“በአርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም ስም በጎፈንድሚ የተሰበሰበውን 73 ሺህ 9 መቶ ዶላር ወደ አካውንት ለማስገባት ፈቃደኛ አይደለሁም። ምክኒያቱም በኮሚቴው እምነት የለኝም” አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ።
“በአርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም ስም በጎ ፈንድሚም ሆነ በማናቸውም መልኩ የተሰበሰበው ገንዘብ በስሙ ወደተከፈተው የባንክ አካውንት መግባት አለበት” የአርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም የህክምና ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ።
ይህ እሰጣ አገባ የተካሄደው ቅዳሜ ጥቅምት 24 በአፍሮዳይት ሆቴል የአርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም የህክምና ገቢ ለማሰባሰብ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው ኮሚቴ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
ኮሚቴው ለሁለት የተከፈለበትን ጉዳይ አንስቶ ባቀረበው ሪፖርት ላይ እንደገለጸው በአርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም ስም የተሰበሰበው ገንዘብ ጉዳይን አስመልክቶ የተጓዘባቸውን ርቀቶች ዘግቧል። ከአርቲስት ፍቃዱ የህክምና ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ አማካኝነት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተው አካውንት ላይ በአሁኑ ወቅት 1,200,895.69 (አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ ስምንት መቶ ከስልሳ ዘጠኝ ሳንቲም) ብር እንደሚገኝ ገልጸው ቀሪውን በጎፈንድሚ የተሰበሰበውን 73,900 ዶላር ወደ አካውንት እንዲያስገባ ለቴድሮስ ተሾመ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ቢያቀርቡም ለመቀበል እንዳልቻለና በኮሚቴው አባላት ላይ እምነት የለኝም በማለቱ ልዩነት እንደተፈጠረ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ጥቅምት 23 ቀን 2011 ዓ.ም በጊዮን ሆቴል ተሰብስቦ የወሰነውን ቃለ ጉባኤ በንባብ አስደምጧል። ይህንን አስመልክቶም ምላሽ የሰጠው አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ “ህዝብ ገንዘቡን የሰጠኝ የእኔን ስም አይቶ ነው። በአርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም ስም የተሰበሰበውን ገንዘብ በኮሚቴው የክራይሲስ ማኔጅመንት ችግር ምክንያት እምነት ስለሌለኝ ገንዘቡን ወደ ተባለው አካውንት ገንዘቡን አላስገባሁም። ወደፊትም በዚህ ገንዘብ ላይ ሙሉ ኃላፊነቱን የምወስደውም ሆነ እየወስድኩ ያለሁት እኔ ነኝ። ጠበቃዬም ገንዘቡን ገቢ እንዳላደርግ አማክሮኛል። ለዚህም ለህሊናዬም ሆነ ለፈጣሪ ታማኝ በመሆን ገንዘቡን ህጋዊ ወራሽ ይሆናሉ ብዬ ለማስባቸው ቤተሰቦቹ ጥቅምና ለሀውልቱ ማሰሪያ እንዲሆን እየተንቀሳቀስን ነው” ብሏል።
ሌሎች የኮሚቴ አባላት ደግሞ በአጠቃላይ የተሰበሰበውን ገንዘብ ወደ አንድ ቋት እንዲገባና ፍርድ ቤት የሚያሳውቃቸውን ህጋዊ ወራሾች መጠበቅ አለበት የሚል አቋም ይዘዋል።
ለአርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም ስም ከህዝብ የተሰበሰበው ገንዘብ መጨረሻ ምን ይሆን? አሁንም ምላሽ የለውም። በአርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም ስም በተሰበሰበው ገንዘብ ላይ የተነሳው ንትርክ ከዚህ በኋም የጤና እክል ለሚያገጥማቸው የኪነጥበብ ባለሙያዎች ህዝብ በአግባቡ እንዳያግዝ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳርፍ ስጋት አጭሯል።
(ዘገባ፤ ጴጥሮስ አሸናፊ)
Leave a Reply