የሚፈለገው ለውጥ ዋናው ዓላማ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈለገውን አስተዳዳሪዎቹንና የአስተዳደር ሥርዓትን በነፃነትና በዴሞክራሲ መንገድ ሊመርጥ የሚችልበትን ሥርዓት መመሥረት ነው። ህወሃት የዘረፋ ሥርዓቱን ለማቀላጠፍ እንዲመቸው ዘንድ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መመሪያ በማድረግ ፖለቲካውን የማጭበርበሪያ፣ ኢኮኖሚውን የመዝረፊያ፤ ዳኝነትን የመበቀያ፣ ደህነነትን የማሸበሪያና መከላከያን የማጥቂያ መዋቅሮች አድርጎ ለሃያ ሰባት አመት በኢትዮጵያ ሕዝብና በአገር ላይ ከባድ ግፍና መከራ እየፈፀመ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የመጀመሪያ ዋና ጥያቄ ይህንን ሕዝቡንና አገሪቷን ከላይ እስከ ታች በኢ-አብዮታዊ ዴሞክራሲና በኢ-ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በመጠፍነግ ለጥቂቶች ገነት ለአብዛኛው ሕዝብ ግን መከራና ስቃይ የሆነውን ሥርዓት በሰላማዊ መንገድ መለወጥ ነው። ዶ/ር አብይ ከሚናገሩትም ሆነ ከገዱ ቡድንና ከለማ ቡድን ጋር ያላቸውን አንድነትና ቅርበት በማየት መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ፍላጎት እንዳላቸው መገመት ይቻላል፣ ነገር ግን ይህን ፍላጎታቸውን በተግባር ለማሳየት ይችላሉ ብሎ ለማመን ግን ጠ/ር አብይ ያሉበትን የተቆላለፈ የሥልጣን እርከን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። ፍላጎት አንድ ነገር ሲሆን፣ ፍላጎትን ወደተግባር መለወጥ መቻል ደግሞ በጣም የተለየ ነገር ነው። ፍላጎትና ችሎታ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ለውጥ ሊኖር የሚችለው ግን ሁለቱም በአንድ ላይ ሲቀናጁ ነው።
ዶክተር አብይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ያልተቋረጠ ትግልና በኢህአዴግ ምክር ቤት ውስጥ የኦህዴድንና የብአዴንን ሙሉ ድጋፍና ከደኢህዴንም የተወሰነ ድጋፍ በማግኘት ጠ/ሚ ለመሆን ችለዋል። የሊቀመንበርነቱ ምርጫ በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ቢሆን ኖሮ አብይ ጠ/ሚ ለመሆን አይችሉም ነበር። ምክንያቱም የህወሃት የበላይነት በኢህአዴግ ምክር ቤት ውስጥ እየተወገደ ቢሆንም በተቃራኒው ግን የህወሃት የበላይነት በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ እንደቀጠለ ነው። የህወሃትን የፓለቲካ አቅም ለመገንዘብ እነዚህን የኢህአዴግ ሁለት ቁልፍ የፓለቲካ መዋቅሮች ማለትም የኢህአዴግ ምክር ቤትንና የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴን በሚገባ መረዳት ይገባል።
የኢህአዴግ ምክር ቤት አንድ መቶ ሰማንያ አባላት ሲኖሩት፣ እነዚህም ከአራቱ ድርጅቶች ማለትም ከህወሃት፣ ከደኢህዴን፣ ከብአዴንና ከኦህዴድ ከእያንዳንዳቸው አርባ አምስት አባላት የተወከሉበት ነው። የኢህአዴግ የሥራ አስፈፃሚ ደግሞ ከአራቱ ድርጅቶች ከእያንዳንዳቸው ዘጠኝ አባለት የተወከሉበት በጠቅላላው ሰላሳ ስድስት አባላት ያሉት ነው። መቶ ሰማንያ አባላት ያለውን የኢህአዴግ ምክር ቤት በተለይ በብአዴንና በኦህዴድ አባላት ውስጥ የገዱ ቡድንና የለማ ቡድን ጠንክረው በመውጣታቸው ህወሃት የኢህአዴግ ምክር ቤትን እንደቀድሞው ሊጠቀምበት አልቻለም። የኢህአዴግ ምክር ቤት ከህወሃት ሎሌነት እራሱን ነፃ በማውጣት ላይ የሚገኝ አካል ቢሆንም በህወሃት ኢ-ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የመጠፍነጊያ አሰራር መሰረት የፌደራል መንግስቱን ሥልጣን የሚቆጣጠረውና የሚዘውረው ግን ቱባ ቱባ ባለሥልጣኖች ያሉበትና በህወሃት የሚጋለበው ሰላሳ ስድስት አባላት ያሉት የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሜቴ ነው።
የጠ/ሚ አብይ ሕገ መንግስታዊ ሥልጣንም ህወሃት እንደፈለገ በሚዘውረው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተገደበ ነው። ምክንያቱም በኢህአዴግ አሰራር የግንባሩ ሊቀመንበር የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የሚወስነውን የሚያስፈፅም ነው። ይህንንም በሚገባ ለመቆጣጠር ህወሃት የኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊነትን በሞንጆሪኖ (ፈትለወርቅ) አማካኝነት የተቆጣጠረ ሲሆን፣ ሞንጆሪኖ በቅርቡ ከህወሃት ውስጥ የመለስ ዜናዊን አንጃ በማዳከምና ህወሃትን እንደድርጅት ለማጠናከር እየደከመች ያለች በህወሃት የበላይነት የምታምን ፅኑ የህወሃት ካድሬ ናት። በህወሃት ኢ-ዴምክራሲያዊ ማዕከላዊነት አሰራር መሠረት የኢህአዴግ ሊቀመንበር (አሁን ዶክተር አብይ) የሚሰራው በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውሳኔ መሠረት ብቻ ሲሆን፣ ይህንንም በየቀኑ የሚቆጣጠረውና የሚከታተለው የኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊዋ ሞንጆሪኖ ነት።
በቀላል አገላልፅ ሞንጆሬኖ ጠንካራ የህወሃት ታማኝ ካድሬ የዶክተር አብይ ተቆጣጣሪ እንድትሆን በህወሃት ተመድባለች። በዚህ አሰራር ያልተገደበው መለስ ዜናዊ ብቻ ነበር። መለስ ዜናዊ አምባገነናዊ ሥልጣኑን የተቆናጠጠው የደህንነት (የማሸበሪያ) እና የመከላከያ (የማጥቂያ) መዋቅሮችን በታማኞቹ በማስያዝና በኢህአዴግ ውስጥ ሎሌዎቹን በማጠናከር በኢትዮጵያ ላይ የህወሃትን የበላይነት በማስጠበቅ ነበር። ህወሃቶችን የመለስ ዜናዊ አምባገነንነት ባያስደሰታቸውም የህወሃትን የበላይነት በማስጠበቁ ብቻ ብዙም አልተጨነቁም። የህወሃት ስሌት የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው በመሆኑ ነበር። አሁን ዶክተር አብይ ግን መለስ ዜናዊን ሊሆኑ አይችሉም። ከኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ሲነፃፀር ጠ/ር አብይ አህመድ የታሰሩበት ገመድ ረዘም ብሎ ሊሆን ይችላል እንጂ ከእስሩ ነፃ አይደሉም።
ስለዚህ ለጠ/ር አብይ ጊዜ ስለተሰጣቸው ብቻ መሠረታዊ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ብሎ መጠበቅ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ ዋናው ጥያቄ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን የለውጥ ፍላጎት ለመርዳት ምን ማድረግ ያስፈልጋል ቢሆን ለሕዝባዊ ትግሉ ጥሩ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ይህም የጠ/ር አብይን እውነተኛ የፖለቲካ ሥልጣን ከህወሃት የበላይነት ነፃ ለማድረግ የሚቻልበትን የትግል ዘዴ ለይቶ በማወቅ የሚደረገውን ሕዝባዊ ትግል የህወሃትን የበላይነት ከፖለቲካው ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ በሚቻልበት መንገድ ላይ ለማድረግ ይጠቀማል። ሕዝባዊ ትግሉ የገዱንና የለማን ቡድን በመፍጠር የኢህአዴግን ምክር ቤት ከህወሃት የበላይነት እያላቀቀ የመጣ ሲሆን፣ አሁንም ሕዝባዊ ትግሉ የኢህአዴግን ሥራ አስፈፃሚ ከህወሃት የበላይነት ነፃ በማውጣት ሕዝቡ ለመሠረታዊ ለውጥ የሚያደርገውን ትግል በአንድ እርምጃ ማሳደግ ይችላል።
ስለዚህ አንዱ የወቅቱ የትግል ዘዴ ሊሆን የሚገባው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚን ከህወሃት የበላይነት እንዴት ማላቀቅ ይቻላል የሚለው ሊሆን ይችላል። ለዚህም የመጀመሪያ ሥራ በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ የለማና የገዱ ቡድን ደጋፊ የሆኑትን እና የህወሃት ታማኝ የሆኑትን የብአዴንና የኦህዴድ አባላቶች መለየት ነው። ህወሃት የኢህአዴግን ሥራ አስፈፃሚ በበላይነት የሚቆጣጠረውና እንደ ፈረስ የሚጋልበው ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ ባሉ የህወሃት ታማኝ በሆኑ የደኢህዴን፣ የብአዴንና የኦህዴድ አባላት አማካኝነት ነው። እነዚህ ግለሰቦች ውክልናቸው ተመርጠን መጥተንበታል ለሚሉት ሕዝብ ሳይሆን የትግራይ ክልል ተወካይ ነኝ ለሚለው ህወሃት ስለሆነ ይህንን እውነታ ተመርጠን መጥተንበታል ለሚሉት የምርጫ ወረዳ ሕዝብ በተገቢውና በጥንካሬ በማስረዳት ሕዝቡ አመኔታውን እንዲነሳቸው የማድረግ ሕገ መንግስታዊ መብት ሕዝቡ አለው። ይህ እንግዲህ የቄሮና የፋኖ ዋናው የሰላማዊ ሕዝባዊ ትግል አቅጣጫ ሊሆን ይችላል።
በተለይ ከኦህዴድና ከብአዴን የተወከሉ ግን ለህወሃት ታማኝ የሆኑ የኢህአዴግ የሥራ አስፈፃሚ አባላት ከአስር የማይበለጡ ግለሰቦችን ሕዝቡ ሕገ መንገስታዊ መብቱን በመጠቀም በማንኛውም ጊዜ በሰላማዊ ትግል ከፓርላማም ሆነ ከክልል ምክር ቤቶች ማባረር ይችላል። ይህንንም በማድረግ እነዚህ የህወሃት ታማኞች በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ ያላቸውን ወንበርና በመንግስት ውስጥ ያላቸውን ስልጣን እንዲለቁ በማድረግ በሌሎች የህወሃትን የበላይነት በሚቃወሙና ለውጥ በሚፈለጉ አባላቶች እንዲተኩ ሕዝቡ በሰላማዊ ትግሉ ሊያስገድድ ይችላል። አሁን ባለው ሕገ መንግስ አንቀፅ አምሳ አራት ቁጥር ሰባት መሰረት ”ማንኛውም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የመረጠው ሕዝብ አመኔታ ባጣበት ጊዜ በሕግ መሠረት ከምክር ቤቱ አባልነት ይወገዳል” ይላል። ስለዚህ በሕዝብ አመኔታ በማጣት የተወገደን አባል የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ በአመራር ለማስቀጠል ስለማይችል የብአዴንና የኦህዴድ ማዕከላዊ ምክር ቤቶች በሌሎች አባላቶች እንዲተኩ ማድረግ ይችላሉ።
