ጎልጉል “የዖሮምያ ሰነድ አዲሱ ቃልኪዳን” በሚል ርእስ ባወጣው ፅሁፍ የመክለፍለፍ ፖለቲካ ጎጂ አዝማሚያ በግልፅ መጠቆሙን ሳነብ እኔም “እውነትም መክለፍለፍ” ልል አማረኝ፤ እውነትም መክለፍለፍ።
መቼም በኢትዮጵያ የለውጥ ታሪክ ውስጥ ልሂቃን ፖለቲከኞችና ህዝብ ሆድና ጀርባ ከሆኑ ከ40 አመት በላይ ሆኗል። ህዝብ ለሃቀኛ ለውጥ ደሙን ያፈሳል፤ ብልጡ ልሂቅ ስልጣን ይወርሳል። ህዝብ ለጋራ አላማ ይደማል፤ ልሂቅ ለግል ጥቅሙ ይሿሿማል። ህዝብ ለለውጥ ይደማል፤ ብልጣብልጥ ፖለቲከኛ ስልጣን ይቀማል። ህዝብ ላንድነት ይጮሃል፤ ህዝብ እወክላለሁ ባይ ፖለቲከኛ ለልዩነት ይሰራል። ህዝብ ደማችን አንድ ነው በሚል ሰልፉን ሲያደምቅ ለዝቅም የሚማስነው ፖለቲከኛ ለጠብ ይሮጣል።
በሰሞኑም የሚታየው ይህንኑ የሚመስል ነው። ሞት አይፈሬዎቹ የህዝብ ልጆች ከጨካኝ ባለክላሾች ጋር በባዶ እጃቸው በሚተጋተጉበትና ለፍትህ፣ ዲሞክራሲና አንድነት እየጣሉ በሚወድቁበት ባሁኑ ወቅት የዳያስፖራ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በየስፍራው ቻርተር በማርቀቅና የሽግግር መንግስት በማፅደቅ ስራ ተጠምደዋል ይባላል። ይህን የመሰለ ያገር ጉዳይ በቡድን እንዲወስኑ ከየትኛው ህዝብ እንዴት ያለ ውክልና እንደተቀበሉ የሚያውቁት እነርሱ ብቻ ናቸው። እኛ የምናውቀው ግን ህዝብ የሚለው ሌላ ፖለቲከኛ የሚለው ሌላ መሆኑን ነው።
አንድ ሁሉም ሊያውቀውና ሊጠነቀቅበት የሚገባ ትልቅ አደጋ አለ። ይሄውም በህዝብ ትግልና መስዋእትነት እየመጣ ያለው ለውጥና የህዝብ አንድነት በተለመደው የፖለቲከኞች የማይረካ የስልጣን ጥም ሩጫ እንዳይኮላሽና ዳግም ኢትዮጵያን ለሞት የሚዳርግ የትውልድ ስህተት እንዳይፈፀም ነው። አሁን የሚበጀው አጋጣሚውን በመጠቀም ለሚያልፍ ስልጣን የማያልፍ የታሪክ ስህተት ለመፈፀም መጣደፍ ሳይሆን ከታሪክ ተምረን የህዝብን እውነተኛ ፍላጎት መሰረት በማድረግ ለሀገሪቱ ህልውናና ለህዝቧም ዘላቂ አንድነት የሚበጅ የጋራ ስልት መቀየስ ነው። -9 ክልል ህዝብን እንዳላረካ ሁሉ 80 ቻርተር ለህዝብ ጥያቄ መልስ አይሆንም። ጉልጉል ጋዜጣ እንዳለው ለማይረባ የፖለቲካ አጀንዳ ከመክለፍለፍ ላገርና ህዝብ ዘላቂ ጥቅም በህብረት መጣደፍ ይበጃል።
እባካችሁ ለህዝብ ችግር ከቢሮ ተደስኩሮ ለህዝብ የሚወረወር መፍትሄ ሰልችቶናል። ንጉስ ሀይለስላሴ ስለምንወዳችሁ ህገመንግስት ሰጠናችሁ ብለው ከአርባ አመት በላይ ቀጥቅጠው ከገዙብ በኋላ ለጅብ ሰጥተውን ሄዱ። ደርግ ታሪክ አደራ ጣለብኝ አለና የህዝቡን አደራ በልቶ እሱም ህዝቡም በማያውቀው ባእድ ፍልስፍና ሲደናበር ከርሞ ለባሰበት የቀን ጅብ ሰጥቶን ተፈረካከሰ። ተረኛውም የህዝብ አደራ ቀማኛ ፥እናንተ ዝንበሉ እኔ አውቃለሁ መላ፥ አለና ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ በተሰኘ የእስታሊን ዘፈን 25 አመት ሲደንስብን ኖሮ አሁን ህልፈቱ እንደቀረበች በማወቅ አርፎ እንዳይሞት መቃብር አፋፍ ላይ ተዘቅዝቆ አስቸኳይ አዋጅ አጣዳፊ አዋጅ እያለ ያንቋርርብናል።
ይኼ ሁሉ የህዝብ መከራ በህዝብ ትግል ሊገፈፍ ተቃረበ በሚል ደስ ደስ ሊለን ሲጀምር ልማደኞቹ ፖለቲከኞች የህዝብ እውነተኛ ፍላጎት የሚነበብበትን ገፅ በመገልበጥ የራሳቸውን የስልጣን ጥም ማረጋገጫ ቻርተር ሊፅፉበት ወንበር ይጎትቱ ገቡ። ደግነቱ ጀግናው የዖሮሞ ህዝብ ባደባባይ ያሳየውን የአንድነትና ፍቅር ፍላጎት አሳምረው የሚያውቁ ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ገቢሳንና ዶ/ር ፀጋዬ ረጋሳን የመሳሰሉ ሃቀኛና በሳል የዖሮሞ ምሁራንን ስላፈራን በብስለት ሳይሆን በስሜት የሚነዱ አላዋቂ ፖለቲከኞች ከምንወደው ህዝባችን ሊለዩን አይችሉም። አረ ቀስ ጎበዝ! እየተስተዋለ እንጂ! የህዝብን ሀቀኛ የዲሞክራሲ ጩኸት ወደፖለቲካ ሸቀጥ ከመቀየር ደዌ ፈውስ የምናገኘው መቼ ነው?
ኢትዮጵያ ሆይ፣ የክፋት መልእክተኞች በሰይፍ የለዩት ህዝብሽ በሰልፍ ዳግም በፍቅር ሊተቃቀፍ እየገሰገሰ ነውና ደስ ይበልሽ! ትንሳኤሽን እናይ ዘንድ ጊዜው ቀርቧል።
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply