* “ወደ ኢትዮጵያ ከተመለስኩ ሊገድሉኝ ይችላሉ” ፋይሣ ሊሊሣ
በሪዮ ኦሎምፒክ በማራቶን ሁለተኛ የወጣው ፋይሣ ሊሊሣ “ወደ ኢትዮጵያ ከተመለስኩ ሊገድሉኝ ይችላሉ” በማለት የህወሃትን ጨካኝነት ለዓለም ገለጸ፡፡ የፋይሳ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሁሉ ሊደርሱለት እንደሚገባ ተነገረ፡፡ አትሌቱን “አሸባሪና ተላላኪ” ሲል ኦህዴድ ኮንኖታል፡፡
የወርቅ ሜዳሊያ ከወሰደው ኬኒያዊ በላቀ ሁኔታ የዓለምአቀፍ ሚዲያን ትኩረት የሳበው ፋይሳ እዚያው ሪዮ ብራዚል በሰጠው ቃለምልልስ የኦሮሞ ተቃውሞ የሚያሳመላክተውን እጁን ከአናቱ በላይ በማጣመር ሳየበትን ምክንያት ገልጾዋል፡፡ “ተቃውሞዬን የገለጽኩት ለሕዝቤ ነው፤ ዘመዶቼ እስር ቤት ናቸው፤ እስር ቤት ሄጄ ከዘመዶቼ ጋር መገናኘት፣ እነርሱን መጠየቅ እፈራለሁ፤ ካወራህ ይገድሉሃል፤ ስለንደዚህ ዓይነት ነገር ማውራት በጣም አደገኛ ነው፤ (እዚያ አገር) ነጻነት የሚኖርህ መንግሥትን ከደገፍህ ብቻ ነው፤ ይህንን ካላደረግህ መሥራት አትችልም፤ በጣም መጥፎ መንግሥት ነው” ብሏል፡፡
በድርጊቱ አምኖበት እንዳደረገ በመግለጽ ሲናገር “የኢትዮጵያ መንግሥት ሕዝቤን እየገደለ ነው፤ እኔ ከኦሮሞ ጎሣ ነኝ፤ ስለዚህ ለሕዝቤ እጄን አንስቻለሁ” በማለት ተናግሯል፡፡ “አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ … ይህንን መንግሥት ይደግፋሉ፤ እነዚህ መንግሥታት በሚሰጡት ዕርዳታ የጦር መሣሪያ እየገዛ ሕዝቡን ይፈጃል” ብሏል፡፡
ፋይሣ እሁድ ማምሻው ላይ ከኢሣት ጋር ባደረገው አጭር ቃለምልልስ “አስቤበት ያደረኩት ነው፤ ብሞትም አይቆጨኝም” ያለ ሲሆን የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግምባር በግፍ ስለሚገዛት ኢትዮጵያና ሕዝቧ “የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ላይ ተረባርቦ ይህንን ሥርዓት ሊያስወግደው ይገባል” በማለት መልዕክቱን አሰምቷል፡፡
“(አገር ቤት ብሄድ) ይገድሉኛል፤ ወይም ያስሩኛል፤ ወይም እዚያው አየር ማረፊያ ስደርስ ያግዱኛል” በማለት ፍርሃቱን የተናገረው ፋይሣ ሊሊሣ ወደ ሌላ አገር ለመሄድ እንደሚፈልግ በግልጽ ተናግሯል፡፡
በዓለምአቀፍ የፖለቲካ መድረክ እየከሰረ የመጣው ህወሃት በስፖርቱ መስክ በተለይም አገር ውስጥ በቀጥታ ስርጭት እየተላለፈ በዓለምዙሪያ ፋይሣ ያሳየው ተቃውሞ ዕርቃኑን አውጥቶታል፡፡ ከዚህ አንጻር የሥርዓቱ ደጋፊዎች በማኅበራዊ ገጾች ላይ ፋይሣን ወደ አገርቤት መመለስ ይገባል፤ ሕገመንግሥታዊ መብቱን ነው የተጠቀመው፤ የሚያስፈልገው ርብርብ ተደርጎ የኦሎምፒኩ ጀግና ወደ አገር እንዲመለስ በማለት የህወሃትን ዕርቃን ለመሸፈን ቅስቀሳ ጀምረዋል፡፡ ተመሳሳይ ተቃውሞ ያሳዩ እስከ 1ሺህ የሚጠጉ ኦሮሞዎች በጭካኔ እየገደሉ፤ እነ በቀለ ገርባን በግፍ አስረው እያሰቃዩ ፋይሳን ወደ አገርን ና ማለት የማያስቅ ቀልድ ነው በማለት አስተያየት ሰጪዎች ውድቅ አድርገውታል፡፡
የህወሃት ውርደት ያንገበገባቸው በሌላ መልኩ የአትሌቱን ድርጊት በማውገዝ ሜዳሊያው ሊነጠቅ ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ እኤአ 1968 በአሜሪካ ጥቁሮች ላይ የሚደርሰውን ግፍ በኦሎምፒክ የሚዳሊያ ሥነሥርዓት ላይ ያሳዩትን ቶሚ ስሚዝና ጆን ካርሎስን ሲጠቅሱ ተሰምተዋል፡፡ አትሌቶቹ በ200ሜትር 1ኛ እና 3ና ከወጡ በኋላ ሜዳሊያው በሚሰጥበት ጊዜ “የጥቁር ኃይል” የሚባለውን እጅን በጡጫ መልክ የመጨበት ምልክት፣ የጥቁሮችን ድህነት ለማሳየት ያለጫማ በመሆን እንዲሁም ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ ይገደሉ የነበሩትን ጥቁሮችን ለማመላከት ጨሌ አድገው ታይተዋል፡፡ የአሜሪካ የሕዝብ መዝሙር ሲዘመር አንገታቸውን በማቀርቀር በዝምታ ጨርሰዋል፡፡ በዚህ ድርጊታቸው የአለምዓቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሜዳሊያቸውን እንደሚልሱ አድርጓል፡፡ ከዘመናት በኋላ በአሜሪካ ውስጥ ጀግኖች ተብለው በተለያዩ ቦታዎች ሃውልቶች ቆመውላቸዋል፡፡
በሌላ በኩል የፋይሳ የወደፊት ሁኔታ ያሳሰባቸው አሁን ባለበት ቦታ በቶሎ ድጋፍ ሊደረግለት በማለት የድረሱለት ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡ በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውን የሕግ ባለሙያዎች፣ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች፣ ያገባናል የሚሉ ሁሉ ፋይሣን እንዲታደጉ፣ ሕጋዊ መብቱ እንዲጠበቅለትና ወደ ሦስተኛ አገር መሄድ የሚችልበትን መንገድ እንዲመቻችለት እንዲረዱት ተማጽኖዎች እየቀረቡ ነው፡፡ በሪዮ የዓለምአቀፉን ኦሎምፒክ ኮሚቴን እንዲወተውቱ፤ ጥገኝነት ሊሰጡ የሚችሉ መንግሥታትን እንዲያማክሩ፣ እርሱም ምን ማድረግ እንደሚገባው አስፈላጊው የምክር አገልግሎት እንዲሰጠው ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ በጥብቅ አሳስበዋል፡፡ በአረመኔው ህወሃት ቁጥጥር በምትገኘው ኢትዮጵያ መመለሱ ለበቀል እንደሚዳርገው ያላቸውን ፍርሃት ጨምረው ገልጸዋል፡፡
እሁድ ማምሻው ላይ ፋይሳን በገንዘብ ለመርዳት ድረገጽ ተከፍቷል፡፡ Go fund me በተባለው በዚህ ድረገጽ ላይ $40ሺህ ዶላር ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ $28,150 ዶላር ተሰብስቧል፡፡ ለመርዳት የሚፈልጉ ሁሉ ይህንን በመጫን ወደ ድረገጹ መድረስ ይችላሉ፡፡
በፋይሣ የተቃውሞ ድርጊት ያስቆጣው ኦህዴድ ከህወሃት በተሰጠው ትዕዛዝ አትሌቱን ተላላኪና አሸባሪ ሲል ድርጊቱን በማውገዝ በፌስቡክ ገጹ ላይ ኮንኖታል፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Leave a Reply