• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

“አበበ እንጂ መቼ ሞተ!”         

July 19, 2022 04:57 pm by Editor Leave a Comment

በአሜሪካ ኦሪጎን ጠቅላይ ግዛት እየተካሄደ ባለው የሰሞኑ የአትሌቲክስ ኢትዮጵያ እንደገና ስሟ ከፍ ብሏል። በፖለቲካው የሚታየው መከፋፈልና ጥላቻ በስፖርቱ አከርካሪውን ተመትቷል።

የዚህ ድል ምንጭ ምንድነው? ብለን ወደ ኋላ እንድናይ ያስገድደናል። ተወዳዳሪ የሌለው ወደፊትም የማይኖረው የጀግኖቹን ጀግና አበበ ቢቂላ ማስታወስ የግድ ይላል።

አበበ ሮም ላይ በባዶ እግሩ ሲያሸንፍ የዓድዋ ድል ነው በድጋሚ የተበሰረው። ጣሊያኖቹም ይህንን አልካዱም። የክብር ዘበኛው ወታደር አበበ ሲያሸንፍ “ሮምን የወረረ ኢትዮጵያዊ” ብለው ዘግበውለታል። “ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር ግዙፍ ጦር አዝምቶ ነበር፤ ሮምን ለመውረር ግን አንድ ኢትዮጵያዊ ወታደር ብቻ በቂ ሆኗል” በማለትም አትተዋል።

እነ ማሞ ወልዴና እነባሻዬ ፈለቀ “ኢትዮጵያ” የሚል ቱታ ለብሰው ሲያይ ለአገሩ ተሰልፎ ስሟን ማስጠራት የተመኘው አበበ ሐሳቡ መና ሆኖ አልቀረም። ያውም በሮም ላይ፣ ያውም ባዶ እግሩን፣ ያውም የኦሎምፒክን ሬኮርድ ሰብሮ፣ ያውም የመጀመሪያው አፍሪካዊ በመሆን በድል ላይ ድል በመቀዳጀት እናት አገሩን ከተመኘው በላይ ሰንደቋ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርጎ ያለፍ ዘመን የማይሸረው በማንም የማይረታ ጀግና ነው።

ይህ የኢትዮጵያዊነት ወኔ ወደ እነ ምሩጽ፣ መሐመድ፣ ኃይሌ፣ ደራርቱ፣ ቀነኒሳ፣ መሠረት፣ ጥሩነሽ፣ እና እጅግ በርካታዎች ደም ውስጥ አልፎ አሁን ደግሞ በኦሪገኑ ሌሎች ወርቆችን አፍርቷል። በዚህ ሁሉ ውስጥ አበበን ማሰብ ድሉን እጅግ ስለሚያደምቀው አዲስ አድማስ ጋዜጣ የዛሬ አምስት ዓመት አካባቢ “… ሳተናው እግረ ጆቢራ፤ ሎጋ ቢቂላ ዋቅጂራ …” በሚል ርዕስ ያስነበበውን እዚህ ላይ አትመነዋል።

ታላቁ ገጣሚ ጸጋዬ ገብረመድኀን በትክክል እንዳስቀመጠው አበበ አልሞተም። አለመሞቱን በኦሪገኑ እልህ አስጨራሽ ፉክክር አይተነዋል። ጀግናው አበበ ቢቂላ “አበበ እንጂ መቼ ሞተ?” ገና ወደፊትም ይኖራል። ዛሬም ባለድል ነው፤ ወደፊትም ባለድል ሆን ይቀጥላል። ኢትዮጵያም ባሸናፊነትና በክብር ትቀጥላለች።

“…ሳተናው እግረ ጆቢራ፤ ሎጋ ቢቂላ ዋቅጂራ…”

አበበ በቂላ በልጅነቱ ስፓርተኛ ነበር – በትውልድ መንደሩ፡፡ በወጣትነቱ ክብረ ወሰኖችን በመስበር የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ሆኗል – ዓለምን ያስደነቀ፡፡ በጎልማሳነቱ በመኪና አደጋ ተሸከርካሪ ወንበር ላይ ሆኖም ስፖርተኛ ነበር – ተወዳድሮ ያሸነፈ፡፡

