* በሁሉም ባንኮች ያለው ሒሳብ ታገደ
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ አራት አመራሮች በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሌሎች ተያያዝ ጉዳዮች ክስ ተመሰረተባቸው። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በሁሉም ባንኮች ያለው ሒሳብ ታገደ።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፤ ዐቃቤ ነዋይዋ ዶ/ር ኤደን አሸናፊ፣ ዋና ፀሐፊ አቶ ዳዊት አስፋው እና ምክትል ፀሐፊ አቶ ገዛኸኝ ወልዴም ከተከሳሾቹ መካከል ነው።
ክሱን የመሰረቱት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ_ገብረሥላሴ፣ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ናቸው። በከሳሾቹ ጠበቆች በኩል ክሱ የቀረበለት የፌደራል አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት አራድ ምድብ ችሎት ኮሚቴው ፤ ግንቦት 5 እና ሰኔ 4፤ 2016 ዓ.ም. ያካሄዳቸው ጠቅላላ ጉባኤዎች እና ውሳኔዎች እንዲታገዱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የከሳሽ ጠበቃ የሆኑት አቶ አያሌው ቢታኔ “ከፓሪስ ኦሊምፒክ ጋር በተያያዘ [ተከሳሾቹ] ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ተሰማርተዋል ብለን እንጠረጥራለን። የወንጀል ተጠያቂነቱ እንዳለ ሆኖ ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ በመጠቀም ኦሊምፒክ ኮሚቴውን [በዝብዘዋል]” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ጠበቃው አክለው “ደብዳቤ ስለተጻፈ ብቻ የማይመለከተው ሰው [ወደ ፓሪስ] ይሄድ ነበር” ብለዋል።
የሰው ዝውውር ተብሎ በደምሳሳው የተጠቀሰው ክስ በተለይ የኦሎምፒክ ውድድሮችን ምክንያት በማድረግ የሚመጣውን ቪዛ ከአገር ለመውጫ ከመሸጥ ጀምሮ ለሌሎች ማስተላለፍን የሚጠቀልል ነው።
የሕገወጥ የሰው ዝውውር በዓለምአቀፍ ሕግ ጭምር የሚያስከስስ ወንጀል በመሆኑ እንደተባለው ክሱ በማስረጃ ከተረጋገጠ በዚህ ሥራ ላይ የተሳተፉ በሙሉ በዓለምአቀፉ ሕግ ይቀጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ የተላለፉ ውሳኔዎችና ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ያካሄደው የኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ምርጫ እንዲታገድ በቀረበው የፍትሐብሔር ክስ መሠረት በፍርድ ቤት ዕግድ ተሰጠ (ሪፖርተር)፡፡
በከሳሾች አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽንና በኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን በቀረበው የፍትሐብሔር ክስ አቤቱታ፣ ክስ የቀረባበቸው፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ (ዶ/ር) አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ፣ ኤደን አሸናፊ (ዶ/ር)፣ አቶ ዳዊት አስፋውና አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ናቸው፡፡
ተከሳሾቹ በዋናነት የቀረበባቸው ክስ የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 154 እና 205 ድንጋጌዎችን በመተላለፍ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ጠቅላላ ጉባዔ በማካሄድ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፋቸውና ሕገወጥ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ምርጫ አካሄደዋል በሚል ነው፡፡
በመሆኑም ተከሳሾች ባደረጉት ሕገወጥ ጠቅላላ ጉባዔ የተላለፉ ውሳኔዎች፣ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ምርጫ እንዲታገድ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም. የክስ አቤቱታ ቀርቧል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በሁሉም ንግድ ባንኮች ያለው ተቀማጭ ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ ዕግድ እንዲሰጥበትም ከሳሾች ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡
የክስ አቤቱታውን የተመለከተው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍትሐብሔር ጊዜ ቀጠሮ ችሎት፣ በከሳሾች የተጠየቀውን ዕግድ ተቀብሎ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በሁሉም ባንኮች ያለው ሒሳብ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ እንዳይንቀሳቀስና ግንቦት 6 እና ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቦርድ ምርጫ ጋር ተያይዞ የተላለፉ ውሳኔዎችም ታግደው እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ክሱ ፍርድ ቤቶች መደበኛ ሥራ ሲጀምሩ የሚንቀሳቀስ መሆኑም ታውቋል፡፡
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply