አምስት ዓረፍተ ነገሮች፤
ኢሰመጉ መንፈሳዊ ተልእኮ ያለው መንፈሳዊ ድርጅት ነው፤ ዓላማው በሰው ልጆች መሀከል የሚከተሉትን ተልእኮዎች መዝራት ነው፡–
1.1. እኩልነትንና ነጻነትን
1.2. ፍቅርንና ስምምነትን
1.3. ፍትሕንና ሕጋዊነትን
1.4. ሰላምንና ማኅበረሰባዊ እድገትን
1.5. የእውነትንና የእውቀትን ብርሃን ማስፋፋትን
ኢሰመጉ የተቋቋመው በሁለት ምክንያቶች ነው፤–
2.1. የደርግ አገዛዝ ወድቆ አዲስ መንግሥት በአዲስ ሥርዓት ይመሠረታል በሚል ተስፋ አዲሱ ሥርዓት የኢትዮጵያን ሕዝብ ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲመራ ለመርዳት ነበር፤
2.2. የኢትዮጵያን ሕዝብ በመብት ጉዳይ ለማንቃትና ራሱን ከተገዢነት ወደገዢነት ደረጃ እንዲለውጥ ለማስቻል ነበር፡፡
ለትውልድ የሚተላለፍና ስምን ሲያስጠራ የሚኖር ሥራ ለመሥራት ሀብት ጥሩ መሣሪያ ነው፤ በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው ሰዎች ለኢሰመጉ ሀብት ማውረስን ቢለምዱ የኢሰመጉ ዓላማዎችን ለማስፋፋትና ማኅበረሰባችንን ወደተሻለ አቅጣጫ ለመግፋት የተሻለ ኃይል ይኖር ነበር፤ ከውጭ ሰዎችም ጥገኛነት ለመውጣትና ራሳችንን ወደሰውነት ደረጃ ለመግፋት ያስችለን ነበር፡፡
እንዲያም ሆኖ በአለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ ጠንካራ በጎ መንፈስን ብቻ በታጠቁ ጥቂት ሰዎች፣ በትንሽ ገንዘብ አዲስ የትውልድን አቅጣጫ የሚያመለክት ሥራ የሠራ ከኢሰመጉ ጋር የሚወዳደር ድርጅት የለም፤–
3.1. ከውጭም ከውስጥም የተሰነዘረበትን ዛቻና ግፊት ተቋቁሞ ቀጥ ብሎ ዓላማውን ሳይስት የቆየ
3.2. ቢከሳም ሕይወቱን ያላጣ ድርጅት ነው፤
3.3. የኢሰመጉ መክሳት የማኅበረሰቡን መክሳት የሚያመለክት ነው፤
3.4. በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ማኅበረሰቡ ኢሰመጉን በሚገባ ባለመደገፉና እንዲከሳ በማድረጉ ራሱንም አከሳ፤ ራሱን ጎዳ፤ እስከዛሬ አንድም ባለሀብት ለኢሰመጉ ቋሚ ሀብት ያወረሰ አለመኖሩ አስተሳሰባችን ከግለሰብ ወደማኅበረሰብና ወደትውልድ አለመሸጋገሩን ያመለክታል፤
3.5. እስከዛሬም ድረስ ቢሆን ማኅበረሰቡ የኢሰመጉን መንፈሳዊ ተልእኮ በትክክል ተገንዝቦ ኢሰመጉን በመርዳት ራሱን ለመርዳት የሚያስችለው ደረጃ ላይ ገና አልደረሰም፡፡
በዚህ በዓል ላይ እኔ ያረቀቅሁትን የኢሰመጉን ደንብና ቃል ኪዳን ሁለት የሕግ ባለሙያዎች፣ ወርቁ ተፈራና ዓሥራት ገብሬ ብዙ ጊዜ አጥፍተውበት በማሻሻላቸውና የባለሙያ ሥራ በማድረጋቸው፣ በተጨማሪም የመጀመሪያው የኢሰመጉ ቢሮ በዓሥራት ገብሬ ቢሮ ውስጥ ሆኖ የሱ ጸሐፊም የኢሰመጉን ሥራ እንድትሠራ በማድረግ ያበረከተው እርዳታ ኢሰመጉ በራሱ እግር እስቲቆም ድረስ ደግፎታል፡፡
መደምደሚያ
የኔ ትውልድ አንድ በአንድ እያለ በመመናመን ላይ ነው፤ የእኔም ተራ እየደረሰ ነው፤ ለኢሰመጉ የማወርሰው መሬትና ቤት የለኝም፤ መጻሕፍት ሞልተውኛል፤ የአዋሳ ሕዝብ አሁን ኢሰመጉ ያለውን የመጻሕፍት ቤት ለሕዝብ የሚጠቅም ሊሆን በሚችልበት ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ቤት ቢያገኝለት አብዛኛዎቹን ለአዋሳ ለማውረስ ወስኛለሁ፤ ቤትና አስተናባሪ ከአልተገኘለት ውርሱን ለማስፈጸም አስቸጋሪ ይሆናል፤ በአዲስ አበባ ብዙ አማራጭ የመጻሕፍት ቤቶች ስላሉ የአዋሳን ኢሰመጉ መጻሕፍት ቤት ማጠናከሩ የተሻለ ይመስለኛል፤ በተጨማሪም ከኢሰመጉ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ አዋሳ በጣም ልቆ የቆየ በመሆኑ ለማበረታታት ነው፤ ከአዋሳ ነዋሪዎች መሀከል አንድ ቤተ መጻሕፍቱን በስሙ ለማስጠራት የሚፈልግ ሰው ለኢሰመጉ አንድ ቤት የሚሰጥ ወይም የሚያወርስ እንዲገኝ ጥረት ሊደረግ ይገባል፡፡
በመጨረሻም ለዛሬ በዓል፤
በስደት ላሉት ለአበበ ወርቄና ለዓሥራት ገብሬ
በሕመም ምክንያት በመሀከላችን ላልተገኙት አንዳርጋቸው ተስፋዬና ለጌታቸው ተሰማ
በሕይወት ለሌለው አብሮ-አደጌ ወርቁ ተፈራ፣ ነፍሱን ይማረው፤
ለቸርነቱ ወደር ለሌለው ጓደኛዬ አባተ የኔው — ኢሰመጉ ከስዊስ አምባሳደር ጋር ውዝግብ በተነሣበት ጊዜ መኪናዬንም ቢሆን ሸጬ አሥር ሺህ ዶላርህን እመልስልሃለሁ ያልሁትን በጋዜጣ እንብቦ፣ እቤቴ ድረስ መጥቶ የአሥር ሺህ ዶላር ቼክ ጽፎ ‹‹መኪናህን እንዳትሸጥ፤ ያውልህ አፍንጫው ላይ ወርውርለት!›› ያለኝ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ሰው ነው፤ ነፍሱን ይማረው፡፡
በነዚህ በስድስት ሰዎች ስም የአምስት ወር ጡረታዬን አውጥቼ የአምስት መቶውን ብር ቲኬት በስማቸው በመግዛት ላስታውሳቸው እፈልጋለሁ፡፡
ላስታውሳቸው እፈልጋለሁ፡፡
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
ጥቅምት 2009
Tesfa says
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም አንጡራ የሃገራችን ሃብት ናቸው። ለዚህም በዘመናት መካከል ያላቸው አይበገሬ እይታና የግልና የቤተሰብ የህይወት ስኬታቸው ምስክር ነው። ሰው ሁሉ በየወገንህ ሲባል አይመቸኝም እኔ ኢትዮጵያዊ እንጂ ሌላ ልሆን አልችልም በማለት የቀኑ አለቆቻችንን የተንሻፈፈ የፓለቲካ ስልፍ አጥፊነት ገና ከጅምሩ በይፋ የተጋፈጡና በመታገል ላይ ያሉ የእድሜ ባለጸጋ ናቸው።
አልፎ አልፎ እርሳቸውን የሚያጥላላ መጣጥፍ በዚህም በዛም በየስርቻው የተሰገሰጉ የወያኔ ፍርፋሪ ለቃሚዎች የሚለጣጥፉትንም እናውቃለን። ህዝባችን ግን ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም ማን እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል። በአንድ ወቅት ፕ/ሩ ከወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ጋር ቆመዋል። በድንገት ጠበንጃ ያነገቱ የወያኔ ተቀላቢዎች በስፍራው ግር ግር ይፈጥሩና ወይዘሪቱን ወደ ማረፊያ ቤት (ለእሥር) ለመውሰድ ዙሪያውን እንደ ጅብ ከበዋታል። ፕ/ሩም ተው እኛ ወደእናነተ ጋ እናመጣታለን አታዋክቧት በማለት ይናገራሉ። የወንድምና የእህቱ ሬሳ ወድቆ ካላየ የበላየነት የማይሰማውና በብሄር ጥላቻ ውስጡ የተመረዘው ታጣቂ ፕ/ሩን በሰደፍ መታቸው። ዛሬም ወያኔ ያስፈራራቸዋል። ይምከሩን ከማለት ይልቅ እንዳይጽፉ፤ እንዳይናገሩ አፈና ያረግባቸዋል። ሌላ ሰለ ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያምና መሰሎቹ ብዙ ማለት ይቻላል። ግን ሥፍራና ጊዜ የለም። በተቻለን ሁሉ የህዝባችንንን ሰቆቃ ለማስታገስ ዘርና ወገን ሳንለይ የወያኔን ከፋፋይና እኛ ብቻ እንብላ ባይነት እንታገለው።
ሙናች says
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም!
በተግባር የተገለጸ ለሃገር/ለሕዝብ ያለዎት ከልብ የመነጨ እውነተኛ ፍቅር እጅግ የሚገርመኝና በሕይወት ዘመኔ ሁሉ የማረሳው ሃብት ነው፤ ለዚህ አባባሌ ማስረጃ የሚሻ አእምሮ ላላችሁና ፕ/ርን እንደ እኔ ቀርባችሁ ሳታውቋቸው በጭፍን ጥላቻ ለምትጠሏቸውና አንዳንዶችም በዚህ ጉዳይ ላይ በግል ከእኔ ጋር ለተጋጫሁ ወገኖቼ ለማንነታቸው መረጃ እንካችሁ፡
1/ እኔ እንኳ ባልነበረኝ አቅም መኖሪያ ቤት ተንደፋድፌ ሥሠራ አቅሙ እያላቸው ለሕዝቡ ሕይወት ቅድሚያ መስጠታቸው በቀበሌ ቤት መወሰናቸው
2/ ብዙዎቻችን ከሃገር ለመውጣት ነፍስ ውጪ ግቢ ጥረት ስናደርግ በረካታ የውጭ ሃገር ዩኒቨርስቲዎች በሌክቸረርነት ሲለምኗቸው ሃገሬን ለማን ትቼ?
3/ ከማንም ሰው ወይም ድርጅት ወይም መንግሥት ጋር የሚጋጩት ለሃገር/ለሕዝብ መሻሻልና ጥቅም ባለ አመለካከትና ተግባር ላይ እንጂ በግል ማንነትና ምንነት ላይ አለመሆኑ ከማንም ሰው ለየት ያደርጋቸዋል (ለምሳሌ የሕዋት አባላትንና ድርጊታቸውን ለየተው የመፈረጅ እይታ)
4/ ቂመኞችና በቀለኛች በሁለቱም ሃገሮች (ኢትዮጵያና ኤርትራ)ውስጥ በተደረገው የማስወጣት ሥራ ላይ የፈጸሙትን ግፍና በደል አጥብቀው መቃወማቸውና ወቅታዊ መግለጫ በማውጣት መጋፈጣቸው
5/ መንግሥትም ሆነ አንዳንድ ውሃ አላማጮች ኢሰመጉ የፕ/ር መስፍን የግል ሃብት ወይም የፖለቲካ ድርጅት ነው ለሚሉ የሃሰት አባቶች አፍ ማስያዣ ይሆን ዘንድ ኢሰመጉን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃብት ለማድረግ ከድርጅቱ አመራር እራሳቸውን ያገለሉበት ጊዜ እንደነበረ ምስክር ነኝ
6/ በአጠቃላይ ፕ/ር መስፍን እንደ ሰው ለራሳቸው ያልኖሩ ሃብት ለማካበትና ስልጣን ለመያዝ ያልደከሙ ነገር ግን ከጃንሆይ ጀምረው ለራሳቸው እንጂ ለሕዝብ ያልቆሙትን 3ቱንም መንግሥታት ለሚወዱት ምስኪን ወገናቸው ፍትህና እድገት ሲሉ ብቻ በድፍረት የተጋፈጡ፣ የተንገላቱ የታሰሩና የታመሙ የምድሪቱ በረከት መሆናቸውን ለ4 ዓመታት አብሬያቸው በመሆን በቅርብ የማውቃቸው ካለመጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስ ኢየሱስን ወንጌል በተግባር የሰበኩ እውነተኛ ሰው በመሆናቸው ሁላችንም አርያነታቸውን ብንከተልና ለሃገር ጥቅም ብናውለው መልካም ይሆናል!!!
ለፕ/ር መስፍን ግን የሚያነቡኝ ከሆነ:
ካመሰገኗቸው ሰዎች መካከል እነዚያ በነፍሳቸው ጨክነው ከጎንዎ በመሆን መረጃዎችን ከማይደፈሩ ከሚመስሉ ቦታዎች/ምሳሌ ከእስር ቤት/ ፈልፍለው በማውጣት መግለጫዎች እንዲወጡ ያደርጉ የነበሩና አሁን በውጭ አገር ተበትነው አሁንም እርስዎ ያስተማሯቸው ለወገን የመጮህ ሥራቸውን ያላቋረጡትን ወጣቶች ባለማካተትዎ ቅር ብሎኛል!!! ሽምግልናው ተጭኖዎት ከሆነ ምንም አይደለም KKKKKKKKKKK = የራስዎ ሳቅ!
ሰላምና ጤና ይስጥዎ
እጅግ ወዳጅዎ
ሙናች ነኝ