ደብረብርሃን አቅራቢያ ጃቶ በተባለች ቦታ የተወለደው አበበ በቂላ፤ እንደአገሬው አኗኗር በልጅነቱ የ‹ቄስ ትምህርት ቤት› ሄዷል፤ የቤተሰቡን ከብቶች አግዷል፡፡ በትውልድ አካባቢው ተወዳጅ የሆነው ግን በስፖርት ነው – የገና ጨዋታ ላይ ጎበዝ ስለሆነ፡፡

ከ1944 ዓ.ም. በኋላ፤ በሃያ አመቱ፤ ክቡር ዘበኛ ሠራዊት ውስጥ ሲገባም፤ ከስፖርት ጋር ይበልጥ ተቀራረበ እንጂ አልተራራቀም፡፡ ከውትድርና አገልግሎት ጎን ለጎን፤ በሠራዊቱ የስፖርት እንቅስቃሴ በተለይም በአትሌቲክስና በገና ጨዋታ ጎልቶ ለመታየት ጊዜ አልፈጀበትም፡፡

ከአራት አመታት በኋላ ደግሞ፤ የአበበን የህይወት አቅጣጫ የሚቀይር፤ የኋላ ኋላም የኢትዮጵያን ስም የሚያደምቅ፤ አፍሪካውያንን የሚያኮራ፤ ዓለምን የሚያባንን አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ የበአል ሰልፍ ላይ፤ ‹ኢትዮጵያ› የሚል ፅሁፍ ያረፈበት ቱታ የለበሱ ስፖርተኞችን ሲመለከት፤ በዝምታ ማለፍ አልቻለም፡፡

‹እነዚህ ስፖርተኞች እነማን ናቸው› ብሎ ጠየቀ። ስፖርተኞቹ እነማሞ ወልዴና እነባሻዬ ፈለቀ ናቸው፤ ኢትዮጵያን በመወከል በሜልቦርን ኦሎምፒክ የተካፈሉ አትሌቶች፡፡ ከዚያች አጋጣሚ ነው፤ ውስጡ የነበረው የአትሌቲክ ፍቅር ወደ ውሳኔ የተቀየረው፡፡ ‹ኢትዮጵያ› ተብሎ የተፃፈበት ቱታ ለመልበስና በዓለም አቀፍ ውድድር አገሩን ወክሎ ለመሳተፍ ቁርጠኛ ጥረት ጀመረ፡፡ በዚሁ አመት የጦር ሠራዊት ብሄራዊ ሻምፒዮና የማራቶን ውድድር ተካፈለ – በወቅቱ ታዋቂ ከነበሩት አትሌት ዋሚ ቡራቱና ሌሎችም ጋር ተወዳደረ፡፡

ዋሚ ቢራቱ የ5ሺና የ10ሺ ሜትር የኢትዮጵያ ሪከርድ የጨበጡ ጀግና ስለነበሩ፤ በዚሁ የማራቶን ውድድር እንደሚያሸንፉ ቢጠበቅ አይገርምም፡፡ ሩጫውን በቀዳሚነት እየመሩ ነበር፡፡ ከተወሰኑ ኪ.ሜትሮች በኋላ ግን ስታዲዮም የነበረው ህዝብ ያልተጠበቀ ዜና ሰማ – ውድድሩን ከሚዘግቡ ጋዜጠኞች፡፡ አበበ ቢቂላ እየመራ ነው፡፡ ‹ማን ነው አበበ፤ ይህ አዲስ ባለታሪክ ማነው› በማለት በአድናቆት ሲጠብቅ የነበረው ህዝብ መልስ አገኘ – አበበ ቢቂላ ለመጀመርያ ጊዜ በተሳተፈበት የማራቶን ውድድር አሸነፈ፡፡ የጥረት እንጂ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም፡፡ ጀግና፤ ጀግናን ያፈራል፡፡

አበበ ቢቂላ በሌሎች ውድድሮችም አሸነፈ፤ በ5ሺ ና በ10ሺ ሜትር በአትሌት ዋሚ ቢራቱ ተይዞ የቆየውን ብሔራዊ ሪኮርድ ሲሰብር፤ ኢትዮጵያ አዲስ ጀግና አትሌት ማፍራቷን ተመልክታ በተስፋ በራች፡፡ የአበበ የመጀመሪያ ህልምም እውን ሆነ – በውድድሮች ባሳየው ድንቅ ብቃት ለኦሎምፒክ ቡድን ተመረጠ፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለሁለተኛ ጊዜ በምትሳተፍበት የሮም ኦሎምፒክ፤ ‹ኢትዮጵያ› ተብሎ የተፃፈበት የብሄራዊ ቡድን ትጥቅ በማድረግ ወደ ሮም አመራ፡፡