የኦህዴድና የብአዴንና ማዕከላዊ ምክር ቤቶች ከህወሃት ሎሌነት ነፃ በመውጣት ላይ የሚገኙ በመሆኑ ለህወሃት ሳይሆን ለድርጅታቸው ታማኝ የሆኑ አዳዳሲ አመራሮችን መሾማቸው የግድ ይሆናል። በዚህ መንገድ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚን ከህወሃት ታማኞች በማፅዳት የህወሃትን የበላይነት ከፖለቲካው ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ይቻላል። ጠ/ር አብይን ለመርዳት የሚቻለው አንዱ መንገድ የለውጥ አካል የሆነው የነለማና የነገዱ ቡድን በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ የበላይነት እንዲኖረው ማድረግ ነው። ሕዝባዊ ትግሉ ይህንን የማድረግ ብቃት አለው። ስለዚህ ሕዝባዊ ትግሉ የለውጥ ኃይልንና የለውጥ እንቅፋት ቡድንን በመለየት፤ በአሁኑ ወቅት የህወሃት ሎሌ ሆነው የለውጥ እንቅፋት የሆኑትን ግለሰቦች ከኦህዴድና ከብአዴን ውስጥ አሁን ያለው ሕገ መንግስት በሚፈቅደው መሠረት በሰላማዊ ሕዝባዊ ትግል ማስወገድ ይቻላል። ህወሃትን በፓለቲካው መዋቅር ውስጥ በተለይም ቁልፍ በሆነው በፌደራል መንግስቱ ውስጥ ያለውን የበላይነቱን ማስወገድ ከተቻለ ለሕዝባዊ ትግሉ የለውጥ ጥያቄ አንድ ታላቅ ድል ይሆናል።
በህወሃት የዘረፋ መር በሆነው መርዕ መሠረት ፓለቲካ የማጭበርበሪያ፣ ኢኮኖሚ የመዝረፊያ፤ ዳኝነት የመበቀያ፣ ደህነነት የማሸበሪያ እና መከላከያ የማጥቂያ መዋቅሮች ናቸው። ህወሃት የፖለቲካ (የማጭበርበሪያ) የበላይነቱን ከተነጠቀ የሚቀረው የኢኮኖሚ (የዘረፋ)፣ የደህንነት (የማሸበሪያ) እና የመከላከያ (የማጥቂያ) ኃይል የበላይነት ናቸው። እነዚህ የዘረፋና የመጨቆኛ መዋቅሮቹ ብቻቸውን ያለፖለቲካ መዋቅር የህወሃትን አገዛዝ ሊያስቀጥሉ አይችሉም። ያለኦህዴድ፣ ብአዴንና ደኢህዴን ሎሌነት የህወሃት የግፍና የዘረፋ አገዛዝ በኢትዮጵያ ውስጥ እውን ሊሆን አይችልም ነበር አሁንም አይቻልም። ህወሃት የፓለቲካ (የማጭበርበሪያ) የበላይነቱን በመነጠቁ የእብደት መንገድ የሚመርጥ ከሆነ የሚቀረው አማራጭ በጥቂት ጀነራሎች የሚመራ ግልፅ የወጣ ወታደራዊ መንግስት መመስረት ሊሆን ይችላል። ይህም ደግሞ በኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ በአፍሪካና በዓለም በፍፁም ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ የህወሃትን የአገዛዝ እድሜ በፍፁም ሊያራዝመው አይችልም።
ከአሁን በኃላ የኢትዮጵያ ሕዝብ የህወሃትን የግፍ አገዛዝ የሚሸከምበት ትዕግስትም አቅምም የለውም። ህወሃቶችም ይህ በሚገባ ገብቷቸዋል። ነገር ግን አሁንም ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ህወሃት የሚወገዘው የበላይነቱን ተጠቅሞ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይና በአገር ላይ ከፍተኛ ወንጀሎችን ስለፈፀመ ነው እንጂ አመጣጡ ከትግሬይ ስለሆነ አይደለም። ህወሃትን መቃወም ትግሬን መጥላት አይደለም። ህወሃት ግፈኛና ወንጀለኛ ድርጅት ነው የሚባለው በዋንኛነት ንፁሃን ኢትይጵያውያንን ወንጀሎችንና ወንጀለኞችን ስለተቃወሙ ብቻ በመግደሉ፤ ንፁሃን ሰዎችን በእስር ቤት በጨለማ ክፍል በማጎር ለአመታት በማሰቃየቱ፤ የሕዝብና የአገርን ሀብት በመዝረፉ፣ በመመዝበሩና በማስመዝበሩ፤ ማጭበርበርን እንደ ፓለቲካ መሣሪያ በመጠቀም በሕዝብ ላይ ውሸቶችን በማሰራጨት ሕዝብን በማበጣበጡና በመከፋፈሉ እንዲሁም ለቡድናዊ ጠባብ ዓላማው ሲል የአገርና የሕዝብ ጥቅሞች አሳልፎ በመስጠቱ ነው። ህወሃትን መቃወም ማለት በህወሃት የግፍ አገዛዝ ለሚሰቃየው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ወገናዊነት ማሳየት ማለት ነው። በአለማዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወት ወንጀልንና ወንጀለኞችን መቃወም ወንጀል ወይንም ጥላቻ ሳይሆን የተቀደሰ ተግባር ነው። ይህም ደግሞ በሰብአዊነትም፣ በሞራላዊነትም ሆነ በመንፈሳዊነትም የተገባና የተቀደሰ ተግባር ነው።
