የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ስሙን ቀይሮ “ኢትዮቴሌኮም” በሚል ከተሰየመ በኋላ አስተዳደሩን ለፈረንሳዩ ፍራንስ ቴሌኮም ማስረከቡን ተከትሎ ኢህአዴግ ለወደፊቱ ያቀደውን እቅድ ይፋ የሚያደርጉ መረጃዎች ለንባብ በቅተዋል። በዛሬው እለት የመገናኛና የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል “ቴሌ ከዚህ በኋላ ለውጪ ካምፓኒ አይሰጥም። በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ይቀጥላል” ሲሉ የማሳረጊያ ንግግር አሰምተዋል። የሚኒስትሩን ንግግር ያደመጡ “ቴሌን ህወሃት ጠቀለለው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ “አዲሱ ቴሌና ኢንሳ” በሚል ርዕስ ከወራት በፊት ለንባብ ባበቃው ጥናታዊ ጽሁፍ እንዳስታወቀው ቀደም ሲል “አዲሱ ቴሌ” በሚል አሮጌው ቴሌን የሚረከቡ የህወሃት ሰዎች የበዙበት፣ ለማዛነቂያ ከተለያዩ ብሄሮች በጣም ጥቂት ተተኪዎችን በማካተት ስልጠና ሲያካሂድ ነበር።
በህወሃት ሰዎች የሚመራውን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ተቋም (NISS) ዘመናዊ ለማድረግ ኢንሳን ሲያቋቁም ዋናው ዓላማው ከቴሌ ጋር በማቆራኘት ነበር። በጥናቱ እንደተገለጸው አሮጌው ቴሌ ውስጥ ያሉት አገር ወዳዶች ለተፈለገው የስለላ ስራ የሚታመኑ ባለመሆናቸው ሰራተኞቹን በሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ስም ተጠራርገው እንዲወጡ ተደርጓል።
የፈረንሳይ ቴሌኮም ቴሌን እንዲረከብ ስለመደረጉ “ህወሃት አዲሱ ቴሌ በሚል እያሰለጠነ ያዘጋጃቸው የራሱ ሰዎች አሮጌውን ቴሌ ባደባባይ እንዲረከቡ ማድረግ የሚያስነሳውን ተቃውሞ በጥራትና በአገልግሎት ኋላቀርነት እንዲሁም በውጪ ካምፓኒ አሳብቦ ለመስጠት የማመቻቸት ስራ ለመስራት” መሆኑ አካሄዱ የገባቸው የቴሌ የበላይ ሃላፊዎች ውስጥ ውስጡን የሚያወሩት ጉዳይ ነበር።
ከፍተኛ በጀት መድቦ በአሜሪካን አገር ባለሙያዎች ስልጠና ሲሰጣቸው የነበሩት የአዲሱ ቴሌ ምልምሎች ዝግጅታቸው ከተጠናቀቀ በኋላ መረጃዎች በማፈትለካቸው፣ አዲሱ ቴሌ “ኢትዮቴሌኮም” በሚል ተቀይሮ ለፈረንሳይ ኩባንያ አስተዳደሩ በኮንትራት እንዲሰጥ ተደረገ። በወቅቱ ውሉ በየሁለት ዓመቱ እንደሚታደስ ይፋ ተደረገ። ከሰባት ሺህ በላይ የአሮጌው ቴሌ ሰራተኞች እጣ ፈንታ ፍርድ ቤት መመላለስ ሲሆን፣ አዳዲሶቹ የፈረንሳዩን ኩባንያ እየታከኩ ቴሌን እንዲወሩ መደረጉን ሰለባዎቹ ይፋ አደረጉ። መንግስት ውሳኔው አስተዳደሩን የያዘው አካል እንደሆነ በመጥቀስ “የተባረሩት ሰራተኞች ተደራጅተው መስራት ከፈለጉ አደራጃቸዋለሁ” አለ።
“መተካካቱ” ከተጠናቀቀ በኋላ ፍራንስ ቴሌኮም ስራ እንደጀመረ በስራው ጥራት የሌለው፣ ደካማ ምዘና እንዳለውና ካላስተካከለ ውለታው ሊሰረዝ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ይሰጠው ጀመር። በተለይም ከስድስት ወር በፊት የቦርድ ሰብሳቢው ዶ/ር ደብረጽዮን ኩባንያው ሊባረር እንደሚችል አስረግጠው ተናገሩ። አስቀድሞ ለተጠና ምክንያት እና ቴሌን ከኢንሳ ጋር በማጋባት በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ (ስልክ፣ ኢተርኔት፣ …) ከፍተኛ የስለላና የቁጥጥር መረብ ለመዘርጋት በታሰበ ዕቅድ ፍራንስ ቴሌኮም ሽፋን እንዲሆን መጠቀሚያ መደረጉ እየታወቀ ዶ/ር ደብረጽዮን ይህንን መሰሉን ነቀፋ መሰንዘራቸው የሙያውን ባለቤቶች በወቅቱ ያስደመመ ጉዳይ ነበር፡፡ ይህንኑ የድብብቆሽ ሥራ በተመለከተ የአኢጋን ጥናታዊ ዘገባ አዲሱ ቴሌ ለማዋቀር በሚል የፍራንስ ቴሌኮም እንዴት የሽፋን መጠቀሚያ እንደሆነ አስቀድሞ በዝርዝር አስረድቷል፡፡
አርብ ታህሳስ 26፤ 2005 ዓም ኢቲቪ በዜናው እንዳረጋገጠው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎትና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት፣ በእውቀት ሽግግር በኩል ውጤታማ መሰረት በመጣሉ በዛሬው ዕለት ኢትዮ ቴሌኮም በአገር ልጆች እንዲመራ በተወሰነው መሰረት ርክክብ መፈጸሙን ይፋ አድርጓል።
ዶ/ሩ በመጀመሪያ አድንቀው “በሞባይልም ሆነ፣ በኢንተርኔት ጥራት ተገልጋዩ የረካበት ሁኔታ የለም” በማለት ቅር መሰኘታቸውን አስታውቀዋል። አያይዘውም “የእኛ ልጆች ውጪ ሄደው ተምረዋል። እዚህ ሆነውም ስራውን አውቀዋል። ከዚህ በኋላ ኢትዮ ቴሌኮም ለውጪ ኩባንያ አይሰጥም” ብለዋል። በዘገባው እንደተገለጸው ከፈረንሳይ ከመጡት 24 ባለሙያዎች መካከል ዋና ስራ አስኪያጅና ምክትላቸው አዲሶቹን አመራሮች ለመርዳት እንዲቆዩ ሲደረግ፣ የተቀሩት ወደ አገራቸው ተሰናብተዋል። ጎልጉል ያነጋገራቸው የቀድሞ ቴሌ ሠራተኛ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ከመስጠት ይልቅ ዶ/ር ደብረጽዮን “የእኛ ልጆች” ያሏቸው እነማን እንደሆኑ ቢዘረዝሩ የተሻለ ነበር በማለት ንግግሩን አጣጥለውታል፡፡
ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለጎልጉል እንዳሉት “ቴሌን ፕራይቬታይዝ የማድረግ ጥያቄና ምላሹ በቅርቡ ይፋ ይሆናል። የመጀመሪያው ባለድርሻ ኤፈርት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ይህ ሲሆን የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን መጨረሻ ይሄው ነው” ብለዋል። ኤፈርት አሁን ከጀመረው የማዕድን ዘርፍ እንቅስቃሴ በተጨማሪ በቴሌኮም ስራ ለመሰማራት እቅድ እንዳለው በተለያዩ መገናኛዎች መዘገቡ አይዘነጋም።
ርክክቡ ይፋ ከመደረጉ ሁለት ቀን በፊት ሪፖርተር እንደዘገበው ፍራንስ ቴሌኮም በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የተጠቀሱትን በመንግሥት የታለሙ ግቦች ለመምታት የሚያስችል ብቃት ያለው መሆኑ በመረጋገጡ እንደተመረጠ በወቅቱ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ 30 ሚሊዮን ዩሮ ለኩባንያው መክፈል ደግሞ ከመንግሥት የሚጠበቅ ኃላፊነት ነበር፡፡
የሁለት ዓመታት የኮንትራት ጊዜው እ.ኤ.አ. ታኅሳስ 23 ቀን 2012 ያጠናቀቀው ፍራንስ ቴሌኮም በተጠቀሱት ዓመታት ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወኑ ቢነገርም፣ ከኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በእጅጉ የተለየ ሚና እንዳልነበረው ሲተች ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ በመንግሥት በኩል ኢትዮ ቴሌኮምን በውጭ ኩባንያ አማካይነት በማስተዳደር ስለተገኘው ውጤት በይፋ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ በኮንትራት ስምምነቱ ሰነድ መሠረት ፍራንስ ቴሌኮም በሚያስመዘግበው ውጤት የኮንትራት ጊዜው እንደሚራዘም ይገልጻል፡፡ በዚህም መሠረት ኩባንያው ጥያቄውን ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ቢያቀርብም ተቀባይነትን አላገኘም፡፡ ከዚህ ይልቅ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች አስተዳደሩን እንዲረከቡ በመንግሥት መወሰኑን ሰሞኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የተሾሙት ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል።
ከመቶ ዓመት በፊት አጼ ምኒልክ ለኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽን ጥበብን ቢያስተዋውቁም እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ በዘርፉ ተገቢውን ዕድገት ሳታካሂድ ቀርታለች፡፡ ዓለማችን በ21ኛ ክፍለዘመን ፈጣን የቴሌኮሙኒኬሽን ምጥቀት እያሳየ ባለበት ባሁኑ ወቅት በህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ከሁለት ዓስርተ ዓመታት በላይ የተገዛችው ኢትዮጵያ አገር ከሌላት ሶማሊያ ሳትሻል በመገኘቷ እጅግ በርካታ ወገኖች አገር ውስጥም ሆነ ውጪ በሚታተሙ የሚዲያ ውጤቶች ቁጭታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ከዚህም አንጻር ህወሃት/ኢህአዴግ በአገዛዝ በቆየባቸው 21ዓመታት ለበርካታ ጊዜያት ቴሌ ወደ ግል ይዞታ እንዲቀየር (አገዛዙ ውስጥም ባሉ ጭምር) ጥያቄ ቢቀርብም ኢህአዴግና አቶ መለስ የቴሌን ጉዳይ እስካሁን ይዘው የቆዩት የስለላ መረቡን እና ታማኝ ተዋናዮቹን በሙያው አሰልጥኖ እስኪያዘጋጅና በትርፍ በኩል ደግሞ ኤፈርት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ በቂ ጊዜ ሲያመቻች መቆየቱን በአኢጋን ዘገባ የተጠቀሰ ሲሆን ቴሌ በበኩሉ ደረጃውን በማሻሻል እድገት ማስመዝገቡን ይናገራል። ኢህአዴግ ቴሌን “የምትታለብ ላም” እያለ እንደሚጠራው ይታወሳል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
በለው ! says
ከመንገድ ሥም እስከ አካሄድ… ከክፍለ ሀገር እስከ ቀበሌ.. ከግለሶች ሥም እስከ ድርጅት ምን ያልተቀየረ ያልፈረሰ አለ? ሲፈርስ እና ሲቀየር የሚያመጣው ፋይዳ መበተን, ማጋጨት, ማተራመስ, የጥቂት ቡድኖችን ባለቤትነት ማንገስ የሥርዓቱ ጠቃሚና ታማኝ ጫጩቶችን ፈልፍሎ ማራባት ብቻ ነው። የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ስሙን ቀይሮ “ኢትዮቴሌኮም”ሲሆን በህወሃት ሰዎች የሚመራውን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ተቋም (NISS) ዘመናዊ ለማድረግ ሳይሆን ቃሉ እራሱ (እኩሌታ ድረሻ )ማለት እንደሆነ እንረዳ!?ይህ የተደረገው የባለቤትነት (የአስተዳደር)ለውጥ ኢትዮጵያ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በቂ ባለሙያዎችን አፍርታ ከፈረንሳይ ባለሙያዎች የተሻለ ሥራ የሚሠሩ የኢህአዴግ አባላት አሜሪካ ተገኙ የሚለው ቱማታ… ዶክተሩ ከወዲሁ “ዶከኩ”። እርግጠኛ ነኝ ከተባረሩት ነባር የቴሌ ሠራተኖች ውስጥ አደለም።ግን የዚች ሁለት ዓመት ኮንትራትና የኮንትራት ማቋረጥ ዓላማ ነገሩ ሌላ ነው አስተዳደርን(ባለቤትነትን) በመለወጥ(…) ነባር ሠራተኛን ለፓርቲው ካልተገዛ ማብረር፣ ከጡረታ፣ ከአገልግሎት ዘመን መቀነስ፣ ከሚስጥር ዕውቀት ማግለል፣ ከሙያ ተካፋይት ማራቅ፣ከሥራ ልምድና ዕድገት ማሸሽ፣ለሥርዓቱ ታማኝ የሆነን ቤተሰብ, ዘርና ነገድን መሠረት ያደረገ አንድ ወጥ (ህገ መንግስቱ) እንደሚጠቅሰው ‘በአንድ የፖለቲካ ጥላ ሥር የመሰባሰብ አሠራር…በሁሉም ታላላቅ ኩባንያ ድርጅቶችና ተቋማት ሁሉ ለገዢው ፓርቲ የሥልጣን ማስቀጠያ የንፁሀን ዜጎችን ማቃጠያ ማዋቀር።ለዚህም ‘በክላስተር’ አሠራር ሳይሆን “ክላስተር ቦምብ”ማጥመድ ይሆናል!።
ከሰባት ሺህ በላይ የአሮጌው ቴሌ ሰራተኞች እጣ ፈንታ ፍርድ ቤት መመላለስ ሲሆን፣ አዳዲሶቹ የፈረንሳዩን ኩባንያ እየታከኩ ቴሌን እንዲወሩ መደረጉን ሰለባዎቹ ይፋ አደረጉ። መንግስት ውሳኔው አስተዳደሩን የያዘው አካል እንደሆነ በመጥቀስ “የተባረሩት ሰራተኞች ተደራጅተው መስራት ከፈለጉ አደራጃቸዋለሁ” አለ። ሰባት ሺህ ሠራተኛ እያንዳንዱ ቢያንስ ከትዳር አጋርና ከአንድ ልጅ ጋር ሲሠላ…በአንድ የፈረንሳይ ኩባንያ በተሰጠው ውል በ፳፬ ባለሙያዎችን ወደ ሀገር በማስገባት ፳፩ ሺህ ኢትዮጵያዊ ዜጋን እንዲተካ ተደርጓል ማለት ነው!።አሁንም አበክሬ እደግመዋለሁ “የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሲል”…’ብሔር’ ማለት(አውራው ፓርቲ ጤፍ መብላት ስኳር መላስ ያስተማረህ ማለት ነው!።) ‘ብሔረሰቦች’ ማለት ጥንት ያልነበሩ ማንነታቸው ያልታውቀ ኢህአዴግ ፈልጎ ያገኛቸው ዘፈንና መጨፈር ተነፍገው የነበሩ አሁን የአጫፋሪነትንም(አዳማቂ)ሆነው የሚያገለግሉ ‘ሆድአደር’ የሚሏቸው ቀለም ቆጠሩን ያካትታል። ‘ሕዝቦች’ መጀመሪያ በውጭው ዓለም ማጭበርበርን መስረቅን መግደልን መዝረፍን በደንብ የተካኑ “ዲያስፖራ”(ፈላሽ) ሆነው ወደ ድሃውና የዋሁ ሕዘብ አስጨብጭበውና አስጨፍረው ሊግጡት የተመለሱ ሲሆኑ ሌሎች ተከትለው የሚመጡ አዛኝ ቅቤ አንጓች በንግድ፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ፣ በጤና፣ በትምህርትና በሕክምናው ዘርፍ ((ከጥቂት ልበ ብርሃን በቀር))አብዛኛዎቹ ነዋሪውን ዜጋ ከመተካት እስከማጥፋት በማጅራት መቺነት የተሰማሩ ወሮበሎች ይሆናሉ። እንግዲህ “ቤታቸውን ሳይዘጉ ሰው ሌባ ይላሉ” የሚለው በእኛ ደርሷል ወጣቱ ትውልድ “እንቢኝ በሀገሬ!”… “እንቢኝ በመብቴ!” ሊል ግድ ነው… እንቢኝ ባለ ነው መይሳው! እንቢኝ ባለ ነው ምን ይልክ! ሸዋ ንቃ በለው!! በቸር ይግጠመን ከሀገረ ካናዳ