ነገር ግን፤ ከ83 አገራት የተውጣጡ ከ5ሺ በላይ አትሌቶች በተካፈሉበት የሮም ኦሎምፒክ ላይ፤ የዓለም ህዝብ ትኩረት በአውሮፖውያን አትሌቶች ላይ ነው፤ ስለኢትዮጵውያን አትሌቶች በተለይም ስለ አበበ በቂላ የሚያውቀው ነገር አልነበረም፡፡ አበበ ቢቂላ ወይም ሌላ አፍርካዊ አትሌት ሊያሸንፍ እንደሚችል አልተጠበቀም – ከዚያ በፊት አንድም አፍሪካዊ በኦሎምፒክ ታሪክ ሜዳሊያ አግኝቶ አያውቅም፡፡

የሮም ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ግን፤ የዓለምን ታሪክ ቀየረ፡፡ የውድድሩ ውጤት፤ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፤ ለመላው አፍሪካና ለዓለም ጥቁር ህዝብ ድል ያበሰረ ችቦ አቀጣጣለ፡፡ ኢትዮጵያዊያው አትሌት አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ  ሮጦ ታላቁን የኦሎምፒክ ማራቶን በአንደኝነት ከማሸነፍም በተጨማሪ፤ 2፡16፡2 በሆነ ሰዓት አዲስ የዓለም ሪከርድ አስመዘገበ፡፡ በኦሎምፒክ ታሪክ; የሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን የቻለ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ስፖርተኛ ሆኖ ስሙ በታሪክ መዝገብ በወርቃማ ቀለም ሰፈረ፡፡

አበበ ቢቂላ የማራቶንን ርቀት ሮጦ ያሸነፈውና ሪከርድ ያስመዘገበው፤ በባዶ እግሩ መሆኑ ደግሞ የመላ ዓለም ስፖርት አፍቃሪዎችን በእጅጉ ያስደነቀ ነበር – የአበበ በቂላን ስምና የኢትዮጵያን ዝና በመላው ዓለም ተቀርፆ እንዲቀር ያደረገ። ጋዜጠኞች አበበ ለምን ያለ ጫማ በባዶ እግሩ እንደሮጠ ጠይቀውታል – ዓለም ሁሉ እንዲያውቅ ፈልጌ ነው ሲል የተናገረው አበበ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ሁሌም የምናሸንፈው በጀግንነትና በወኔ እንደሆነ፤ ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ በመፈለጌ ነው ብሏል፡፡ የጣሊያንና የኢትዮጵያን የጦርነት ታሪክ እየጠቀሰ ይሆን…

የማራቶን ሩጫው አለወትሮው በምሽት ነው የተደረገው። የሮም ከተማን በቲቪ ለዓለም ህዝብ ለማስቃኘት ውድድሩን እንደጥሩ አጋጣሚ ስለተቆጠረ፤ የሩጫው መስመር የከተማዋን ዋና ዋና ክፍሎችና አደባባዮችን እንዲያካልል ሆኗል፡፡ ፈፅሞ ያልተጠበቀው አበበ በቂላ፤ ከጥቂት ኪ.ሜትሮች ሩጫ በኋላ ከሌሎች ሶስት አትሌቶች ጋር ይመራ ጀመር፡፡ የአበበ ሃሳብ ከሃያ ኪሎሜትር በኋላ መሪነቱን ለብቻው ለመቆጣጠር ነው። ግን ቀላል አልሆነለትም፡፡ ሞሮካዊው አትሌት ርሃዲ ወጥሮ ይዞታል፡፡ እንዲህ ጎን ለጎን እንደተናነቁ አርባ ኪሎሜትር ሮጠው፤ የአክሱም ሃውልት የተተከለበት አደባባይ ላይ ደርሰዋል፡፡ አበበ ድንገት ፍጥነቱን ሲጨምር፤ ሞሮካዊው አትሌት ሊቋቋመው አልቻለም፡፡ ከውድድሩ በኋላ ከጋዜጠኛ የቀረበለት ጥያቄም፤ ‹ለምንድነው ሃውልቱን ስታይ ፍጥነትህን የጨመርከው;› የሚል ነበር፡፡ ሃውልቱን ሳይ ቁጣ ስለተሰማኝ ነው ብሎ መለሰ አበበ፡፡

ምሽት ነው፤ ሃውልቱን እንዳለፉ ያለው መንገድ ላይ የተተከሉት ኤሌክትሪክ አምፑሎች ግን ጠፍተዋል፡፡ ሮም ሃያል በነበረችበት በጥንት ዘመን፤ ቆፍጣና ወታደሮች አካባቢውን እያንቀጠቀጡ በሰልፍ የሚያልፉበት ታሪካዊ መንገድ ነው። ይህንን ታሪክ ለማስታወስም ነው በአምፑሎች ፋንታ፤ በጥንታዊ የወታደር አለባበስ ያሸበረቁ ሰልፈኞች ችቦ ይዘው መንገዱን ለሯጮች እንዲያበሩ የተደረገው፡፡ የሮምን ሃያልነት ያስታውሳል በተባለው የወታደሮች ሰልፍ መሃል ሰንጥቆ በመግባት ታሪክ ቀየረ – አበበ፡፡ በማግስቱ የጣሊያን ጋዜጦች በትልልቅ ፊደሎች ጎልቶ የሚታይ ርእስ በመፃፍ፤ አዲስ ስም አወጡለት፤ ‹ሮምን የወረረ ኢትዮጵያዊ› የሚል፡፡ የክብር ዘበኛ ወታደር እንደሆነ ጋዜጠኞቹ ስለሚያውቁ፤ ‹ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር ግዙፍ ጦር አዝምቶ ነበር፤ ሮምን ለመውረር ግን አንድ ኢትዮጵያዊ ወታደር ብቻ በቂ ሆኗል› በማለት ፅፈዋል፡፡

በሚቀጥለው አመት በግሪክ፤ በጃፓንና በቼኮዝላቫኪያ በተደረጉ የማራቶን ውድድሮች ያሸነፈው አትሌት አበበ፤ ከዚያ በኋላ ለበርካታ ወራት በዓለም አቀፍ ውድድሮች ባይካፈልም፤ ስሙ ከዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አልጠፋም። አንዳንዶቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ልምምዱንና ውድድሩን እንደቀጠለ ይዘግባሉ፡፡ ሌሎቹ ጋዜጦች ደግሞ፤ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ባለው የጦርነት ስጋት ሳቢያ ወደ ድንበር እንዲዘምት መመደቡ ይወራል በማለት ፅፈዋል፡፡    

የዓለም ሚዲያዎች እንዲህ እንደጓጉ አራት አመት አለፈና የጃፓን የቶክዮ ኦሎምፒክ ደረሰላቸው – ዝነኛውን አበበ በኦሎምፒክ ማራቶን ለማየት፡፡ ይሁንና፤ በዚህ የጉጉት ፈንጠዝያ መሃል፤ አስደንጋጭ ወሬ ተሰማ – አበበ ታመመ፡፡ ኢትዮጵያውያን በድንጋጤና በሃዘን ሲዋጡ፤ ስፖርት አፍቃሪ የዓለም ህዝብ ግራ ተጋባ፡፡ አበበ በትርፍ አንጀት ህመም መሮጥ ተቸግሯል፤ ካልታከመ መኖር አይችልም፡፡ የቀዶ ጥገና ህክምና ቢደረግለት ደግሞ የማገገሚ ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ ለኦሎምፒክ የቀረው ጊዜ ከሁለት ወር ያነሰ ነው፡፡ ወከባ ሆነ፡፡
የቶኪዮ ኦሎምፒክ 6 ሳምንታት ሲቀሩት፤ የቀዶ ህክምና ተደረገለት፡፡ በፍጥነት እንደሚያገግም ተስፋ በማድረግ፤ የኦሎምፒክ ቡድን ውስጥ መካተቱ አልቀረም፡፡ ገና ጤናው ስላልተመለሰ እያነከሰ ነው የሚራመደው፡፡ ቢሆንም በቶክዮ የተደረገለት ልዩ የአድናቆትና የፍቅር አቀባበል፤ በፍጥነት እንዲያገግም እንዳገዘው ይነገራል፡፡ እንዲህም ሆኖ፤ በውድድር ይሳተፋል ተብሎ አልተጠበቀም፡፡ በእርግጥ በሮም ከተማም ያሸንፋል ተብሎ ሳይጠበቅ ነው፤ ዓለምን ጉድ ለማሰኘት የበቃው፡፡ በቶክዮ ተመሳሳይ ታሪክ እንዲደገም ተስፋ ያደረጉ አልጠፉም፡፡

አበበ ከእነማሞ ወልዴ ጋር እዚያው ቶክዮ ውስጥ ለጥቂት ቀናት አነስተኛ ልምምድ ለማድረግ ከሞከረ በኋላ፤ ሙሉ ለሙሉ ባያገግምም ለሩጫው ብቁ ነኝ ብሎ ገባ፡፡ እንደለመደው ከዋና ዋናዎቹ መሪዎች ጋር መሮጥና ከግማሽ ርቀት በኋላ መሪነቱን ለመቆጣጠር አስቧል፡፡ ያሸንፋል ብለው ያላሰቡት አድናቂዎቹ፤ በውድድሩ በመሳተፉ ብቻ ፈንድቀዋል። ገና ብዙ ደስታና ፈንጠዝያ እንደሚጠብቃቸው አላወቁም፡፡ ከግማሽ ርቀት በኋላ በቀዳሚነት መምራት ጀመረ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ከ6 ሳምንት በፊት ቀዶ ጥገና የተደረገለት አይመስልም – አሯሯጡ የአትሌቲክስ ባለሙያዎችን የሚያስደንቅ ነበር፡፡
የኦሎምፒክ ማራቶን አስደናቂ ውድድሮች ተብለው በመፅሃፍ ከታተሙት ታሪኮች ውስጥ፤ አበበ በቶክዮ ያሳየው ብቃት ዋና ተጠቃሽ በመሆን፤ ‹እንከን የለሽ ማራቶን ሯጭ› የሚል ስያሜ አስግኝቶለታል፡፡

መፅሃፉ እንዲህ ይላል -‹አበበ ደረጃ በደረጃ ፍጥነቱን ጨመረ፤ ሳይዋዥቅ በሚፈልገው ፍጥነት እቅጩን ነው የሚሮጠው – ከተሟላ ትኩረት ጋር፡፡ ከዚህ የላቀ ፍፁምነት የለም፤ እንከን የለሽ ማራቶን ሯጭ እንዲህ ነው፡፡ የቀዶ ጥገና ህክምናውም ሆነ የቶክዮ ከባድ የአየር ፀባይ አበበን የሚበግሩ አልሆኑም፡፡ ብዙ ጉልበት ሳያባክን የመሮጥ ጥበብ የተካነው አበበ፤ አንገቱን እንዳቀና የመፍሰስ ያህል ይሮጣል፤ የሩጫው መንገድ በአበበ እግሮች ስር የተንሳፈፈ ይመስላል›፡፡

የማራቶን ጥበበኞች የተሰኘ ሌላ መፅሃፍም፤ ተመሳሳይ አድናቆት አስፍሯል – ጎበዝ ሯጮች በርካታ መመዘኛዎችን ያሟላሉ፤ አበበ ግን የማራቶን አትሌት ሊመኝ የሚችለውን ሁሉ መመዘኛ ያሟላል፤ ታይቶ የማይታወቅ አትሌት ነው› ሲል ፅፏል፡፡ በውድድር መሳተፉ አጠራጣሪ የነበረው አበበ በአስደናቂ ብቃት፤ ሌሎች ተወዳዳሪዎችን በአምስት ኪሎሜትር ርቀት አስከትሎ ስቴድዮም ሲገባ… ከ70ሺ የሚበልጥ ህዝብ በዚህ ዓለም እንደገና ለማየት የሚናፍቅ ጀግንነት በአይናቸው በብረቱ ለመመልከት በመብቃታቸው ከተቀመጡበት ተነስተው፤ ደስታና አድናቆታቸውን በሆታ ገለፁ፡፡ አድናቆታቸው ሳይበርድ፤ ሌላ ተጨመረበት፡፡

