካ አስተሳሰብም ኤሊታዊ ቢመስልም፣ በሱ አስተሳሰብ መሰረት ግለሰብአዊ ነፃነትና ህብረተሰብአዊ ነፃነት አንድ ላይ ተጣምረው የሚሄዱ ሲሆን፣ የፖለቲካ ኤሊቱ ተግባር በህብረተሰብ ውስጥ አኩልነት የሰፈነበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ ነው።
ይሁንና በዛሬው እጅግ በተወሳሰበና ለብዙዎቻችን ግልጽ ባልሆነ ዓለም ውስጥ በየትምህርት ቤቱ ወይም በየኮሌጅ ውስጥ የሚሰጠው የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት በነሶክራተስ፣ በእነፕላቶንና አርስቲቶለስና፣ በተለይም ደግሞ በኢንላይተንሜንት ዘመን በሰፊው የተጠናውንና እንደመመሪያ የተወሰደውን፣ የእነ ስፒኖዛ፣ የእነካንትና የነሌሲንግና የሌሎችንም የፖለቲካል ቲዎሪና መመሪያ ያካተተ አይደለም። በነዚህ የኢንላይተንሜንት ምሁሮች ዕምነት ማንኛውም የፖለቲካ ሂደት በዕውቀትና በአርቆ አስተሳሰብ ላይ የተመርኮዘ መሆን ሲገባው፣ የመጨረሻ መጨረሻም የህዝብ ሌጂቲሚሲ የሚኖረውና የህዝብን ችግር የሚፈታ መሆን አለበት። የነዚህ ምሁሮች መመሪያ ሪፑብሊካዊነት ቢሆንም፣ ዲሞክራሲያዊና ሪፑብሊካዊነት ሊረጋገጡ የሚችሉት ህዝባዊ ንቃተ-ህሊናና ተሳትፎ ሲኖር ብቻ ነው። ያልነቃና ያልተማረ ህዝብ ደግሞ በቀላሉ የገዢዎች ወይም የፖለቲካ ነን ባዮች ሰለባ በመሆን የመጨረሻ መጨረሻ ዕውነተኛ ነፃነቱን እንደሚያጣ የታወቀ ነው። ከዚህ ስንነሳ፣ ካንትም ሆነ ሺለር፣ ስፒኖዛና ሌሎችም አያሌ የፖለቲካ ፍልስፍና ተመራማሪዎች ከመቃብራቸው ተነስተው የዛሬውን ዓለም ቢመለከቱ ኖሮ ራሳቸውን ይዘው ይጮሁ ነበር። እንዴት እንደዚህ ዐይነት እኩልነት የጎደለበት፣ ድህነት የተስፋፋበት፣ የፓለቲከኞች ፖለቲካ ትርጉም ሁሉ እንዴት ወደ ጦርነት ሊለውጥና፣ መንግስታትም ይህንን ዐይነቱን የተወሳሰበ የጦር መሳሪያ በመስራት ወደ ጦርንት ያመራሉ ብለው እሪይ ብለው መጮሀቸው አይቀርም ነበር።
የዚህ ሁሉ ችግር ምንድነው? አንደኛ ፓለቲከኛ ነን የሚሉ የማኪያቤሊን የመሳንፍት ጽህፍ በተሳሳተ መልክ በመረዳት፣ ፖለቲካን ወደ ንጽሁ ተንኮልነት መሳሪያነት ለውጠውታል። በሁለተኛ ደረጃ፣ የነሆበስ የሰውን ልጅ ባህርይ ወደ ቀበሮነት የለወጠና ዝቅ አድርጎ የመመልከት አጉል ፍልስፍና በምዕራቡ የፖለቲካ ዲስኩርስና አስተሳሰብ ውስጥ ተስፋፍቷል። በሌላ አነጋገር የሰው ልጅ የጭንቅላት ባህርይ አንዱ ሌላኛውን በመፍራትና በመጠራጠር ክልል ውስጥ የተቀረጸ ስለሆነ፣ አንደኛው ሌላውን እየፈራና እየተጠራጠረ የሚኖር ነው። በሁለት ግለስቦች ውስጥም ሆነ በአንድ የፖለቲካ ድርጀትም ሆነ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጀቶች መሀከል ምንም ዐይነት መተማመን ሊኖር አይችልም። የሰው ልጅም ባህርይ ስግብግብነትን የተላበሰ ስለሆነ፣ ይህንን ባህርዩን ስለሚያስቀድም ሌላውን ይቀናቀነኛል የሚለውን በተቻለ መጠን ለማሸነፍ ይጥራል፤ ወይም ያጠፋዋል። በሌላ አነጋገር በሆበስ አመለካከት የሰው ልጅ አርቆ የማሰብ ኃይሉን በመጠቀምም ሆነ በመቅረጽ ስሜቱን ሊቆጣጠር አይችልም። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ በብዙ የካፒታሊስት አገሮች ቀሰ በቀስ የተወገደ ቢመስልም፣ አሁንም ቢሆን የተስፋፋና በተለይም በውጭ ፖለቲካ ላይ ተግባራዊ የሚሆን ነው። ወደ ውስጥ ደግሞ ስርዓቱን በሚደግፉ ፓርቲዎች መሀከል ካልሆነ በስተቀር በተለይ የኃይልን አሰላለፍንና የሀብት ዘረፋን በሚቃወሙ ሌላ አመለካከት ባላቸው ሰዎች ላይ የሚውል ነው። በሌላ አነጋገር ማንኛውም በፖለቲካ ህይወት ውስጥ የሚሳተፍ ሁሉ የስርዓቱን ምንነት መጠየቅ የለበትም። በተቻለ መጠን ከስርዓቱ ጋር ለመዋሃድ መሞከር አለበት።
በአገሮች መሀከል ያለውን የፓለቲካ ግኑኝነት ስንመረምር ደግሞ፣ የዓለም ፖለቲካ የሚባለው ነገር እነፕላቶንም ሆነ፣ ስፒኖዛና ካንት ያዋቀሩት ዓለም-አቀፋዊ የፖለቲካ ኖርም ሳይሆን መመሪያው፣ ኃያላን መንግስታት የሚባሉት አገሮች የዓለምን የፖለቲካ ሂደት የሚወስኑበት ሁኔታ በግልጽ ይታያል። አሁንም በሌላ አነጋገር የብዙ የካፒታሊስት አገሮች የፖለቲካ ግኑኝነት መመሪያ የነካንት ሳይሆን፣ ንጹህ በንጹህ በሆበስ ላይ የተመሰረተና፣ ፓለቲካን በአመጽ ላይ ያስረገጠ ነው። በካንት የፖለቲካ ፍልስፍና መሰረት በዓለም ላይ ሰላም ሊሰፍን የሚችለው ማንኛውም አገር የሌላውን ነፃነት ሲያከብርና መከባበር ሲኖር ብቻ ነው። አንድ መንግስት እኔ ኃያል ነኝ በማለት በሌላ አገር ላይ የራሱን ተፅኖ ማሳረፍ የለበትም። ይሁንና ግን አብዛኛዎች የካፒታሊስት አገሮች እነ ፕላቶንም ሆነ እነ ካንት ያዘጋጁትን የፖለቲካ ፍልስፍና እንደመመሪያ አይጠቀሙም። የሆበስን ቲዎሪ ነው የሚጠቀሙት። በዚህ መሰረት ደካማ አገሮች የካፒታሊስት አገሮች ጥገኛ መሆን አለባቸው። እነሱ የሚዘምሩትን ሙዚቃ አብረው መዘመር አለባቸው። የየራሳቸውን አስተሳሰብ በግልጽ ማስቀመጥ የለባቸውም። ሁሉም ነገር በዲፕሎማሲ ሽፋን ስር እየተድበሰበሰ መቅረት አለበት። ስለሆነም ሁሉም አገሮች አንድ ዐይነት የአሰራር ኖርም እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። ለምሳሌ የፀረ-ሽብርተኞች ህግ የሚለው የብዙ አገሮች መመሪያ የሆነውን ስንመለከት ተጠርጣሪ ሁሉ ክትትል የሚደረግበት ከእንደዚህ ዐይነቱ ሆብሳዊ አመለካከት በመነሳት ነው። ይሁንና ግን ሽብርተኝነትና አነሳሱን ስንመለከት ደግሞ ከግሎባል ካፒታሊዝም ልቅ በሆነ መልክ መስፋፋትና፣ የባህል ውድቀትን ካመስከተልና፣ በየአገሮች ውስጥ ራሱን የቻለ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳይኖር ከሚካሄደው የኒዎ-ሊበራሊዝም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋርም እንደተያያዘ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በተጨማሪም የቀዝቃዛው ጦርነት በሚባልበት ዘመን በሁለት ተፎካካሪ ኃይሎች በተፈጠረው ግብግብ፣ አክራሪ ኃይሎች በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በመኮትኮትና ድጋፍ በማግኘት ለሽብርተኝነት መስፋፋት ምክንያት እንደሆኑ ብዙ ጥናቶች ያሳያሉ። ከዚህ ስነንሳ የዓለም ፖለቲካ መዘበራረቅና የእኛም ግራ መጋባት፣ ግሎባል ካፒታሊዝም የስልጣኔ አራማጅና አጋዥ መሆኑ ቀርቶ አደናቃፊና በረቀቀ መልክ በአገሮች መሀከል የተስተካከለ ዕድገት እንዳይኖር ማድረግ የፖለቲካን ግንዛቤያችንን አበላሽቶብናል። ፖለቲካ ከዕውነተኛ ነፃነት ጋር የተያያዘ መሆኑ ቀርቶ በአሜሪካን የፖለቲካ መነጽርና ጥቅም አንፃር የሚታይ ሆኗል።
በተለይም ባለፈው ስድሳ ዐመት በአሜሪካን ግንባር ቀደምትነት የተካሄደው የዓለም ፖለቲካና የዘመናዊነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ በየአገሮች ውስጥ ያስከተለው ውዝግብ፣ ጥቂቶች ሀብትን ማካበት፣ የየመንግስታት የተወሳሰበና አሰፈሪ መሳሪያ እየታጠቁ ወደ ሀብት ዘራፊነት ማምራት፣ ህዝቦች ረጋ ብለው ታሪክን መስራት እንዳችይሉ ማድረግ፣ በየአገሮች ውስጥ ካለው ኋላ-ቀር አስተሳሰብ አንፃር ብቻ የሚታይ ሳይሆን፣ የዛሬዎቹ የሶስተኛው ዓለም የመንግስታት አወቃቀርና፣ የጦር ሰራዊት፣ የፀታ-ኃይል፣ ፖሊስ እነዚህ ሁሉ በአሜሪካን የአመጽና ያለመረጋጋት ሎጂክ የሰለጠኑ ናቸው። ነገሩ ቀላል ነው። አገሮች በሙሉ ወደጦር አውድማነት ተቀንሰው መታየት ያለባቸው እንጂ፣ የባህል ተሀድሶ የሚካሄድባቸው፣ ቆንጆ ቆንጆ ከተማዎች የሚገነቡባቸው፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚያብቡባቸው፣ በዚህም አማካይነት ህዝብ የሚተሳሰርበት አገር መፈጠር የለበትም። ባጭሩ በተለይም አፍሪካ የጥሬ-ሀብት አቅራቢና ወደ ፕላንቴሽን ኢኮኖሚ መቀየር አለባት። የአገራችንም ፖለቲካና መንግስታዊ አወቃቀር በዚህ ላይ የተመሰረተ ነው። የህዝቡን የእጅ አሻራና ፎቶ ለአሜሪካ የስለላ ድርጅት ማስተላለፍና፣ የየአገሮች የፓስፖርት ፎቶ በሙሎ ቢዮሜትሪክ ሆኖ መነሳት የሚያመለክተው የዓለምን ህዝብ በቁጥጥር ስር ለማድረግ ከታሰበው የአሜሪካ የተበላሸ ፀር-ሳይንስና ፀረ-የሰው ልጅ ፖለቲካ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም። የዛሬው በአገራችን የሰፈነው አገዛዝና ከታች ያሉት ወጣት ፖለቲከኛ ነን ባዮች ዋናው ችግርም ይህንን የአሜሪካንን አሻጥርና ደባ ባለመረዳት አሻራችንና ፎቶአችንን አሳልፈው በመስጠት የታሪክ ወንጀል እንደሰሩ እንዲረዱት ያስፈልጋል።
ያም ሆነ ይህ ለብዙዎች የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪዎችና ተንታኝ ነን ባዮች ግልጽ ያልሆነ እጅግ የተወሳሰበ ብዙ ነገር አለ። ፓለቲካ ጥበብና ፍልስፍና መሆኑ ቀርቶ የቀን ተቀን ሁኔታዎች መተንተኛ በመሆን ሳይንስነቱን እያጣ ነው። ችግርን መፍቻ መሆኑ ቀርቶ ችግር ፈጣሪና ጦር መቀስቀሻ እየሆነ ነው። በሊበራል ዲሞክራሲ፣ በነፃ ገበያ፣ በጂኦ ፖለቲካና በአሸባሪነት ወይም በአምባገነንነት እየተሳበበ የብዙ ሺህ ዐመታት ታሪክ ያላቸው አገሮች ሁሉ እንዲወድሙ እየተደረገ ነው። እኔን እስከጠቀመከኝ ድረስ አልነካህም በማለት፣ ሌሎች የራሳቸውን መንገድ ለመከተል የሚፈልጉ አገሮችን ደግሞ በሰበብ አስባቡ በመጥለፍ ወደ ውስጥ የርስ በርስ ጦርነት አንዲስፋፋ እያደርጉ ነው። በኢራክ፣ በሊቢያና በሶሪያ ላይ የሚካሄደው ዘመቻና፣ ኢራንን ደግሞ ለመምታት የሚደረገው ደባ ከዚህ አጉል የአሜሪካን ኢምፔሪያሊስት የጦርነት ሎጂክ በመነሳት ነው። እንደሚታወቀው ኢራክ፣ ኢራንና ሶሪያ ከሶስት ሺህና ከአምስት ሺህ ዐመታት በላይ የስልጣኔ ታሪክ ያላቸው አገሮች ናቸው። ለዓለም ስልጣኔ ብዙ አስተዋፅዖ ያደረጉና፣ ዛሬ የምዕራቡ ዓለም የሚንደላቀቅበት ሳይንስና ቲኮኖሎጂ ከነዚህ አገሮችና ከግብጽ የተወሰደ ነው። ታዲያ እነዚህን አገሮች ቀስ በቀስ ከመንከባከብና ለዓለም ሰላም የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ ጥበብ የተሞላበት ፖለቲካ ከማካሄድ ይልቅ ለምን ይህ ሁሉ ዛቻና ዘመቻ ይካሄዳል? ነገሩ ቀላል ነው። ጥንታዊ መንግስታት በሙሉ፣ በተለይም ደግሞ የአሜሪካን ቡችላ ለመሆን የማይፈልጉ መንግስታት መደምሰስ አለባቸው። ሌላው ተራው የኢምፔሪያሊስቶች ሎጂክ ታሪክንና ስልጣኔን በማውደም ላይ ያተኮረ ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ ዐይነቱ ውዝግብ የዓለም ህዝብ ቁጥር መቀነስ አለበት ከሚለው ተፈጥሮን ከሚቀናቀን የተተለም እጅግ አደገኛ አስተሳሰብ ነው።
እንደሚታወቀው ነጭ ያልሆነው የሰው ዘር ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ በተለይም አክራሪና ሀብትን የሚቆጣጠሩ ኃይሎችን አስፈርቶአቸዋል።ስለዚህም በየቦታው ጦርነት ማወጅ ነው። ይሁንና ግን በታሪክ ውስጥ እንደተረጋገጠው የህዝብን ዕድገት ቁጥር በበሽታ፣ በረሃብና በደህነት እንዲያም ሲል መረን በለቀቀ ጦርነት መቀነስ ቢቻልም፣ ይኸኛው መንገድ እጅግ አደገኛ የሰውንም ልጅ ተፈጥሮአዊ የመዋለድና የመባዛት፣ እንዲሁም የመኖር መብት የሚቀናቀንና የሚደገፍም አይደለም። በየአገሮች ውስጥ የህዝብ ቁጥር ሊቀንስ የሚችለው ወይም እንዳያድጉ የሚደረገው፣ በየአገሮች ውስጥ የተስተካከለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት ሲኖር ብቻ ነው። ይህ በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ የተረጋገጠ ነው። ምክንያቱም ቀላል ነው። ዕውቀትና ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ዕድገት ሲኖር በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ በሰራ ስለሚወጠርና የበለጠ ማሰብ ስለሚችል፣ አስር ልጅ ከመውለድ ይልቅ በሁለትና በሶስት ልጆች ብቻ ይገደባል። ልጅ ከማሳደግም ባሻግርም ራሱም በልዩ ልዩ ባህላዊና ህብረተሰበአዊ ድርጊቶች መሳተፍ ስለሚፈልግ በጥቂት ልጆች ብቻ ይወሰናል።
ያም ሆነ ይህ የአገራችንና የዓለም ፖለቲካ አወዛጋቢና ፈሩን እየለቀቀ በመምጣቱ የአንድን አገር ፖለቲካ በአንዳች ዐይነት ፍልስፋናና ሳይንሳዊ መለኪያ ለማዋቀርና መመሪያ ለማድረግ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። በየአገሮች ውስጥ በመሪነት ደረጃ የሚቀመጡ ወይም የሚመረጡ ምሁራዊና ሳይንሳዊ ባህርይ ያላቸው መሆናቸው ቀርቶ ማንም እየተነሳ ለምርጫ የሚቀርብበትና ህዝብን የሚያታልልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚህ ስንነሳ ፖለቲካ ምሁራዊነት ያስፈልገዋል ወይ? የሚለውን ጥያቄ በመጠኑም ቢሆን እንቃኝ።
ፓለቲካ ምሁራዊነት ያስፈልገዋል ወይ?
ለመሆኑ ምሁራዊነት ወይም ምሁር ማለት ምን ማለት ነው? በምሁርና በአንድ ተራ አካዴሚሽያን ወይም ቴክኖክራት መሀከል ምን ዐይነት ልዩነት አለ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለማብራራት ልሞክር።
በብዙዎቻችን ዘንድ ያለው ችግር በምሁርና በአንድ ተራ አካዴሚሽያን ወይም ቴክኖክራት መሀከል ያለውን ልዩነት ለመለየት ያለመቻል ነው። በመሰረቱ አንድ ሰው በስነስርዓት ያነበበ ብቻ ሳይሆን፣ አንድን ነገር ከሁሉም አንጻር ለመተንተን(analytical capacity) የሚችል ከሆነና፣ ለአንድ ችግር ተቀራራቢ መፍትሄ የሚሰጥ ከሆነ ይህ ሰው ምሁር ነው ማለት ይቻላል። የተወሳሰበን ሁኔታ በቀላሉ ሊገልጽ የሚችል ከሆነ፣ ወይም ደግሞ አንዱን ነገር ከሌላው ነጥሎ የማያይ ከሆነ፣ በነገሮች መሀከል መተሳሰር ያለ መሆኑንና ከዚህ በመነሳት ትንተና ለመስጠት የሚችል ከሆነ ይህ ሰው በእርግጥም ምሁር ነው ማለት ይቻላል። ይህ ብቻ ሳይሆን በሰፊውና በጥልቀት መተንተን የሚችል ምሁር ድርጊቱ ሁሉ በስሜት ላይ የተመረኮዘ አይሆንም። የራሱን አተናተን ብቻ ሳይሆን የሌላውንም የማዳመጠና የመረዳት ችሎታ እንዲኖረው ያስፈልጋል። አንድ ምሁር ነኝ የሚል ሰው የግዴታ የሱ አተናተን ብቻ የተሟላ ላይሆን እንደሚችል መገንዘብ አለበት። እንደሚባለው ፍጽሟዊ ዕውቀትና ምሁራዊነት ስለሌለ የተለያዩ ምሁሮች እንደፍልስፍና መሰረታቸው አንድን ነገር በተለያየ መልክ ሊተነትኑት ይችላሉ። በተጨማሪም ደግሞ የተወሰነ ጥቅምንና እሴትን የሚያራምዱ ከሆነ አተናተናቸውም በዚያ ክልል ውስጥ የሚሽከረከር ይሆናል።
ምሁር የሚለውን አስተሳሰብ ለመረዳት የሚያስቸግረውና፣ ብዙ ስዎችም ተምረው እንኳ አንድን ነገር በሰፊውና በተወሳሰበ መልኩ ለመረዳት የማይችሉት በመጀመሪያው በየዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት በክስተት ላይና በተናጠል ነገሮች ላይ የተመሰረተ ትምህርት ስለሚሰጥ ነው። ስለሆነም አንዳንድ ሰዎች ኢንተለጀንት ቢሆኑም አንድን ነገር አናሊቲካሊ በማየትና በመተንተን መፍትሄ ለመስጠት ይችግራቸዋል። በተጨማሪም እንደህብረተሰብ ሳይንስ፣ በተለይም ኢኮኖሚክስ የመሳሰሉት በከፍተኛ ደረጃ በርዕዮተ-ዓለም የተሸፈኑና በሞዴልና በማቲማቲክስ ያሸበረቁ ስለሆነና፣ ከተጨባጭ ሁኔታዎችም ርቀው የተዘጋጁ ስለሆነ አንድን ነገር ሁለንታዊ በሆነ መልክ እንዳንተነትንና እንዳንረዳ ያግዱናል። በዚህም ምክንያት አንድ በኒዎ-ክላሲካል ወይም ኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚክስ ትምህርት የሰለጠነ ሰው የአንድን ህብረተሰብ የኢኮኖሚ ዕድገት በዲያሌክቲክስና በሜታፊዚክስ መነጽር ስለማይመለከት ችግሩ በገበያ ኢኮኖሚና በሊበራል ሪፎርም የሚፈታ ይመስለዋል።
በሌላ አነጋገር፣ በአቀራረቡ ውስጥ፣ ከመጀመሪያውኑ በአንድ አገር ውስጥ ያለውን የኃይል አሰላለፍ(power relationship)፣ የምርት ኃይሎችን ግኑኝነትና የሀብት ቁጥጥር፣ ከዚህም በመነሳት ይህ ሁኔታ ዕውነተኛ ህዝባዊ ሀብት ለመፍጠር መሰናክል መሆኑና አለመሆኑን፣ በታሪክ ውስጥ ተግባራዊ የሆነውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የፍልስፍና መሰረት ምርምር ውስጥ የማያካትት ከሆነና፣ በተጨማሪም ጠቅላላው ህብረተሰብ ራሱን ለማስተዳደር በምን ዐይነት የማምረት ሂደት ነው የተዘጋጀው የሚለውንና፣ ከዚህም በላይ አገዛዙም ሆነ ህዝቡ የሚመራበትን ዕውቀት በሞዴል ውስጥ ያማያካትት ከሆነ የሚያመጣው ውጤት የባሰ ድህነት የሚፈጥር ይሆናል ማለት ነው። ስለሆነም በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚና በነፃ ገበያ መርሆች ላይ የሰለጠነ ምሁር የሌላን ሰው አስተሳሰብና የታሪክን ሂደትና የህብረተሰቦችን ዕድገት ለመረዳት አይፈልግም። ወይም ከመጀመሪያውኑ ይህ ነገር እንዲነሳበት አይፈልግም። ፕሮፌሰር ኤሪክ ራይነርትና ሌሎችም የወጣላቸው ምሁሮች እንደሚያስተምሩን ከሆነ ኒዎ-ሊበራሊዝም ታሪክንና ልምድን የሚቃወም ሆኗል።
ወደ ፖለቲካ ዓለም ውስጥ ስንመጣ እንደዛሬው ዓለም ልዩ ልዩ ፓርቲዎች እየተመሰረቱ ህዝብን ግራ በማያጋቡበት እስከ አስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ በፈላስፋዎች ዘንድ ፖለቲካ ከምሁራዊነት አስተሳሰብና ሰፋ ካለ ዕውቀት ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። ከላይ እንደተዘረዘረው በመጀመሪያ ደረጃ ፖለቲካ ጥበባዊ የህዝብ ማስተዳደሪያ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ የገባ በመሆኑ ፖለቲካና ፍልስፍና፣ ፖለቲካና ሳይንስ፣ ፓለቲካና ድራማ፣ ፖለቲካና አርክቴክቸር፣ ወዘተ… ተነጥለው የሚሄዱ አልነበረም። ይህ ማለት ግን አንድ ሰው በእያንዳንዱ ነገሮች ላይ የተለቀ ዕውቀት ይኖረዋል ማለት አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። በአጠቃላይ ሲታይ ግን አንዳንድ መሪዎች ሁሉን ነገር የማየት ስጦታ ስላላቸውና፣ አብዛኛዎችም በፈላስፋዎችና በደራሲዎች ወይም በሳይንቲስቶች የሚመከሩ ስለነበር የፖለቲካን ትርጉም ስፋ ያለ አድማስ በመስጠት አንድን ህብረተሰብ መገንቢያ አድርገው ነው የሚወስዱትና መመሪያቸው ያደርጉ የነበረው። በዚህም ምክንያት ስለፖለቲካ ቲዎሪ የሚጽፉ ሳይታክቱ ለማሳየት የሞከሩት ፖለቲካ ከፍልስፍናና ከምሁራዊ ባህርይው ተነጥሎ መታየት ከጀመረ አንድን ህብረተሰብ መቀመቅ ውስጥ ነው የሚከተው። ማንም እየተነሳ ይህንን ወይም ያኛውን ፓርቲ በመመስረትና ግብ ግብ በመፍጠር ስራ እንዳይሰራ፣ ዕውነተኛ ነፃነት እንዳይኖር፣ ዲሞክራሲ እንዳያብብ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ግንባታ እንዳይካሄድ ያግዳል። የሃሳብ መንሸራሸርና ክርክር እንዳይኖር ዕንቅፋት ይሆናል። በዚህ ዐይነቱ የፖለቲካ አወቃቀር ውስጥ የውጭ ኃይሎች ተጽዕኖ ካላቸውና በጥቅም የሚተሳሰሩ ከሆነ ዕድገትና ነፃነት የሚባል ነገር አይኖርም ማለት ነው። ለዚህ ነው ዛሬ በአገራችንም ሆነ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ፖለቲካ ከምሁራዊነት ባህርይው በመላቀቅ አገሮች ወደ ንጹህ የሸቀጣ ሸቀጥ ማራገፊያነት ሊለወጡ የቻሉት።
ከዚህ ስንነሳ ፖለቲካና ምሁር አንድ ላይ መሄድ የለባቸውም፤ ምሁር የፖለቲካ ስልጣንን ከጨበጠ ነገረ-ዓለሙ ተበላሸ የሚለው አስተሳሰብ አደገኛ የሚሆነው ከላይኛው አስተሳሰብ በመነሳት ነው። እንደሚታወቀው በአንድ አገር ውስጥ የሚካሄድ ፖለቲካ በአንድ ሰው የሚወሰን አይደለም። በተለይም በካፒታሊስት አገሮች ያለው ችግር ፖለቲካ ከጥቅምና ከመደብ ትግል ጋር የተያያዘ ስለሆነ የካፒታሊስት አገር መሪዎችና ፓርቲዎች የግዴታ የካፒታሊዝም ጎታች ሳይሆኑ ወደ ተጎታችነት ተቀይረዋል። ፖለቲካቸውንና ድርጊታቸውን የሚወስነው ኢኮኖሚው እንጂ ፖለቲከኞች አይደሉም። ለምሳሌ የፕሬዚደንት ኦባማን ችግር ስንመለከት ፕሬዚደንቱ ጥሩ ፍላጎትና አስተሳሰብ ቢኖረውም ያለው የከረረ የኃይል አሰላለፍና የኢኮኖሚ ቁጥጥር የግዴታ የቡሽን ዐይነት የጦር ፖለቲካ እንዲያራምድ አስገድዶታል። ከፍለግ አድርግ፣ ካልፈለግ ትመነገዳለህ የሚል የአሜሪካኖች ፖለቲካ አስተሳሰብ አለ። ከዚህ ስነሳ ባራክ ኦባማ የወጣለት ምሁር ቢሆንምና ከፍተኛ ኮመን ሴንስ ቢኖረውም እንደፈለገው እንዳይንቀሳቀስ የአሜሪካ የኢንዱስትሪ-ሚሊቴሪ ኮምፕሌክስ አወቃቀር አላላውስ ብሎታል። የስራ መስክ ፈጣሪና ኢኮኖሚውን በአዲስ መልክ በማደራጀት ለአሜሪካ ህዝብ ተስፋ ከመስጠት ይልቅ ፖለቲካዊ ተግባሩ ወደ ጦርነት ተቀንሷል። በዚህ ፍልስፍና መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ የማያቋርጥ ጦርነት መካሄድ አለበት። ይህ ነው የአሜሪካ የፖለቲካ ዶክትሪን ትላንትም ሆነ ዛሬ።
ወደ አገራችን ስንመጣ ደግሞ ያለፈውን የሰባ ዐመታት ፖለቲካ ስንመለከት አገዛዞቹ ምንም ዐይነት ፍልስፍናዊና ምሁራዊ ይዘት አልነበራቸውም ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ይህ ማለት ግን በየምኒስትሮች ውስጥ የተማሩ ወይም ምሁራዊ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች አልነበሩም ማለት አይደለም። ብዙ ባለስልጣናትንና ደራሲዎችንም መጥራት ይቻላል። ችግሩ ግን እንደ አውሮፓ ሞኖርኪዎች የሚያዳምጣቸው ሰው አልነበረም።ይህም የሚያሳየው በአገራችን የአገዛዝ መዋቅር ውስጥ ከፍተኛ የአስተሳሰብ ክፍተት ነበር ማለት ይቻላል። ንጉሱና አጋዛዛቸው ፖለቲካን ሁለንታዊ በሆነ መልክ ስለማይመለከቱና ስለሰው ልጅም ያላቸው አስተሳሰብ በጣም ደካማ ስለሆነ የፖለቲካን ትርጉም የሚረዱት ከራሳቸው ጥቅም አንጻር ብቻ ወይም ደግሞ አገርን የሚገዙት እግዚአብሄር ስለመረጣቸው ነው ከሚለው የተሳሳተ አስተሳሰብ በመነሳት ነበር። በዚህም ምክንያት ለኋላ-ቀርትነት ምክንያት ሆነዋል። ነፃነትንና የኢኮኖሚ ዕድገትን አፍነዋል። ህብረተሰቡ እንዳይፍታታ መንገዱን ሁሉ ዘግተውበት ነበር። ባጭሩ ታሪክ እንዳይሰራ ዕንቅፋት ሆነውበት ነበር።
ከዚህ ስንነሳ እንደኛ ያለውን በብዙ በሽታዎች የተተበተበና የሚሰቃይ አገር በአንድ መሪ ብቻ መፍታት አይቻልም። በአንድ በኩል ኮሌክቲቭ ሊደርሺፕ ሲያስፈልግ፣ በሌላ ወግን ግን ጠቅላላው የፖለቲካ ክንዋኔና ዕድገት በሰፊ ምሁራዊ እንቅስቃሴ መደገፍ አለበት። ፖለቲካው የተለያዩ ፓርቲዎች መጨፈሪያ እንዳይሆን ዕውነተኛ ምሁራን በድፍረት እየገቡ የፖለቲካውን ሂደት ለማስተካከል፣ ለማስተማርና አገር በጋራ የሚገነባ መሆኑን ማሳየት አለባቸው። መመሪያቸውም ሬናሳንስ ውይም ሁለ-ገብ ምሁራዊ እንቅስቃሴ መሆን አለበት። ይህንን መሰረት በማድረግ በተለይም ባለፉት ሃያ አንድ ዐመታት ተቃዋሚ ነኝ በሚለው ዘንድ የተሰራውን ስህተት በመጠኑም ቢሆን እንመልከት።
የፓርቲዎች ጋጋታና ውዥንብር መንዛት!