ነገር ግን ለመሠረታዊ ለውጥ የሚደረገው ትግል ትልቅ ጥንቃቄን ይጠይቃል። የህወሃት አወዳደቅ ሕዝብና አገር ላይ እንዳይሆን በሕዝቡም ሆነ በተቃዎሚዎች መሀከል በመከባበር ላይ የተመሠረት ትብብር የሚፈለግ ብቻ ሳይሆን ያለው ብቸኛ አማራጭ ነው። ህወሃት ሕዝቡንና የተቃዋሚውን ጎራ ለመከፋፈል የማይፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም። ይህም አሁንም በተግባር እየታየ ነው። አገር ቤት ካሉት የተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ድርድር ሳይቀመጥ፣፤ በውጭ ካሉ ተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ድርድር ጀምሬያለው ማለት ህወሃት ፓለቲካን እንደ ማጭበርበሪያ መሣሪያ የሚጠቀማበት መሆኑን አንዱ ማሳያ ነው። ድርድር ከተቃዋሚዎች ጋር ለመጀመር ትክክለኛውና ቀላሉ መንገድ በቅርብ ከሚገኙት አገር ቤት ውስጥ ካሉት ጋር መጀመር ነው።
ነገር ግን የህወሃት አላማ እውነተኛ ድርድር ሳይሆን እንደለመደው ሕዝቡንና ተቃዋሚዎችን በመከፋፈል የፓለቲካ ቁማር ለመጫወት ነው። ስለዚህ ህወሃት የመከፋፈልና ሕዝባዊ ትግሉን የማዳከም ዓላማው እንዳይሳካለት በሕዝቡና በተቃዋሚዎች በኩል ትልቅ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። በቀላሉ ሊቀጣጠሉና ሊያተራምሱ የሚችሉ ብዙ አደጋዎች አሉ። ብዙ የሚጠብቁን አደገኛ ዳገቶችና ቁልቁለቶች አሉ። የዲሞክራሲ መንገድ አልጋ በአልጋ አይደለም ግን የሚያዋጣን መንገድ እሱ ነው። ለምንናፍቀውና ሊመጣ ለሚገባው የፖለቲካ ሽግግር ምዕራፍ በጠላትነት ሳይሆን በመከባበርና በመደማመጥ የተለያዩም ሆነ የተቃረኑ አስተሳሰቦችን ማራመድ እንዲቻል በተቃዋሚዎች በኩል መሠረት መጣል ከአሁኑ ያስፈልጋልም ይገባልም። ያለፈው ታሪኮቻችንን መድገም አይገባም። ካለፉት የፖለቲካ ውድቀቶቻችን ልንማር ይገባል። ካለፉት ስህተቶቻችን በመማር እነሱን ላለመድገም እጅግ ትልቅ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
ከባድ ፈተና ከፊት ለፊት ስለሚጠብቀን መንገዳችን በጣም አስቸጋሪ እንዳይሆንና እንደገና እንዳንወድቅ ትልቅ ሃላፊነት፣ ሆደ ሰፊነትና ብልሃት ያስፈልጋል። እንድንከፋፈልና እንድንበጣበጥ የሚፈልጉ ኃይሎች ሁልጊዜም እንደሚኖሩ መዘንጋት የለበትም። በተቃዋሚዎች መሀከል ቅራኔዎችና መለያየቶች ወደ ጠላትነት እንዳይቀየሩ በመከባበር መለያየትም ሆነ መተባበር እንዲኖር ሁሉም ሀላፊነቱን ቢወጣ መልካም ይሆናል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ እንኳን ተጣልተን ተዋደንም ቢሆን እጅግ አስቸጋሪ ነው። የተጀመረውም የትብብር መንፈስ እንዳይጐዳ ትልቅ አርቆ አስተዋይነት ያስፈልጋል። በመከባበር ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዞ ጠቃሚና ገንቢ ባህል መፍጠር ከአሁኑ ይገባል።
ብርሃኑ ጉተማ ባልቻ
ለአስተያየት፧ berhanugbalcha@gmail.com
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply