ማስታወሻ ከቃኚው፤ ይህ የልዑል ራስ እምሩ ሃይለ ሥላሴ መፅሀፍ ቅኝት በቅድሚያ ጥቅምት 2004 ዓ/ም – ኖቬምበር 2011- በሌሎች ድረገፆች ላይ ለንባብ ቀርቧል። በዚህ ወቅት በጎልጉል ድረገፅ ጋዜጣ ላይ መቅረብ ያስፈለገበት ምክንያትም በቅርቡ ጎልጉል ‘የኢትዮጵያ አርበኞች ውለታና የባንዳዎች ዕዳ’ በሚል በግንቦት ወር ላይ አርበኞቻችንን ለመዘከር ባወጣው ፅሁፍ ራስ እምሩ ከ’ባንዳዎች’ የስም ዝርዝር ውስጥ መካተታቸው ባስነሳው ውዝግብ ነው። ይህ ፅሁፍ/ቅኝት እዛ ውዝግብ ውስጥ አይገባም። ሆኖም ክቡር ልዑል ራስ እምሩ ሀገራችን ከነበረቻቸው ታላላቅና ስመጥር ኢትዮጵያውያን አርበኞቻችን አንዱ መሆናቸውን ቃኚው የሚያምንና እጅግም ከበሬታ ያለው በመሆኑ በህይወት ዘመናቸው ፅፈው የተዉልንን ማስታወሻ መመርመሩ መቃኘቱ ተገቢ መሆኑን ስላመነበት እነሆ የተከበረው የጎልጉል ድረገፅ ጋዜጣ ፈቃዱ ከሆነ ያትመው ዘንድ ተልኳል። (መስፍን ማሞ ተሰማ)
ካየሁት ከማስታውሰው
ደራሲ፤ ልዑል ራስ እምሩ ሃይለ ሥላሴ
ቅኝት፤ መስፍን ማሞ ተሰማ
መነሻ
የልዑል ራስ እምሩ ሃይለ ሥላሴን “ካየሁት ከማስታውሰው” እያነበብኩ አስቀድሞ በተመሳሳይ ዘመን ታሪክ ዙሪያ ባጠነጠኑ ኦቶባዮግራፊዎች ላይ ያነበብኳቸውና አልፎ አልፎ ያልተብራሩልኝ አልያም የደበዘዙብኝ ግዙፍ የታሪክ ሁነቶችንና ደግሞም እማላውቃቸውን ክስተቶችን ራስ እምሩ እያፍታቱ፤ እያበራዩ፤ እየገላለጡ … ሲያወጉ ባገኛቸው ጊዜ፤ ነፍስያዬ ተመስጣ ጣቶቼም ገፅን በገፅ እያጣፉ ስፈተለክ፤ ስሜቴ ደግሞ አንዴም በአግራሞት፤ አንዴም በመቆዘም…ይናወጥብኝ ነበር። እንዴትና ለምን? ብሎ መጠየቅ መቼም አግባብ ነው። መልሱንም በሁለት ቃላት መቋጨት አይከብድም – መፅሀፉን ማንበብ – በሚል።
ግና የልዑል ራስ እምሩን “ካየሁት ከማስታውሰው”ን በደፈናው ‘አንብቡት’ ማለቱ ‘ወንጀል’ የመስራት ያህል ሆኖ ውስጤን ይሰማኛል። እናም ያነበብኩትን ላካፍላችሁ፤ ስሜቴን ላጋራችሁ፤ እንዲያም ሲል መፅሀፉን ያላነበባችሁ ዱካውን አፈላልጋችሁ ታገኙት ዘንዳ፤ ያነበባችሁትም ቅኝቴን ቃኝታችሁ የጎዶሎውን በመሙላት የተዛባውን በማቃናት እንማማርበት ዘንዳ – እነሆኝ ብያለሁ የልዑል ራስ እምሩ ሃይለሥላሴን “ካየሁት ከማስታውሰው” – መልካም ንባብ!
መግቢያ
“ለመላው አለም ሰው፤ የትምህርትና የእውቀት ነገር መጀመሪያው ፅሁፍ መፃፍና የተፃፈውን ማንበብ ነው። ይኸውም ወደ እውቀት ሁሉ የሚመራ የመጀመሪያው ደረጃ መሳሪያ ነው።” ልዑል ራስ እምሩ “ካየሁትና ከማስታውሰው” በሚለው መፅሀፋቸው መግቢያ በክሽን አገላለፅ ካቀለሙት የነጠረ እውነት።
‘ካየሁት ከማስታውሰው’ የተፃፈው ራስ እምሩ ሃይለሥካሴ ለሰባት አመታት በቁም እስር በቆዩበት በፓንዛ ደሴት ጣሊያን ውስጥ ነበር። ዘመኑም 1929 ዓ/ም። ፋሽስት ጣሊያን በ1928 ዓ/ም ኢትዮጵያን ወርራ፤ የሀገሪቱም አውራ ቀዳማዊ ሃይለሥላሴ ተሰደው፤ አርበኞች በዱር በገደል ከጣሊያን ወራሪ ጋር በሚዋደቁበት ወቅት በፍልሚያው ረድፍ የመጀመሪያው መስመር ላይ ከቆሙት የሀገራችን አርበኛ መሪዎች አንዱ ራስ እምሩ በጠላት እጅ ከወደቁ በዃላ ነበር ወደ ጣሊያን የተጋዙት።
‘ካየሁት ከማስታውሰው’ በዘጠኝ ሰፋፊ ምእራፋትና በበርካታ ንኡሳን ርእሶች ተዋቅሮና የፎቶግራፍ ማስረጃዎችንና የደብዳቤ ልውውጦችን አባሪ አድርጎ በ345 ገፆች የተካተተ መፅሀፍ ነው። ይህ አኻዝ የልጅ ልጃቸው የፃፉት የምስክርነት ቃልና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ መምህር የሆኑት ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ያሰፈሩት 35 ገፆች ሳይደመሩበት ይሆናል።
የመፅሀፉ ቀዳማይ ህትመት 2002 ዓ/ም አሳታሚው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ይሆንና በ2003 ዓ/ም ቀዳማዩ ህትመት ተሻሽሎ 2ኛው እትም በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ፕረስ ታትሟል።
‘ካየሁት ከማስታውሰው’ የራስ እምሩ ሃይለሥላሴ ግለ ታሪክ /ኦቶባዮግራፊ/ ሲሆን አፃፃፉ የራስ እምሩ ብቻ የሆነ ወርጅናሌነት /ኦሪጅናሊቲ/ ያለውና መነሻና መድረሻው “እኔ’ን በማግዘፍ ላይ ያልታለመ፤ ደግሞም የታሪክን ክንውንና ባለታሪከኞቹን አሉታዊና አዎንታዊ ምግባርንና ባህሪን በሚዛናዊነት የዘገበ፤ ስፋትና ጥልቀት ያለው የታሪክ ቅርስ ታሪካዊ መፅሀፍ ነው።
በዚህ መፅሀፍ ውስጥ አንባቢ ከበርካታ ጥንታውያን ጋር አካላዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ትውውቅና ቁርኝትም ይኖረዋል፤ እድሜ ለራስ እምሩ የአፃፃፍና የአቀራረብ ለዛና ስልት ይሁንና።
ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል፤ አጤ ምኒልክ፤ እቴጌ ጣይቱ፤ ንግሥት ዘውዲቱ፤ ልጅ ኢያሱ፤ ተፈሪ መኮንን፤ ነጋድራስ ኢድልቢ፤ ንጉሥ ሚካኤል፤ ፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ተክለማርያም፤ ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ፤ ቱሉና የቦርከና ድልድይ፤ አሳዛኝ የህይወት ፍፃሜ ስለገጠማቸው የአድዋው አርበኛ ራስ አባተ…’ካየሁትና ከማስታውሰው’ ከሚያስተዋውቀን አያሌ ጥንታውያን መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
የዘመኑን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ወገንተኝነት፤ ለስልጣን መጠላለፍንና አስተዳደራዊ ዘይቤን፤ የአርሶ አደሩን አኗኗርና ባህል፤ የተፈጥሮ ሀብትንና ታሪካዊ ስፍራዎችን፤ በድምሩ የሀገራችንን የዘመኑን ታሪክ ፖለቲካና ማህበራዊ ፈርጆች እየተረተሩ ያሳዩናል – ራስ እምሩ በኦቶባዮግራፊያቸው።
የአውሮፓን ሥልጣኔና እድገት ከህብረተሰቡ ህይወትና ኑሮ አንፃር መዝነው የሰጡት አስደማሚ አስተያትና ትዝብት፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ህገ መንግስት ላይ ስለተካሄደው ውይይት፤ ስለ ጎጃም አመፅ፡ ስለ ኢትዮጵያና ጣሊያን ጦርነትና በጦርነቱም ስለወቅቱ ጦራችን የሚያትቱት ደረቅ ሃቅ፤ ስለሆለታ የጦር አካዳሚ ወጣት ጀግኖች መስዋዕትነትና እሳቸውና እነ ኮሎኔል ሃይለአብ ስለዋሉባቸው የውጊያ አውድማዎች…ራስ እምሩ ሃይለሥላሴ በጥልቀት አውግተዋል።
አንባቢ ሆይ! ‘ካየሁት ከማስታውሰው’ ባህረ ታሪክ ነው። የራስ እምሩ አፃፃፍና የታሪክ አወቃቀር ደግሞ ትረካው ሳይጎረብጠን፤ ሳያዛጋን፤ ሳያንጎላጅጀን እንደዋዛ እያዋዛን ይነጉዳል ይዞን በታሪክ ታንኳ እያስቀዘፈን፤ በዘመን ጅረት እያንሳፈፈን። የሚከተለውን ያስተውሏል፤
“ንባብ በማወቅ የጥንቱን የተፃፈ ታሪክ ሁሉ ማንበብ ይቻላል። ታሪኩንም በማንበብ የጥንቱን ዘመን ስራውን፤ የሰዉንም ኑሮ የነገሩንም አኳዃን ሁሉ እንደምን እንደነበረ፤ የሩቁን፤ ብዙ ዘመን የሆነውን፤ የቅርብ ጊዜ አስመስሎ ያሳያል። እንደዚሁም በየጊዜው የተፃፈው ታሪክ ሁሉ የሰው አእምሮ የእውቀት ደረጃ በምን አኳዃን ከፍ ከፍ እያለ እንደተጓዘ ያስረዳል። ይኸውም ታላቅ ትምህርት ሰጪ ነው።…
“አንባቢ ሆይ፤ እኔ ከህፃንነቴ ጀምሮ እድገቴና አብሬም የኖርሁት ካፄ ሃይለሥላሴ ጋር ስለሆነ የፃፍኩትን የህይወቴን ታሪክ ስታነቡ ካፄ ምኒልክ ወደ መጨረሻው ያለውን፤ ደግሞም የልጅ ኢያሱን ቀጥሎም የንግሥት ዘውዲቱንና ያፄ ሃይለሥላሴ ዘመን እንደምን እንደነበረ ማናቸውንም ነገር ታገኙታላችሁ” ይሉናል ራስ እምሩ በመፅሀፋቸው መግቢያ ሲያነጥቡ። እነሆ መግቢያችንን በዚሁ የራስ እምሩ መግቢያ ዘግተን እንዝለቅ ወደ ቅኝታችን።
ውልደትና ዕድገት
“እኔ እምሩ ሃይለሥላሴ በ1885 ዓ/ም ህዳር 15 ቀን ጉርሱም ወይም ፉኛ ቢራ እሚባለው አገር ተወለድሁ። ይኸውም አገር ከሀረር ከተማ ወደ ምስራቅ 7 ሰዓት የእግር መንገድ የሚያስኬድ ነው።”
እነሆ ራስ እምሩ ግለ ታሪካቸውን የጀመሩት በእንዲህ ያለ አንባቢን ገፅ ለገፅ የሚያወያዩ/የሚያነጋግሩ በሚመስል መስህባዊ አቀራረብ ነው። ከውልደት እስተ እድገት ያለውን ታሪክ አንጓ አንጋውን እየመዘዙ አንቆርቁረውታል። በዚህ ንኡስ ርእስ ስር ላጠቃላይ ስእል ምልከታ ሰጪ የሆኑትን ብቻ እንመዛለን።
ራስ እምሩ ከሶስተኛው እድሜያቸው ጀምሮ እድገታቸው በራስ መኮንን የሀረርጌው አስተዳዳሪ እጅ ነበር፤ ከተፈሪ መኮንን ጋር። ኑሯቸውም በሞግዚት። ተፈሪና እምሩ የሀገራቸውን ትምህርት የጀመሩት በአምስተኛ ዓመታቸው ሲሆን የሁለቱ የእድሜ ልዩነትም አራት ወር ከአራት ቀን ብቻ ነበር። ተፈሪ ነበሩ ቀዳሚው። እንጥቀስ እምሩን፤
“ወደ ስምንት ዓመት ሲሆነን ራስ መኮንን በሐረር ከተማ አጠገብ ወደ ደቡብ ወገን፤ ማዶውን አለው ቦታ ፤ ጥምቀተ ባህር ወደሚባለው እንድንቀመጥ ከኮምቦልሻ ጨርሰው አስወሰዱን።…
“ያን ጊዜም የፈረንሳይ ቋንቋ መማር ጀመርነ። የሚያስተምሩንም ራስ መኮንን ከፈረንሳይ አስመጥተውት የነበረው ሀኪም ዶክትር ቪታሊያ የሚባልና አባ ሳሙኤል የሚባል ኢትዮጵያዊ…ነበሩ።…ያገራችንን የሚያስተምሩን መምህር ገብረሥላሴ ይባላሉ።…ኑሯችንም ከኮምቦልሻው ኑሮ በምግብም ሆነ በልብሳችን ፅዳት ነበረው። የጨዋታም የመማሪያም ጊዜያችን የተለየ ነበር።…” በማለት ያወጉናል ስለዛን በልጅነት ዘመን ስለነበረው የትምህርትና ሥነ ሥርዐት አጠባበቅ ደንብ።
በእኒህ ወጣቶች የትምህርትና የሥነምግባር ኩትኮታ አሻግረን የምንመለከተው ግን ራስ መኮንንን ይሆናል፤ ቀንዲል ራእያቸውን። ራስ መኮንን ያስመጡት የህክምና ዶክተር ሐረር ውስጥ በስማቸው በተገነባው የበሽተኞች መታከሚያ ሆስፒታል ብዙ በሽተኞችን ያክም እንደነበርም ራስ እምሩ በመፅሀፋቸው አስፍረዋል። ለመሆኑ ጥምቀተ ባህር ስለተባለው መኖሪያቸው ምን አውግተዋል?