የወያኔ ስልጣን ላይ መውጣት የኢትዮጵያን ፖለቲካ ጥራት ከመስጠት ይልቅ ውዥንብር እንዲፈጠር አድርጓል። በመጀመሪያ ደረጃ የወያኔ ስልጣን ላይ መውጣት የርዕዮተ-ዓለምንና የአመለካከት ዝንባሌን ደብዛውን አጥፍቶታል ማለት ይቻላል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ራሱ ወያኔ ሳያስብ የወሰዳቸው የተለይዩ የተበላሹ ፖለቲካዎች በመሉ ወንጀለኛውንም ሆነ ዕውነተኛ ታጋዩን በአንድ ላይ እንዲሰለፉ አድርጎአቸዋል። ስንዴውን ከእንክርዳዱ መለየት የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። ይሁንና ግን ብዙ የዋሆችና አገራቸውን በቅን የሚወዱና ለአገራቸውም የሚቆረቆሩ ሊሰባሰቡና የፓለቲካውን መድረክ ሊሞሉት ችለዋል። በሶስተኛ ደረጃ፣ ግሎባል ካፒታሊዝም የነዛው አንድ አመለካከትና ዓለም ወደ መንደርነት ተለውጣለች የሚለው ኢ-ሳይንሳዊ አባባል ውሽትን ከዕውነት ለይተን ማይት የማንችልበት ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል። በዚህም የተነሳ ስለፖለቲካ ምንነት፣ ስለ አገራችን የፖለቲካ አወቃቀር፣ ይህ ጉዳይ ከውጭው ዓለም ጋር ስለመተሳሰሩና፣ ዓለም አቀፋዊው ፖለቲካ የሚያደርግብንን ጫና በዝርዝር እያስረዳ የሚያስተምረን የለም። ችሎታ ያለው እንኳ ቢኖር ምን አደከመኝ በማለት እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥ ተገዷል።
ይህ ሁኔታ የፓለቲካን ትርጉም በሚገባ ባልገባቸውና ዘርዝረውም ለማስረዳት ለማይችሉ የፖለቲካውን ውዥንብር በመጠቀም እዚህና እዚያ በተለያየ ስም ፓርቲዎች እንዲመሰርቱ አስችሎአቸዋል። ይህ በራሱ ደግሞ አራዳዎችን፣ በየጊዜውና እንደየሁኔታው አስተሳሰባቸውን የሚለዋውጡና፣ የዚህ ወይም የዚያኛው ፓርቲ አባል በመሆን መድረክ የሚያጣብቡ በየፓርቲዎች ጉያ ስር መመሸግ ጀምረዋል። የአንዳንድ የታወቁ ግለሰቦችን ስም በመጠቀምና ባንዲራ በማውለብለብ ዕውነተኛና የሰከነ፣ እንዲሁም ደግሞ ግልጽ ትንተና እንዳይሰጥ አግደዋል። በዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ ፓርቲ ነን ብለው ራሳቸውን የሚጠሩ ሰፋ ካለ የምሁራዊነት እንቅስቃሴ የራቁና፣ የተወሳሰበውን ዓለም ሁኔታ ለመረዳት በማይችሉ ሰዎች ተወጥሯል። የእሴት ወይም የርዕዮተ-ዓለም ጥራት የሌለው የፖለቲካ ፓርቲዎች አመሰራረት ወይም አደረጃጀት ደግሞ በግሎባል ካፒታሊዝም የትርምስ ዓለም ውስጥ ገብተው ሲያተራምሱ ለከረሙ ሰዎች ክፍት በመሆኑ በውዥንብር ላይ ውዥንብር እንዲከፈት ተደርጓል። በየፓርቲዎች ውስጥ ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ ትንተና የማይሰጥበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል ማለት ይቻላል። ይህም በራሱ በተለይም ይኸኛውን ወይም ያኛውን ፓርቲ ወይም ቡድን እደግፋለሁ የሚለውን የዋሁንና፣ አንዳች ተስፋ ነገር የሚጠባበቀውን በጥርጣሬ ውስጥ እየጣለው ነው። አንዳንዱ ደግሞ በጭፍን ፍቅራዊ ስሜት በመጠመድ ጥያቄ የሚያቀርቡትን ወደ መጥላት እያመራ ነው፤ ወይም በክፉ ዐይን ይመለከታቸዋል። በአንዳንዶች ዘንድ እንዲያውም አንዳንድ ታወቅን የሚባሉትን መጠየቅ ወይም መተቸት የእግዚብሄርን ቃል ከጣሰ በላይ አድርገው የሚቆጥሩ አሉ። ፖለቲካ ክርክርና ውይይት እንደሚያስፈለገውና ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ እንደሚያመራ መንገድ መታየት እንደሌለበት የማይገነዘቡ ብዙዎች ናቸው።
እንደዚህ ዐይነቱ ምሁራዊነት የጎደለው የፓርቲዎች አደረጃጀት ደግሞ አጀንዳው አገራዊና ታሪካዊ መሆኑ ቀርቶ ቡድናዊ በመሆን፣ የአንድ አገር ዕድል በጥቂት ሰዎች እንዲወሰንና ታሪካዊ ስራ እንዳይሰራ ያግዳል። ወደድንም ጠላንም ይህ ዐይነቱ አካሄድ ደግሞ ለሙስና፣ ፍርዳዊነት ለጎደለው አስተዳደር፣ ተጠያቂነት ለማይኖረውና ታሪካዊ ኃላፊነትን ለማይረዳ የህብረተሰብ ክፍል ክፍት በመሆን ፖለቲካው የሚሽመደመድና የህዝብን ሰቆቃ የሚያባብስ ይሆናል። በብዙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የምናየው የከተማዎች በስነስርዓትና በዕቅድ አለመሰራት፣ እንዲሁም የሀብት መባከንና የድህነት መስፋፋት ዐይነትም በአገራችንም ምድር ይቀጥላል ማለት ነው።
ዛሬ የፖለቲካ ፓርቲዎች መስርተናል የሚሉትንና የጦር ትግልም የሚያካሂዱትን ስልትና ዓላማ ስንመለከት ሁሉም የኢትዮጵያን ባንዲራ የሚያውለበልቡ ናቸው። ይህ ሁኔታ በአንድ በኩል ጥሩ የሆነውን ያህል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሂደቱና ወይም የአሰራር ስልቱ እንዲሁም ዓላማው በግልጽ የማይታወቅ ከሆነ የመጨረሻ መጨረሻ ላይ ሁሉንም የሚጎዳ ይሆናል። በሌላ ወገን ግን ግራም ወይም ቀኝ ነኝ የሚል፣ ወይም ደግሞ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው ብሎ የሚታገል ሁሉ አንድ የሚመኘው ነገር አለ። ሰላም የሰፈነባትና የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየቱ ነው። እቺ አገር አንድ ቀን አልፎላት ዐይቼ የማይል እንደ እኔ ግራ የገባው ብዙ የዋህ አለ።ለምሁሮች ወይንም የፖለቲካ ትግል ገባን ለሚሉ ይህንን የሰፊ ህዝብ ህልም ዕውን ወይም ተግባራዊ የማድረጉ ላይ ነው ዋናው የትግሉ ሂደትና ስልት መነጣጠር ያለበት።
ከዚህ ስነሳ በአገር ውስጥ ካለው የፖለቲካ ጥራት እጥረት ባሻገር የሚናፈሰው ወሬ ከአሜሪካን ፈቃድ ወይም ፍላጎት ውጭ ምንም ማድረግ አይቻልም የሚለው አባባል ተራውንም ሆነ ታጋይ ወይም ምሁር ነኝ የሚለውን ጭንቅላት ውስጥ በመግባት አላላውሰም ብሎታል። አሜሪካን እግዚአብሄር የፈጠረው ኃያል መንግስት ብለው እንጂ የታሪክ ክስተት መሆኑን የማይቀበሉ ብዙዎች ናቸው። ስለዚህም አሜሪካን የፈለገውን ማድረግ ይችላል ብለው የተገንዘብ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ናቸው። አንዳንዱ ደግሞ ዐይን በወጣ መልክ አሜሪካን ቶሎ ብለህ አፍሪካ ውስጥ ሰተት ብለህ ግባ፣ አሸባሪዎችና ቻይና ጥሬ-ሀበትን ሲቀራመቱ ዝም ብለህ ታያለህ እያሉ እየጨቀጨቁና ብዙ የዋህ ሰዎችን እያሳሳቱ ነው። ይህ ዐይነቱ አመለካከት በመጀመሪያ ክርስቶሲያዊዉን የሰው ልጅ ምስል የሚጻረር አባባል ነው። ምክንያቱም የሰው ልጁ ሁሉ በእግዚአብሄር አምላክ ምስል የተፈጠረ ስለሆን እንደ እግዚአብሄር በራሱ ኃይልና መንፈስ እንዲሁም የማሰብ ኃይል የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ሊፈጥር ይችላል የሚለውን የሚጻረር ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ የፊዚክስን ህግ የሚጻረር ነው። ይህም ማለት ማንኛውም ተንቀሳቀሽም ሆነ የማይንቀሳቀስ ነገር ውስጣዊ የማደግ ኃይል አለው። በራሱ ውስጥ ባለው ክንዋኔ ይባዛል፤ ወይም ያድጋል። በእርግጥ አንድ ነገር ውስጣዊ ኃይሉን በመጠቀም ለመንቀሳቀስና ለማደግ አመቺ ሁኔታዎች መፈጠር አለባቸው። ለዚህ ምሳሌ የሰውን ልጅ ከትንሽ ነገር ተነስቶ ማደገ መስፋፋትና፣ ልዩ ልዩ ኦርጋኖች ማብቀል ስንመለከት ማንኛውም ነገር በዚህ ዐይነት ኢቮሉሺናዊ ሂደት የሚያድግ ነው። ይሁንና ለሰው ልጅ ዕድገት ምግብ፣ ውሃና ፀሃይ ወሳኝ ናቸው። ወደ ፖለቲካምና ወደ አገር ግንባታ ስንመጣ የብዙዎች ካለ አሜሪካን አይቻልም ባዮች ይህንን የተፈጥሮ ህግን የሚጻረርና የሰውን ልጅ የመፍጠርና ራሱን የመቻል ኃይል የሚቃወም ነው። እንደ ጀርመን የመሳሰሉት አገሮች በአስራስምንተኛውን በአስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን እንደዚህ ዐይነት አስተሳሰብ ቢኖራቸው ኖሮ የሳይንስና የቴኮኖሎጂ ባለቤት መሆን ባልቻሉም ነበር። እንደዚሁም አሜሪካ በእንግሊዝ የተጫነባትን የነፃ ንግድ ፖሊሲ አሽቀንጣራ ባትጥል ኖሮ ታላቅ አገር ባልሆነች ነበር። ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያና ቻይና የተፈጥሮንና የሳይንስን ህግ ባይረዱ ኖሮ እዚህ ዐይነት የዕድገት ደረጃ ላይ ባልደረሱ ነበር። በራሳቸው ታሪክ ሰሪነት ላይ ዕምነት ባይኖራቸው ኖሮ እንደዚህ ተከብረው ባልኖሩ ነበር።
ስለዚህ ከዚህ ዐይነቱ አጉል ዘመቻና ተስፋ ከሚያስቆርጥ አስተሳሰብ መላቀቅ ያስፈልጋል። ማንኛውም ግለሰብም ሆነ አገር በራሱ ላይ ዕምነት እንዲኖረው ማምንና መቀበል አለበት። ሌላው የሰራውን እኔም መስራት እችላለሁ ብሎ መነሳት አለበት። አጉል ትልቅ ሰው እየመሰሉ የሚቀርብ የጨዋዎች ፖለቲካ የትም ሊያደርሰን አይችልም። የፖለቲካ ትግል ምሁራዊነት ብቻ ሳይሆን ግልጽነት ያስፈልገዋል። ድፈረትን ይጠይቃል። የአንድ አገር ዕድል በሌሎች ቡራኬ የሚወሰን አይደለም። እነሱም ጋ እየሄዱ መናዘዝ አያስፈልግም። በአሜሪካንም ሆነ በተቀረው የምዕራቡ ዓለምና በሶስተኛው ዓለም መሀከል የጌታና የሎሌ ግኑኝነት ተፈጥሮ የተደነገገ ያለ ህግ ይመስል አንዳንዶቻችን ፈረንጅን ስንመለከት መቅለስለስ እናበዛለን። እነሱ የሚነግሩንና የሚመክሩን ሁሉ ትክክል ነው ብሎ በመውሰድ አገራችን ምን ዐይነት ውድቀት ላይ እንደደረሰች የማንረዳ በሚሊዮን የምንቆጠር ነን። ይህ ሁኔታ በዚህ ዐይነቱ የፓርቲዎች አወቃቀር፣ የህግ የበላይነት፣ የሊበራል ዲሞክራሲና የነፃ ገበያ በሚባሉ በደንብ ባልተብራሩ ጽንሰ-ሃስቦች ሽፋን ስር መድበስበስ የለበትም። በመሰረቱ የእኛ ፍላጎትና ምኞት ከአሜሪካኑ የጦርና የወራሪነት፣ እንዲሁም አገሮችን ከማፈራረስ አደገኛ ርዕይ ጋር የሚጣጣም አይደለም። የኛ ርዕይ ዘላቂ ሰላምን ማምጣት ነው። ዕውነተኛ ነፃነትን መጎናጸፍ ነው።
የተከበረችና ቆንጆ ኢትዮጵያን መገንባት ነው። ሁሉም በጋራና ተስማምቶ የሚኖርባት፣ የሚሰራባትና የሚኮራባትን አገር መመስረት ነው። ለአካባቢው አገሮች ደግሞ የሰላምን ጮራ በማፈንጠቅ ለሰላምና ለዕድገት እንዲነሱ የሚያደርግ ነው። በአካባቢያችን ደግሞ ጦርነት የሚባል አጉል ፈሊጥ እንዲጠፋ የሚያደርግ ነው። ከዚህ ስንነሳ በአሜሪካንና በተቀረው የምዕራቡ ዓለም መሀከል ሰፊ የሆነ የጥቅምና የፍላጎት አመለካከት አለ። የኛው ዓለም የጥበቡና የዕውቀት ዓለም ነው። የሰላምና የብልጽግና ነው። የመፈቃቀርና የሰላም ነው። የምዕራቡ ደግሞ የወረራ ዓለም ነው። የሀብት ዘረፋ ዓለም ነው። ሰዎችን የማዋከብ ዓለም ነው። የመፈቃቀር ዓለም ሳይሆን የትርፍ ትርፍን ለማካበት ሲባል በሰው ሬሳ ላይ መሄድ ነው። የምዕራቡ ፖሊሲ እነ ቄስ ኩዛኑስ፣ ላይብኒዝ፣ ሺለርና ካንት ከፈለሰፍት የፖለቲካ ፊሎሶፊ ጋር የሚጣጣም አይደለም። ከዛሬ ሁለት መቶ ዐመት ጀምሮ የሚካሄደው የባሪያ ንግድ፣ የቅኝ ግዛት አስተዳደር፣ አሁን ደግሞ የእጅ-ቅኝ አዙር አገዛዝና መረኑን የለቀቀ ግሎባላይዜሽን በመሰረቱ የእነካንትን የፖለቲካ ፍልስፍና የሚጻረሩ ናቸው። እኛ እንግዲህ ከዚህ ከሁለቱ ዓለም አንዱን መመረጥ አለብን ማለት ነው። የተቀደሰውን ወይም የጥፋትን ዓለም የመምረጡ ጉዳይ ላይ።
የተቀደሰውን ዓለም የምንመርጥ ከሆነ፣ በእኔ ዕምነት የፓርቲዎች ጋጋታ አያስፈልግም። ለእንደኔ ላለው ለተወናበደውና በውዥንብር ዓለም ውስጥ ለሚገኘው ሁለት ወይም ሶስት ፓርቲዎች ብቻ ይበቃሉ። እነዚህም ቢሆን መመሪያቸው ኢትዮጵያዊነት ወይም ብሄርተኝነት መሆን አለበት። ባለ በሌለ ኃይል አገርን ማሳደግ የሚለው የሁሉም መመሪያ መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ ሁሉንም የተማረ ኃይል ሊያሰባስብና ወደ ስራ ሊያሰማራ የሚችል ፕሮግራም ወይም ዕቅድ መንደፍ ያስፈልጋል። ሁሉም እንደየችሎታው ከርዕዮተ-ዓለም ባሻገር ሊሰባሰብና ዕውቀቱን ሊያካፍልና ተግባራዊ ሊያደርግ የሚችልበት መድረክ ያስፈልገዋል። እንደ ኢትዮጵያ የመሰለን ሰፊ አገር ለመገንባት በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢንጂነሮች፣ ሳይንቲስቶች፣ ፈላስፋዎች፣ ሃኪሞች፣ አርኪቴከተሮች፣ ዕቅድ አውጭዎች፣ ወዘተ… ያስፈልጉናል። እነዚህን ሁሉ ለማሰባሰብ ከተፈለገ የዛሬው የፖለቲካ አወቃቀርና አካሄድ አመቺ አይደለም። የግዴታ ጥራት ያለው ፖለቲካ፣ ዓላማው የታወቀ፣ ለክርክርና ለውይይት የሚያመች፣ ግን ደግሞ ወደ ጠብ የማያመራ ሁኔታ መፈጠር አለበት። የአገራችን ዕድል በጥቂት ሰዎች ትከሻ ላይ ብቻ የሚወድቅ አይደለም። የእየአንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጉዳይና፣ መብቱና ግዴታውም ነው። ለጥቂት አዋቂ ነን ለሚሉ የሚለቀቅ መሆን የለበትም። መልካም ንባብ!!
fekadubekele@gmx.de
ማሳሰቢያ፣ ለጥናት የሚሆኑ መጽሀፎች
- Bernal, Martin (1987) Black Athena: The Afroasiatic Roots of Classical Civilization,
New Jersey
- Charles, Covell (1998) Kant and the Law of Peace, Japan
- Goetschel Willi (2004), Spinoza`s Modernity: Mendelson, Lessing, and Heine,
Wisconsin Press
- Klein, Naomi (2007) The Shock Doctrine, London and New York
- ጋንሰር ዳንዬለ፣ የኔቶ የህቡዕ ወታደር በአውሮፓ ወይም ግላዲዮ በሚል ማግኘት ይቻላል፤ በአማርኛ የጻፍኩት ለጥንቃቄ ነው።
Minwuyelet says
አንዳንድ የእንግሊዘኛ ቃላትን በአማርኛ አቻ ፍቻቸዉ ብታስቀምጧቸዉ የበለጠ ይመረጣል፡፡