• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ከኢሳያስ አፈወርቂ ቃለ-ምልልስ በስተጀርባ

April 12, 2017 06:15 am by Editor Leave a Comment

ጠንቋይና ፖለቲከኛ የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ። ሁለቱም ተገልጋያቸውን ለማምታታት የትኩረት አቅጣጫ ማስቀየርን ተክነውበታል። ኢሳያስ አፈወርቂ በዚህኛው – የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ – ገለጻቸው ራሳቸውን ሳይቀይሩ ሌላውን ለመቀየር የተነሱ ግብዝ ነው የሆኑት።

ይህ “ቃለ-ምልልስም” አንድ አላማ አለው። አላማውን ለማወቅ ቃላቶችን መሰንጠቅም አያስፈልግም። ግልጽ ነው። ‘ብዙ ስላልተሰራበት’ መልዕክቱ የተጠበቀውን አላማ የመታ አይመስልም። ቃለ-ምልልሱ የተደረገበት ወቅት፣ የተመረጠበት ሰዓት የሚሰጠን ግልጽ የሆነ ግን የተለየ ትርጉም አለ።

ጠያቂዎቹ በሻዕቢያ ላይ የነበራቸው የፖለቲካ አቋም ከመቅጽበት መቀየሩ በራሱ የሂደቱን ግራጫ ምስል ያሳየናል። “ሁሉን ቢናገሩ ሆድ ባዶ ይቀራል” ይላሉ አበው።  እነዚህ ጉዳዮች ውስጥ ገብቶ መላ-ምቶችን መዘርዘሩ አስፈላጊ ባይሆንም (አንዱ መላ ምት ግንቦት ሰባት ከሻእቢያ እየተፋታ ነው የሚለው ነው)፣ ይህንን የፖለቲካ ሂሳብ ለመቀመር ግን ሮኬት ሳይንቲስት መሆን የሚጠበቅ አይደለም።

ነቢያት በቀየሱ ሐዋርያት ገሰገሱ ነውና ነገሩ፣ ዞሮ-ዞሮ ያለፈ ታሪክ ሲደገም ነው የምናየው። ከሻዕቢያ ጋር በፍቅር መውድቁ እጅግ ቀላል እንደሆነ ከበርካቶች አይተነዋል። ከባዱ ነገር አብሮ መቆየቱ እንደሆነም ተገንዝበናል። የሰው ልጅ አንዴ ይሸወዳል። ሁለቴ ለመሸወድ ራስን ማሳመን ግን ብልህነት አይደለም። “ወደ ፊት የምንራመድ ከሆነ ታሪክን መድገም ሳይሆን አዲስ ታሪክ መፍጠር አለብን” ይሉናል ማሀተመ ጋንዲ።

ይህች ጎንበስ-ጎንበስ ታዲያ የቁቤው ትውልድ የአስመራን “ወዳጅነት” ፍለጋ ለመሆንዋ የፖለቲካ አቡጊዳን ለቆጠረ አዲስ አይሆንም። ጋዜጠኛ አርጋው አሽኔ በዋዜማ ራዲዮ የኦሮሞ ወጣቶች ትግል በአስመራ ስለሟሟቅ የተናገረውን ተከትሎ – ከቁቤው ትውልድ ውግዘት ደርሶበታል። ውግዘቱ ባይኖር ነበር ሚደንቀው። ውግዘቱ ወደ ተለመደው የአቤቱታ ፊርማ ላለማደጉም ዋስትና የለም።

ፖለቲካ ተለዋዋጭ ነው በሚል ብሂል ብቻ ተነሳስተን ፖለቲካውን ባልተገራ ፈረስ መጋለብ መሞከር የከፋ አደጋም እንዳለው ሳይረዱት ቀርተው ሊሆን አይችልም። በዲፕሎማሲ ሀ-ሁ “ቋሚ ወዳጅ እና ቋሚ ጠላት የለም” ተብሎ ብቻ የቅርቡን ትዝታ ወዲያ ብለው፣ በብርሃን ፍጥነት የሚጓዙበት ጉዳይም አይደለም። ከነዚህ ሁሉ ቀደም ብለው የሚወራረዱ ሂሳቦች ይኖራሉ። ለመቀበል በመጀመርያ መስጠት ግዴታ ነውና። ኢሳያስ አፈወርቂ ይህንን ሁሉ ለጽድቅ እየሰሩት እንዳልሆነ ሕጻን ልጅም አያጣውም።

ግና የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት የቀረው “ብቸኛው አማራጭ የትጥቅ ትግል ነው” እየተባለ በሚነገርበት በዚህ ወሳኝ ወቅት በጦር ተደራጅተው ለአመታት አስመራ የመሸጉት ኦቦ ዳውድ ኢብሳን እብብታቸው ስር ሸጉጠው፤ ይልቁንም እነ ጃዋር መሃመድ እንደ ሸቀጥ የሚያዞሩትን የ”ኦሮሚያ አብዮት” ወደ አስመራ ለማስገባት መጣራቸው የሚደነቅ ነው። ይህንን ለማድረግ  ቃል መግባታቸው “የፖለቲካ ዝሙት”  ብቻ ብለን የምናልፈው ጉዳይ አይደለም። በኢትዮጵያ የምትካሄደዋ እያንዳንድዋ እንቅስቃሴ የአስመራ ይሁንታ እንዲኖራት የሚደረግ ሸፍጥም አለበት።

***

በኦሮሚያ ሚድያ ኔትወርክ የቀረበው ጉዳይ “ቃለ ምልልስ” ነው? ውይይት ነው? ወይንስ የኢሳያስ አፈወርቂ የአቋም መግለጫ?… የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳቱም ተገቢ ይመስላል። ጥያቄው ከመልሱ ሲረዝም፣ ጥያቄዎች ተጽፈው ቀርበው ሲነበቡ እና ጠያቂዎች ፈራ-ተባ እያሉ፤ አንዳንዴም በፈገግታ ሲናገሩ ከተጠያቂው የተሰጡትን የቤት ስራዎች መስራታቸውን ያሳብቃሉ። በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ቃለ-ምልልስ ራሱን የቻለ ጥበብ እና አካሄድ አለው። ጠያቂው ከተጠያቂው በልጦ ካልተገኘና፣ ባላመነበት ጉዳይ ተጠያቂውን መሞገት ካልቻለ … ነገሩን ቃለ-ምልልስ ነው ልንለው ይከብደናል። ከጠያቂዎቹ (ገረሱ ቱፋ እና ደረጀ ሃዋዝ) የሚሰነዘሩት ጉዳዮች በሙሉ ስለ ኦሮሞ እና በኦሮሚያ የተቃኙ ናቸው። ኢሳያስ አፈወርቂ የሚሰጡት ምላሽ ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ ነው። ሁለቱ አልተጣጣሙም። ፕሬዝዳንቱ የሚጠየቁትን ሳይሆን ማስተላለፍ የፈለጉትን ነገር ነበር የሚናገሩት።

ህዝባዊ አመጹ የሃገሪቱን ፖለቲካ ለወራት እያናወጠው በነበረበት ግዜ፣ ኦቦ ዳውድ ኢብሳ አስመራ ላይ ተኝተዋል። ሃገር ሲደበላለቅ፣ እሳቸው ልክ እንደ ሕጻን ልጅ ተጋድመው ከባድ እንቅልፍ ወስዷቸው ነበር። የሱናሚው ማዕበል ነበር ከዚያ ለ20 ዓመታት ከተኙበት ከባድ እንቅልፍ ቀስቅሶ ያነቃቸው። ከእንቅልፋቸውም ሲነቁ እንዲህ አሉ።

“ሕዝባዊ አመጹን እየመራሁ ያለሁት እኔ ነኝ!”

ይህ አነጋገራቸው ከፌስቡኩ አርበኛ ጃዋር መሃመድ ጋር ገመድ ያጓትታቸው እንጂ ለወያኔ ግን ጃክፖት ነበር የሆነለት። ይህንን ማለታቸው፣ የኦሮሞን ወገን እንዲመታ ለወያኔ ቦንብ አቀበሉት። ያንን ግዙፍ የህዝብ ንቅናቄ የኦነግን ኩታ አልብሰውና በስልቻ ልክ አጥብበው ድባቅ እንዲመታ አደረጉት።

ኢሳያስ አፈወርቂን ገረሱ ቱፋ ስለ አመጹ ጠይቋቸው ሲመልሱ፤ “በዚያ የሱናሚ ማእበል ውስጥ የአንድም ፖለቲካ ድርጀት እጅ የለበትም። የሕዝብ በደል ለሁለት አስርተ አመታት ተጠራቀሞ በመጨረሻ ፈነዳ” ነበር ያሉት።

ይህንን በተናገሩ ግዜ በጉያቸው አንቀላፍቶ ለታሪክ ሽሚያ የነቃው ዳውድ ኢብሳ እጅግ አሳዘነኝ። እጉድጓድዋ ተደብቃ እንደምትቁለጨለጭ ትንሽ አይጥ መሰለኝ። ኢሳያስ አፈወርቂ ስለ ኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር የተናገሩት በዚህ አላበቃም። ሰለ ድርጅቱ በተደጋጋሚ የሚናገሩት “የታሪክ ስህተት” ጉዳይም ያስደምማል። አንደኛው 20ሺ የሚያህል የኦነግ ሰራዊት እሳቸው መርገምት ብለው ለሚጠሩት ወያኔ አስረክበው መፈርጠጣቸው። ይህ ታሪካዊ ስህተት አሁን ውጤቱ እየታየ ስለሆነው ጉዳይ ሲሆን፤  ሁለተኛው ደግሞ የአማራ ሕዝብ ጨቁኗል እየተባለ የሚነገረው ፍጹም ሃሰት እንደሆነ በዚህ ገለጻቸው ማስረገጣቸው ነው። ልብ እንበል። ጠያቂዎቹ ጃዋር መሃመድ ከሚመራው የኦሮሚያ ሜዲያ ኔትወርክ ናቸው።

ኢሳያስ አፈወርቂ “የገዥ ቡድን እንጂ የአማራ ጨቋኝ አልነበረም። ይህ የወያኔ ፈጠራ ነው። ይህ ዘራፊ ቡድን እንዲህ ካላደረገ መቆየት አይችልም” ባይ ናቸው። አማራ የኦሮሞ ጠላት ሆኖ አያውቅም ከሚለው ተነስተው፣ የአማራው ሕዝብ ሲጨቁን ነበር እየተባለ የሚነገረው ብሂል ስህተት እንደሆነ ሲናገሩ ለመጀመርያ ግዜ መሆኑ ነው። ለዚያውም በኦሮሚያ ሜዲያ ኔትወርክ።

ወያኔ ያጎረሳቸውን ሁሉ ሳያላምጡ ጥሬውን ውጠው፣  በትላንት ላይ ለተጠመዱት ሁሉ ይህ ትልቅ መልእክት ይመስላል።

ፕሬዚዳንቱ ይህንን የተናገሩበት ምክንያት ከጀርባ ቢጠናም፣  ምክንያቶች ቢደረደርም – ባይደረደርም፤ መራራው ሃቅ ከአንደበታቸው ወጥቷል። ለማመን እንጂ ላለማመን ምክንያት የሚፈልጉ የሜዲያው መልእክተኞችም በዚህ ጉዳይ ላይ ዝምታን ከመምረጥ ውጭ አማራጭ የነበራቸው አይመስልም። ከጀግናው ጃገማ ኬሎ ይልቅ ጃዋርን ለሚያደንቅ ትውልድ፣  ከአቡነ ጴጥሮስ ይልቅ ለሊበን ዋቆ የሚያጨበጭብ ትውልድ አልሰማ ብሎ እንጂ የታሪክ ምሁራንም የሚነግሩን ይህንን ሃቅ ነው።

በ1991 (እ.ኤ.አ) የሽግግር መንግስቱ ሲመሰረት ኢሳያስ አፈወርቂ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ሲናገሩ፣ ይህንን ተረት-ተረት እዚያው ዩኒቨርሲቲያችሁ ጣሉት ነበር ያሉት። በዚሁ ቃለ-ምልልሳቸውም የምንኮራባቸው ኢትዮጵያ እሴቶች፤ በተለይ ደግሞ የሃገሪቱ የሶስት ሺ ዘመን ታሪክ ተረት-ተረት (ሚት) ነው ይሉናል። ኢትዮጵያ ታሪክ እንደሌላት የሚያሳየውን ማስረጃ ግን አሁንም አላሳዩንም።

ከኢትዮጵያ ተነጥሎ መኖር በሕዝባቸው ላይ ያደረሰው መከራ አሁንም ትምህርት የሰጣቸው አይመስልም። ላለፉት 25 አመታት በባርነት የተያዘውና ለስደት የተዳረገውን የኤርትራ ሕዝብ ችግር ችላ ብለው አሁንም ስለ ኢትዮጵያ ቅኝ ገዥነት ነው የሚናገሩት።

በመላው ኢትዮጵያ የተነሳው ሕዝባዊ አመጽ ውስጥ የኤርትራ እጅ አለበት መባሉ ኢሳያስ አፈወርቂን አስቋቸዋል። ምላሻቸው ባሳቅ ብቻ አላበቃም፤ “ይህንን ባደረግነውና ደስ ባለን ነበር። ግን ሁኔታዎች እና የአቅም ጉዳይ ሆኖ አላደረግነውም” ይላሉ። ካሁን በኋላ ግን እጃችንን አጣጥፈን አንቀመጥም በሚል ቅላጼ በኢትዮጵያ የሚደረገውን የመብት ትግል የመደገፍ ግደታ እንዳለባቸው ተናግረዋል። ይህንንም የሚያደርጉት ለውጡ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኙት እንደሆነ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሚደረገውን የለውጥ ትግል አስመራ በምን መንገድ ለመደገፍ ማቀድዋ ግልጽ ባይሆንም “የትጥቅ ትግሉ” ከትብብሩ ፓኬት ውስጥ ለመውጣቱ ግን ጨረፍ አርገውታል።

የኤርትራ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ለትጥቅ ትግሉ ድጋፍ አስቸጋሪ እንደነበርም ኢሳያስ ሳይናገሩ አለለፉም። የሁኔታዎች አለመምቻቸት እና የአቅም ጉዳይም ድጋፍ እንዳይደረግ አስተዋጻኦ አድርገዋል ይላሉ አይቴ ኢሳያስ አፈወርቂ።

ስርዓቱን በጦር ለመፋለም የወሰኑ ሃይሎች ወደ አስመራ ያመሩት ኤርትራ በኮሪደርነት እንድታገለግላቸው ነበር። ጦርነት ፋይዳ የሌለው መሆኑን ኢሳያስ የሚነግሩን ከሆነ ታዲያ “ካሁን በኋላ ለመርዳት” ያሰቡት ምንድነው? ለጦርነት ካልሆነ ኤርትራ መግባቱ ለምን አስፈለገ?  ሰላማዊው ትግሉም የነሱን ቡራኬ ይሻል ማለት ነው?

ከዚህ ሁሉ የትጥቅ ትግል እና የጦርነት ወሬ በኋላ “ሁኔታዎች አላመቹም”ና፤ “የሽግግር መንግስት” እንደገና እንዲቋቋም ሃሳብ ሰጥተዋል።  “በ1991 ድል ተቀዳጅተናል። ያለምነው ነገር ግን ግቡን አልመታም። 25 ዓመት እንዲሁ ባክኗል፣ አሁን የምመክረው ሁሉም የሚሳተፍበት የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ነው” ብለዋል። አዲዮስ! ግራም ነፈሰ ቀኝ፣ ተከካም ተቦካ ትልቁ ዳቦ ግን እዚህ ላይ ሊጥ ሆነ!

ክንፉ አሰፋ

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Opinions, Politics Tagged With: Left Column

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • “ሚካኤል ችግኝ ነው። … ችግኝ ይተክላል” ቴዲ አፍሮ June 29, 2022 03:30 am
  • “የእኔን ልጆችና የልጅ ልጆች (22ቱንም) የቀበርኩት እኔ ነኝ” አቶ መሀመድ የሱፍ ከምዕራብ ወለጋ June 28, 2022 01:07 pm
  • የገዳ ሥርዓት እና የኦሮሞ ገዢ መደብ June 20, 2022 11:34 pm
  • “የወልቃይትን ጉዳይ ለድርድር የማናቀርበው ቀይ መስመራችን ነው” ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል June 12, 2022 07:09 pm
  • የሰሜን ምዕራብ ዕዝና የአማራ ልዩ ኃይል ተከዜ ክፍለ ጦር ዕውቅናና ሽልማት ተሰጣቸው June 12, 2022 06:21 pm
  • ሀገር በቀል ባህላዊ የግጭት አፈታቶችን በተገቢው በመጠቀም ዘላቂ እርቅና ሰላምን ማምጣት ይቻላል June 12, 2022 05:40 pm
  • የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በገረጂና በቀበና ያስገነባቸውን የመኖሪያ አፓርትመንቶች አስመረቀ June 12, 2022 05:35 pm
  • በኦነግ ሸኔ ፈርሶ የነበረውና ወታደራዊ ጠቀሜታ ያለው ድልድይ ተጠግኖ አገልግሎት መስጠት ጀመረ June 10, 2022 09:13 am
  • ጃዋር በዳውድ ኢብሣ ቀይ መስመር ተሰመረለት June 8, 2022 12:59 pm
  • ወልቃይት: ቢመረንም ለመዋጥና ራሳችንን ለመመልከት እንሞክር June 8, 2022 11:53 am
  • እብድ ይሻለዋል እንጂ አይድንም፤ ሐጂ ጃዋር አሁን ለምን ብቅ አለ? June 8, 2022 05:59 am
  • ሕዝብ ድምፅ የነፈጋቸው “ፓርቲዎች” የሽግግር መንግሥት ይቋቋም አሉ June 7, 2022 01:11 am
  • “አድጌ እንደናንተ መሆን እፈልጋለሁ” June 5, 2022 06:58 pm
  • በሳምንት ለ100 ያህል ሕሙማን አገልግሎት የሚሰጥ የኩላሊት ዕጥበት ማዕከል ሥራ ጀመረ May 30, 2022 02:20 am
  • የጥቁር አንበሳ ዕጩ መኮንኖች (ካዴቶች) ተመረቁ May 29, 2022 04:01 pm
  • “ኢትዮጵያን መንካት አይቻልም!!” በሚል ቁጭት ነው እየሠራን ያለነው May 29, 2022 01:04 pm
  • “ከሞፈርና ቀንበር ወደ ትራክተር” በሚል መርህ ለአማራ ገበሬዎች የግብርና ሜካናይዜሽን ተሰጠ May 29, 2022 02:02 am
  • ኢትዮ 360 “የወያኔ፣ የጁንታ ሚዲያ ነው” – ባለከዘራው ጄኔራል May 27, 2022 02:51 am
  • “እኛ የምናውቀው ነገር የለም፤ የሚያጣሉን ፖለቲከኞች ናቸው” የአማራ ወዳጃቸውን አደራ ቤት የመለሱ የቅማንት ተወላጅ May 27, 2022 01:40 am
  • ትግራይን አገር እናደርጋለን፤ “በውይይት እና በጦርነት” ሁሉንም ጉዳይ እንቋጫለን – የወንበዴው መሪ ደብረጽዮን May 26, 2022 09:18 am
  • “ሁለቱ የምዕራብ ዕዝ ተዋጊ ዶክተሮች” May 26, 2022 08:19 am
  • ወደ ትህነግ ሊተላለፍ የነበረ አምስት ሚሊዮን ብር ከ20 ተጠርጣሪዎች ጋር ተያዘ May 25, 2022 01:57 am
  • የጦርነቱ ስትራቴጂያዊ እውነታዎች May 19, 2022 09:37 am
  • በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን ለማቋቋም የሚውል የ15 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ድጋፍ የዓለም ባንክ May 16, 2022 10:22 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2022 · Goolgule