ክፍለ ጦሩ በሸኔ ላይ እየተወሠደ ያለውን ወታደራዊ እርምጃ ለማጠናከር በጉጂ ዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ሚሊሻዎችን በማሰልጠን የቀጠናውን ሠላምና ፀጥታ በማረጋገጡ ረገድ ውጤታማ ሥራ መሠራቱን አሥታውቋል፡፡
የስልጠናው ዋና አስተባባሪ ሻምበል ባቡ ባላባት እንደገለፁት የፀረ ሽምቅ ግዳጅን በብቃት ከመወጣት ጎን ለጎን የዞኑን የፀጥታ ሀይል ለማጠናከር በርካታ ሚሊሻዎችን የአካል ብቃት የስልት እንዲሁም የተኩስ ልምምድ ሥልጠና በመስጠት ማሥመረቅ ተችሏል፡፡
በአካባቢው በንፁሃን ላይ የሽብር ተግባር ሲፈፅም በቆየው የሸኔ ታጣቂ ቡድን ላይ እየተወሠደ ለሚገኘው የተጠናከረ ዘመቻ ሠልጣኝ የሚሊሻ ሃይሉ እገዛ ከፍተኛ መሆኑንም የሥልጠና አሥተባባሪው ገልፀዋል፡፡
አሰልጣኝ ዋና ሳጅን ዝናው በበኩላቸው እንደገለፁት የሚሊሻ አባላቱን አሠልጥኖ ማሥመረቁ በቀጠናው የሚገኘውን የፀጥታ ሃይል የሚያጠናክር ከመሆኑም ባሻገር ከህዝቡ ጋር ተናቦ የጥፋት ቡድኑን አባላት ለመከታተል እና ለመመንጠር አሥፈላጊነቱ ጉልህ ነው፡፡
በሚሊሻ አባላቱ ምርቃት ላይ አባ ገዳዎች የወረዳ ሽማግሌዎች የተገኙ ሲሆን በዘላቂነት የቀጠናውን ሰላም እና ፀጥታ ለማረጋገጥ ከመከላከያ ሰራዊቱ እና ከክልሉ የፀጥታ ሃይል ጋር በጋራ እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡ (መከላከያ ቴሌግራም፤ እዮብ ሰለሞን፤ ፎቶግራፍ እሱባለው ስሜ)
ከሸኔ ጋር በተያያዘ ዜና የአሸባሪው ሸኔ ቡድን አባል ሆነው ከቡድኑ አመራሮች ጋር በተለያየ የመገናኛ ዘዴ በመገናኘት በአዲስ አበባና ዙሪያ ለሽብር ተግባር ሲንቀሳቀሱ ነበሩ የተባሉ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ÷ ኢፋ መኩሪያ፣ ናስረሰ ያሲን ፣ ገለታ ከተማ፣ ሰኔሳ አበራ፣ ሞሲሳ ቶሎሳ፣ ኢማሚ ደርበው፣ ኢፋት አሕመድ፣ ደበላ አማኑ እና አማንኤል በርኬሳ ናቸው፡፡ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ተጠርጣሪዎቹን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት አቅርቦ ጉዳያቸው ዛሬ ታይቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ሕገመንግሥቱንና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ በማሰብ የሸኔ የሽብር ቡድን አባል ሆነው ከሽብር ቡድኑ አመራሮች ጋር በተለያየ መገናኛ ዘዴ እየተገናኙ ተልዕኮ መቀበላቸውን ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡
በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ እና ዙሪያ በሕዝብ መገኛ ቦታዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ÷ በህቡዕ በመደራጀት በሽብር ቡድኑ ስልጠና በመውሰድ፣ የከተማ እርምጃ ወሳጅ የአባቶርቤ አባላትን እና የተለያዩ የሎጅስቲክ አቅርቦትን በማቅረብ ታኅሣሥ 15 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ እና በዙሪያው የሽብር ተግባር ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ መያዛቸውን አብራርቷል፡፡
በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ÷ ቃላቸውን የመቀበል፣ ፎቶና ዐሻራ የማስነሳት ሥራ ማከናወኑን እንዲሁም በፍርድቤት ትዕዛዝ በመኖሪያ ቤታቸው ብርበራ ማካሔዱን አንስቷል፡፡ በእጃቸው ላይ የተገኘ የሞባይል ስልክን ለምርመራ መላኩንና ከግልና ከመንግስት ባንኮች የገንዘብ ዝውውር ለማጣራት ማስረጃ መጠየቁንም ገልጿል።
መርማሪ ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ማስረጃ ለማምጣት፣ የምስክሮችን ቃል ለመቀበል፣ ተጨማሪ ማስረጃ ለማሰባሰብ ለመቅረብ በወ/መ/ስ/ህ/ቁግር 59/2 መሰረት የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል። ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ወንጀል አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው÷ ማስረጃ ለማሰባሰብ ተብሎ ተጨማሪ ጊዜ ለፖሊስ ሊሰጥ እንደማይገባ እና የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ችሎቱን ጠይቀዋል።
የተወሰኑት ተጠርጣሪዎች ደግሞ በመንግስት መስሪያ ቤት ሠራተኛ መሆናቸውን እና ቋሚ አድራሻ እንዳላቸው፤ በዋስ ቢወጡ ወደ ሌላ ቦታ መሸሽ እንደማይችሉ ጠቁመው ÷ የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።
የሁለቱን ወገን መከራከሪያ ነጥብ የመረመረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የተጠርጣሪዎችን ዋስትና ጥያቄ ለጊዜው በማለፍ ተጨማሪ ምርመራ መደረጉ አስፈላጊ መሆኑን አንስቷል፡፡ በዚህ መሰረትም ፖሊስ ከጠየቀው የ14 ቀን ጊዜ ውስጥ ማስረጃ አሰባስቦ የምስክር ቃል ተቀብሎ እንዲቀርብ የስምንት ቀን የምርመራ ጊዜ መፍቀዱ ተመላክቷል፡፡ (ታሪክ አዱኛ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply