
የኢትዮጵያ መንግስት በውስጥ ጉዳዬ ላይ ገብተዋል፣ ከተፈቀደላቸው ዓላማና ተግባር ውጭ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል ያላቸውን 7 በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ግከለሰቦችን በ72 ሰአታት ውስጥ የኢትዮጵያን ግዛት ለቀው እንዲወጡ ሲል አዟል።
ይህንን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ “በኢትዮጵያ ውሳኔ ደንግጫለሁ” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ በአሸባሪው ህወሓት በርካታ ንጹሀን ሲገደሉ፣ ከ400 በላይ መኪናዎች በአሸባሪው ድርጅት ታግተው ሲቀሩ፤ አሸባሪው ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራሁ ነው ሲል ድምጻቸውን አጥፍተው አሁን ላይ መንግስት የአገር ሉአላዊነትን በተጋፉ የድርጅቶቱ ሰራተኞች ላይ እርምጃ ሲወስድ ደንግጫለሁ ማለታቸው ተገቢነት የጎደለው ነው ሲሉ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ተችተዋል።
አቶ አንዳርጋቸው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት አስተያየት፤ “አገር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚደነግጡት መቼ መቼ ነው?” ሲሉ ትዝብታቸውን ገልጸዋል።
አቶ አንዳርጋቸው፤ አሸባሪው ህወሓት በአንድ አገር ሉዓላዊ ሰራዊት ላይ የክልል መንግስት ጥቃት ፈጽሞ ንጹሀን ዩኒፎርም የለበሱ ወንድና ሴት ወታደሮች ሲጨፈጨፉ አንቶኒዮ ጉተሬዝ መደንገጣቸውን አልነገሩንም ብለዋል።
አሸባሪው ድርጅት ባደራጃቸው ገዳይ ቡድኖች ከ1000 በላይ ንጹሀን የአማራ ብሄር ተወላጆች በማይካድራ ሲጨፈጨፉ ዋና ጸሀፊው እንደደነገጡ አልነገሩንም ያሉት አቶ አንዳርጋቸው፤ በአፋር ጋሊኮማ የራሳቸው ድርጅት አባል የሆነው ዩኒሴፍ ሳይቀር ባጋለጠው ጭፍጨፋ ከ240 በላይ ንጹሀን ህጻናትና ሴቶች ጭምር በተጠለሉበት ሲጨፈጨፉ ጉተሬዝ ያሉት ነገር የለም።
አማራ ክልል ጭና ላይ በርካታ ንጹሀን በአሸባሪው ታጣቂዎች ሲጨፈጨፉ ዋና ጸሀፊው ድንጋጤ ብሎ ነገር አልተሰማቸውም፤ በቆቦ በአንድ ቀን ከ600 በላይ ንጹሀን መጨፍጨፋቸውን ሰምተው ዋና ጸሀፊው ድንግጥም ስለማለታቸው የተሰማ ነገር የለም ሲሉም ነው አቶ አንዳርጋቸው የዋና ጸሀፊውን አቋም የተቹት።
አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ፤ ከ30 ሚሎዮን በላይ ከሆነው ከአማራ ህዝብ ጋር ሂሳብ አወራርዳለሁ ብሎ በግልጽ ሲናገርና ወረራ ሲፈጽም አንቶኒዮ ጉተሬዝ መደንገጣቸውን አልነገሩንም፤ መንግስት ሀምሌ ወር ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች ከአሸባሪው ህወሓት ጋር አብረው እየሰሩ ነው፤ ከዚህ ድርጊታቸው ካልተገቱ እርምጃ እወስዳለሁ ብሎ ሲያስታውቅ በሰራተኞቻቸው ድርጊት ዋና ጸሀፊው አላፈሩም፤ አልደነገጡም ነው ያሉት አቶ አንዳርጋቸው።
የእርዳታ እህል ይዘው ወደ ትግራይ ክልል ከገቡ 400 መኪናዎች ውስጥ የተመለሱት 38 ብቻ ናቸው፤ ምግብ ለማድረስ መኪና ተቸገርኩ ብሎ ድርጅታቸው አቤቱታ ሲያቀርብ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ምንም አለማለታቸውን ያስታወሱት አቶ አንዳርጋቸው፤ መንግስት ከተደጋጋሚ ማሳሰቢያና መስጠንቀቂያ በኋላ ሰባት የእርሳቸው ድርጅት ግለሰቦችን ስላልተገባ ድርጊታቸው አገር ለቃችሁ ውጡ ሲል ግን አንቶኒዮ ጉተሬዝ ደንግጠዋል፤ መደንገጣቸውንም በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል፤ ይህ የእርሳቸውንም ሆነ የድርጅታቸውን ሚዛን የለሽነት ያሳብቃል ነው ያሉት።
“ለመሆኑ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የሚደነግጡት መቼ መቼ ነው?” ሲሉ የሚጠይቁት አቶ አንዳርጋቸው፤ ከዋና ጸሀፊው አቋም ተነስቶ ለዚህ ጥያቄ መልሱ “አሸባሪው ህወሓት የተጎዳ ሲመስላቸው አብዘተው ይደነግጣሉ፤ አብዝተውም ይጮሃሉ” የሚል ብቻ ነው ሲሉ ተችተዋል። (ኢፕድ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
አንቶኒዮ ጉተሬዝ ለነጭ መብት የቆመ በአሜሪካ የሚገፋ ምህታታዊ ሰው ነው። ራሺያ ህገ ወጥ በሆነ መልኩ ክሪሚያን አጥቅታ ስትይዝ ይህን ያህል ጫጫታና የተመድ ስብሰባ አልተደረገም። ሳውዲ በአሜሪካ እየተረዳች በየመን ላይ የቦንብ ዝናብ ስታዘንብ ምንም የተባለ ነገር የለም። አውሮፓውያንና አሜሪካ የራሳቸው ጥቅም እስካልተነካ ድረስ ለሌላው አይገዳቸውም። ለወያኔ ወገባቸውን ይዘው የሚታገሉት የአውሮፓ ሃገራት ከወያኔና ከተላላኪዎቻቸው የሚያገኙት የቀጥታም ሆነ የተዘዋዋሪ ጥቅም ቀርቶባቸው ነው። ከዚህ በጎላ መልኩ ደግሞ ነጩ ዓለም ጥቁሩ ዓለም በራሱ አስቦ እንዲኖር አይፈልጉም። ቆም ብሎ ላሰበ ነገሩ ሁሉ ወደ እብደት ተለውጧል። አምስቱ የወያኔ ወታደራዊ ጄኔራል ነን ባዪች ጦርነቱን ለመቀጠል፤ ከክልላቸው አልፈው ውጊያውን ለማጧጧፍ ሲደነፉ፤ እርዳታ ጭነው የተላኩ መኪናዎች በዚያው ተጠልፈው ሲቀሩ፤ እልፍ የአማራና የአፋር ሰዎች ሲፈናቀሉና ሲገደሉ ተመድ የሚለው የለም። አሁንም የሚያላዝነው ያንኑ ወያኔን ለማትረፍ ያቀደውን ብልሃት ተገን አርጎ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያን የሚወድትን ሁሉ መኮነን ነው። የተመድ ሰራተኞች ለወያኔ ሰልፈኛ ሆነው ቁሳቁስ ማቀበላቸው እውነት ሆኖ እያለ መረጃ ይቅረብልኝ የሚሉት አንቶኒዮ ጉተሬዝ መረጃው ቢቀርብላቸው ምንም እንደማያደርጉ ከአሁኑ የታወቀ ነገር ነው። አይናቸው ላይ ፈጦ የሚታየውን እውነት አንቀበልም ያሉት አውሮፓዊያንና አሜሪካኖች ልክ እንደ ሊቢያ የሃበሻዋ ምድር የዘረኛና የጎሰኛ መንጋ የሚንጋጋባት እንድትሆን ይሻሉ። ያኔ ነጩ ህዝብ ደራሽና መልአክ ጥቁሩ ህዝብ ደግሞ እርስ በርሱ የሚባላ እንደሆነ አድርገው በሚዲያቸው ያጠቁሩናል። በኢትዮጵያ የፓለቲካ ታሪክ ውስጥ ነጻ ምርጫ የሆነበት ጊዜ አንድም አልነበረም። አሁን ግን ፍጽም ነጻ ነው ባይባልም ሰው የፈለገውን ያለ ምንም ጫና መርጧል። ይህን እውነታ እንኳን አምኖ የማይቀበል የአሜሪካ የውጭ ፓሊሲ እንዴት ባለ ሂሳብ ነው ለኢትዮጵያ በጎ የሚያስበው?
አሁን እንሆ የሰሜኑ ችግር ካልተፈታ የአውሮፓ ህብረት የኢኮኖሚ ማዕቀብ በኢትዮጵያ ላይ እንደሚያደርጉ ዝተዋል። አትፍረድባቸው ታዘው ነው በአሜሪካ። ግን ይሰማኛል የኢትዮጵያውን ጉዳይ ከልባቸው የሚያወጣ ዓለምን የሚያናውጥ የፓለቲካ ንፋስ በቅርብ ይፈጠራል። ያኔ እኛ እንረሳለን። ላንባቢ ምን እያልክ ነው ለምትሉ እኔ ጠንቋይም/ነብይም አይደለሁም። ግን የጊዜውን ሁኔታና የዓለምን የጂኦፓለቲካል መፋተግ በማየት ብቻ የተወሰደ ግምት መሆኑን ተረድልኝ። ጠብቆ ማየት ነው። እስከዚያው በዚህም በዚያም እየተገፋንና ራሳችን ለማገዶ እያዘጋጀን በወያኔና በአጋሮቹ መሪነት መገዳደላችን ይቀጥላል። ወያኔ ማለት የሌቦች ሁሉ ቁንጮ ማለት ነው። በቅርብ በአማራና በአፋር ክልል ካደረጉት ብዙ ወንጅሎች የመርካቶ ሌባ አይነት የሆነውን እውነተኛ ታሪክ ላካፍላችሁ። ገበሬው በሬውን እንዲሸጥላቸው ሲጠይቁት ግምቱ 10 ሺ ብር ነው ይሏቸዋል። እረ እኛ 20 ሺህ እንሰጥሃለን በማለት የድሮውን ብር ማለትም ወያኔ ከስልጣን ከተባረረ በህዋላ የተለወጠውን ቆጥረው ይሰጧቸዋል። እነርሱ ብር መቀየሩን አላወቁም። ግን ሌባው ወያኔ ይህን ያህል ወርዶ አፈር ገፊውን ገበሬ የሚያታልል እጅግ ጨካኝና መራራ ገዳይና አፋኝ ነው። ከዚህ ሃይል ጋር ነው እንደራደር የሚባለው? ወያኔ በምንም መንገድ ለሰላም ዝግጅ አይደለም። ሁሌም ውጊያ እንደ ጀብድ የሚታይበት ወንድምና እህቱን ገድሎ የሚፎክር ገበሬው እንዳሉት የአውሬ ስብስብ ነው። የሰውነት ባህሪያቸው ተሟጧል። ጀሮ ያለው ይስማና አቋሙን ያስተካክል። መገዳደላችን ለጠላት እንጂ ለህዝባችን አንድም አይበጅም። በቃኝ!