የትምህርት ሚኒስቴር አካሄዱኩት ባለው የዳሰሳ ጥናት፣ በበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከ30 በመቶ በላይ መምህራን እንደማያስፈልጉ መታወቁን ሚኒስትሩ አስታወቁ፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የተቋማቸውን የ2015 ዓ.ም. ሩብ ዓመት አፈጻጸም ማክሰኞ ኅዳር 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ለፓርላማ ሲያቀርቡ፣ ዩኒቨርሲቲዎች በአማካይ በሴሚስተር አራት ኮርስ ወይም 12 ክፍለ ጊዜ መያዝ እንዳለባቸው ቢጠበቅባቸውም፣ ብዙዎቹ መምህራን በሴሚስተር አንድ ኮርስ አስተምረው የሙሉ ጊዜ መምህራን ተብለው እንደሚጠሩ ተናግረዋል፡፡
በዚህም የተነሳ የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆን ከበጀታቸው ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል የመምህራን ቁጥር በመያዝ፣ በልካቸው ሊራመዱ እንደሚገባ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዎች ከሌሎች የገንዘብ ምንጮች በሚያገኙዋቸው ገቢዎች ተወዳዳሪና ተመራጭ የትምህርት ተቋም የሚያደርጓቸው ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩሩ፣ ውድድርን መሠረት አድርገው ለመምህራኖቻቸው የተሻለ ደመወዝ ሊከፍሉ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የተሻለ የደመወዝ ክፍያ መፈጸም ምንም ጥያቄ የሌለው ጉዳይ ቢሆንም፣ ባለው አገራዊ ሁኔታ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በሲቪል ሰርቪስ ሕጉ እስከተገዙ ድረስ፣ መንግሥት ደመወዝ ልጨምር ቢል ጭማሪው ለዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ሳይሆን፣ ለሁሉም ተቋማት መጨመር ስላለበት ይህ የማይቻል ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
“አገሪቱ አሁን ካለችበት የጦርነት ድባብ ውስጥ ወጥታ የደመወዙ ጉዳይ በድጋሚ ታይቶ እንዲታሰብና መምህራን የተከበሩ እንዲሆኑ እናደርጋለን፡፡ ድሮ ‹ሙሽሪት ኩሪ ኩሪ ወሰደሽ አስተማሪ› ይባል ነበር፡፡ አሁን ግን መምህርነት በገቢ ልክ ከሆነ መምህርነት ሚስትም የሚያስገኝ አይመስለኝም” ብለዋል፡፡
በመሆኑም ይህ አሠራር መቀየር እንዳለበት የገለጹት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ መምህር የተማሪዎቹ ወላጆች ጓሮ ውስጥ ተከራይቶ እየኖረ “መምህር ተከብሮ ይኑር” ማለት ከባድ በመሆኑ መስተካከል እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከጥቂት ወራት በፊት የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ባቋቋሟቸው ማኅበራት አማካይነት፣ መንግሥት የደመወዝ ጭማሪና የእርከን ዕድገት እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ (ሪፖርተር)
Berelea says
አይ ብሬ ማይክ በያዝክ ቁጥር ቀልድህ ይጨምራል ምን እንደምትናገር ስለማታውቀው እላይ የተናገርከውን ከታች ታፈርሰዋለህ መገለባበጥ የተሰራህበት ስለሆነ ለመከርበት ችግር የለብህም ለስርአቱ በጣም አስፈላጊ ሰው ነህ።