“…የጥምቀተ ባህር ግቢ ሠፊ፤ ዙሪያውንም በግንብ አጥር የታጠረ፤ ብዙ ቤቶችም ያሉበት፤ በልዩም አንድ ትልቅ ባለ ብዙ ክፍል ሶስት ፎቅ ያለው በኖራ አምሮ የተሰራ የግንብ ቤት ይገኛል። እዚያው እግቢው ውስጥና ከግቢውም ውጪ ዙሪያውን ብዙ አትክልትና ቡና፤ ሎሚ፤ የባህር ሎሚ፤ ኮክ፤ ሌላም አይነት ፍሬ ሁሉ በአንድ በተቀጠረ ፈረንጅ የሚሰራ፤ ውሃም በቦይ ከላይ ወገን ከምንጩ መጥቶ የሚጠጣው ላትክልቱ ሁሉ ስላለ ሁልጊዜም በግቢውና በዙሪያውም የሚታየው ለምለም ብቻ ነው።…” ይላሉ።
በዚያን ዘመኒቱ ኢትዮጵያ ወቅትን ጠብቆ ከሚከወን እርሻ ባሻገር እንዲህ ያለ ዘመናዊ የአትክልትና የፍራፍሬ እርሻ መኖሩን ስናነብ እኛ የዛሬዎቹ መደመም ይነሰን? ከገረመን አይቀር ፈረንጅ በሚመለክበት በዚያን ዘመን አትክልተኛ ፈረንጅ መቀጠሩን ራስ እምሩ ሲያወጉን – አጀብ እንጂ ለራስ መኮንን – ሌላማ ምን ልንል? ታዲያ ዛሬ በዚህ ዘመንና በዚህ ትውልድ ፈረንጅ አምላኩ የሆንን – ዝም እንጂ ውስጣችንን ታዝበን፤ ራሳችንን መዝነን – ሌላማ ምን አንደበት ኖሮን? እንቀጥል ቅኝታችንን ከራስ መኮንን ሞት በዃላ በእምሩ ህይወት አዲስ አበባ ውስጥ የሆነውን።
“በዚያም ሰሞን አፄ ምኒልክ ከግብፅ 3 የውጪ ቋንቋ አስተማሪዎች አስመጥተው…እነ ልጅ ኢያሱንና ደጃች ተፈሪን፤ እኛንም የመኳንንቱን ልጆች ሁሉ እዚሁ /አዲስ አበባ/ እተማሪ ቤት አስገቡን።
“አስተማሪዎቻችንም አለቃው ሙሴ ሐና፤ ሌሎችም ነሲብ አፈንዲና እስክንድር አፈንዲ፤ አነጋጋሪያቸውም /አስተርጓሚያቸውም/ አቶ ካሳ ይባላሉ። የሚያስተምሩንም ፈረንሳይኛ፤ እንግሊዝኛ፤ አረብኛ ነበር። ተማሪውም ሁሉ ከጧቱ በሁለት ሰዓት ገብተን ስንማር ውለን ምሳም እዛው እየበላን ማታ 11 ሰዓት ሲሆን እንወጣ ነበር” በማለት ስለዛን ዘመኒቱ ኢትዮጵያ የትምህርት አሰጣጥ ራስ እምሩ ካወጉን በዃላ በዚያን ዘመን በዚያ ት/ቤት ውስጥ ይማሩ የነበሩት ቁጥራቸው ወደ ሁለት መቶ ሃያው ይሆኑ እንደነበርም ይገልጣሉ። ትዝታም አላቸው፤ ያውም አስደማሚ። እንደሚከተለው ተነቅሷል።
“በዚሁ ተማሪ ቤት ሳለን እነ ልጅ ኢያሱና እነ ልጅ ብሩ ቅብጠት ያበዙ ነበር። አንድ ጊዜም የተሰጣቸውን የሚፃፍ ትምህርት እኔን ስራልን ብለው ስላስጨነቁኝ ‘ይታወቃል፤ እኔ አስቀድሜ ለምጃለሁ፤ እናንተ ገና ናችሁ፤ ስሩም ያሏችሁ እንደሆን አትችሉም፤ እንደታዘዛችሁት ብትፅፉና ብታቀርቡ ነው የሚሻለው’ ብላቸው እየለመኑ ስላስቸገሩኝ፤ የልጅ ኢያሱን፤ የልጅ ብሩን እና የልጅ ጌታቸውን የሶስቱንም ተቀብዬ ደህና አድርጌ ፅፌ ሰጠዃቸው። በማግስቱም ጧት እተማሪ ቤት እንደገባን አስተማሪው ሙሴ ሐና የሁሉንም ሲቀበል የነሱንም ተቀብሎ ካየ በዃላ ፤ ልጅ ኢያሱን ጠርቶ ያንኑ የሳቸውን ደብተር አሳይቶ ‘ማነው ይህንን የፃፈ?’ ብሎ ቢጠይቃቸው ‘እኔ ነኝ’ አሉት። ወረቀትና ቀለም አቅርቦ ‘እንካ አሁን ፃፍ’ ቢላቸው ‘እቤት በሰያፉ የተቀረፀ ብዕር አለኝ፤ በዚያ ነው የፃፍኩት አሁን በሌላ ብዕር መፃፍ አልችልም’ አሉት።…እኔን ካለሁበት ክፍሌ በመጠርጠር ጠርቶ እነሱው ፊት እነሱ የፃፍነው ነው ብለው የሰጡትን አሳይቶኝ ‘ይህን ማነው የፃፈው?’ ብሎ ጠየቀኝ። መልሱንም ‘እኔ ነኝ’ አልኩት።…ያን ጊዜም ልጅ ኢያሱ እንኳን እጅግም ባይደነግጡ፤ ሌሎቹ አፍረው ነበር።…” በማለት ያወጉናል እምሩ የሆነውን ሁሉ ዘርዝረው።
ከዚህ የራስ እምሩ ገለፃ ልጅ ኢያሱን አስመልክቶ ሶስት አንጓ ነቁጦችን እናወጣለን። የልጅ ኢያሱ ቅብጠት፤ የልጅ ኢያሱ ሃላፊነትን በራስ አለመወጣት፤ ልጅ ኢያሱ በስህተታቸው /በዋሾነታቸው/ አለማፈር። በለጋው እድሜያቸው አፍጥጠው የወጡት እኒህ ባህሪያት ወደፊት በልጅ ኢያሱ ህይወት ላይ ምን አንደምታ ይኖራቸው ይሆን? ‘ካየሁት ከማስታውሰው’ ስለ ልጅ ኢያሱ በጥልቀት ያወጋናል። ዘግየት ብለን እየጨለፍን እንቀምሳለን። እነሆ በዚህ ወፋዊ እይታ እምሩ ሃይለሥላሴ እድገታቸው ከእነ ኢያሱና ከተፈሪ መኮንን ጋር ብቻ ሳይሆን ከዘመኑ የሀገራችን አንጋፋ መሪዎች ዙሪያ እንደነበርም እንገነዘባለን። በዚህም ስለ እድገታቸው የጀመርነውን ቅኝት ሸብበን እንዝለቅ አሁን እምሩ ስለራስ መኮንን ወዳወጉን፤
ቃኘው መኮንን
“ራስ መኮንን ፊታቸው ጥቂት ረዘም ያለ፤ አይናቸው መጠነኛ፤ አፍንጫቸው ቀጥ ያለና የሚያምር፤ ጠጉራቸው በራነት የሌለው፤ ጥርሰ መልካም፤ አንዱ የፊት የላይ ጥርሳቸው ብልዝ፤ ፅህማቸው ልከኛ፤ ጠይም፤ ቁመታቸው ድልድል /ልከኛ/ ቀጠን ያሉና አቋቋማቸው ቀጥያሉ ናቸው።…” እነሆ ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል ከነሙሉ ግርማ ሞገሳቸው ግዘፍ ነስተው፤ ነፍስ ዘርተው በእዝነ ልቡናችን ይመጣሉ፤ በዚህ የራስ እምሩ ገለጣ።
የባለታሪክን /ገፀ ባህሪን/ መልክና ፀባዩን በቃላት ቀመር በመሳል አንባቢ ባለታሪኩን በእዝነ ልቡናው ቀርፆ እንዲያየውና እንዲዳስሰው የማድረግ ሥነ ፅሁፋዊ ክህሎት በተለይ የልብ ወለድ ደራሲያን አይነተኛ መመዘኛ ሆኖ ይገኛል። የሀገራችንን ቀደምት ታሪክ በዘገቡ ፀሀፍትም ሆነ ግለ ታሪካቸውን ባወጉን ጥንታውያን መፃህፍት ውስጥ እንዲህ ያለው ያቀራረብ ስልት ተስተውሎ አያውቅም – ቢያንስ የዚህ ቅኝት አቅራቢ ከየህ ቀደም አላጋጠመውም። የልዑል ራስ እምሩ ሃይለሥላሴ ‘ካየሁት ከማስታውሰው’ ግና የባለታሪከኞችን መልክና አቋም በቃላት ቀመር እንደ ፎቶ ቀርፆ፤ ፀባያቸውንም እንደ ጥጥ ነድፎ ትርክቱን ሲያንቆረቁረው እናገኛለን፤ አስቀድሞ እንዳየነው የራስ መኮንን አካላዊ ገለጣ… ‘ካየሁት ከማስታውሰው’ የራሱ የሆነ ወርጅናሌነት /ኦሪጅናሊቲ/ ያለው የታሪክ መፅሀፍ ነው ማለታችንም አንዱ ምክንያት እንዲህ ያለው ስልት ነው። ሌላው የዐረፍተ ነገር አወቃቀራቸው ይሆናል፤ እዚያ ውስጥ ግን አንገባም። የተነሳንበትን እንቀጥል። ለመሆኑ የቃኘው መኮንን ፀባይስ እንዴት ይሆን? ያወጉናል ራስ እምሩ፤ እንዲህ እያሉ፤
“…ዓመላቸው ደግ፤ ለሰው አዛኝ መንፈሳዊ እግዚአብሄርን ፈሪ፤ ሰው አክባሪ፤ በክፉ ሰዎችም ላይ ቁጡ ቀጭ፤ ተፀፃችም ነበሩ። በዚሁም ባመላቸው የሐረር የየወረዳው ባላገር ሁሉ እንደ አባት ነበር የሚያያቸው። ከበላተኛውም መልከኛ እንዳይጎዳው በብዙ ነገር አጥብቀው ይከላከሉለት፤ ከተሰጠውና ከተፈቀደለት አበል በላይ ባላገሩን ነክቶ አጉላልቶ የተገኘውን መልከኛ ቀጥተው ካገሩም ይነቅሉት ነበር።” ይላሉ እምሩ።
ይህ የራስ እምሩ ገለጣ ራስ መኮንንን በቅርብ የምናውቃቸው አይነት ሆኖ እንዲሰማን ያደርገናል። ራስ መኮንን ለባላገሩ ተቆርቋሪ፤ ግፈኛን ቀጪ፤ ሩህሩህና ደግሞም ጠንካራ መሪ መሆናቸውን መረዳታችንም የቀድሞ ጥንታውያን የኢትዮጵያ መሪዎችን በአግባቡ እንድንረዳቸው አይናችንን ይከፍትልናል፤…እንቀጥል ትረካችንን።
“ራስ መኮንን ብዙ ጊዜ ሐረር ግዛታቸው አይቀመጡም ነበር። ላፄ ምኒልክ ታማኝ ወንድማቸውና አሽከራቸው ስለነበሩ በየታላላቁ ዘመቻና ወደ አውሮፓም እየተላኩ ስለሚሄዱ፤ እሳቸውን በምናገኝበት ጊዜ ሁሉ እንደ ብርቅ ነበር የምናያቸው።” ይላሉ ራስ እምሩ ስለ አሳዳጊያቸው ራስ መኮንን። በዚያን ዘመን የመንግሥት ባለሟል ‘ሎሌ’ ወይም ‘አሽከር’ ይባል ነበርና ነው ራስ እምሩ ስለ ራስ መኮንን ሲገልጡ ‘ያፄ ምኒልክ ወንድምና አሽከር’ ማለታቸው።
ራስ መኮንን በዛን ዘመን እንደኖሩት ሌሎች መሪዎች ሁሉ ነፍስያቸው እረፍትንና መዝናናትን ሳታውቅ፤ ለሀገር ስለሀገር እንደባተሉ ኖረው ያለፉ ናቸው፤ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንኳን ጊዜያቸውን በበቂ ማሳለፍ ሳይችሉ። ለዚህም ነበር “…እሳቸውን በምናገኝበት ጊዜ ሁሉ እንደ ብርቅ ነበር የምናያቸው” ሲሉ እምሩ ስለአሳዳጊያቸው ቤተሰቦቻቸው የነበራቸውን የናፍቆት ሰቀቀን መግለጣቸው።
በ1884 ዓ/ም የእንግሊዝ ንጉሥ ኤድዋርድ 7ኛ ሲነግሥ አፄ ምኒልክ ራስ መኮንንን ወደ አውሮፓ በልዑክነት ሰደዋቸው እንደነበር ራስ እምሩ ያወጉንና አያይዘውም ሲፅፉ፤
“የእንግሊዝ ንጉሥ ከነገሠ በዃላ ሌላውንም የአውሮፓን ሀገር ጎብኝተው ተመለሱ።…ወደ ሐረር እንደደረሱም…ምንም ያህል ቀን ሳይቆዩ ወዳዲስ አበባ ወጡ። በዚያን ጊዜም በአማርኛ የታተመ መፅሀፍ ቅዱስ ብዙ ይዘውልን መጥተው ነበር። መፅሀፍ ቅዱስም መጀመሪያ በአማርኛ የታተመ መምጣት የጀመረው ያኔ ነው።” ይሉናል።
የአንባቢን ቀልብ ከሚገዛው ከዚህ ትረካ መኻል የመፅሀፍ ቅዱስ ጉዳይ አይነተኛው ይሆናል። ለመሆኑ መፅሀፍ ቅዱስ ወደ አማርኛ የተተረጎመው በማን ነበር? የትስ ታተመ? የአተረጓጎሙ ታሪክስ እንዴት ነው? የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለዘመናት ክርስትናን ስታስተምር የኖረቸው በምንና እንዴት ነበር?…እኒህ ጥያቄዎች ከአእምሯችን ተግ ብለው የሚወጡት ድንገት ነው – ካየሁት ከማስታውሰውን ስናነብ። ራስ እምሩ እኒህ ጥያቄዎችን የማንሳትም ሆነ ምላሽ የመስጠት ጣጣ ውስጥ አልገቡም፤ የሆነውን እንደነበረ አቀረቡልን እንጂ። ይህ ቅኝትም ለጥያቄዎቹ መልስ ዝርዝር ውስጥ የመግባት አቅም የለውም። ሆኖም ቅኝቱን የሚያነቡ ታዳሚያን በተነሱት ነቁጦች ዙሪያ የሚያካፍሉን ዕውቀት ቢኖር ለግንዛቤያችን ይበልጥ እንደሚረዳን ለመጠቆም እንወዳለን። ይህን በዚሁ እናብቃና ለመሆኑ ስለ ራስ መኮንን ሞትና ስላስከተለውም ሀዘን ራስ እምሩ ምን አውግተውናል? ልብን ከሚነካው ሰፊ ትረካቸው እንደሚከተለው ቀንጭበናል፤
“…/ራስ መኮንን/ ከሞሞታቸው ስምንት ቀን በፊት በጣም ብዙ የሆነ ቁራና ጭልፊት ከኩለ ቀን ጀምሮ እስኪጨልም እርስ በርሱ ሲጣፋ፤ ሲጯጯህ፤ ሠማዩን ከድኖት በብረቱ ትንቅንቅ አምሽቶ ሰው ሁሉ ሲያየው እዛው እከተማው ዛፍ ላይ ሰፍሮ አደረ።”
የዚህ ትርጉም ምንድን ነው? ራስ እምሩስ እንዲህ ያለውን ክስተት በዚያን ዘመን ልብ ማለታቸው ብቻ ሳይሆን ከራስ መኮንን የሞት ትንቅንቅ ጋር አጣምረው እንደምን ሊፅፉት ቻሉ? በአጭር አገላለፅ ትልቅ ትዕይንት ነው ያወጉን ራስ እምሩ። ቁራና ጭልፊት ሠማይን እንደ ደመና ጋርዶ ሲጠፋጠፍ። የዚህ ፍልሚያ መንስኤስ ምን ይሆን? በበኩሌ ቁራና ጭልፊት ደመኞች መሆናቸውን አላውቅም ነበር። እናንተም፤ ቢያንስ አብላጫዎቻችሁ፤ እንዲህ ያለ ታሪክ ሰምታችሁ የምታውቁ አይመስለኝም። አዎ! ራስ እምሩ በወጋቸው መኻል ይህንን የመሳሰሉ ከዋናው ታሪክ ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ የሌላቸው የሚመስሉ ግና እጅግ የጎሉ ሀገራዊም ሆነ ዓለም ዓቀፋዊ ክስተቶችን በየመኻሉ በስፋት ያወጉናል፤ እንደዋዛ እያዋዙ። እንቀጥል መነሻችንን፤
“…የራስ መኮንን ሞት አስር ቀን እንደሆነው ደጃዝማች ተፈሪና ዋና ዋናዎቹ የሐረር ሹማምንት ሁሉ በቶሎ ይምጡ…የሚል ከአዲስ አበባ ያፄ ምኒልክ ትዕዛዝ አለፈ።…
“ሾላ እሚባለው መሳፈሪያ በደረስነ ማግስት እፍልውሃ ሜዳ ታላላቅ አጅባር ድንኳን ጣራው ብቻ ተቀጣጥሎ ተተክሎ፤ ተነጥፎ፤ አፄ ምኒልክ ከታላላቆች መኳንንቶቻቸው ጋር ተቀምጠው …የራስ መኮንን መሳሪያ ሁሉ በአሽከሮቻቻው እጅ ተይዞ ፤ ፈረሶቻቸው፤ በቆሎዎቻቸው በአማረ ዕቃ እንደተጫኑ፤…አፄ ምኒልክ ወዳሉበት ድንኳን እንደተጠጋነ የራስ መኮንን የፎቶግራፍ ስዕል ተገልጦ የተያዘ ከኛው ጋር ነበርና፤ ጃንሆይ አፄ ምኒልክ ተነስተው እያለቀሱ ስዕሉን ተቀብለው ሳሙት። ደጃች ተፈሪንም አጠገባቸው አድርገው እጅግ ብርቱ ልቅሶ ተለቀሰ። እዚያው ፍልውሃ የተሰበሰበውም ሰው ወደ መቶ ሃምሳ ሺህ ይገመት ነበር። ያንጊዜም ስለ ራስ መኮንን የማያለቅስ ዐይን አልነበረም።…በራስ መኮንን ሞት አፄ ምኒልክ በጣም አዝነው ነበር።” ይላሉ።
ከመቶ አመት በፊት በሆነው ይህ የራስ እምሩ የሀዘን ገለጣ የጊዜን ባህር ተሻግሮ ትዕይንቱና ስሜቱ ወለል ብሎ እየታየን ልባችን በሀዘን መነካቱ፤ አይናችን በእንባ ጭጋግ መጋረዱ አይቀሬ ነው። ይታዩናል አፄ ምኒልክ ፎቶ እየሳሙ፤ እንባቸውን እያዘሩ ደረታቸውን ሲደቁ። ይታዩናል መኳንንቱና ህዝቡ በእንባ ሲራጩ፤ ዋይ ዋይ ሲሉ…አዎ! በራስ መኮንን ሞት አፄ ምኒልክ ታላቅ አጋራቸውንና መከታቸውን ነበር ያጡት። በዘመኑ ለራስ መኮንን ከተገጠሙት የሀዘን መግለጫዎችም ራስ እምሩ አካፍለውናል – እነሆ ለቅምሻ፤
ያ ቃኘው መኮንን የንጉሱ ታዛዥ ፈጣን መልዕክተኛ
ተሳነው መሰለኝ ተዳክሞ ይሆናል ተከናንቦ ተኛ።
አፄ ምኒልክ ሆይ እግዚአብሄር ያጥናዎ
በየበሩ ቋሚ ከልካይ ሞተብዎ።
ራስ መኮንን ሃይለሚካኤል መጋቢት 13 ቀን 1897 ዓ/ም አረፉ። አንባቢ ሆይ! እነሆ ስለ ራስ መኮንን ህይወትና ሞት ካየሁት ከማስታውሰው ካወጋን የነቀስነውን በዚሁ እናሳርጋለን። ቀጣዩን ግን እንቀጥላለንና በርታ።
አባ ዳኘው
ራስ እምሩ በማህደር ያስቀመጡልን የታሪክ ቅርስ ታሪኩ በተከወነበት ዘመን የነበሩትን ዐበይት ሁነቶች ብቻ አይደለም። ተዛማጅ ነገር ግን እምብዛም ትኩረት ያልተቸራቸውን ወይም በሌሎች ተመሳሳይ ዘመን ላይ ባተኮሩ መፃህፍት ውስጥ ያላነበብናቸውንም ገራሚ ክስተቶችንም ጭምር እንጂ። እንጥቀስ፤
“አፄ ምኒልክ ትጉህና ሥራ ወዳድ ስለሆኑ በክረምቱ ጥቢ ሣር በማሣጨድ፤ መንገድና የጣቢያቸውን ቤት፤ የቤትም ዕቃ በማሰራት በጣም ይጣጣሩ ነበር። የሚሰራውንም ሥራ እሳቸው እራሳቸው እየተመላለሱ እየዞሩ የጎደለውንም ነገር እያዩ ደህና አድርጎ እንደሚሰራ ያዩ ነበር። አንድ ወደ ራሷ ወገን ትንሽ ባላ ያላት በትር ሁል ጊዜ ወዲያ ወዲህ ሲሄዱ የሚይዙዋት ምርኩዝ ላይ የሜትር የሳንቲም ልክ እላይዋ ላይ ተቀርጿል። አንዳንድ ነገርም ለመለካት ሲሹ በዚያው ነው የሚያዩ። የሥራም እቅድ ደህና አድርገው የሚያውቁ ናቸው።”
በዚህ ትረካ ጎልቶ የሚወጣው አፄ ምኒልክ ሥራ አክባሪ ብቻ ሳይሆኑ ሥራ የማይመርጡ፤ ሥራ የማይንቁ መሆናቸውም ጭምር እንጂ። ለምሳሌ ሣር አጨዳ። ይበልጡን ፏ ብሎ ስሜታችንን የሚኮረኩረው ግን የምርኩዟ ጉዳይ ይሆናል። አፄ ምኒልክ በዚያች ምርኩዝ ሜትር ስንቱን ክውን ለክተውባት ይሆን? ለመሆኑ እንዲያ ያለች በትረ መንግሥትስ ማን አበጀላቸው? ያቺ የአፄ ምኒልክ በትር ከህመማቸውና ሞታቸው በዃላስ የት ደረሰች? እሷንም አፈር በልቷት ይሆን?
ቅርስ የማሰባሰብና ለትውልድ የማስረከብ ባህልና ልምድ ባልነበራት ሀገራችን ስንትና ስንት ጥንታዊ የታሪክ አሻራ ባክኗል? ተዘርፏል? ትቢያ ሆኗል? እንዲህ እንደ ራስ እምሩ በፅሁፍ ካኖሩልንና በምናባችን ብቻ ቀርፀን ምናብ ሆነው ከሚቀሩብን ይልቅ በግዑዝ አካላቸው ተጠብቀው ቢኖሩ ዛሬ ከአውሮፓውያኑ ሙዚየሞች ያልተናነሰ የታሪክ ላንቲካ በኖረን! ዳሩ አውሮፓውያኑ ምናልባትም ግብፃውያኑም ኦቶማውያኑም የወሰዱብንን ቅርሳ ቅርስ መች ስራዬ ብለን ልናስመልስ ጣርንና?…ይብስ ብለን ታሪክም አልነበረን የሚልና ቀደምት ኢትዮጵያውያንን የሚያወግዝ ትውልድ እንኮኮ ብለን እንኖር የለምን?…ለማንኛውም የኛን ነገር ለጊዜ ትቼ እንመለስ ወደ ራስ እምሩ – ካየሁት ከማስታውሰው ትረካ።
አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን ለዘመናት ከጆቦናት ዃላ ቀርነት ለማላቀቅና ወደ እድገትና ሥልጣኔ ጎዳና ለማውጣት ያደረጉትን ጥረትና የጣሏቸውንም መሰረቶች ራስ እምሩ በዝርዝር ፅፈዋል። አንባቢያን ከዚያው ከምንጩ መቅዳት ይቻላቸዋልና በዚህ ረእስ አናነሳቸውም። የሚከተለውን ግን ቀንጭበናል፤
አፄ ምኒልክ ህመማቸው መበርታቱንና የመዳናቸውም ተስፋ የመነመነ መሆኑን ሲረዱ ጳጳሱን አቡነ ማቲዎስን፤ እጨጌ ወልደጊዮርጊስንና ሹማምንቱን ሁሉ እንዲሰበሰቡ አድርገው ኑዛዜያቸውን በፀሀፊ ትእዛዙ አማካይነት እንዲነበብ ማድረጋቸውን አውግተዋል ራስ እምሩ፤ እንዲህ ይነበባል ኑዛዜው፤
“የኢትዮጵያ ሰው የወገኔ ህዝብ ሆይ፤ እስካሁን በትልቁም ሆነ በትንሹ እየተጋገዝን ነፃነታችንን ጠብቀን በደህና ቆየን። አሁን ግን ስለታመምኩና መስራትም ስላልቻልኩ የዘውዴ ወራሽ ልጅ ኢያሱ መሆኑን ፤ ለጊዜውም እሱ ህፃን በመሆኑ እራሱን እስኪችል ሞግዚት ሆኖ የመንግሥቱን ሥራ ሁሉ የሚሰራ ራስ ቢተወደድ ተሰማን ማድረጌን እንድታውቀው ይሁን…” ይላል።
ራስ እምሩ በዚያን ወቅት ስለነበረው የተሰብሳቢው ስሜትም ሲገልጡ፤ “የተሰበሰበውም ሰው አፄ ምኒልክ ከህመማቸው ባለመዳን ተስፋ ቆርጠው ይህንን ቃል በማስነበባቸው በጣም አዘነ። ብዙዎችም ሹማምንት ያን ጊዜም የሚያለቅሱ ነበሩ።” ብለዋል።
ከዚህ የራስ እምሩ ገለፃ “…ይህንን ቃል በማስነበባቸው /ህዝቡ/ በጣም አዘነ…” የሚለው የአንባቢን ትኩረት ይስባል።
አጤ ምኒልክ መዳን የማይችሉበት የቁርጡ ቀን መቃረቡን የሚያረዳ ቃል በመሆኑ ህዝቡ ማዘንና ማልቀሱ አንደኛው ሲሆን ምናልባት ግን ለተሰብሳቢዎቹ በሀዘናቸው ላይ ተጨማሪ ሀዘን የሆነባቸው የምኒልክ ዘውድ ወራሽ ልጅ ኢያሱ መሆናቸውን መረዳታቸው ይሆን? ብለን ራሳችንን የምንጠይቀው ሌላው ጉዳይ ይሆናል።
አጤ ምኒልክ በታህሳስ 3 ቀን 1906 ዓ/ም አረፉ። ዘመነ ምኒልክም አበቃ፤ የኢትዮጵያና የምኒልክ ታሪክ ግና እስከ ዘመነ ፍፃሜ ይኖራል! !
አባ ጤና
“እራስ ቢተወደድ ተሰማ ከሞቱ በዃላ ልጅ ኢያሱ እራሳቸው አለሞግዚት መግዛት ጀመሩ። ያን ጊዜ ግን ያስራ አምስትና ያስራ ስድስት ዓመት ልጅ ይሆኑ ነበር።” ይላሉ ራስ እምሩ ዘመነ ኢያሱ መጀመሩን ሲያወጉ።
እነሆ ከምኒልክ ሞት በሁዋላ ኢትዮጵያ በአባ ጤና ኢያሱ አስተዳደር እጅ ወደቀች። ይሁንና ልጅ ኢያሱ በራሳቸው ከመግዛታቸው በፊት ግና በምኒልክ መንበር ውስጥ በእቴጌ ጣይቱና በሌሎቹ መኳንንት /ባለሥልጣናት/ መካከል ብርቱ የሥልጣን መጠላለፍ ትርዒት መካሄዱን እምሩ በስፋት ፅፈዋል። እቴጌ ጣይቱ ተሰሚነታቸውንና ሃላፊነታቸውንም ስለምን እንዳጡ ዘርዝረዋል። ይህንን ታሪክ እንደቀደምቱ የዚህ ቅኝት አብላጫ የታሪክ ዘርፎች ሁሉ ከምንጩ ለሚቀዱ አንባቢያን እንተዋለን፤ የዚህ ንኡስ ርእስ ትኩረት አባ ጤና ኢያሱ ናቸውና። እንቀፅል ስላባ ጤና፤
“…ልጅ ኢያሱ እጅግ ነፃነት ያላቸው በማናቸውም ነገር እንደ ፈቃዳቸው ለመሆን ስለነበረ አሳባቸው ብዙ ጊዜ ወደ ፍልውሃ ወደ አራዳም ወገን እጅግ መቦረቅ አብዝተው፤ በዙሪያቸውም ብዙ የሚያዳምቁ ጎረምሶች ነበሩዋቸው። ዘመናቸውም የጎልማሳነት መጀመሪያ ስለሆነ ለመንግስቱ ስራ ጉዳይ ዋና እንደራሴም ስላልነበራቸው፤ ሥራው ሁሉ የተሰበሰበ አልነበረም።
“…ልጅ ኢያሱ እንደልባቸውና እንደ ፈቃዳቸውም መሆን የሚያበዙ፤ ደፋር፤ ብዙ የጨዋታ ነገር ወዳጅ፤ ከባድ ነገር የሚጠሉና የማይችሉ፤ አይናቸው ሰው አፍቃሪና አቅራቢ፤ ረጅም ጎራዴ መታጠቅና መጎላመም የሚወዱ፤ ሴቶችን አፍቃሪ ነበሩ።”
ከዚህ የራስ እምሩ ገለፃ ተነስተን ዘመነ ኢያሱ ከሁለት አቅጣጫዎች በአንዱ ሊጓዝ ይችላል ብለን እንገምታለን።
አንድም ልጅ ኢያሱ በእጩ ንጉሥነታቸው በእድሜና በምክር ታርቀውና ተሰብስበው ሃላፊነታቸውን በአግባቡና በወጉ ይወጡት ይሆናል፤ አልያም ጅምሩን ሁሉ በትነው ሀገርና ህዝብን በአጓጉል ምግባራቸው ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይዶላሉ። ከኒህ ሁለት ግምቶቻችን ውስጥ ዘመነ ኢያሱ ወዴትኛው ያመራ ይሆን? እንኮምኩም ከራስ እምሩ ትረካ እየቀነጨብን፤
በእድሜ እምብዛም የማይበላለጡት ደጃዝማች ተፈሪና ልጅ ኢያሱ በባህሪም ሆነ በተግባር የሚገናኙ አልነበሩም። ልጅ ኢያሱ ጨዋታና ቡረቃ ወዳድ ሲሆኑ “…ደጃዝማች ተፈሪ ግን ለጨዋታ የተፍታቱ ስላልሆኑ ከልጅ ኢያሱ ጋር በአመል እጅግ አይስማሙም።” ይላሉ ራስ እምሩ። ይህ የባህሪና የተግባር ልዩነታቸውም በወደፊቷ ኢትዮጵያ ውስጥ በሁለቱ መካከል ለሚኖረው ግንኙነት ጠቋሚ ሆኖ ይገኛል።
ልጅ ኢያሱ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመሩ ወዲህ ለመንግሥቱ ስራ መቀመጫ የተወሰነ ክልል አልነበራቸውም። በሀረርጌ በወሎ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተዘዋወሩ ሲሆን ወደ ጅቡቲም አቅንተው ጉብኝት አድርገዋል። ‘ካየሁት ከማስታውሰው’ ልጅ ኢያሱ በተጠቀሱት ክልሎች ውስጥ ስላከናወኑት ተግባር በዝርዝር ይተርካል። በዚያን ወቅት እምሩ ሃይለ ሥላሴ በተለያዩ የማእረግ ደረጃዎች በደጃዝማች ተፈሪ መኮንን ተሹመው ሀረርጌ ውስጥ ያገለግሉ ነበር። የመንግሥቱ የበላይ ከሆኑት ልጅ ኢያሱ ጋርም ቅርበት ነበራቸው። እንጠቅሳለን፤
“…እኔ ከልጅ ኢያሱ ጋር በጣም ልማድ ስለነበረኝ…ሁለታችን ብቻ ተገናኝተን በሳቸው ሁኔታ ሁሉ አንዳንድ ነገር ተናገርኳቸው።…ንግግራችንም መጀመሪያ በሃይማኖት ሁለተኛው በጊዜው ስለነበረው ያለሙ ፖለቲካ አኳሆን ነው።
“ስለ ሃይማኖት ከብዙ ንግግርና ክርክር በዃላ አሳባቸውን ገለጡልኝ። ‘የክርስቲያን ሃይማኖት አስቸጋሪ ነው። ጥቂትም መልካም መስሎ የሚታየኝ የስላም ወይም የቴይስት ነው’ አሉኝ” ይላሉ።
ከዚህ ትረካ አንባቢን የሚያስደምመው አባ ጤና ኢያሱ ከክርስትና ሃይማኖት ይልቅ እስልምና የሚመቻቸው መሆኑን መግለጣቸው ብቻ ሳይሆን የቴይስትነትንም እንደ አማራጭ ማቅረባቸው ይሆናል። ለመሆኑ የቴይስት ምንድን ነው? ራስ እምሩ ማብራሪያ አልሰጡንም። ግና በትርጉሙ ዙሪያ ለግንዛቤ ማስጨበጫ ጥቂት እነሆ፤
የቴይዝም በማንኛውም መጠሪያ ያለን የሃይማኖት አምላክ የማያምን አስተሳሰብ ማለት ነው። አለማመን ሲባልም የቴይስት የየትኛውንም አይነት እምነት አምላክ አምላክነት አይቀበልም፤ መኖሩንም አያምንም።
የቃሉ ቅድመ መሰረት ግሪክ ሲሆን ይህም ‘ኤቶስ’ በመባል ይታወቃል፤ ፈጣሪ አልባ /ዊዝ አውቶ ጎድ/ ለማለት።
የቴይስት የሚለው አገላለፅ በፈጣሪ መኖር/ህልውና ለማያምን የተሰጠ መለያ ሲሆን ምንጩም ከፈረንሳይ ቋንቋ የተቀዳ ሆኖ ይገኛል። የቴይስትስ በማንኛውም መጠሪያ በሚገኝ የሃይማኖት/እምነት አምላክ /እግዚአብሄር፤ ኢየሱስ፤ መሀመድ፤ ቡድሃ…/ መኖር ላለማመናቸው የሚያቀርቧቸው የፍልስፍና፤ የማህበራዊ እና የታሪክ መከራከሪ ነጥቦች በርካቶች ናቸው። ለምሳሌ ፅድቅና ኩነኔ። የቴይስት እንደ አንድ ንድፈ ሃሳብ /በፈጣሪ ህልውና ያለማመን/ ተግባራዊ መገለጫ ሆኖ ቢያንስ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በዓለም ላይ መሰራጨት ለመጀመሩ የፅሁፍ ማስረጃዎች ይገኛሉ። እነሆ አባጤና ኢያሱ ከክርስቲያን ሃይማኖት ይልቅ የቴይስት የተሻለ ነው ማለታቸው አስቀድመን ባጣቀስነው የየቴይስት አመለካከት በሆኑት የፍልስፍና የማህበራዊና የታሪክ ግንዛቤዎች ላይ ተንተርሰው ይሆን? በማለት ራሴን መጠየቄ አልቀረም። በዚያን ወቅት ልጅ ኢያሱ “የቴይዝምን’ ‘እንዳማራጭ’ ማንሳታቸውቸው በራሱ የሚያነጋግርና የሚያመራምር ነውና።
ለልጅ ኢያሱ ‘የቴይስትነት’ ወይም ወደ ‘የቴይስት’ አይዲዮሎጂ ለማጋደላቸው አመላካች ‘ካየሁት ከማስታውሰው’ ውስጥ ይገኛል – ምንም እንኳን ራስ እምሩ የልጅ ኢያሱን ተግባር ከዚህ አኳያ ፈርጀው ባያቀርቡም። እንጥቀስ አብነት፤
እምሩ ሃይለ ሥላሴ ልጅ ኢያሱን ወደ ወሎ አጅበው በሄዱ ጊዜ የታዘቡትን ሲያሰፍሩ፤
“ልጅ ኢያሱ አባ ጤናም እዚያው ደሴ ከተማ ሳሉ ቃሊቾችን ሁሉ እየሰበሰቡ እዚያው እግቢው አንዱ ክፍል እልፍኝ ድቤው እየናረና እተጨፈረ ማደር ብሶ ነበር። እኔንም እየወሰዱኝ ሁሉንም ስላየሁ ልጅ ኢያሱ ይህንን ነገር የሚወዱት ምክንያት ከቃሊቾቹ ይልቅ ጭፈራው ደስ እያሰኛቸው መሰለኝ።” ብለዋል።
እርግጥ ነው አባ ጤና በቃልቾቹ ላያምኑ ይችሉ ይሆናል። ቃሎቾቹ ደግሞ በፈጣሪ መኖር አያምኑም። ድቤና ዝየራው ግና የቃልቾቹ እምነት መንፀባረቂያ፤ ዛር ማምጫ፤ ዛር ማስወጫ ጭምር ነውና አባጤናም ይህንን መዘየራቸውና ማስዘየራቸው የዬቴይስትነት ዝንባሌ ወይም በዬቴይስት ማመን ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል?
ይሁናና አባ ጤና ለእስልምና ሃይማኖትም በጣም አድልዖ እንዳለቸው ራስ እምሩ የገለጡ ሲሆን አባ ጤናም በየመስጊዶች በመገኘት ይፀልዩ ነበር። ይህም በዘመኑ ከነበሩት የኢትዮጵያ ክርስቲያን ባለሥልጣናትና ህዝብ ጋር እሳትና ጭድ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
‘ካየሁት ከማስታውሰው’ የታሪክ ቀረፃ ውስጥ አባ ጤና ኢያሱ በሀይማኖት ላይ ያላቸው አመለካከትና ግንዛቤ አስገራሚና ደግሞም አመራማሪ ሆኖ ይገኛል። ለአብነት በጅቡቲ ጉብኝት ወቅት ራስ እምሩ ካሰፈሩት የሚከተለውን ያስተውሏል፤
“…እልጅ ኢያሱ ዘንድ ሙሴ ጋሌብ የሚባል ነጋዴ መጥቶ ከነጋድራስ ኢድልቢ ጋር የሃይማኖት ክርክር አንስተው፤ ጋሌብ ካቶሊክ ኢድልቢ ፍራማሶን ስለሆኑ በብዙ ሲጨቃጨቁ ልጅ ኢያሱ ደስ እያላቸው ይሰሟቸው ነበር። ኢድልቢ፤ ‘እግዚአብሄር የለም፤ ካለ እስቲ አሁን ይግደለኝ’ እያለ ሲናገር፤ ጋሌብም ‘እግዚአብሄር ትዕግስተኛ ነው፤ ላታመልጠው አሁን ከአንተ ጋር አይፎካከርም፤ ምናልባት ልቦና ቢሰጥህ ብትመለስለት ይጠብቅሃል፤ ማዳንን እንጂ በቶሎ ሰውን ማጥፋት አይሻምና’ ሲለው ነጋድራስ ኢድልቢም የቀልድ መልስ ይናገር ነበር።
“እኛ ግን…ከዚያን ቀን በፊት እንዲህ ያለ የድፍረት ቃል በእግዚአብሄር ላይ ሰው ሲናገር ሰምተን አናውቅም ነበርና ካሁን አሁንም የሚቀሰፍና የሚሞት እየመሰለን ብንመለከተው ለጊዜው ምንም የሆነው ነገር አልነበረም፤ በኛም እንኳን አሳባችንን የሚናውጥ ጥቂት እስኪያገባብን ድረስ።” በማለት አንጥበዋል ልዑል ራስ እምሩ።
እነሆ አስቀድመን በጠቀስነው ሃይማኖታዊ ውይይት አራት ጎራዎችን እናገኛለን። ፍራማሶናዊው ኢድልቢ፤ ካቶሊኩ ጋሌብ፤ ኦርቶዶክሳዊያኑ እነ እምሩ፤ ጎራቸው በውል ያልለየው አባ ጤና ኢያሱ።
በሁለቱ የእምነት ፍልስፍና /በፍራማሶንና በካቶሊክ/ መኻል በተካሄደው ውይይት በሰሙት መናፍቃዊ ንግግርና ድፍረት በገሃነም ብረት ምጣድ የተንቸሰቸሱ የመሰላቸው ኦርቶዶክሳውያኑ እነ እምሩ ይገኛሉ። በፈጣሪ ላይ እንዲህ ያለ እብሪታዊ የድፍረት ንግግር ሰምተው የማያውቁት ኦርቶዶክሶቹ የእግዚአብሄር ብርቱ ቁጣ ድንገት እንደ መብረቅ ባርቆ ኢድልቢን ዶጋ አመድ ሲያደርገው፤ አልያም ምድር አፏን ከፍታ መቀመቅ ሲወርድ፤ አልያም እንደ ሎጥ ሚስት ደርቆ ሲቀር፤ ካልሆነም ፈረሰኛው ግዮርጊስ ደርሶ በጦር ሲሸቀሽቀው…እየታያቸው ካሁን አሁን የጌታ ቁጣ ይፈፀም ዘንዳ ቢጠባባቁ…ቢጠባበቁ…ሁሉ ከንቱ ይሆንባቸዋል። ያሰቡት ሲሆን ባለማየታቸውም ነበር “…በእኛም እንኳን አሳባችንን የሚናውጥ ጥቂት እስኪገባብን ድረስ” ማለታቸው ራስ እምሩ። በአጭሩ ለጊዜውም ቢሆን እምነታችንን ኢድልቢ አናጋብን ወይም አዞረብን – ማለታቸው ነበርና።
ልጅ ኢያሱስ? አባ ጤና ኢያሱማ ሠርጋቸው ነበር። ነፍሳቸው እየዘለለች፤ እየቦረቀች፤ እያጨበጨበች ጮቤ ትረግጥ ነበር – “እግዚአብሄር አለ – እግዚአብሄር የለም” እያሉ ኢድልቢና ጋሌብ በቃላት ሰንሰለት ሲተናነቁ። አባ ጤና ኢያሱ በኢድልቢና በጋሌብ ሃይማኖታዊ ትንቅንቅ ይፈነድቁ ነበር እንጂ ወላ መብረቅ፤ ወላ መቀመቅ፤ ወላ ሎጥ፤ ወላ ግዮርጊስ ላፍታም አልታሰቧቸውም። ነፍሳቸው ለገሀነምም ሆነ ለገነት ደንታ አልነበራትምና።
ታዲያ ልጅ ኢያሱ አስገረሙኝ፤ እንቆቅልሽ ሆኑብኝ። እኚህ ሰው ማን ናቸው? የዕውቀታቸውስ ደረጃ እስከ ምን ነበር? ነፍስያቸውስ የፈላስማነት ነፍስ ነበራት ይሆን? ነጋድራስ ኢድልቢ የልጅ ኢያሱ ወዳጅና ባለሟል ነበር። ኢድልቢ ፍራማሶን ነበር። እንግዲህ ልጅ ኢያሱ የምሥጢራዊው ‘ፍራማሶን ሶሳይቲ’ አባል ነበሩ ይሆን? ወይስ ኢድልቢ ለፍራማሶናዊነት እያዘጋጃቸው ነበር?…ይሁንና በአንባቢ ህሊና ውስጥ ሁለት ጉልህ ጥያቄዎች እየደወሉ እንደሆን ይሰማኛል። ለመሆኑ ‘ፍራማሶን’ ምንድን ይሆን? የሚል እና ነጋድራስ ኢድልቢ ማን ነበር? የሚለው። ለቀዳማዩ ጥያቄ ራስ እምሩ የሰጡን ማብራሪያ የለም፤ ለተከታዩ ጥያቄ ግና መልስ አላቸው። የኢድልቢን ማንነትና ሚና ዘግየት ብለን እንመለስበታለን። ስለፍራማሶን ምንነት ግን እነሆን በጥቂቱ፤
ፍራማሶን የፈረንሳይኛ ቋንቋ አጠራር ሲሆን በእንግሊዝኛው ፍሪማሰን በመባል ይታወቃል። ለዚህ ቅኝት የምጠቀመው የራስ እምሩን የፈረንሳይኛ አጠራር ፍራማሶንን ይሆናል። ፍራማሶን ራስ እምሩ ከገለፁልን የኢድልቢ ተግባርና አስተሳሰብ ከቶም የተለየ ከመሆኑም አልፎ እጅግ ጥልቅና ሰፊ ፍልስፍናዊም ፅንሰሃሳብ ያለው ሲሆን አወቃቀሩና አሰራሩም በዛው መጠን ረቂቅ ሆኖ ይገኛል። ይሁንና ቀልበጭ ባለ መንገድ ለተጨማሪ ንባብና ምርምር ፍንጭ ሊሰጥ በሚችል መልኩ ለማቅረብ እንደሚከተለው ተዋቅሯል።
ፍራማሶን በሰው ልጅ ወንድማማችነት /ብራዘር ሁድ ኦፍ ማን/ መሰረት ላይ የቆመና በ’ታላቁ ህልው አባት’ /ፋዘር ኦፍ ሱፕሪም ቢንግ/ ጥላነት የሚያምን ጥንታዊ ተቋም ነው። ፍራማሶን የሃይማኖት ተቋም አይደለም፤ እንደ ፍራማሶናውያን ዘገባዎች። ይሁንና በፍራማሶንነት የተጠመቁ /ኢኒሺየት/ የሆኑ አባላቱ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት አባላት ሊሆኑ ይችላሉ። ናቸውም።
የፍራማሶን ውልደት በቀጥታ ከሠለሞን ቤተ መቅደስ ግንባታ ጀምሮ እንደሆን የሚያትቱ ዘገባዎችና መፃህፍት ቢኖሩም በተጨባጭ ማስረጃዎች የተደገፉ ግን አይደሉም። ሆኖም የጥንታውያን ማሶናውያን (በሳይንስ፤ በጥበብ/አርት፤ እና በሥነ ህንፃ/አርኪቴክቸር/ ዕውቀቱ ያላቸው ማለት ነው) የፅሁፍ ማስረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1390 የእንቅስቃሴው አስኳል እንደነበር ነው።
ፍራማሶን በዘመናዊ መልኩ በመደራጀት በዓለም ላይ መስፋፋት የጀመረው ግን ከ1717 ጀምሮ ሲሆን ይህም እንግሊዝ ውስጥ አራት ሎጅስ (የፍራማሶናውያን መሰብሰቢያ መጠሪያ) ተቀናጅተው የመጀመሪያውን ‘ግራንድ ሎጅ’ አቁመው ‘ግራንድ ማስተር’ ከመረጡ በዃላ ነበር።
ፍራማሶን በሶስት መርሆዎች ላይ የተገነባ ሲሆን እኒህም ወንድማማችነት፤ በጎ አድራጎት፤ ሐቅ/ዕውነት የሚሉ ናቸው። እኒህ ሶስቱ በፈረንሳውያኑ ፍራማሶኖች ሲገለፁ ደግሞ ወንድማማችነት፤ እኩልነት፤ ነፃነት /ፍራተርኒቲ፤ ኢኳሊቲ፤ ሊበርቲ/ የሚሉ ሆነው ይገኛሉ።
በፍራማሶን ሎጅ ወይም ግራንድ ሎጅ ማንኛውም አይነት የሃይማኖት ሰበካም ሆነ የእምነት አምላክን ስም (ለምሳሌ የኢየሱስን፤ የቡድሃን፤ የመሀመድን…) መጥራት በጥብቅ የተከለከለ ነው፤ ‘ሱፕሪም ቢንግ’ /ታላቁ ህልው/ ከሚለው የፍራማሶንነት መገለጫ በስተቀር።
በአንድ ሎጅ ወይም ግራንድ ሎጅ ውስጥ ክርስቲያኖች፤ እስላሞች፤ ቡድሃዎች፤ ሲኮች፤ ጂዊሾች…የሃይማኖት ልዩነቶቻቸውን አግልለው በፍራማሶን ሶስት መርሆዎች ላይ በመቆም የጋራ አስተሳሰባቸውንና የጋራ ግባቸውን በጋራ ያራምዳሉ። የፍራማሶን መለያ ወይም አርማ ‘ኮምፓስ’ እና የድንጋይ ፈልፋይና ቅርፅ አውጪ ግንበኞች የሚጠቀሙበት የማዕዘን መለኪያ ‘ስኩየር’ ተጣምረው የሚፈጥሩት ቅርፅ ነው። ይህም በፍራማሶን ህንፃዎች ላይ ሁሉ ተቀርፆ ከነስማቸው ይገኛል። እኒህ የጥንት ማሶኖች /ድንጋይ ቀራጮችና ገንቢዎች/ በዓለም ላይ በተለይም በአውሮፓ የሚገኙትን ታላላቅ ካቴድራሎችና ቤተ መቅደሶች የገነቡ ለመሆናቸው ታሪካቸው ያትታል። ይሁንና ከመካከለኛው ዘመን /ሚድል ኤጅ/ በዃላ ይህ የማሶኖች የግንባታ ሥራ ተቋርጧል።
የተለያዩ ፀሀፍት በፍራማሶን አደረጃጀት አንፃር በተለይ በከፍተኛው የፍራማሶን ዲግሪ /የሥልጣን ተዋረድ/ ላይ የሚገኙት የተለየ ምሥጢር እንዳላቸው ብቻ ሳይሆን ፍራማሶን ራሱ ምሥጢራዊ ድርጅት ነው በማለት የፃፉ ቢሆንም ፍራማሶን በበኩሉ ይህንን አገላለፅ በመቃወም የፍራማሶን ሎጅ/ግራንድ ሎጅ ምንም ምሥጢር የሌለበትና መዛግብቱንም አገላብጦ መመርመር የሚቻልና ይፋዊ እንደሆንም ይናገራል። ሌሎች ደግሞ ፍራማሶን በመንግሥት ውስጥ ያለ መንግሥት ነው በማለት ቢፅፉም ፍራማሶን ግን ይህንን መቃወም ብቻ ሳይሆን አባላቱና በየሀገሩ ያሉ ግራንድ ማስተሮች ሳይቀሩ በአደባባይ በህዝብ የሚታወቁ ናቸውና አባባሉ ሚዛን አያነሳም በማለት የበኩሉን ነጥቦች ያቀርባል።
በአሜሪካና በአውሮፓ ዛሬ ለተደረሰበት ሥልጣኔ፤ የሀሳብ ነፃነትና የዴሞክራሲያዊ መዋቅር መስፋፋትና መጎልበት ፍራማሶን ያበረከተው ጉልህ ተዋፅፆ ውጤት እንደሆን በርካታ ማስረጃዎችን አስደግፈው የወጡ መፃህፍትና ጥናታዊ ፅሁፎች ያትታሉ። ለዚህ ምክንያትም ፍራማሶናውያኑ በአስተሳሰብና በእውቀት እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆናቸውም ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም በየሚኖሩበት ሀገር ያላቸው የሥልጣንና የተሰሚነት ደረጃ ጭምር እንደሆንም አክለው ይገልጣሉ።
ለምሳሌ ከዩ ኤስ አሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ከአስር በላይ የሚሆኑት ፍራማሶንስ ለመሆናቸው በይፋ የወጡ ማስረጃዎች ያመለክታሉ። በፍራማሶንነታቸው በየሀገሩ ከሚገኙ የፍራማሶን ሎጅስ እና ግራንድ ሎጅስ በተገኙ የፅሁፍ መረጃዎች የሚታወቁ ታላላቅ ሳይንቲስቶች፤ ደራሲያን፤ የሙዚቃ ጠበብቶች፤ ፈላስፎች፤ የጦር መሪዎች፤ ነገሥታት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፤ ፕሬዚዳንቶች፤ የህግ ባለሙያዎች፤ የስለላ መዋቅር ሃላፊዎች፤ ስመጥር ስፖርተኞች፤ ተዋንያንና አክተሮች ወዘተርፈ ቁጥራቸው የትለሌ ነው። ከፍራማሶን በወጡ ዘገባዎች መሰረት በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ አራት ሚሊየን ፍራማሶንስ ይገኛሉ።
ከታዋቂ ፍራማሶንስ መካከል ለአብነት ያህል ለዚህ ቅኝት አንባቢያን ግንዛቤ የሚከተሉትን ይመለከቷል።
ከዩ ኤስ አሜሪካ ፕሬዚዳንቶች፤- ጆርጅ ዋሽንግተን የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት፤ ቤንጃሚን ፍራንክሊን፤ ቲዮደር ሩዝቬልት፤ ሃሪ ትሩማን። ከፊሊፒንስ፤ ኢሚሊዮ አጉናልዶ። ከሩማኒያ፤ ኮንስታንቲን አርጀንቲኑ። ከጋቦን፤ ኦማር ቦንጎ። ከቺሊ፤ ሳልቫዶር አሌንዴ። ከጠቅላይ ሚኒስትሮች፤- ሰር ሮበርት ሜንዜስ አውስትራሊያ፤ ዊንስተን ቸርችል እንግሊዝ፤ ፍራንሲስኮ ክሪስፒ ጣልያን፤ ጆን አቦት ካናዳ፤ ፕራክሴዴ ሳጋስታ ስፔን። ከንጉሶች፤- ሊዮፖልድ 1ኛ ቤልጂየም፤ ናፖሊዮን ቦናፓርት ፈረንሳይ። ከስለላ ተቋማት ጄ ኢድገር ሁቨር የኤፍ ቢ አይ የመጀመሪያው ዳይሬክተር። ከደራሲያን አሌክሳንደር ፑሽኪን፤ ማርክ ቱዌን፤ ኮናን ዶይል፤ ኦስካር ዋይልድ። ከሙዚቃ ጠበብት፤- ዎልፍጋንግ ሞዛርት፤ ሉድዊንግ ቤቶቨን። ከህግ ባለሙያዎች የዩ ኤስ አሜሪካን ‘ሱፕሪም ኮርት’ ዛሬ በሚገኝበት አቋሙ ያዋቀሩት ‘ቺፍ ጀስቲስ’ ጆን ማርሻል። ከኢንደስትሪያሊስቶች ሄነሪ ፎርድ ወዘተርፈ ሲሆኑ ከኢትዮጵያ የአባጤና ኢያሱ ወዳጅና ባለሟል ነጋድራስ ኢድልቢ ይገኛል(?)። ምንም እንኳን ከኢድልቢ አስቀድሞ የተዘረዘሩት ለፍራማሶንነታቸው ከየሎጅ እና ግራንድ ሎጅ የወጡ የፅሁፍ ማስረጃዎች ቢያረጋግጡም የነጋድራስ ኢድልቢን ፍራማሶንነት ግን ራስ እምሩ የነገሩንን በማመን ብቻ ይሆናልና።
ታዲያ እስካሁን ከተዘረዘረው የፍራማሶን መርህ አኳያ የሚነሳ ጥያቄ ይኖራል። ከፍራማሶን መመሪያዎች አንዱ ማንኛውም ፍራማሶን በግልም ሆነ በአደባባይ በተለያዩ የሃይማኖት ቀኖናዎችና እምነቶች ላይ መከራከር፤ ማላገጥ፤ ወይም ሃይማኖትን ከሃይማኖት ማበላለጥ በጥብቅ የተከለከለ ሆኖ ሳለ ኢድልቢ ካቶሊኩን ጋሌብ መፈታተኑ የፍራማሶንን ህግና መመሪያ መጣሱ አይደለምን? የሚለው ይሆናል። አዎ! እርግጥ ነው ኢድልቢ በእርግጥ ፍራማሶናዊ ከሆነ ታላቁን የፍራማሶንን ተከባብሮና ተቻችሎ መራመድ የሚለውን ህግ ጥሷል። ለምን? ለሚለው የቃኚውን መላ ምት እነሆ።
ክርክሩ በተካሄደበት ስፍራና ጊዜ ኢድልቢ ጋሌብን ለመፈታተን በእግዚአብሄር ላይ ሲሳለቅ ሁኔታውን ለፍራማሶን ሎጅ ሪፖርት የሚያደርግበት ሌላ ፍራመሶን አለመኖሩን በማወቁና አጋጣሚውን መጠቀም ወዳጁ የሆኑትን አባጤና ኢያሱን የሚያስደስት መሆኑን በመረዳቱና ምናልባት ለአባ ጤና ያጠመደላቸው ወጥመድ ካለ ሙሉ ለሙሉ ለመሸምቀቅ ይቻለው ዘንዳ አስልቶ ሊሆን ይችላል። እንግዲህስ በፍራማሶን ዙሪያ ያነሳነውን በዚሁ ቋጭተን ወደ ቀጣዩ ነቁጥ እናምራ።
ለመሆኑ ካየሁት ከማስታውሰው ስለ ነጋድራስ ኢድልቢ ምን አውግቷል? እየነቀስን እንመልከት።
“…የሐረርጌን የበላይነት ነጋድራስነት መስየ ኢድልቢ የሚባል ሶሪያዊ ከልጅ ኢያሱ ተሾመ።…ነጋድራስ ኢድልቢ ከልጅ ኢያሱ በጣም ባለሟል ስለሆነ የድሬደዋን ከተማ ፈፅሞ የሱው ግዛት አደረጋት።
“አንዲትም ልጃገረድ ልጅ፤ አስራ ስድስት አመት የሚሆናት አባጤና ኢያሱን የምታቀብጥ ነበረችው።…ኢድልቢ የሐረርጌን ነጋድራስነት ሳይሾም በምእራብ ኢትዮጵያ አንድ የሚገዛው አገር የሰጡት ነበረው።
“የሐረርንም ነጋድረራስነት እንደያዘ የጉምሩክን ሥራ ደህና አድርጎ አሻሽሎ ደንብ አፅፎ አሳትሞ እንዲቆም አደረገ። የሰራተኛውንም ደሞዝ እንደስራው መጠን ከፍ አድርጎ እየወሰነ አዘጋጅቶ ሰጠ። ይኸንም ሁሉ እንደ ፈቃዱ እንዲያሰናዳ ከልጅ ኢያሱ ፈቃድ ተቀብሎ ነበር…” ይላሉ እምሩ ሃይለሥላሴ።
አንባቢ ሆይ! እንግዲህ ስለ ነጋድራስ ኢድልቢ ማንነትና ከአባ ጤና ኢያሱም ጋር ስለነበረው ግንኙነት ከላይ የተነቀሰው ገለጣ አንዳች ስዕል ፈንጥቋልና ቀሪውን ለመፅሀፉ አንባቢያን አቆይተን፤ ቀጣዩን እንቀጥል።
ራስ እምሩ ከሃይማኖት ሌላ በፖለቲካው መስክ ከልጅ ኢያሱ ጋር መወያየታቸውን እንደገለጡልን መቼም ያስታውሷል። ለመሆኑ ውይይታቸው ስለ ምን ነበር?
ዘመኑ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ነበር። በዚህ ጦርነት ውስጥ ልጅ ኢያሱ ጀርመን አሸናፊ ሆና እንድትወጣ እንደሚፈልጉ ለዚህም ምክንያታቸው የጀርመን አጋር የሆነቸው ቱርክ እንደሆነች፤ ቱርክንም መደገፋቸው የእስላም ሀገር በመሆኗ እንደሆነ ለእምሩ ይነግሯቸዋል። ስለዚህም እምነታቸው ወይም ድጋፋቸው አዲስ አበባ ካለው የጀርመን ሚኒስትር ጋር መቀራረብ ማድረጋቸውንም ያጫውቷቸዋል። የእምሩ ሃይለሥላሴ መልስ ምን ነበር? ከራስ እምሩ አንደበት እንስማ፤
“የአውሮፓ ጦርነት አሸናፊነቱ የእንግሊዝና የፈረንሳይ ነው የሚመስለኝ።…እነዚህ ጎረቤቶቻችን ለጀርመን መርዳታችንን ካወቁ ገና የነሱን በአውሮፓ የሚሆነውን የጦርነት መጨረሻ ሳናይ ነው በዙሪያችን ተነስተው የሚያጠፉን። እንደኔ አሳብ ከሆነ ነፃ ሆነን ከሁሉም ሳንሆን መጨረሻቸውን ማየት ይሻላል። ይኸውም ባይሆን ከነዚሁ ከጎረቤቶቻችን ጋር አንድ ስምምነት የባህር ጠረፍ የምናገኝበትን ተነጋግሮ ለእንግሊዝና ለፈረንሳይ መርዳት የሚጠቅም ነው። ጣሊያን ከጀርመን ተነስቶ ከነዚህ ጋር ሲሆን የኛ እድል ጠፍቷል” አልኳቸው ሲሉ ፅፈዋል።
ይሁንና ልጅ ኢያሱ ምንም እንኳን የእምሩ ስጋትና ምክር ቢገባቸውም ሀሳባቸውን እንዳልተቀበሏቸው አያይዘው አስፍረዋል። የእምሩን ስጋትና ምክር ከዘመኑ ዓለም ዐቀፍ የፖለቲካና ወታደራዊ የሀገራት ግንኙነትና አሰላለፍ አንፃር ስንመለከተው እጅግ አርቆ አስተዋይነት የተሞላው ብቻ ሳይሆን የግንዛቤያቸውም ደረጃ መጥቆ ይታያል።
ከዚህ ትረካ የምንረዳው ሌላው ነጥብ በዚያን ዘመን ከውጪው ዓለም ጋር የነበረን ኮሙዩኒኬሽን በተቀላጠፈ መንገድ የሚካሄድና የመረጃ /ኢንፎርሜሽን/ ፍሰቱም በእጅጉ የተገደበ ቢሆንም መሪዎቻችን ግን በዓለም የፖለቲካ ፍትጊያ ውስጥ የማይናቅ ግንዛቤ እንደነበራቸው ማስተዋላችን ይሆናል። ኢያሱና እምሩ ስለሀገራቸው መፃዒ ዕድል ያላቸው ራዕይና አሰላለፋቸውም ለየቅል ቢሆንም ቅሉ።
ካየሁት ከማስታውሰው በዘመነ ኢያሱ ዙሪያ የሚያወጋን ታሪክ ዘርፈ ብዙ ነው። ዝርዝር ታሪኩን ከዚህ ቅኝት ባሻገር ታገኙታላችሁና አሁን ለልጅ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት ማክተም ራስ እምሩ ከተዉልን ታሪክ ቀንጭበን ንኡስ ርእሳችንን እንሸብባለን። የሚከተለውን ያነቧል፤
“…ህዝቡ ልጅ ኢያሱን አጥብቆ በመጥላቱ ውስጥ ውስጡን ነገር መቋጠር፤ መገናኘትና መዶለት ጀምሮ በጣም ይሰራ ነበር።
“ልጅ ኢያሱንም የጠላበት ምክንያት ብዙ የብልግና ነገር ስለሚሰሩ፤ የክርስቲያኑን ወገን ስለናቁት፤ የመንግሥቱንም ሥራ ችላ ብለው በያገሩ ዙረት ስላበዙ፤ የመንግሥቱንም ሥልጣን የተዉላቸው ሚኒስትሮች ለህዝቡ አንድ የረባ ሥራ ባለመስራታቸው፤ ባፄ ምኒልክ የተጀመረው የሥልጣኔ ሥራ ሁሉ የሚያስታውሰው ጠፍቶ የሚጨምረው ነገር ባለመኖሩ በሁሉም ነገር ተያይዞ በጣም ጠልቷቸው አቂሞባቸው ነበር።” ይላሉ ራስ እምሩ። አያይዘውም በዚያን ወቅት ውሃ ቀጂዎች በልጅ ኢያሱ ላይ ገጥመው ያንጎራጉሩት ከነበረው ግጥም ጥቂት ስንኞችን አንጥበዋል…
እሺ ናና ናና እሺ ናና ናና
ስወጣም አዝዬ ስገባም አዝዬ
ጀርባዬ ተላጠ ና ውረድ ሰውዬ።
እንዴት አደርክ ብለው እንዴት አደርሽ አለኝ
እግዚአብሄር ይመስገን ሊቀር ነው መሰለኝ
ለአባ ጤና ኢያሱ ውድቀት ግፊት ያደረጉ ሌሎች ግዙፍ ምክንያቶች እንዳሉ ራስ እምሩ ዘርዝረው ፅፈዋል። እንዲህ ይነበባል በጥቂቱ፤
“…በሁለት ነገሮች ምክንያት የልጅ ኢያሱ አወዳደቅ በረታባቸው። መጀመሪያ ራስ ተፈሪን ከሐረር መሻር፤ ሁለተኛው የጀርመን ወገን በመሆናቸው የውጪ ሀገር ሰዎችም ብዙ ስለጠሉዋቸው ነበር” ይሉና ይህንኑ አፍታትውታል፤ እንደሚከተለው፤
“ስለመጀመሪያው፤ አስቀድሞ የኢትዮጵያ ታላላቁና ታናናሹም ሁሉ በሁሉም ነገር ገምቷቸው ልጅ ኢያሱን ሲጠላ በሳቸው ስፍራ የሚያደርገውን ማሰብ ከጀመረ ቆይቷል።
“ራስ ተፈሪ አመላቸው ክት በመሆኑ፤ ጥቂትም የፈረንሳይ ትምህርት ስላላቸው ቸርነታቸውም በብዙ በኢትዮጵያ ሰዎች ዘንድ የተመሰገነ በመሆኑ፤ ላዲሱም እውቀት ሥራና ትምህርት ሁሉ ወጣቱ ወገን፤ ልጅና አንዳንድም አስተዋዮች የሆኑት በጣም ተስፋ ያደርጓቸው ስለነበር፤ የሁሉም ዐይን ወደሳቸው ተመልክቶ ሳለ ሐረርጌን በመሻራቸው ምክንያት እሳቸውን ይዞ በግልጥ ለመቃወም የቆረጠበት ይህ ነው።” በማለት ያብራሩና አያይዘውም፤ ልጅ ኢያሱ በዘመኑ በነበረው የአውሮፓ ጦርነት ምክንያት የጀርመን ደጋፊ በመሆናቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፈረንሳይ የእንግሊዝ እና ሌሎች የውጪ ሀገር ሰዎች መውረዳቸውን ያበረታቱም ነበር – ብለዋል እምሩ ሲፅፉ።
እነሆ ልጅ ኢያሱ ኢትዮጵያን ባስተዳደሩበት ዓመታት አስቀድሞ በተጠቀሱት ግዙፍ ምክንያቶች በአዲስ አበባ የሚገኙት የወቅቱ የሀገሪቱ መሪዎች ተመካክረው የኢያሱ ዘመን እንዲያከትም ደጃዝማች ተፈሪ መኮንንን አልጋወራሽ እንደራሴ፤ ዘውዲቱን ደግሞ ንግሥተ ነገሥታት አድርገው ሲሾሙ ልጅ ኢያሱና ደጋፊዎቻቸው ይህንን በመቃወም የተለያዩ ጦርነቶችን ቢገጥሙም ውጤቱ ሽንፈት፤ ማሳረጊያውም የልጅ ኢያሱ መታሰር ሆኖ አክትሟል።
ካየሁት ከማስታውሰው ይህን የዘመኑን ፖለቲካዊና ወታደራዊ ውስብስብ ታሪክ በስፋት አቅርቦልናል። የአባጤና ኢያሱን ታሪክ ቅኝት በዚሁ ገትተን እናመራለን ወደ ተከታዩ።
ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ
ልዑል ራስ እምሩ ሃይለሥላሴ ካየሁት ከማስታውሰው ውስጥ ካሰፈሩልን የበርካታ ጥንታውያን ኢትዮጵያውያን ታሪክ መኻል የነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ ታሪክ ይገኛል። እነሆ ነጋድራስ ገብረህይወት በራስ እምሩ አንደበት፤
“ነጋድራስ ገብረህይወት አገሩ ትግሬ፤ መልኩ ቀላ ያለ፤ ፊቱ ከበብ ያለ፤ ፅህማም፤ ጠጉረ በራ፤ መልከ ቀና፤ አፍንጫው ሰንደድ ያለ ቁመቱም አጠር አካሉም ደልደል ያለ ጎናም ነው።…አመሉም ጥቂት ቁጡ፤ ደፋር፤ አስተዋይና ሥራ ወዳጅ፤ ስንፍና የሌለው ብርቱ ሰው ነበር። ትምህርትም የጀርመን ቋንቋ ደህና አድርጎ የተማረ የፈረንሳይም በጥቂቱ መነጋገር በሚችል መጠን ያውቅ ነበር።…”
በዚህ ቅልብጭ ባለው የራስ እምሩ ሥዕላዊ ገለጣ አጭሩና ራሰ በራው ምሁሩ ገብረህይወት ባይከዳኝ በምናባችን የሚታየን ብቻ ሳይሆን በአካል የምናውቀውም ያህል መስሎ ይሰማናል። ለመሆኑ ገብረህይወትን ራስ እምሩ ስለምን አስተዋወቁን? እነሆኝ መልሳቸው ሲቀነጨብ፤
“…ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ የሐረርጌን ነጋድራስነት ካዲስ አበባ ተሹሞ መጣ። ይኸውም ነጋድራስ ገብረህይወት የተማረ፤ በጣም ያስተዋለ መልካም ብርቱ ሰው ነበር። እንደመጣም ሥራውን ሁሉ ተረክቦ የሥራውን አካሄድ ሁሉ ነጋድራስ ኢድልቢ የወሰነውን ጉምሩክ ሥራ አስተካክሎ…የጎደለውን ሁሉ አሻሽሎ…አቋቋመ።” ይላሉ።
ካየሁት ከማስታውሰው ላይ ከሚስተዋለው የራስ እምሩ አንዱና ጉልህ ታላቅነት ከራሳቸው በፊት የሌሎችን ታሪካዊ ምግባር በአግባቡና በወጉ ሚዛኑም ሳያጋድል ማቅረባቸው ነው። ስለራሳቸውም ሲፅፉ በአብላጫው ‘እኔ’ ከሚለው ይልቅ ‘እኛ’ እያሉ በወል ተሳትፎ የተከወነ ታሪክ መሆኑን እያጎሉ ሲያወጉን እንመለከታለን። ወደ ነጋድራስ ገብረህይወት ታሪክ እንመለስ፤
“…ነጋድራስ ገብረህይወት ሁለት መፃህፍት ፅፏል። መጀመሪያ የፃፈው ባፄ ምኒልክ በጊዜው የነበረውን አኳሆን ሁሉ የሚያሳይ ነው።
“ሁለተኛው እጅግ ጥቅም ያለው መፅሀፍም የሕዝብ አስተዳደር የሚባል የኢኮኖሚ ፖለቲክ ጉዳይ ሁሉ በዝርዝሩ ያገራችንን የተለምዶውን፤ የሕዝቡን ኑሮ የሚጎዳውን እየተቃወመ በነገሩም እያስረዳ ነው የፃፈ። ይኸውም የፃፈው መፅሀፍ እሱ ከሞተ በዃላ አልጋወራሽ ራስ ተፈሪ በማህተም ባማርኛ አሳትመውት ብዙ መፅሀፍ ተሽጧል።”
ከዚህ ታሪክ ውስጥ ሁለት ነቁጦችን እንመዛለን። ነጋድራስ ገብረህይወት በተሰጠው ሃላፊነት /ለምሳሌ በነጋድራስነቱ/ ሥራውን በሚገባና ዘላቂ ትሩፋት ባለው መንገድ የሚያከናውን አርቆ አስተዋይ ምሁር ብቻ ሳይሆን ደራሲ እንደነበርም የምንገነዘብበት፤ ሁለተኛው ደጃዝማች ራስ ተፈሪ ‘የሕዝብ አስተዳደር’ የሚለውን የገብረህይትን የኢኮኖሚ ፖለተካ መፅሀፍ እንዲታተምና በሕዝብ እጅ እንዲገባ የማድረጋቸው ዕውነታ ይሆናል።
ገብረህይወት በኢትዮጵያ የሰፈነው ድቅድቅ ጭለማ ተገፎ ሀገራችን ከዃላቀርነት ተላቃ በሥልጣኔና በእድገት ጎዳና እንድታመራ ጎጂ የሆነው የተለምዶ አሰራርና የህዝቡንም ህይወት የሚጎዳው ሁሉ ይወገድ ዘንዳ እየተቃወመ መፃፉ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያለውንም ሥርነቀል የለውጥ ማኔፌስቶ በማሳተም እንዲሰራጭ ያደረጉት ተፈሪ መኮንንም /በገብረህይወት መፅሀፍ ጭብጥ አመኑም አላመኑም/ ሁለቱም በየፊናቸው በዚህ ታሪክ ውስጥ የሚያስገርሙን ባህሪያት ሆነው ይገኛሉ።
ገብረህይወት በመፅሀፉ ጭብጥ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅን ዴሞክራሲያዊ መብት ሲያሳየን፤ መሪው ተፈሪ መኮንን ደግሞ ይህንን ዴሞክራሲያዊ መብት አምነው የአስተዳደርን ዘይቤ የሚቃወም መፅሀፍ ማሳተማቸው ሀሳብን በነፃ የመግለፅ ዴሞክራሲያዊ መብትን መቀበላቸውንና ማክበራቸውን ያመለክተናል። እንመለስ ወደ ገብረህይወት ታሪክ፤
“…ነጋድራስ ገብረህይወት ወዳዲስ አበባ ወጥቶ ሳለ በብርቱ ታሞ፤ ሀኪሞቹም ማዳን አቅቷቸው ይሻለው እንደሆን በማለት ወደ ጅቡቲ እንዲሄድ አመልክተውት፤ እዚያም ሄዶ ጥቂት ሰሞን ሰንብቶ ምንም ያህል ሳይሻለው ወደ ድሬደዋ ተመለሰ።… ድሬደዋ ጥቂት ሲሻለውም ሲያመውም አንድ ሁለት ወር ያህል ቆይቶ በመጨረሻ በጣም ስለጠናበት ወደ ሐረር ወጥቶ ጥቂት ቀን አስታመነው ሞቶ እዚያው አደሬ ጢቆ ቤተክርስቲያን በክብር አስቀበርነው። ዕድሜውም ወደ 35 ይሆን ነበር።…ያን ጊዜ በመላው ኢትዮጵያ እንደሱ ያለ /የተማረ/ አስር የሚሞላ ሰው አልነበረም።” ይላሉ ራስ እምሩ በገብረህይወት አጭር መቀጨት የውስጣቸውን ሀዘን ሲገልጡ።
ይህን የነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ ታሪክ የምናነብ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ልባችን በሀዘን መነካቱ ግድ ነው። እንዲህ ያለ ታላቅ የኢትዮጵያ ልጅ ኢትዮጵያዊ ለሀገሩና ለወገኑ ብዙ የሚያበራው ጧፍ እያለው ብርሃኑ በጠዋት ሲጨልምበት እንዴት ውስጣችን አያዝን? እንደምንስ በአጭር የህይወት ዘመኑ ባበረከተው ታላቅ ሀገራዊ ምግባር አንኮራ? እንኮራበታለን እንጂ አሳምረን፤ ዛሬም ቢሆን ገብረህይወትን እያሰብን! ይፈሩ እንጂ ዘረኞቹ፤ የገብሬን ኢትዮጵያዊነት የሚክዱ ህወሃቶቹ! ይብላን እንጂ ለነሱ ለህወሃታውያኑ እኛስ አሉን ሺህ በሺህ ኢትዮጵያዊ ገብረህይወቶች፤ በትግራይ መንደሮች በትግራይ ኮረብቶች።
ወገን አንባቢ ሆይ! ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከ አስር አስከ አስራሁለት ሚሊዮን ይገመታል ይባላል። በዚህ ህዝብ መኻል የነበሩን የተማሩ የሚባሉ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከአስር አይበልጡም ነበር – እንደ ራስ እምሩ ገለጣ። እንግዲህ እኒህ አንድ ለአንድ ሚሊዮን ከምናምን በሆነ ሬሾ ውስጥ የኖሩ ኢትዮጵያውያን በዘመኑ ከነበሩ በተፈጥሯቸው ብሩህና አርቆ አስተዋይ ከሆኑት መሪዎቻችን ጋር ሆነው በመሥራት ነበር ዛሬ የምትገኘዋን ኢትዮጵያ መሰረት የጣሉትና ዳር ድንበሯን አስከብረው ለትውልድ ያስተላለፉት።
ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር እስከ መቶ ሚሊዮን ይገመታል። የተማረው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ከዛን ዘመኒቱ ኢትዮጵያ አንፃር አስሩ ቁጥር በሚሊዮናት እጥፍ ጨምሯል። ታዲያ ይህ ዛሬ ላይ የሚገኘው የተማረው ሀይል ከእኒያ ከአስሩ ጥንታውያን አኳያ ምን ያህል ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ዕድገት፤ ብልፅግና፤ ሰላም፤ ዳር ድንበር መከበርና ለህዝቧም መልካም አስተዳደር ምስረታና ግንባታ የዜግነት ግዴታ ድርሻውን ተወጥቷል? በመወጣትስ ላይ ይገኛል? ብለን መጠየቃችን አግባብ ይሆናል። እርግጥ ነው አስተዛዛቢና አሳፋሪ የሆነ ገመና ነው የሚኖረን እኒህ ጥያቄዎች ተበራይተው ሚዛን ላይ ሲወጡ። ያም ቢሆን ግን በያድባራችን በጥልቅ መወያቱና መምከሩ ቢያንስ ለነገይቷ ኢትዮጵያ የዛሬው የተማረ ትውልድ ሊተገብር የሚገባውን የዜግነት ሃላፊነትና ግዴታ አፅንዖት በመስጠት አንፃር ድርሻ ሊኖረው ይችል ይሆናል ብለን እናምናለን።
የሐረርጌው እንደራሴ
እስከ አሁን ራስ እምሩ በመፅሀፋቸው ውስጥ ካሰፈሩልን የታሪክ ሁነቶችና ባለታሪከኞች ታሪክ እየቀነጨብን ኮምኩመናል። እንግዲህስ ትኩረታችንን በባለታሪኩ በራስ እምሩ ላይ እናደርጋለን።
እምሩ ሃይለሥላሴ ዕድገታቸው በቤተመንግሥት ክልል መሆኑንና ከኢያሱና ከተፈሪ መኮንን ጋር የነበራቸውንም ግንኙነት አስቀድመን አይተናል። እምሩ የሐረርጌን እንደራሴነት በአልጋወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ከመሾማቸው አስቀድሞ በተለያዩ ማዕረጎችም አገልግለዋል፤ ትኩረታችን ግና በእንደራሴነታቸው ይሆናል። እንቀጥል፤
“…እኔ የሐረርጌን እንደራሴነት ይዤ ብዙውን ነገር የውስጡን ሁሉ ተመለከትኩ። ጉዳት ያለበትን ወገንና ጥቅምም ያለበትን አስተዋልሁ።…” ይላሉ ራስ እምሩ ስለሐረርጌ እንደራሴነታቸው በፃፉት ሰፊና ማራኪ ታሪክ።
ስለ ሐረርጌ አውራጃዎች መልክዐ ምድሩን፤ አቀማመጡንና የተፈጥሮ ሀብቱን፤ ስለ ህዝቡ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ህይወት፤ የታሪክ ተዋረዱን፤ የህብረተሰቡን ሃይማኖታዊ፤ ጎሳዊ፤ ማህበራዊ አኗኗር፤ ልማድ፤ ባህልና ወግ፤ ወንዝና ሸንተረሩን፤ አዝርዕት ቡቃያውን፤ ከብትና እንስሳቱን…በየዘርፉ ተንትነው ስናነብ ሐረርጌን በበቅሎና በእግር አፋፉን ወጥተን ቁልቁለቱን ወርደን…ከባላገሩ ጋር አድረን፤ ከባላገሩ ጋር በልተን…የሰብሉን መዐዛ አሽትተን፤ ከወራጅ ወንዝ ጨልፈን ተጎንጭተን…ከቆላ ዳጋ የዳሰስናትና የኖርንባት ያህል እናውቃታለን – የዛን ዘመኒቷን ሐረርጌ፤ በራስ እምሩ ትንታኔ።
ራስ እምሩ የሐረርጌን ዳር ድንበር ሲዳስሱ በዘመኑና ከዚያም ዘመን በፊት የነበሩት የሀገራችን መሪዎች የባህር በሮቻችንን በመጠበቅም ሆነ በመገልገል አኳያ የነበራቸውን ግንዛቤና አቅም እንደሚከተለው አንጥበዋል፤
“በሺህ ስምንት መቶ ሠባ ዘጠኝ ዓመተ ምህረት አፄ ዮሀንስ አስቀድመው በተነጋገሩበት ጉዳይ ግብፆችን አስለቅቀው አፄ ምኒልክ እጅ አደረጉትና እንደ ቀድሞው የኢትዮጵያ ግዛት ሆኖ ነበር። ያን ግዜም ጅቡቲም ሆነ በርበራም፤ ሞቃዲሾም የባህሩ በር ሁሉ ክፍት ስለሆነ አውሮፓውያን ገና አልገቡበትም ነበር። ያገሩም ባላባቶች አንዳንዶቹ ወደ አፄ ምኒልክ እየመጡ የሳቸው ዜጋ መሆናቸውን እያሳወቁ ተቀምጠው ሳለ፤ በዚያው ዘመን የጠረፉ ጥቅም ባለመታወቁ፤ መንገዱም የብዙ ቀን በረሃ ስላለበት፤ አገሩም በጣም ቆላ በመሆኑ ወደዚያ ሹም ተልኮ ከተማ እንዲቆረቆርና የንግድ በርም እንዲከፈት ማንም የተመለከተውና ያሰበው ኢትዮጵያዊ አልነበረም። ባፄ ዮሀንስ ንግግር ያን ጊዜ ምፅዋ ሳይቀር ተለቆ እንደዚሁ ቆላ በመሆኑ በረሃውን በመፍራት ሥራዬ ብለው ሳይዙት በመቅረቱ ወደ ውጪ ሀገር መንግሥታት በየጊዜው እየተላለፈ ሄዶ፤ ሌሎቹም አሰብ፤ ጅቡቲ፤ ዘይላ፤ በርበራን የመሳሰሉትን ጠረፎች የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዬ እንዳላላቸው ስላዩ፤ አውሮፓውያኖች ባላባቱን እያባበሉና እየተስማሙ እየገቡ ይዘው የኢትዮጵያን ባህር በር ዙሪያውን ዘጉ።”
ራስ እምሩ በአንድ አንቀፅ ሸብበው ያስቀመጡልን ታሪክ ቢፍታታ የደለበ ጥራዝ ያለው መፅሀፍ ይወጣዋል። ከዚህ የታሪክ አንቀፅ ሶስት ነጥቦችን እንመዛለን።
በዘመኑ የነበረው የድንበራችን ስፋትና የባህር በሮቻችን ዝርዝር ብዛት ቀዳሚው ነጥብ ሲሆን፤ ተከታዩ ደግሞ በዘመኑ የነበሩት መሪዎቻችን ከነበራቸው የባህር በር ጥቅም ግንዛቤና እኒህ የጠረፍ ወደቦችን ከማዕከላዊው መንግሥት ሹም ልኮና ከተማ ቆርቁሮ ለመገንባት አንድም ከርቀቱና ከበረሃው፤ ሁለትም ዘላቂ ጥቅሙን መገንዘብ ካለመቻል፤ ሶስትም የተጠናከረ ማዕከላዊ መንግሥት /ከዘመነ መሳፍንት ሙሉ ለሙሉ ለመላቀቅ/ በመገንባትና በማጠናከር ላይ ዋናው ትኩረትና ርብርቦሽ ስለነበር – በእኒህና ተዛማጅ እሙን ድክመቶችና ችግሮች ሳቢያ ኢትዮጵያ ወደቦቿን መጠቀምም ሆነ መጠበቅ ያለመቻሏ፤ ሶስተኛም የወደብ ሀገሮችን በመያዝ የሚዛቀውን ህልቆ መሳፍርት ጥቅም አስቀድመው የቀመሱት አውሮፓውያን በድክመቶቻችን/ክፍፍሎቻችንና በኢኮኖሚም ባለመጠንከራች ተጠቅመው የኢትዮጵያን የባህር በር ዙሪያ መክበባቸው፤ ማጠራቸው።
ይህ የታሪክ ዘለላ እንደሚያስረግጠን ሀገራችን የወደቦች ድሃ ያልነበረችና ሆኖም አጠቃቀሙን ወይም ጥቅሙን ዘግይታ የተገነዘበች መሆኗንም ጭምር ይሆናል። ይሁንና ከትውልድ በዃላ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል አሰብና ምፅዋን አደራጅተን፤ መዋዕለ ንዋያችንንም አፍስሰንና የባህር በር ጠባቂ ዘመናዊ የባህር ሃይል አቁመን ሀገራችን ትጠቀም እንደነበር ሁለት አስርታትን ያስቆጠረ የቁጭት ትዝታችን ሆኗል።
እነሆ የዘመን ተገላቢጦሽ ይሏል ያለንበት ዘመን ነው፤ ዘመነ ህወሃት/ኢህአዴግ። ምፅዋን ሸጠን፤ አሰብን ውሰዱልን ብለን ገፀ በረከት አቅርበን፤ እድሜ ለሞምባሳ፤ ኬንያ ለዘለዓለም ትኑር! እንላለን – እናት ሀገራችንን – ኢትዮጵያችንን – አስገድለን ገድለን።
‘እዚያ ላይ /አስመራ/ አንድ መንግሥት እዚህ ታች / አዲስ አበባ/ አንድ መንግሥት አቆማለሁ’ በማለት ወዲ ዜናዊ ቢነግረን ‘ይኩን ፈቃድከ ትምፃ መንግሥትከ’ አልነው እራሱ በጠራው ሸንጎ ላይ ተንጋግተን ተገኝተን፤ ቆመን አጨብጭበን። እና…ይኸው አለን እንላለን…የወዲ ዜናዊን የግፍ ጥንስስ እየተጋትን…ዘመንን በዘመን እያጣፋን…
እናብቃና የእኛን፤ እንመለስ ወደ ጥንቱ የጠዋቱ፤ ታሪከ እምሩ።
ልዑል ራስ እምሩ በሐረርጌ እንደራሴነታቸው ወቅት ከዘመኑ አኳያ ስር ነቀል ሊባል የሚችል የመንግሥታዊ አሰራር ለውጥ አምጥተዋል። ይኸውም ቢሆን ግን ከአልጋወራሽ እንደራሴ ራስ ተፈሪ መኮንን ጋር እየተመካከሩና እየተፃፃፉ ነበር። ራስ እምሩ በተለይ የባላገሩን ህይወት ለመቀየር በብርቱ ሰርተዋል፤ የችግሩንና የድህነቱን እንብርት አብጠርጥረው ጨብጠውት ነበርና – እነሆ አብነት።
“…እጅግ አለልክ ባላገሩን የጎዳው በስፍር የሚከፍላቸው ነገሮች፤ በየወሩ ከሚከፍለው የእንጨት፤ የዱቄት፤ በሶስቱም አመትባል የሚከፍለው ጌሾ፤ ደግሞም ባመት የሚሰፍረው ማሩ፤ የእህል ቀለቡ ነው። ይኸውም መልከኛው /ባላባቱ ባለመሬቱ/ ሁሉ እየቤቱ ገረዱንና አሽከሩን እየላከ እያሰፈረ ስለሆነ የሚቀበለው ዱቄቱ፤ ማሩ፤ እህሉ እየታመቀ እንጨቱ በጣም እየጠበቀ፤ የመስፈሪያውንም ልክ እያደገ፤ ያመጣው ሁሉ አልሞላለት እያለ በብዙ መጉላላት ስለሚደርስበት፤ ገባሩ የርሻውና የሥራው ጊዜ በመጨቃጨቅ እንዳያልፍበት ጉቦ እየሰጠ እንዳቅሙ፤ ሞላህ እየተባለ የሚሄደው እጅግ ብዙ ነው። ያለጉቦም አይሞላለትም፤ በጉቦም የጎደለው ይሞላል። በእንደዚህ ያለው ነገር እየተካሰሰ ወደ ዳኛ ለመለካካትና ለመበያየን የሚመጣው ከመቶ አስርም አይሆን፤ አቅም ስለሌለው። ዳኞችም ትዳራቸው እንደዚሁ ገባር በመግዛት ስለሆነ አጥቂው መልከኛ /ባላባት/ እንደሚገባው ትልቅ ቅጣት የሚያገኘው ጥቂት ነው፤ ያውም በግልጥ ሆኖ የተመሰከረበት። በየቤቱ ለሚሰራው ምስክሩስ የት ተገኝቶለት!”
ስለባላገሩ ግብር አሰፋፈርና እንግልት በስፋት ከፃፉት ውስጥ የተመዘዘው ይህ አንቀፅ እምሩ የህዝብ አገልጋይና የህዝብ ተቆርቋሪ እንደራሴ እንጂ በህዝብ የሚገለገሉ አናት ላይ ቂብ ያሉ አገረ ገዥ እንዳልነበሩ ያስረዳናል። እንቀጥል፤
“…በማናቸውም አኳሆን የዚሁ ያስራት አሰፋፈር ጉዳይ ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከ መጨረሻው ለሰራተኛው ስርቆት፤ ለባላገሩና ለመንግሥት ጉዳት ብዙ ስላለበት ያሰራሩ ረገድ ፈፅሞ ካልቀረና በሌላ መንገድ ካልሆነ መዳኛ እንዳልነበረው ተረድተነው ነበር። በቁርጥ ብቻ በየመሬቱ መጠን የተወሰነ ገንዘብ እንዲከፍል ታስቦበት ባላገሮቹ መውደድና መጥላታቸውን እንዲጠየቁ በየወረዳው ሁለትም ሶስት ሰው እንዳገሩ ትልቅነት ወኪል እንዲልኩ ተደርጎ መጥተው ቢጠየቁ፤ የሚበዙት እንደነበረው እየተሰራ እንዲቆይ ስለፈቀዱ ለጊዜው ሳይለወጥ ቆይቶ ነበር…” በማለት አስቀምጠዋል።
አንባቢ ሆይ! የህዝብን ድምፅ የበላይነት ማክበርና መቀበል በዴሞክራሲ መርሆ ማመን ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል?
ባላገሩ ተበድሏል። የግብር አሰፋፈሩ ለድህነትና ለመከራ ዳርጎታል። ይህንን የአሰራር ልማድ ማሰወገድ ተገቢ ነበር፤ በጉልበትና በሃይል ሳይሆን በመተማመን። ባለጉዳዩን ሰብስቦ በማነጋገር።…አብዛኞቹ የባላገሩ ተወካዮች የልምድ እስረኞች በመሆናቸው ‘አሰራሩ ለጊዜው እንደነበር ይቆይልን’ አሉ። ጉዳዩን በግድ ለማስፈፀም እምሩ ቢነሱ መዘዙ አያምርም፤ ህዝቡ ያላመነበት ነውና…ለመሆኑ ባላገሮቹ እንዲህ ያለ ውሳኔ ስለምን አሳለፉ? እምሩ ሃይለሥላሴ ከወሎው የሥራ ልምዳቸው ተነስተው አውግተውናል፤ ዘግይተን እንመለከታለን። አሁን ሌላ ነቁጥ እናንሳ፤
“በሺህ ዘጠኝ መቶ አስራ ስምንት ዓመተ ምህረት ክረምቱ በጣም የከፋና የበረታ ሆኖ የተዘራው እህል ሁሉ በጣም የሚበዛው በሐረር አውራጃ ጠፋ።…ቀጥሎም በ1919 ዓ/ም አንበጣ ከልክ ያለፈ ከቆላው ተፈልፍሎ መጥቶ የተዘራውን ብዙ ስለበላ በየአገሩ በጣም ረሀብ ሆነ። እኛም ያን ጊዜ በሐረር ወረዳ ያለውን እህል ቀለብ የሚቀበለውን እንደሚያስፈልገው እየቀረበት ብዙውን ቀነስንበት፤ ለህዝቡ ለማብቃቃት።
“የቆላው አገር ህዝብና የደጋውም ብዙው ባላገር እጅግ ተርቦ ነበርና ካልጋወራሽ አስፈቅጄ ሐረር ጅጅጋ ድሬደዋ ላይ የመንግሥት የእህል ጉድጓድ ተከፍቶ ለረሀብተኛው ሁሉ በየቀኑ አንዳንድ ኩባያ እህል ተሰጠ። የብዙም ሰው ነፍስ ዳነ።…አዲስ አበባም ከህንድ አገር ብዙ ማሽላ ተገዝቶ ወጥቶለት ነበር።” ብለዋል ራስ እምሩ ስለዛን ዘመን ረሀብ ሲተርኩ።
እነሆ ከዚህ ትረካ ቢያንስ ሶስት ያፈጠጡ ሀቆች ይወጣሉ። በዘመኑ የገባውን ረሀብ ለመቋቋምና የህዝቡን ህይወት ለማትረፍ የሐረርጌ አስተዳዳሪዎች ለባላባቶች የሚሄደውን እህል በማስቀረት ለህዝቡ እንዲከፋፈል ማድረጋቸው፤ ሁለተኛው በመንግሥት የእህል ጎተራ የተከማቸው እህል ለክፉ ቀን እንደዋለ፤ ሶስተኛም የወቅቱ ማዕከላዊ መንግሥት ከሀገሪቱ ካዝና አውጥቶ ማሽላ በመግዛት የዜጎቹን ህይወት እንደታደገ።
በተፈጥሮ ጭካኔ የሚደርስ ረሀብ በዚያን ዘመንም ሀገራችን ውስጥ ነበር። ታዲያ በዚያን ዘመን የነበሩ መሪዎች ረሀብን ለመቋቋም ደፋ ቀና ብለው ሠሩ እንጂ እንደዛሬዎቹ አቁማዳ እያንጠለጠሉ ርጥባን አልለመኑም። ብር ከሀገሪቱ ካዝና፤ እህል ከመንግሥት ጎተራ አውጥተው ረሀብን ተፋለሙት እንጂ በህዝብ ረሀብ እንደዘመነኞቹ አልነገዱም።
ካየሁት ከማስታውሰው ውስጥ የሐረርጌው እንደራሴ አንባቢን በእጅጉ የሚመስጡ በርካታ የታሪክ ዘለላዎችን አስቀምጠውልናል። የዚህ መፅሀፍ ግዝፈቱና ትሩፋቱ ጠልቆ የሚሰማን ግና ስናነበው ብቻ ይሆናል። ለማንኛውም የጀመርነውን ንዑስ ርእስ ያለአባሪ አስተያየት በሚቀፅለው ዘለላ እንሸብበው ዘንዳ ወደናል፤
“በሺህ ዘጠኝ መቶ አሥራ አንድ ዓመተ ምህረት በሮፓና በእስያ አድርጎ የመጣው የንፋስ (የግሪፕ) በሽታ በኢትዮጵያም በመላው አገር ገብቶ ብዙ ሰው ሞተ። ያን ግዜም ሐረር ነበርኩ። እዚሁም እሐረርጌ ከህዳር ወር ጀምሮ እስከ ጥር መጨረሻ ሰሞን ድረስ በጣም ከፍቶ ከከተማው ውስጥ ብቻ እንኳን ከሰማንያ እስከ መቶ ሃያ በየቀኑ ይሞት ነበር። የታመመውም ሰው ልክ አልነበረውም። በሽታውም ትኩሳቱ በጣም እየበዛ፤ እራስ እያዞረ፤ አእምሮ እያጠፋ፤ ደም እያስታወከ ነው። በቶሎም ካንዱ ወዳንዱ የሚተላለፍ በመሆኑ ብዙው ቤተሰብ እንዳለ እየተኛ አስታማሚው ብዙ ችግር ሆነ። የነበሩት ጥቂት ሀኪሞችም ምንም ያህል ሰው ለማዳን አልቻሉም፤ በሽታውም እያጣደፈ የሚገድል ስለሆነ።
“ያን ጊዜም የታመመውንና አስታማሚ ያጣውን በመጎብኘት፤ የሞተውንም በመቅበር እተቻለ ድረስ ደከምነ። በሀኪሞቹም ምክር የካሊፕቱስ /ባህር ዛፍ/ ቅጠል እየበሽተኞቹ ቤት እየተቀቀለ በላቦቱ አየሩን በመለወጥና ትኩሱንም ውሃውን በመጠጣት ብዙ ሰው አሻለ። በየቦታውም በሞተው ሰው መቃብር ላይ ኖራ በብዙ ተረጨበት። ይኸውም በሽታው እንዳይተላለፍ የሚያግዝ ነበረ። ከየካቲት ወር ጀምሮ ግን እየተሻለ ሄደ” በማለት አንጥበዋል ልዑል ራስ እምሩ ስለ ዘመኑ ወረርሽኝ ሲያወጉ።
የወሎው እንደራሴ
በ1922 ዓ/ም በወሎ ግዛትና አካባቢው ከፍተኛ ችግር ተከስቶ ነበር – በተለይ በራስ ጉግሳ ወሌ ማመፅ። በዚሁ ዓመት የሐረርጌው እንደራሴ ከሐረርጌ ወደ ወሎ እንዲዛወሩ ሆነ። ካየሁት ከማስታውሰው ስለዚህ ዘመን ፈታኝ አመፅ ምክንያቱንና መዘዙን ውጤቱንም አካትቶ አበራይቶ አቅርቧል፤ ግን እዚያ ዝርዝር ውስጥ እንገባ ዘንዳ አይቻለንም። አመፅ ከተነነ፤ ሠላም ከሰፈነ ወዲያ እምሩ ከዘረዘሩልን ታሪክ ግን እናቀርባለን እየቀነጨብን። ለህዝብ የቆሙት የህዝብ አገልጋይ እምሩ ሃይለሥላሴ ለመሆኑ በወሎ ምን ከወኑ?
“…እኔ ደሴ ከተማ እንደገባሁ…ከያገሩ ብዙ የመጡ ሽማግሎች ሰዎች ስለነበሩ በታላቅ ስብሰባ ጉባኤ አድርገን ስላስራቱ ሰፈራ ጉዳይ ተነጋገርን።
“ያስራቱም አሰፋፈር የወሎውም እንደ ሌላው አገር ሁሉ በዳኛና በፀሀፊ ጎልማሚ በሚባሉ ታዛቢዎች፤ መልከኛው ጭምር እየሆኑ፤ በየወረዳው ክፍል ሁሉ ሄደው እያስወቁ ያሰፍሩ ነበር። እነሱም ሳይሄዱ ማናቸውም እህል አይወቃም፤ የተወቃውም የማይገባ በመሆኑ ብዙው እህል በድንገተኛ ዝናብ ይበላሽ ነበር። የስርቆቱና የጉቦውም አኳሆን ሁሉ በሐረርጌው ክፍል እንደፃፍኩት አይነት ነው።” ይላሉ።
እነሆ የወሎው እንደራሴ ስለወሎ ህዝብ የዘወትር ህይወትና አኗኗር መረዳትና ማወቅ ቀዳሚው ዓላማቸው ነበርና የባላገሩን ኑሮ ከሀገሬው አዛውንቶች ጋር ሸንጎ ተቀምጠው መከሩበት።
አንባቢ ሆይ! በዚህ መፅሀፍ ውስጥ የሚገርመው የመንግሥት መንበር በሆነችው አዲስ አበባ ላይም ቢሆን መኳንንቱና ባለስልጣናቱ በማንኛውም ሀገራዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ተሰብስበው ሳይመክሩና ሳይከራከሩ፤ ሀሳባቸውንም በነፃነት ሳይገልጡ /ለምሳሌ ፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ተክለማርያም፤ ራስ እምሩ ሃይለሥላሴና ደጋፊዎቻቸው በአንድ ወገን በሌላው ወገን ደግሞ በወቅቱ ሃይለኛ ተደማጭነት /ኢንፍሉዌንስ/ በነበራቸው ራስ ካሳና ደጋፊዎቻቸው መካከል በህገ መንግሥት ላይ ያካሄዱትን አስገራሚ ውይይትና ክርክር አብነት ይጠቅሷል/ በዘፈቀደ በአንድ ሃይል ፈላጭ ቆራጭነት ውሳኔ የማይተላለፍ መሆኑን በየደረጃው የምናየው ክስተት መሆኑ ነው። እንቀጥል የወሎውን ጉባኤና ውጤት፤
“ማናቸውንም ነገር በዝርዝር ሁሉንም ተነጋግረን የሥራውንም ጥፋት አስቀድመው እነሱ ስለሚያውቁት ነገሩ በስራት ከገባቸው በዃላ፤ በተለመደው ማሰራቱ በቁርጥ እህል የሚሻል እንደሆነ፤ ወይም በግምቱ ብር ማስገባት ፤ ሰፋሪዎቹ ሁሉ ቀርተውለት የሚሻልም ቢሆን፤ እንዲመርጡ አስታወቅናቸው።”
እነሆ ምርጫ። እምሩ ሃይለሥላሴ አገረ ገዥ አልነበሩም። ሆነውም አያውቁም፤ ሀገር አስተዳዳሪ እንጂ። እናም ህዝብ ያላመነበትን፤ የህዝብ ድምፅ የሌለውን የግላቸውን ‘ቀጭን’ ትእዛዝ በህዝብ ጫንቃ ላይ አሳርፈው አያውቁም – ካየሁት ከማስታውሰውን አንብበን ከጭብጦቹ መኻል አንዱን ጭብጥ ስንጨብጥ። እንቀፅል
“በማግስቱም ሁሉም ተሰብስበው በየራሳቸው የሚፈቅዱትን የሃሳባቸውን አስታወቁ።…ከመቶ ዘጠና አምስት የሚሆነው ‘ባላገሩ እንደልቡ እህሉን ያግባ…’ ብለው አስታወቁ። ለጉባኤውም የተሰበሰቡት ጨዎች ከያገሩ የመጡት ወደ አምስት መቶ ስልሳው ይሆኑ ነበር…
“…ይህንኑ በምክሩ የተቆረጠውን እንዲፈቀድልንና እንድናስፈፅም በስልክ ላፄ ሃይለሥላሴ አስታውቀን፤ መልሱም ‘መልካም ነው ይሁን’ የሚል ስለመጣልን በነጋሪት ባዋጅ ‘እህልህ እንደደረሰልህ እየወቃህ እንደፈቃድህ አግባ። አሰፋሪዎች በጭራሽ እንዳይመጡብህ አድርገናል። የምትከፍለውን አስራት በቁርጥ በምትችለው መጠን በየወረዳህ እናስታውቅህአለን’ ብለን አወጅንለት። ለመስማትም የተሰበሰበው ህዝብ ሁሉ በታላቅ ደስታ አጨብጭቦ እልል! አለ።…እኔም ስለወሎ ህዝብ ደስ አለኝ፤ ለየሌላውም ለማሻሻል ጉዳይ ሁሉ የሚረዳ በመሆኑ” በማለት ፅፈዋል የወሎው እንደራሴ።
በዚህ ትረካ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አሰራር ቦግ ብሎ ይታየናል። ህዝቡ ተጠየቀ። የሚበጀውን ወሰነ። ውሳኔውም ወደ በላይ ተላለፈ። የበላይም አፀደቀ። የፀደቀውም አዋጅ ሆነ፤ ተግባራዊ። የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አሰራር ማለት ይህ ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?! በዚህ አገላለፅ ለማሳየት የፈለግነው ዐቢይ ነቁጥ ያ ሥርዐተ ማህበር ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ነበር ለማለት ሳይሆን በዚያ ሥርዐት ውስጥም እንኳን ቢሆን ዴሞክራሲያዊ አሰራር ይንፀባረቅና ይተገበርም እንደነበር ለማመላከት ነው።
በአንፃሩ ታዲያ በዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ውስጥ በዘመነ ህወሃት ትዋኛለች በምትባለዋ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በተጨባጭ ዴሞክራሲያዊ አሰራርና አስተዳደር ከቶም ደብዛው የማይታይ መሆኑን በግርምት ንፅፅር አንባቢ ያስተውሏል።
ወደ ቀደመ ጉዳያችን እንመለስ፤
ቀደም ባሉት ገፆች የሐረርጌ አርሶ አደሮች የግብር ሥርአቱ እንዲቀየርላቸው ቢጠየቁ ‘እንደድሮው ይቆይልን’ ማለታቸውን ያስታውሷል። ታዲያ እምሩ ከወሎ ህዝብ ውሳኔ አንፃር ስለሐረርጌው ህዝብ ምን ብለው ይሆን? እንቀንጭብ ከምንጩ፤
“…የሐረር ህዝብ የመከራውን ሥራ ወዶ እንደነበር እንዲቆይለት መምረጡ፤ ይኸ የወሎ ህዝብ ግን የተሻሻለውን ሥራ ፈቅዶ ያንኑም ወዶ ደስታ በማድረጉ በምን ምክንያት እንደሆነ ነገሩን ለማወቅ ስለፈለግሁ፤ አንዳንዶቹን ሹማምንት ጠየቅሁ። እነሱም ያስታወቁኝ ምክንያቱ ‘በፊት በንጉሥ ሚካኤል ዘመን በየሁለትና በየሶስት ዓመት በያንዳንድ ምክንያት ካስራቱም በላይ፤ ፈሰስ እያሉ ብዙ እህል ያስወጡት ነበር። አገሩ ግን ወደ አፄ ሃይለሥላሴ ከዞረ ወዲህ እንደዚህ ያለው ፈሰስ ቀርቶለታል።…አስራት አሰፋሪዎቹንም ህዝቡ በጣም ይሰቀቋቸዋል’ አሉኝ።
“በሌላውም ወገን እኔ እንደተመለከትኩት በጥቂቱም ጊዜ ቢሆን የወሎ ህዝብ ቋንቋው ያው አማርኛ በመሆኑ ከገዢዎቹ ጋር በመነጋገር ነገሩን ቶሎ በማስተዋሉ፤ የሚጠቅመውንም በማወቅ ከሐረር ባላገሮች ይልቅ በጣም የተሻለ ነው። እነዚያ አዲስ ነገር ምንም የተሻለ ቢሆን አስቀድሞ ይከብዳቸዋል። ስለዛውም እንደነበር መቆየት ይመርጣሉ፤ ብዬ ተመለከትኩ” በማለት ግንዛቤያቸውን አስፍረዋል።
አዲስ ሀሳብን ተቀብሎ ልምድን ወይም የነበረ አሰራርን ለመቀየር ለሐረርጌዎቹ ባላገሮች የመክበዱ ምክንያት የልምድ ቁራኛ የመሆናቸው ብቻም ሳይሆን አዲሱን ሀሳብ በሚገባቸው ቋንቋ እንዲረዱት አለመደረጋቸውም ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ ነው ራስ እምሩ ከወሎው ህዝብ ልምድ የነገሩን። በዚህም የራስ እምሩን የአስተሳሰብና የግንዛቢ አድማስ ስፋትን እንመለከታለን።
የወሎው እንደራሴ ስለ ወሎ በፃፉት ሰፊ ታሪክ ውስጥ የባላገሩ ህይወት ከቀድሞው በተሻለ መንገድ እንዲቀየር ማድረጋቸው ብቻም አይደለም የሚነበበው። ለአብነት የሚከተለውን ያስተውሏል፤
“…የደሴ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በስራት አልተቋቃመም ነበርና የከተማው መንገድ በሰፊው እየተቀየሰ እንዲሰራ፤ የገበያውም ቦታ እንዲለይ፤…ምድሩም እየተከነዳ፤ ካርታ እየተነሳ፤ እመዝገብ እየገባ ሰው እንዲቀበል። አስቀድሞ መሬት ይዞ የቆየ ሰው አዲስም የሚቀበለው የሚደራጅበትን ህግ በዝርዝር ተፅፎ፤ በጠቅላላውም ስለ ከተማው ሥራ ልዩ ልዩ ጉዳይ ለማዘጋጃ ቤቱም የሚያስፈልገውን ሠራተኛ ሁሉ ተዘጋጅቶ፤ የተፃፈውንም ደንብ ሁሉ ወዳዲስ አበባ አስተላልፈን አስፈቅደን፤ በዚያው ትክክል እንዲሰራ…ለማዘጋጃ ቤቱ ከንቲባ አስተላለፍንለት።
“…መንገዱም በሁሉም ወገን በሰፊው እየተቀየሰ ተበጀ።…ቦታም በፊት አስር ብር የሚያወጣው ዋጋው እስከ አስር ሺህ ብር ድረስ ሆነ። በዚሁም በከተማው እርስት ምክንያት በተገኘው ገቢ ገንዘብ አንዳንድ በከተማው ውስጥ የነበሩ መጥፎ ወንዞች በኖራና ባሸዋ በጥርብ ድንጋይ ማለፊያ ማለፊያ ድልድዮች ተሰሩ።
“የከተማው ዘበኞችም በሠላምና በፀጥታ ደህና አድርገው የሚጠብቁ በየወሩ የብር ደሞዝ የሚቀበሉ ነበሩ።” ብለዋል እምሩ ሃይለ ሥላሴ ካየሁት ከማስታውሰው ላይ ባስቀመጡልን ታሪክ።
ለምሳሌ የቦርከናን ድልድይ ግንባታ አስመልክቶ ካየሁት ከማስታውሰው አስደናቂ ታሪክ አውግቷል። እምሩ የዚህን ድልድይ ቅየሳና ግንባታ ሃላፊነት የሰጡት ለፈረንጆች ሳይሆን ቱሉ ለተባለ ግንበኛ ኢትዮጵያዊ ነበር። በዚህ ቅኝት ውስጥ ለመፅሀፉ /ካየሁት ከማስታውሰው/ አንባቢያን እንደተውናቸው በርካታ የታሪክ ሁነቶች ሁሉ የቦርከናን ድልድይ ገንቢ ቱሉን አስደማሚ ታሪክም ከምንጩ ትኮመኩሙት ዘንዳ ጋብዘናል።
እንደ ሐረርጌው ትረካ ወሎንም ደጋ ወጥተን ቆላ ወርደን የህዝቡን ሃይማኖቱንና ባህሉን፤ ታሪክና ልምዱን፤ አዝርዕት እንስሳቱን በእዝነ ልቦናችን እናይ ዘንዳ በየፈርጁ እየተረተሩ አስተዋውቀውናል – ልዑል ራስ እምሩ ሃይለሥላሴ።
ለመሸበቢያ
በዚህ ቅኝት መላልሰን እንዳነጠብነው ‘ካየሁት ከማስታውሰው’ የታሪክ ባህር ነው። የቅኝታችንም ዓላማ ከታዳምያን ጋር ለማስተዋወቅ ብሎም ለተጨማሪ ንባብ አቀጣጣይ ክብሪት ለመሆን ብቻ።
እምሩ ሃይለ ሥላሴ በህመም ሳቢያ በ1924 ዓ/ም ወደ አውሮፓ ለህክምና በሄዱበት ወቅት በፈረንሳይም ሆነ በስዊስ ስለገጠሟቸው አስገራሚ ገጠመኞች ዘርዝረው ያጫወቱን ብቻ ሳይሆን በተለይ ከፈረንሳይ ሚዲያ የቀረቡትን ዘገባዎችና ከመንግሥቱም ባለሥልጣናት ጋር ያደረጓቸውን ውይይቶችና የእነሱንም አስተሳሰብ /በተለያዩ ጉዳዮች/ አስቀምጠዋል – ምንም እንኳን አካሄዳቸው ለኦፊሴላዊ የመንግሥት ሥራ ባይሆንም። የኤሮፓን ሥልጣኔም አስመልክቶ ትዝብታቸውንም ሆነ አድናቆታቸውን ዘርዝረዋል። እንደሌሎቹ ታሪኮች ሁሉ የአንባቢን ቀልብ ይስባል፤ ይፈትናል፤ ይሞግታል…የኤሮፓው ትረካ። እነሆ ቅምሻ…
“…አንዱን ቀን ብቻዬን ሄጄ…አትክልት ቦታ /ፓርክ/ ተቀምጬ ሳለሁ፤ አንድ ጠና ያለ ዘመኑ ወደ አርባው ውስጥ የሚሆን ፈረንሳዊ ሰው ከሩቅ ወደኔ አቅንቶ ሲመጣ አየሁት፤ የለበሰው ደህና ልብስ ነው። አረጋገጡ ግን ሲሄድ እንደ ደህና ሰው አልነበረም። እንደ ሰከረ ሰው ጥቂት ጥቂት ወልገድ ወልገድ ይል ነበር። እንደዚያውም እየተወናከረ እኔ ዘንድ እንደ ደረሰ ወደኔ ቀረብ ቦሎ፤ አርጀት ያለ ባርኔጣ መሳይ አድርጎ ነበር፤ ያንን አውልቆ ዘቅዝቆ ይዞ እኔን እየተመለከተ ቆመ። ምን መሆኑ ነው በማለት ጥቂት ግር ብሎኝ ከተመለከትኩት በዃላ ባኳሆኑ ሁሉ የገንዘብ መለመን አይነት መሆኑን የሚያሳይ ስለሆነ ነገሩ ገባኝ። ምንም ቃል ግን አልተናገረም። እኔም አሳቡን ስለተረዳሁት፤ ቶሎ ብዬ ፖርት ምኔዬን ከኪሴ አውጥቼ ጥቂት ፍራንኮች ሰጠሁት፤ እጅግ ደስ አለው፤ የሰጠሁትም እሱ ይሰጠኛል ብሎ ካሰበው በላይ ይመስለኛል። ‘ወንድም ሆይ፤ ወንድም ሆይ፤ አመሰግንህአለሁ በስጥወታህ። ይኸው እህል ከቀመስኩ ሶስተኛ ቀኔ ነው’ ብሎ ተናገረኝ። እኔም በምን ምክንያት አልኩት፤ ‘በማጣት፤ በድህነት’ አለኝ። በጣም አዘንኩ። ሲናገረኝም በደከመ ቃል ነበር እንጂ የብርታት አልነበረውም፤ ለካም እንዲያ ሲሄድ ሲወላገድ የነበረው በችጋሩ ድካም ኖሯል።…
“እሱ ከሄደ በዃላ በዚሁ ሰው ምክንያት አሳብ በሰውነቴ ገብቶ፤ በሰው ኑሮ አኳሆን በጣም አእምሮዬ እየታወከና እየተበሳጨ ብዙ ነገር አወጣ አወርድ ነበር። ያውሮፓውያንን የሥልጣኔ ማደግ ስሰማ እንደዚህ የእለት ምግቡንና የዓመት ልብሱን የሚያጣ፤ በጣም ድሃ ሰው የሚገኝ አይመስለኝም ነበርና። ደግሞም…የጌቶቹ የቅምጥልነት ኑሮ የት ላይ እንደወጣና ከፍ እንዳለ በማየቴ፤ ይህንንም ሰው በድንገት በማግኘቴ ሌሎችም ብዙ እንደሱ ያሉ መኖራቸውን ስለተረዳሁ አሳቤ እያደር ደግሞ በጣም ተነክቶ ነበር። የሠው ህይወት አንዱም እንዲህ፤ ሌላውም እንዲያ ሆኖ በመኖሩ፤ ይልቁንም የሠው ዕውቀት ከፍ አለ በተባለበት አገር አስገረመኝ።…በአውሮፓ… እንደተመለከትኩት እጅግ የጭካኔ ነገር ሞልቷል። ገንዘብም ከሰው ይልቅ የተወደደና የተከበረ ነው።” በማለት አስፍረዋል።
ይህ የራስ እምሩ ትዝብታዊ ግምገማ ፓሪስ በገቡ ሁለት ሳምንታት ውስጥ የሆነ ነው። እምሩ ሃይለ ሥላሴን የፓሪስ ሥልጣኔ አነሁልሎ በሰው ልጆች እለታዊ ህይወት ውስጥ ያለውን አድሎአዊ አስተዳደር ከማየትና ከመረዳት አላገዳቸውም።
ለመሆኑ ዛሬ በሰለጠነው ዓለም ውስጥ የምንኖር ኢትዮጵያውያን ወደ እነዚህ ሀገራት በገባን ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የነበረን አስተውሎትና ግንዛቤ ምን ይመስል ነበር? መልሱን ለእያንዳንዳችን ልቦና እተዋለሁ።
እምሩ ከኤሮፓ ህክምና እንደተመለሱ አፄ ሃይለሥላሴ በጎጃም ውስጥ የተነሳው አመፅና ጃውሳነት/ሽፍትነት/ ያሰጋቸው በመሆኑ ከወሎ አስተዳዳሪነታቸው አንስተው ወደ ጎጃም እንዲዛወሩ አድርገዋቸው ነበር።
የጎጃሙን አመፅ ምክንያትና መዘዙን እንደምንስ እንደተረጋጋ እምሩ በዝርዝር ፅፈውታል፤ የመፅሀፉን አንባቢያን ከሚጠብቁት የቤት ሥራዎች አንዱ ይሆናል።
ካየሁት ከማስታውሰው ስለ ኢትዮጵያና ጣሊያን ጦርነት በስፋት ያወጋል። የኢትዮጵያንና የጣሊያንን ጦርነት መነሾና ኢትዮጵያም ጦርነቱ እንዳይነሳ ያደረገቻቸውን ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጥረቶች አብራርተዋል፤ እምሩ። ለምሳሌ የጣሊያንን የጠብ አጫሪነት አስመልክቶ አፄ ሃይለሥላሴ ፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ተክለማርያምን ወደ ሶሲቴ ደ ናሲዮን በመላክ ሀገራችን አቋሟን በይፋ ለመንግስታቱ መሪዎች እንድታሳውቅ ተደርጎ ነበር፤ ሲሉ ይገልፁና ሆኖም የጣሊያን መንግሥት ተወካይ ባሮን አልኮዚ ፊታውራሪ ተክለሃዋርያት የኢትዮጵያን አቋም ለጉባኤው በሚናገሩበት ወቅት የኢትዮጵያን አቋምና አቤቱታ አንሰማም በማለት ከጉባኤው ተነስቶ እየወጣ እንደሚያስቸግር እንሰማ ነበር በማለት ስለወቅቱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ገልጠዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የጦርነት ክተት አዋጅ ባወጀበት ወቅት እምሩ ጎጃም ነበሩ። በዚህ ሰፊ የጦርነት ትረካ እምሩ የኢትዮጵያን ጦር አቋምና የሞራል ብቃትም ፍንትው አድርገው አሳይተዋል። አርበኛው እምሩ ሃይለ ሥላሴ በፋሽስት ጣሊያን እጅ ወድቀው ወደ ፓንዛ ጣሊያን ደሴት እስከተጋዙበት ድረስ በጦርነቱ እሳተ ገሞራ መኻል ነበሩና ታሪኩ ስሜትን ይቆነጥጣል፤ ህሊናን ይሞግታል።
በጎጃም፤ በጎንደር፤ በወሎ፤ በትግራይ፤ በሸዋ፤ በጅማ፤ በወለጋ በኢሊባቡር እየተዘዋወሩ ከፋሽስት ጦር ጋር የተደረገውን ትንቅንቅ፤ የጦራችንንም ጀግንነት ሆነ ፍርሃት አብራርተው ፅፈዋል። የሆለታ የጦር አካዳሚ ወጣቶችን አስደናቂ የጀግንነት የጦር ውሎና አሳዛኝ ገጠመኞችንም በየፈርጁ አስቀምጠዋል። የጠላትን አረመኔያዊ የአየር ጥቃትም ገልጠዋል፤ ለአብነት የሚከተለውን ያስተውሏል፤
“…ጠላት ያደረገው ያይሮፕላን አደጋ ካጠፋው ጥፋት ይልቅ ያመጣው ድምጥ፤ የቦንቡ አወዳደቅ ጩኸት ትልቅ ግርማ ስለነበረው፤ ከዚያም ቀን በፊት ከኔ ጋር የነበረው ሠራዊት እንደዚህ ያለውን ሁኔታ ማየቱ መጀመሪያ ጊዜ ነበርና አለልክ አስደንግጦት አሸብሮት ነበር። ይልቁንም በተተኮሰው መከላከያችን ጥይት ሁሉ አንድ እንኳን አይሮፕላን ስላልወደቀ ተስፋ መቁረጥ ይዞ አሳቡ ሁሉ መበለሻሸት ጀመረ።…
“በየቀኑ እየመጣ የሚጥለው ያይሮፕላን ቦንብ አደጋ ምንም ቀላል ቢሆን ያደረገው አደጋ በህዝቡና በሠራዊቱ ላይ ትልቅ የመጨነቅ አሳብ ፈጥሮበት፤ ድምጡ ገና ከሩቅ ሲሰማ ይታወክ ነበር” ይላሉ አርበኛውና የጦር አዛዡ እምሩ የፋሽስት ቦንብ ጣይ አይሮፕላኖች በጦራችንና በህዝቡ ላይ ያሳደሩትን መጠን የለሽ አፍራሽ ስነ ልቡናዊ ተፅዕኖ ሲገልጡ።
ፋሽስት ጣሊያን በመላው ዓለም ታግዶ የነበረውን የመርዝ ጋዝ በጦራችንና በህዝባችን ላይ ደጋግሞ ማዝነሙንና ይህም ያስከተለውን አካላዊና መንፈሳዊ ጥፋት፤ በአይናቸው ያዩትን ለትውልድ ታሪክነት አስቀምጠውታል።
አምስት አመታት በዘለቀው የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት በጦርነቱ መጀመሪያ ወራት ቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ ከሀገር መውጣታቸውን አስመልክተው ሲፅፉ፤
“…የጅቡቲ እራዲዮ የጃንሆይንና የቤተሰቦቻቸውን ጅቡቲ መድረስ ወደ አውሮፓ ሲያስተላልፍ ሰማን።…
“የጃንሆይም እጠላት እጅ ሳይወድቁ መሄድ፤ ምንም አቅማችን ከመርዛቸው ጋር መታገል አቅቶን ብንሸነፍም፤ የተሰራብንንም ግፍ ለማስታወሱና ለኢትዮጵያ ለቀሪው ጉዳይዋም ላለም መንግሥታት ለማስታወሱ እንኳን ቢሆን፤ የመሄዳቸው ነገር ደስ አሰኝቶን ነበር።
“በዚያን ጊዜ ባገር ውስጥም እየተዘዋወሩ ቢቆዩ፤ ምንም የሚጠቅም ነገር የሚሰራም አልነበረም።” ብለዋል።
መደምደሚያ
ካየሁት ከማስታውሰው የሚያበቃው የተፋፋመው የጦርነት ፍልሚያ ውስጥ በድንገት ነው። የዚህን ውጊያ መጨረሻ ወይም ከጦርነቱ በዃላ ስለተከተለው ሁኔታና እምሩም በጠላት እጅ ለመውደቅ ያበቃቸውን አጋጣሚ አይገልፅም።
ፋሽስት ጣሊያንም እንደምን አድርጎ ወደ ፓንዛ ደሴት እንዳጓጓዛቸው፤ በፓንዛ ስለነበረው ህይወታቸው ወይም ከግዞት ሲለቀቁም ሆነ ከዛ ወዲህ ስለነበረው የራስ እምሩ ህይወት ካየሁት ከማስታውሰው አያወጋም።
ይህም በመሆኑ መፅሀፉን አንብበን ስንጨርስ የልዑል ራስ እምሩን ሙሉዕ የህይወት ታሪክ የማወቅ ጥማት ያቃጥለናል። የዚህ ቅኝት አቅራቢ የራስ እምሩን አጠቃላይ ህይወት /ኦቶባዮግራፊ/ የሚተርክ መፅሀፍ አላጋጠመውም። መኖሩንም አልሰማም። የምታውቁ ካላችሁ አሳውቁን። እንዲህ ያለ መፅሀፍ ከሌለም የታሪክ ምሁራኖቻችን አዘጋጅተው ቢያቀርቡ ለትውልድና ለሀገራችን ባለውለታ መሆናቸው ይሆናልና በብርቱ ሊታሰብበትና ዕውንም ሊሆን ይገባዋል ብለን እናምናለን።
ካየሁት ከማስታውሰውን ለትውልድና ለታሪክ እንዲበቃ ላደረጉት የልዑል ራስ እምሩ ሃይለ ሥላሴ የልጅ ልጆችና እንዲሁም መፅሀፉ ምሁራዊ የመተዋወቂያ ማብራሪያን አካትቶ በቀረበልን መልክ በማሰናዳት ላተመው ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕረስ ምስጋና ይድረሳቸው። (የሽፋን ፎቶ: ECADF)
ሐምሌ 2009 ዓ/ም (ጁላይ 2017)
ሲድኒ አውስትራሊያ
mmtessema@gmail.com
መስፍን ማሞ ተሰማ
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Sahlu Mikael says
ውደ ጉልጉልና አንባቢዎቻቸው፤
በዚህ አዳፍኔ የሚባለው መጸሃፋቸው ላይ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ስለራስ እምሩ ከስባቺ የገለበጡትን በሚመለከት ለራስ እምሩ ቤተሰብ የሚከተለውን መልስ ሰጥተዋል። የተሰጠን መልስ በአማርኛ ሲሆን ከነእንግሊዝኛ ትርጉሙ ከዚህ በታች አሰፍረዋለሁኝ::
የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም መልስ
ባዳፍኔ መጽሃፌ ላይ ያወጣሁት በጣሊያን መንግስት ይከፈላቸው የነበሩ ባላባቶች ዝርዝር ከአልቤርቶ ስባኪ የተገኘውን የክፍያ መዝገብ ዝርዝር ነው። ራስ እምሩ የስባኪ ዝርዝር ውስጥ በርግጥ አሉበት። ራስ እምሩ ይከፈላቸው የነበረው ግን እንደሌሎቹ ለጣሊያን በማደራቸው ሳይሆን የእስራት ክፍያ እንደነበረ አውቃለሁ። ይሄን ሳልጠቅስ ቀርቼ ከሆነ ስህተት ነው። ራስ እምሩን ከልጅ ልጆቻቸውም በላይ በቅርብ የማውቃቸው ይመስለኛል። የማከብራቸው እና የምግባባቸው ሰው ነበሩ። እውነተኛ አርበኛ እንደነበሩም አውቃለሁ።
ENGLISH TRANSLATION
The list of names of noblemen who were paid by the Italians, which I listed in my book Adaphne, was obtained from Alberto Sbacchi who listed all such payments. Ras Imru is in this list from Sbacchi. However I know that in the case of Ras Imru, unlike the rest, the payments made were not for his collaboration but rather for his imprisonment. If I failed to mention this it is a mistake. I believe I know Ras Imru even better than his grandchildren do. He was a man for whom I have great respect, and whom I knew very well. I also know that he was a true patriot.
Editor says
Dear Sahlu Mikael,
Many thanks for the update.
Regards,
Editor
Wogene says
ጎልጉል ለፈጸመው ስሕተት ይቅርታ መጠየቁ ያስከብረዋል። ያስመሰግነዋል።
የጎልጉልን መልካም ምሳሌ በመከተል፤ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምም ልዑል ራስ እምሩንንና ቤተሰባቸውን እንዲሁም ወዳጆቻቸውን ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል። የርሳቸውን የተሳሳተ ጽሑፍ መሰረት በማድረግ “ምጽአተ ዐማራ” በተሰኘ አርእስት ሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት ልዑል ራስ እምሩን ጥላሸት ስለ ቀባ፤ ይቅርታ መጠየቅ ይገባዋል። አለበለዚያ በሰማይም በምድርም የሚያስጠይቅ ጉዳይ ይሆናል!