የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤን ያሰናከሉ የህግ አስፈጻሚ አካላት ላይ ፍትሕ ሚኒስቴር ክስ እንዲመሰረት ጠየቀ። በመንግስት መስሪያ ቤቶች ስር የሚተዳደሩ ስብሰባ ቦታዎች እና አዳራሾች ለፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ክፍት እንዲሆኑም ውሳኔ አሳልፏል።
ቦርዱ ይህን ያስታወቀው፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ ያጋጠሙ መስተጓጎሎችን በተመለከተ ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 5፤ 2015 በአዲስ አበባው ሃይሌ ግራንድ ሆቴል በሰጠው መግለጫ ነው። በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ መሰረት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ቢያንስ በሶስት ዓመት አንድ ጊዜ ማካሄድ አለባቸው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን ግዴታቸውን ለመፈጸም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወቅት መስተጓጎል እየገጠማቸው እንደሚገኝ ምርጫ ቦርድ ገልጿል። ባለፈው እሁድ ጠቅላላ ጉባኤውን ሊያካሄድ የነበረው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ፤ ስብሰባውን ሊደርግበት የነበረበት ጋምቤላ ሆቴል ስብሰባውን ማስተናገድ እንደማይችል በመግለጹ ጉባኤውን ሳያካሄድ ቀርቷል።
እናት ፓርቲም በተመሳሳይ መልኩ ከሳምንት በፊት የካቲት 26 ሊያካሄደው የነበረው ጠቅላላ ጉባኤ መስተጓጎሉ ይታወሳል። የፓርቲው ፕሬዝዳንት በዕለቱ በሰጡት መግለጫ “‘ከበላይ አካል በመጣ ትዕዛዝ መሰብሰብ አትችሉም’ መባላቸውን አስታውቀው ነበር። የሁለቱን ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤዎች ለመታዘብ በስፍራው የነበሩ የምርጫ ቦርድ ተወካዮች፤ ክስተቶቹን በቅርበት የተከታተሉ ሲሆን የሚመለከታቸው አካላትንም አነጋግረው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
ባልደራስ ባለፈው ሳምንት ጠርቶት በነበረው ስብሰባ ምክትል ኃላፊው ስብሰባውን ለማካሄድ ወከባ ውስጥ የገቡ ሲሆን ስብሰባው እንዳይካሄድ የከለከለው የበላይ አካል ነው የሚል መረጃ ሲሰራጭ ነበር።
ስብሰባው ሊካሄድበት የነበረው ጋምቤላ ሆቴል በበኩሉ ስብሰባውን የከለከለ የጸጥታ ኃይል የለም፤ ችግሩ ከባልደራስ ነው፤ ሆቴሉ ስብሰባ ለማካሄድ የሥራ ትዕዛዝም ይሁን ክፍያ ያልተቀበለ መሆኑን በጻፈው ደብዳቤ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply