አትሌት ፈይሣ ሌሊሣ ዛሬ በፌሰቡክ ከጋቢና ቪኦኤ ጋር የቀጥታ ውይይት አካሂዷል፡፡ ስላሳ ደቂቃ አካባቢ በፈጀው ቆይታው ከፕሮግራሙ ተከታታዮች ለቀረበለት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ሕወሃት ደንቁሯል እንጂ ከዚህ በላይ መልዕክት አያስፈልገውም ነበር፡፡
ዜግነቱን ለመቀየር ሃሳብ እንደሌለውና ራሱን ጀግና ብሎ እንደማይቆጥር የተናገረው ፈይሣ ለትግራይ ተወላጆች፣ ትግራዮችን በትግሬነታቸው ለሚጠሉ፣ ለትግራይ ወጣቶች፣ በሥልጣን ለሚገኙት ግፈኛ የህወሃት ባለሥልጣናት፣ ለነ ኃይሌ ገ/ሥላሴና መሰል አንጋፋ አትሌቶች፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለወጣቶች፣ … እስኪበቃው ተናግሯል፡፡ የሰላም ታጋይና ዕርቅ ወዳድ የሆነው ፈይሣ ስለ ዕርቅም በሚገባው ሁኔታ አስረድቷል፡፡
በአማርኛ ያደረገውን ሙሉውን ቃለምልልስ እዚህ ላይ መመልከት ይቻላል፡፡
በአፋን ኦሮሞ ያደረገው ቃለምልልስ እዚህ ላይ ይገኛል፡፡
ከተናገራቸው በጥቂቱ፤
“ሰው በጅምላ እየተገደለ፣ እየታሰረ ነው፤ ይህንን አይቼ ነው የተቃወምኩት”
“ለሕዝብ ብዬ ነው ተቃውሞ ሰማሁት፤ ለራሴ ጥቅም አይደለም፤ ጥሩ ኑሮ አለኝ፤ …”
“ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን ነው ምኞቴ”
“ይህ ሥርዓት ተቀይሮ ለአገራችን ብሮጥ ደስ ይለኛል እንጂ ለየትም አገር መሮጥ አልፈልግም፤ ዜግነቴን አልቀይርም”
“አንድ ቀን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ እንደምሮጥ ነው ተስፋ የማደርገው”
“ሕዝቡ እኔን አይቶ መታረቅ አለበት”
“ጀግንነት አይሰማኝም፤ ጀግና አይደለሁም፤ የዜግነት ግዴታዬን ነው የተወጣሁት”
ለነኃይሌ ገ/ሥላሴ፤
“እነኃይሌ … ስለ ሪዮ ሲነጋገሩ ነበር፤ … አሁን የምንነጋገረውና የምናስበው ስለሜዳሊያ አይደለም፤ … ስለ አገራችን ስለ ህዝባችን ለምን አይሰማንም”
“ሕዝብ እየተገደለ፣ እየሞተ እንዴት ስለ ሕዝብ አናስብም”
“እናንተ (አንጋፋ አትሌቶች) ሕዝብንና መንግሥትን ማገናኘት ትችላላችሁ”
ለህወሃት ኃላፊዎች፤
“ብዙ ሃብታም መሆን ይጎዳል፤ ለህዝባችሁ አስቡ፤ ለራሳችሁ ጥቅም ብላችሁ አገራችንን ከማፍረስ ብትቆጠቡ ደስ ይለኛል”
ለትግራይ ተወላጆች፤
“ከኦሮሞ፣ ከአማራ፣ ከጋምቤላ ሕዝብ ጋር ሆነው ይህንን ሥርዓት መቃወም አለባቸው፤ ሕዝቡን መደገፍ አለባቸው”
በአጠቃላይ፤
“የአንድ ብሔር የበላይነት (የትግራይ) አለ፤ግን ብዙም አይደለም፤ የተወሰኑ ሰዎች ናቸው፤ ትግሬ ሆኖ ደሃ አለ – የሚለምኑ ትግሬዎች አይቻለሁ”
“የኢትዮጵያ ሕዝብ በትግሬ ቅር ብሎታል”
“እኔ ትግሬ አልጠላም፤ … ጓደኞቼም አሉ፤ … ትግሬዎችን ግን የሚጠሉ አሉ፤ የሚሳደቡ አሉ፤ (ይህንን) ከማድረግ እንዲቆጠቡ ልንግራቸው እፈልጋለሁ”
“እኛ አንድነት ነው የምንፈልገው፤ ይህ መንግሥት ይወድቃል፤ ስለዚህ እነርሱ ሰዉን እንዳያስከፉ”
“(ወጣቶች) በሰላማዊ መንገድ ትግል መቀጠል አለባቸው፤ ሞትም ቢሆን ለትውልድ ነጻነት ሰጥቶ መሞት ነው፡፡”
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Leave a Reply