ከቀዶ ጥገናው ሙሉ ለሙሉ ሳያገግም አሸናፊ የሆነው አበበ … እሱን ተከትለው የገቡ አትሌቶች እየተዝለፈለፉ ድጋፍ ሲፈልጉ፤ አበበ ግን ጅምናስቲክ በመስራት ስፖርት አፍቃሪውን ህዝብ አስገረመ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ በድጋሚ የዓለም ሪከርድ አሻሽሏል – 2፡12፡11 በሆነ ሰአት በመግባት፡፡ በሁለት የኦሎምፒክ ማራቶን አከታትሎ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች በማግኘት፤ አበበ ብቸኛው አትሌት ነው፡፡

እንዲህ ታሪክን በመቀየር፤ ዓለምን ያስደነቀው፤ ለኢትጵያና ለአፍሪካ አነቃቂ ጀግንነትን ያስመሰከረው አበበ በቂላ፤ በሌሎች ሶስት ማራቶኖችም አሸንፏል፡፡ ከዚህ በኋላ የአበበ እግሮች ያለሙት ወደ ሜክሲኮ ኦሎምፒክ ነበር። የሜክሲኮ ከፍተኛ የመሬት አቀማመጥ ከአዲስ አበባ ጋር ስለሚቀራረብ እንደሚስማማው አውቋል – ለሌላ አገር አትሌቶች ግን ይከብዳል፡፡ በዚያ ላይ ጥሩ የብቃት ደረጃ ላይ እንደሆነ ቀደም ብለው በተደረጉ ውድድሮች አሳይቷል፡፡ አበበ እንደሚያሸንፍ ምንም ጥርጥር አልነበረኝም በማለት ማሞ ወልዴ የመሰከረውም ይህንን በመመልከት ነው፡፡ ነገር ግን እግር ውስጥ የተሰበረ አጥንት ይዞ እንዴት መሮጥ ይቻላል – ለዚያምው ማራቶን፡፡

ኢትዮጵያን በመወከል ለመወዳደር የተሰለፈው አበበ ቢቂላ 15 ኪሎሜትሮችን ከሮጠ በኋላ፤ እንደተፈራው ህመሙ ከአቅም በላይ ሆኖበት ውድድሩን ለማቋረጥ ተገደደ፡፡ አበበ ውድድር ሲያቋርጥ፤ የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካዊያን አሸናፊነት አልተቋረጠም፡፡ ጀግና ጀግናን ያፈራል፡፡ ከአበበ ጋር እየሮጠ የነበረው ኢትዮጵያዊ ጀግና አትሌት ማሞ ወልዴ፤ ሳይጠበቅ ድል አድርጎ የማራቶንን ክብር ለኢትዮጵያ አጎናፀፈ።

ከ26 በላይ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮችን የተካፈለው አበበ፤ ከኦሎምፒክ ውጤቱ በተጨማሪ 1952 እና 54 ዓ.ም. የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በማራቶን አከታትሎ በማሸነፍ ድንቅ ታሪክ ሰርቷል፡፡

በማራቶን ታሪክ በወንዶች የመጀመርያው የዓለም  ሪከርድ የተመዘገበው እኤአ በ1908 በለንደን ማራቶን በአሜሪካዊው ጆን ሄይስ በ2 ሰዓት ከ35 ደቂቃ ከ18 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ነበር፡፡ ይህ የመጀመርያ ሪከርድ ከተመዘገበ ከ32 ዓመታት በኋላ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያዊ አትሌት የተመዘገበው በ1960 እኤአ ላይ በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ባሸነፈው አበበ ቢቂላ ነበር፡፡ በወቅቱ አበበ ያስመዘገበው የማራቶን ክብረወሰን 2 ሰዓት ከ16 ደቂቃዎች ከ23 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ነበር፡፡ ከ4 ዓመታት በኋላ አበበ ቢቂላ ለሁለተኛ ጊዜ የማራቶን ሪከርድን በ1964 እኤአ ላይ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ያስመዘገበ ሲሆን ጊዜውም 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃዎች ከ11 ሰኮንዶች፡፡ አበበ በቂላ በኦሎምፒክ መድረክ ባስመዘገበባቸው ሁለት የዓለም የማራቶን ሪከርዶች ለአምስት አመታት ነግሶ ቆይቷል፡፡ የዓለም ማራቶን ሪከርድን ሊያዝ የበቃው ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ከአበበ ቢቂላ ሪከርዶች 24 ዓመታት  በኋላ በላይነህ ዴንሳሞ ነበር፡፡

ዓለም በመሰከረለት ጀግንነቱና ብቃቱ፤ ዘላለማዊ ህያውነትን የተቀዳጀው አበበ በቂላ፤ በ1960 ዓ.ም. ከአዲስ አበበ ወጣ ብላ በምትገኘው ሸኖ ከተማ መኪናውን እያሽከረከረ የትራፊክ አደጋ ሲደርስበት፤ ዓለም ሁሉ ከኢትዮጵያውያን ጋር ደንግጧል፤ አዝኗል፡፡ በአገር ውስጥና በእንግሊዝ ህክምና ቢወስድም፤ በአደጋው የደረሰበት ጉዳት ከፍተኛ ስለነበረ፤ ከወገቡ በታች የሰውነት አካሉንና እግሮቹን ማንቀሳቀስ አልቻለም፡፡ ነገር ግን፤ የአትሌትነትና የስፖርተኛነት መንፈሱ እንደድሮው ብርቱ ነበር፡፡ በተሸከርካሪ ወንበር የአካል ጉዳተኞች በሚሳተፉባቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ለማሸነፍ በቅቷል፤ እንደገና የሀገሩን ባንዲራ በዓለም መድረክ እንዲውለበለብ አድርጓል፡፡ ከደረሰበት የትራፊክ አደጋ በኋላ ሁለት አመት በማይማላ ጊዜ፤ በኖርዌይ በተከናወነው የ25 እና የ10 ኪ.ሜ. የአካል ጉዳተኛ ውድድሮች በማሸነፍ ፈር ቀዳጅነቱን በድጋሚ አስመስክሯል – ለአገራችን የአካል ጉዳተኞች ስፖርት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ በመሆን፡፡

አበበ ቢቂላ ከሺ አመት እስከ ሺ አመት ሲወደስ የሚኖር ህያው የጀግንነት ታሪክ የሰራው፤ በዚህ ዓለም በቆየባቸው 41 አመታት ውስጥ ነው፡፡ በአንጎል የደም መፍሰስ ምክንያት አበበ በ1965 ዓ.ም. ሲያርፍ፤ በከፍተኛ ሃዘን የተመታው የኢትዮጵያ ህዝብ ታላቁን ጀግና ባለታሪክ በክብር ሽኝቷል፡፡ የአበበ ቢቂላ የቀብር ስነስርአት የተፈፀመው ቀዳማዊ ሃይለስላሴ በተገኙበት በአዲስ አበባ የቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን መካነ መቃብር ነው፡፡

ለማራቶኑ አምበል ሻምበል አበበ ቢቂላ ባለቅኔ ጸጋዬ ገብረመድህን “አበበ እንጂ መቼ ሞተ!!” ሲል የፃፈው ሥነግጥም  እንዲህ ይላል፡፡

የጎበዝ ነባቢት ነፍሱ
የሰው መዝርዕቱ አርአያ፤ የማይታጠፍ መንፈሱ
በጥራት የታጠፈለት፤ የምድር አጥናፍና አድማሱ
የየብስ የአየሩ ነበልባል
የማራቶን እፁብ አይጣል
የምድር አለሙ ገሞራ
አገሩን በክብር ያስጠራ
ሳተናው እግረ ጆቢራ
ሎጋ ቢቂላ ዋቅጂራ፤
የጎበዛዝ ንጥረ ወዙ
የተስፋ ብርሃን መቅረዙ።
ስሙን ላገር ስም ሰይሞ፤ የምስራች ያስደወለ
ስንቱን ስንቱን ልበ ሙሉ፤ ከአድማስ አድማስ ያስከተለ፡፡
የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ
ያረጋት የኦሎምፒክ አርማ
በወገኖቹ ልቦና፤ ቀና ኩራት ያሳደረ
እንደፍላፃ በአክናፉ፤ የአየርን ሰርጥ የሰበረ
የፍስሃዋን አዋጅ ለዓለም፤ በአቅመ ወዙ ያስነገረ
በአገር ፍቅር ልቡን ሞልቶ፤ ላቡን ነጥቦ የዋተተ
የዓለምን ጀግና በአድናቆት፤ በቅን ቅናት ያስሸፈተ
አልሞተም እንበል እባካችሁ፤ “አበበ እንጂ መቼ ሞተ!”   

(ግሩም ሠይፉ፤ አዲስ አድማስ፤24 December 2017)

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Literature, Slider Tagged With: Abebe Bekilla, Ethiopianism, Marathon, Oregon 2022

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • ሦስት ትውልድ የበላ የሐሰት ትርክት! March 23, 2023 11:59 am
  • “ሽብርተኝነቱን ማንሳቱ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም ይረዳል” – ዶ/ር ጌዲዮን March 22, 2023 05:05 pm
  • አስነዋሪ ተግባር ሲፈጸምባቸው የነበሩ የምሽት ክለቦች ተዘጉ March 22, 2023 12:57 pm
  • ህወሓትን ከሽብርተኝነት እንዲሰረዝ የወሰናችሁ ሁሉ ተጠያቂዎች ናችሁ – ኢዜማ March 22, 2023 12:06 pm
  • የኡጋንዳ ፓርላማ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን በእስር የሚያስቀጣ ወንጀል የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ አጸደቀ March 22, 2023 12:44 am
  • በጌታቸው ምርጫ ማግስት በትግራይ ሕዝባዊ ዐመፅ ተጀመረ March 21, 2023 11:01 pm
  • በትግራይ ሥልጣንና ንጉሥ ፈጣሪነት ከአድዋ ወደ ራያ ተሻገረ March 19, 2023 03:45 am
  • ኤርሚያስ ከጌታቸው ረዳ ጋር ምሥጢራዊ የስልክ ግንኙነት ነበረው March 19, 2023 02:44 am
  • እየተገባደደ ያለው የምስራቅ አፍሪቃ የትራንስፖርት ኮሪደርና ለውጥ የናፈቃት ኤርትራ March 15, 2023 04:44 pm
  • በባዶ እግር በሮም አበበን ለመድገም March 15, 2023 01:40 pm
  • አሜሪካ ሁለገብ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ናት – አንቶኒ ብሊንከን March 15, 2023 08:52 am
  • ጠቅላላ ጉባኤን ያስተጓጎሉ ላይ ክስ እንዲመሰረት ምርጫ ቦርድ ጠየቀ March 15, 2023 08:48 am
  • በኦሮሚያ የተሽከርካሪ ፍጥነት መገደቢያ ገጠማ ያለ አግባብ ለአንድ ግለሰብ ተሰጥቷል ተባለ March 15, 2023 01:43 am
  • ምርጫ ለተወዳደሩና እውቅና ላላቸው ፓርቲዎችመንግሥት 106 ሚሊዮን ብር መደበ March 15, 2023 12:52 am
  • አረመኔና Transgender “ደፋር ሴቶች” ተብለው በተሸለሙበት መዓዛም ተሸለመች  March 10, 2023 10:45 pm
  • ዓድዋ 127 በዓድዋ ከተማ March 2, 2023 09:56 am
  • በምኒሊክ አደባባይ የአድዋ ድል በዓል አከባበር ላይ ምን ተፈጠረ? March 2, 2023 09:43 am
  • አውቶቡሶቹ ከዓለም ባንክ በተገኘ ብር ነው የተገዙት February 24, 2023 10:44 am
  • በአውቶቡሶቹ ግዢ ቢያንስ 1 ቢሊዮን ብር ተሰርቋል፤ ዶ/ር ዐቢይ አስቸኳይ ማብራሪያ ጠይቀዋል February 24, 2023 08:39 am
  • የውርደት ፖለቲካና ፕሮፓጋንዳ! February 24, 2023 08:19 am
  • “አማርኛን የአፍሪካ ኅብረት የሥራ ቋንቋ በማድረግ የኢትዮጵያ ብቻ ሣይኾን የአፍሪካም ማድረግ ይገባል” ራህማቶ ኪታ February 21, 2023 10:09 am
  • አማርኛ የአፍሪካ ኅብረት ቋንቋ እንዲሆን የቀረበ ጥሪ February 21, 2023 10:01 am
  • በገፊና ጎታች ሤራ ከመፈንቅለ ሲኖዶስ እስከ መፈንቅለ መንግሥት February 17, 2023 06:39 pm
  • ኦነግ ሸኔ አሸባሪነቱ ሳይነሳለት በሽመልስ የሰላምና የእርቅ ጥሪ “በክብር” ቀረበለት February 17, 2023 12:35 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule