እነሆ ሰንበት ነበረ።
ምዕመኑ በሚኖርበት ከተማ በምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅድሰት ቤተ ክርስቲያን እንዳለፉት አያሌ ሰንበቶች ሁሉ ባለፈው ሰንበትም ተገኝቷል። ቃሉን ሊሰማ፤ ስለ ቃሉም ለመኖር ብርታትን ሊያገኝ፤ ስለራሱና ስለቤተሰቦቹ፤ ስለ ህዝቦቹና ስለ ሀገሩም ሊፀልይ፤ እጆቹንም ወደ ሰማይ አንስቶ ሊለምን። ማረን ለማለት። እግዚኦታም ለማቅረብ። ከትጉሁና ትሁቱ ካህንም ቃለ ህይወት ሊሰማ። ቃለ ህይወትንም ሊማር።
እነሆም ካህኑ ቅዳሴውንና ፀሎቱን ይመራሉ። ድምፃቸውም በመንፈሳዊ ቅላፄ በመቅደሱ ይሞላል። ዲያቆናቱም ይቀበላሉ። ምዕመናኑም ይደግማሉ። ወይ ተንበርክከውና አንገታቸውን ከመሬት ደፍተው፤ ወይ ቀጥ ብለው በመቆም እጆቻቸውን ወደ ፈጣሪ ዘርግተው።
የካህኑ ድምፅ በፀሎትና በቅዳሴ ዜማ እንዲህ ይላል – አምላካችን ክርስቶስ ሆይ፤ የተጨነቀችይቱን ነፍስ ሁሉ አሳርፍ፤ በሠንሠለት የታሰሩትን፤ በስደትና በምርኮም ያሉትን፤ መሪር በሆነ አገዛዝ የተያዙትን አምላካችን ሆይ በቸርነትህ አድናቸው። አቤቱ ህዝብህን አድን ርስትህንም ባርክ፤ ጠብቃቸው እስከ ዘለዓለሙም ከፍ ከፍ አድርጋቸው።
አሜን! ይላል ህዝበ ክርስቲያኑ። ምዕመኑ ዘወትር ሰንበት ይህንን የካህኑን ፀሎት ሲሰማ አንዳች ውስጣዊ ስሜት ወጥሮ ይይዘዋል። ብርቱ ሀዘን ከአንጀቱም ይዘልቃል። ቅፅበታዊ የመንፈስ ጉዞም አድርጎ መሪር በሆነ አገዛዝ የተያዙትን ህዝቦቹን ያስታውሳል። በሰንሰለት የታሰሩትንም በጨለማ ቤት የተጣሉትንም የተጨነቁትን ነፍሶችንም የተጠበቡ ቤተዘመዶችንም ሁሉ ያስባል። አቤቱ ህዝብህን አድን – ሲል በዕዝነ ልቡናው የካህኑን ፀሎት ይደጋግማል፤ ብርቱ ሀዘን በሸመቀቀው ስሜት።
የካህኑ ቃል እንዲህ ይላል – አምላካችን ሆይ ለብዙ ዘመናት ለረዥም ወራት በዕውነትና በሠላም መጠበቅን ጠብቅልን፤ አቤቱ ሀገራችንን ኢትዮጵያን አስባት፤ የሚጠሏትን ጠላቶቿን ፈጥነህ አስገዛላት። አሜን ይላል ህዝበ ክርስቲያኑ። አሜን ይላል ምዕመኑም። ቅድስት ኢትዮጵያ እየናፈቀችውና መከራዋም እያሳቀቀው። ለዚህች ቅድስትና ደግሞም ለልጆቿ የፍዳም ማእድ ለሆነች ሀገር ወደ ፈጣሪ የተዘረጉት የልመናና የምልጃ እጆች መች ይሆን በቃችሁ የሚባሉት? ጠላቶቿስ መች ይሆን ከጫንቃዋ ላይ የሚወርዱትና ሠላም የሚሰጧት? በሠላም ስም ሠላሟ መታመስ የሚያቆመውስ መች ይሆን? በሠላም ስም ዜጎቿ የሚጋዙትስ እስከመቼ ነው? በሠላም ስም ፍትህ በአደባባይ መሰዋት የምታቆመው መቼ ነው? በሠላም ስም ኢትዮጵያ ልጆቿ በአደባባይ በጥይት ግንባራቸውን የማይነደሉበት ጊዜ የሚመጣው መቼ ነው? እናቶች በልጆቻቸው ሬሳ ላይ ተቀምጠው የሚያነቡበት ዘመን የሚያበቃው መቼ ነው? ኢትዮጵያውያን በገዛ ሀገራቸው ‘መንግሥት’ ናዚስት መሪዎች በሚታዘዙ ወታደሮች በአደባባይ በጥይት እየተቆሉ ከማለቅና ሀገር ጥለው በገፍ ከመሰደድ የሚያቆሙበት ጊዜ የሚመጣው መች ይሆን? ያልታጠቀን ህዝብ እየፈጀ “ይቅርታ በስህተት” ነው እያለ የሚያላግጥ ሠይጣናዊ ‘መንግሥት’ ልሳኑ የሚዘጋው ተግባሩ የሚቆመው መች ነው? በምዕመኑ ህሊና ሽው ያለ ቅፅበታዊ ጥያቄ።
እነሆ ደግሞ የካህኑ ቃል እንዲህ ሲል በቤተ መቅደሱ ሞላ – ነፍሳችሁን ተመልከቱ፤ ሰውነታችሁንም ንፁህ አድርጉ፤ የባልንጀራችሁን በደል አታስቡ፤ ማንም ከወንድሙ ጋር በቁጣ እንዳይኖር አስተውሉ፤ እግዚአብሄር ያያል። አቤቱ ጥበብንና ሃይልን ልብንና ልቡናን ዕውቀትንም ስጠን፤ ከሚፈታተነን ከሠይጣን ሥራ ሁሉ እስከ ዘለዓለሙ እንርቅ እንሸሽም ዘንድ።
ምዕመኑም በልቡናው እንዲህ አለ፤ አዎ እውነት ነው፤ ይህንንም እናምናለን። ሰው ስለ ምን ከመሰል ወንድሙ ጋር በቁጣና በበቀል ይኖራል? ሰው ስለ ምን ሁሌም በደሉን ብቻ ይመለከታል? ሰው ስለምን ይቅርታ ይከብደዋል? በቀልስ ይቀለዋል? ሰው ስለ ምን ማስመሰል ይቀናዋል? ፍቅር ግን ይርቀዋል? ሰው ስለምን ከነፍሱ ዕውነታ ጋር አይታረቅም? ሰው ስለምን ጥበብን አይመረኮዝም? ልቡናውንስ ስለምን አያዳምጥም? ሰው ስለ ምን የሠይጣን መንገድ (ክፋት ምቀኝነት በደል ግፍ ግድያ ኢሰብዓዊነት) ይቀለዋል? የፅድቅ መንገድ (ሠላም ፍቅር አንድነት መተሳሰብ መቻቻል አብሮነት ሰብዓዊነት) ስለ ምን ይከብደዋል?
ሽበት በሪዛቸው ላይ መታየት የጀመረው ታታሪው ካህን ቀጠሉ – የፍቅር ባለቤት የሠላም ንጉሥ ሠላማዊው ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፤ ሠላምህን ስጠን፤ ሠላምህንም አፅናልን፤ ሃጢያታችንንም ይቅር በለን፤ በሠላም ወደየቤታችን ሄደን እንገባ ዘንድ የበቃን አድርገን። አሜን አለ ህዝበ ክርስቲያኑ እንስት ወተባዕት።
ክርስቶስ ፍቅር ነው። ክርስትና ሠላም ነው። ቃሉ በምድር የፀናው በሠይፍ አይደለም። ሠላማዊው ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ሲሆን ግን ሰው ሆኖ በምድርም ተመላልሶ በሠላም ሠላምንና ፍቅርን አስተምሮ እንጂ! ሃዋርያቱ ሠላምን አስተምረው ፍቅርንም ሰብከው በሰይፍ ግን ተሰይፈው እንጂ! ስለ ሠላም ስለ ፍቅር ሰው ስለመሆን ሃዋርያቱ በግዞት በግረ ሙቅ ታስረው እንጂ! ምዕመኑ በሀገሩ ግፍና ሰቆቃን የሚቀበሉትና የተቀበሉት የሠላም ታጋዮች ሁሉ ትዝ አሉት። ጠመንጃን በሠላም እጅን በማጣመር ድምፅን በማሰማት የተፋለሙትና የሚፋለሙትም ሁሉ ታወሱት። በሠላም ከቤታቸው ወጥተው በድውይ ሰዎች እጅ እንደ ወጡ የቀሩትም ሁሉ ታወሱት። የፍቅር ባለቤት የሠላም ንጉሥ ሠላማዊው ኢየሱስ ክርስቶስ ሠላማችሁን ያብዛላችሁ ብርታትንም በያላችሁበት ይስጣችሁ፤ ሲል ፀለየላቸው።
እነሆ ካህኑ ቅዳሴና ፀሎት አጠናቀው የሰንበት ትምህርት ጀመሩ። ባለፈው ሰንበትና ካለፈው ሰንበትም በፊት በነበሩት ሰንበቶች ያስተማሩት በምዕመኑ ህሊና እንደ ታተሙ አሉ። ትምህርታቸውም ከላፈው ሰንበትና ከዛኛው ሰንበት ቃለ ህይወት ጋር በህሊናው እየተቆላለፉ በትርጉም ላይ ትርጉም ይሰጡታል። የካሁኑ ረዳት ጎልማሳው ዲያቆንም እያሰለሰ የሚያስተምረው አስደማሚ ትምህርት ከካህኑ መልዕክት ጋር እየተጣመሩ በልቡናው ይመላለሳሉ። መንፈሳዊነቱንም ያዳብሩለታል።
እንዲህ ሲሉ ጀመሩ ታታሪውና ሪዛሙ ካህን። በማለዳ የቤተክርስቲያኗን በር ከፍቼ ስገባ መብራት አበራሁ። ብርሃንም ሆነ። ሁሉን ማየትም ቻልኩ። ወደ መቅደስም አመራሁ። ድንገት መብራት ጠፋ። ሁሉ ጨለማ ሆነ። ድቅድቅ ጨለማ። በዚያች ቅፅበትም በቅርቡ ከእስር ተፈትተው ቃለ ምልልስ የሰጡት የሠላም ታጋዮቹ ወጣት ጋዜጠኞች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና አነቃቂዎች ትዝ አሉኝ። ከመሬት በታች በሚገኝ የጨለማ ክፍል ለብዙ ማዕልትና ሌሊት ታስረናል ያሉት። ወገኖቼ እግዚአብሄር በጨለማ ከመኖር ይጠብቃችሁ። ይህ የጨለማ ዘመን የተፈጠረው ሰው መሆን ባልቻሉ ክፉ ሰዎች ነውና። ወገኖቼ ከሁሉ በፊት ሰው ሁኑ። ሰው መሆን ከሠይጣን ሥራና በርኩሰትም ከመመላለስ በልቡናም ከመታበይ ያድናችዃልና። ሰው መሆን ማለትስ ምንድን ነው? ያላችሁ እንደሆን፤ በራስህ ላይ ሊያደርጉብህ የማትፈልገውን በሌሎች ላይ አታድርግ ይላል የጌታ ትዕዛዝ። ይህን መፈፀም ሰው የመሆን ባህሪ ነው። ሰው መሆን ማለት ነው። ሰውን በሰውነቱ ማክበር። ሰውን ለራስ ሥልጣን ወይም ጥቅም ሲሉ ማንገላታት ማሰር መግደል መግረፍ ከሀገር ማባረር ከሰብዓዊነት የወጣ ግፍና ሰቆቃ መፈፀም በቋንቋው በዘሩ ወይንም በዓይነ ውሃው ሰውን ከሰው ማበላለጡ እኒህ ሁሉ ሰው መሆንን አያሳዩም። ሀጢያትንና የሠይጣን ግዳይ ጣይ መሆንን እንጂ። የሠይጣን አባሪ ተባባሪ መሆንን እንጂ።
ዳዊት ንጉሥ ነበር። እንደ ንጉሥነቱም ባለጠጋም ነበር። ሀገር ያስተዳድራል። ሠራዊት አለው። ነገር ግን ንጉሥ ዳዊት በዕድሜው መጨረሻ ልጁን ሰለሞንን ጠርቶት ምን መከረው? ምንስ አዘዘው? ምንስ አወረሰው? ሲሉ ጠየቁ ካህኑ ምዕመናኑን በዓይኖቻቸው እያዳረሱ። ወደ አትሮነሱ ተመለሱና መፅሐፍ ቅዱሳቸውን ገለጡ። ይህንንም አነበቡ፤ ዳዊትም የሚሞትበት ቀን ቀረበ፤ ልጁንም ሰለሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው፤- እኔ የምድሩን መንገድ ሁሉ እሄዳለሁ፤ በርታ፤ ሰውም ሁን፤ የምታደርገውንና የምትሄድበትን ታከናውን ዘንድ፤ ካህኑ ታላቁን መፅሀፍ አጥፈው ሰበካቸውን ቀጠሉ። አዎን ወገኖቼ እናቶቼና አባቶቼ ወንድሞቼና እህቶቼ፤ የምናደርገውንና የምንሄድበትን አጥርተን ለማወቅ፤ መንገዳችንም ሆነ ተልዕኳችን የፅድቅ መንገድና ተልዕኮ እንዲሆን ከሁሉ በላይ የሚያስፈልገን ሰው መሆን ነው። ዳዊት ልጁን ያዘዘውና የመከረው በሚወርሰው መንግሥት ሀብቱንና ሠራዊቱን ተመክቶ በምድሪቱና በህዝቡ ላይ ያሻውን እንዳይፈፅም ባለሟሎቹም በመንግሥቱ ተገን እንደፈቃዳቸውና እንዳሻቸው በህዝቡ ላይ እንዳይኖሩ ነው። ልጄ ሆይ ሰው ሁን – ነው ያለው። መንገድህ የተቃና ምግባርህም ቀና እንዲሆን ከሁሉ በፊት ልጄ ሆይ ሰው መሆን ያስፈልግሃል – አለው። ንጉሥ ብትሆንም ሰው ካልሆንክ ግን ከንቱ ነው – ማለቱ ነው ንጉሥ ዳዊት ልጁን ሲመክረው።
ምዕመኑ ይህንን የካህኑን ትምህርት መሬት አውርዶ ተረጎመው፤ ኢትዮጵያችን የሚያስፈልጋት እንደ ዳዊት ገዢዎቿን ሰው ሁኑ ብሎ የሚመክርና የሚገስፃቸውን ነው። ሰው ያልሆነ ገዢ ሁሌም የሚመካው በሰይፍና በሠራዊት ነውና። በሰይፍ የቆመ በሰይፍ ይወድቃል፤ አይደለም እንዴ የሚለው ቃሉ? ራሱን ጠየቀ።
እነሆ ደግሞ የካህኑ ቃል ከቅፅበታዊ ጉዞው መለሰው። ወገኖቼ ስለ ኢትዮጵያ ሁላችን ግድ ሊለን ይገባል። ስለ ወገኖቻችን ግድ ሊለን ይገባል። ልመናችን ወደ እግዚአብሄር ሊደርስ አልቻለም። ጩኸታችንን ገና አልሰማንም። ስለምን ይሆን? ብለን ልንጨነቅ ግድ ይላል። ጌታ ልብና ኩላሊትን እመረምራለሁ ይላል። ካህናቷ፤ የሃይማኖት አባቶቿ ፀሎታችንና እግዞታችን ከነፍሳችን ነው ወይስ ከሥጋችን? የምዕመናን ፀሎትና እግዞታስ ከልቡና ወይስ ከአፀደ ሥጋ? ወገኖቼ፤ በቤተ ክርስቲያናችንና በጌታችን መካከል ያለው ድልድይ ልቡናችን ነው። ክርስቶስ የሚመረምረውና የሚመለከተውም ልቡናችንን ነው። ልቡናችን ግን በአመፅና በትዕቢት በነውርና በሠይጣን መንገድ እየሄደና ሰው መሆንን እያረከሰ እንደምን የሠላምና የፍቅር ሰው የመሆንም አምላክ ልመናችንን እና ጩኸታችንን ሊሰማን ይችላል? ወገኖቼ፤ ስለ ኢትዮጵያ ግድ የሚለን ስለ ወገኖቻችን ግድ የሚለን ፖለቲከኞች ሆነን አይደለም፤ ሰው ሆነን በመፈጠራችን እንጂ! ሲሉ በአርምሞ ተናገሩ መካከለኛ ቁመት ደንደን ያለ ሰውነት ያላቸው ባለሪዛሙ ካህን።
ዕውነት ነው አለ ምዕመኑ እንደገና በቅፅበት ሸፍቶ፤ የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሄርን መፍራት ነው። እግዚአብሄርን መፍራትም አሥርቱን ትዕዛዛት መጠበቅና መፈፀም ነው። አሥርቱን ትዕዛዛት መጠበቅም ሰው መሆን ነው። ሰው መሆንም ጥበብን ማወቅ ነው። ጥበብንም ማወቅ ሰው መሆን ነው፤ በአሥርቱ ትዕዛዛት መገዛት። በአሥርቱ ትዕዛዛት መኖርም በፅድቅ መኖር ነውና! አንተ መኖር እየፈለግህ ሌላውን መግደል ሀጢያት ነው። ትዕዛዙን መሻር። አንተ ፍትህ እየፈከግህ ሌላውን በሀሰት መወንጀልና ፍትህ መንፈግ ሀጢያት ነው። ትዕዛዙን መሻር።
ካህኑ ይሁኑ ወይ ጎልማሳው ዲያቆን ከሁለት አንዱ ወይም ሁለቱ ከዚህ በፊት በነበሩ ሰንበቶች ያስተማሩት ቃል በምዕመኑ ህሊና አስተጋባ፤ ትንቢተ አሳይያስ እንዲህ ይላል፤- እጃችሁን ወደኔ ብትዘረጉ ዐይኔን ከናንተ እሰውራለሁ፤ ልመናም ብታበዙ አልሰማችሁም፤ አጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል ታጠቡ፤ ሰውነታችሁንም አንፁ። የሥራችሁን ክፋት ከዐይኔ ፊት አስወግዱ። ክፉ ማድረግን ተዉ። መልካም መስራትን ተማሩ፤ ፍርድን ፈልጉ፤ የተገፋውን አድኑ፤ ለድሃ አደጉ ፍረዱለት፤ ስለመበለቲቱም ተሟገቱ። ይህ ቃል ስለ እኛ ኢትዮጵያውያን የተፃፈ ትንቢት ነውን? ሲል አሰበ ምዕመኑ፤ ሁሉ ቃል ዕውነት ነውና።
ፍርድ ሞልቶባት የነበረ የታመነችይቱ ከተማ እንዴት ጋለሞታ ሆነች! ፅድቅ አድሮባት ነበር፤ አሁን ግን ገዳዮች አሉባት። አለቆችሽ ዐመፀኞችና የሌቦች ባልንጀሮች ሆኑ። ሁሉ ጉቦ ይወድዳሉ፤ ዋጋም ለማግኘት ይሮጣሉ፤ ለድሃ አደጉ አይፈርዱም፤ የመበለቲቱም ሙግት ወደ እነርሱ አይደርስም። እነሆ ምዕመኑ ኢትዮጵያን ሲመለከት ይህንንም የኢሳይያስ ትንቢት አስታወሰ። አዎ ዕውነት ነው፤ የኢትዮጵያ አለቆች ዐመፀኞችና የሌቦች ባልንጀሮች ናቸው ሲል ለራሱ ተናገረ።
እነሆ ደግሞ በመዝሙረ ዳዊት የተፃፈውም በሀገሩ የሰፈነውን የክፋትና የእኩይነት ጣራ ይናገራል ሲል አመነ፤ ዳዊት እንዲህ ብሏልና፤- ሁሉ ዐመፁ፤ በአንድነትም ረከሱ፤ በጎ ነገርን የሚሰራ የለም፤ አንድም ስንኳ የለም። ጉሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸው ሸነገሉ፤ ከከንፈራቸው በታች የእባብ መርዝ አለ፤ አፋቸው መርገምንና መራራን ተሞልቷል፤ ደምን ለማፍሰስ እግራቸው ፈጣን ነው። ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው አለ፤ የሠላምን መንገድ አላወቋትም፤ እግዚአብሄርን መፍራት በዐይናቸው የለም።
ዕውነት ነው አለ ምዕመኑ፤ የኢትዮጵያ ገዢዎች በራሳቸው አንደበት ደግመውና ደጋግመው ያለ አንዳች መሳቀቅ “በስብሰናል፤ ሸተናል” ይሉ የለ? ታዲያ ስለምን በፈቃዳቸው ‘ለሸተተና ለበሰበሰ’ ወደሚሆነው ማረፊያ አይሄዱም? ወይስ ይህም ከከንፈራቸው በታች የሚወጣ መርዝ ይሆን?
እነሆም የካሁኑ ቃል ምዕመኑን ከጉዞው ገታው። ወገኖቼ እንግዲህ ማንም ቢሆን ስለ አትዮጵያ ሲል ስለ ህዝቡና ስለ ቅድስቲቷ ምድር ሲል ልቡናውንና ልቡን ወደ ፈጣሪው መልሶ እግዚኦታ ሊያሰማ ግድ ይላል። ሠላም ለኢትዮጵያ ሠላም ለህዝቧ ይሆን ዘንድ በእግዚአብሄርና በፅድቅ መንገድ ላይ ለታበዩ፤ ወደ ጥፋትና ወደ እልቂትም ጎዳና ለሚጣደፉትም ሁሉ ቅዱስ ፈጣሪ ወደ ልቡናና ልቦናቸው ጊዜው ሳይመሽ ይመልሳቸው ዘንድ እግዚኦ ልንልላቸው ይገባል። በሀዘን ልባቸው ለተሰበረ አይኖቻቸው በእናባ ጅረት ለፈዘዘ እናቶች እግዚኦ ልንልላቸው ይገባል። በበርሃ በስደት ስለሚንከራተቱ ወገኖቻችን እግዚኦ ልንልላቸው ይገባል። እንደ ወጡ ስለቀሩት ወጣቶችና ጎልማሶች ሁሉ እግዚኦ ልንልላቸው ይገባል። በወህኒ ስለተጋዙትና በጨለማ ቤቶች ስለተዘጋባቸው ሁሉ እግዚኦ ልንልላቸው ይገባል። ስለ ደካሞችና በአልጋ ቁራኛ ስለተያዙት ሁሉ እግዚኦ ልንልላቸው ይገባል። ስለራሳችንና ስለ ቤተሰቦቻችን እግዚኦ ልንል ይገባል።
እነሆ ካህኑ በተሰበረ እንባና ሀዘንም በተሞላ ድምፅ እግዚኦታውን ለረዥም ደቂቃዎች መሩ፤ ዲያቆናትና ምዕመናን እየተቀበሉ ልመናቸው በቤተ መቅደሲቱ አስተጋባ። ድምፃቸውም ከዕጣኑ ጢስ ጋር ወደላይ አሻቀበ።
አድነነ ከመዓቱ ሰውረነ በምህረቱ በእንተ ማርያም ወላዲቱ! እያሉ ተማፀኑ።
እነሆም እግዚኦታው አበቃ። እትዉ በሠላም! ተባለ – በሠላም ወደየቤታችሁ ግቡ!
ጌታ ሆይ ትጉሁን ካህናችንን በሠላምና በጤና ጠብቅልን፤ ዲያቆናቱንና መዘምራኑን በሠላምና በጤና ጠብቅልን፤ ምዕመናኑንም በሠላምና በጤና ጠብቅልን፤ አቤቱ የኢትዮጵያን ጠላቶች በቃችሁ በላቸው፤ አለ ምዕመኑ የካህኑን እጅ ተሳልሞ ሲወጣ።
መስፍን ማሞ ተሰማ
መጋቢት 2010 ዓ/ም (ማርች 2018)
ሲድኒ አውስትራሊያ
mmtessema@gmail.com
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Mulugeta Andargie says
እናንት ጨበርባሪዎች!!! ትናንት ቦጠሊቃ ትሰብኩን ነበር በዚሁ ዌብ ሳይት፣ ዛሬ ደግሞ ተገምጥሎ ቤተ ዕምነት ገብታችሁ ትፈተፍቱ ጀመር??? ቂቂቂ!!!ቂቂቂ!!!ቂቂቂ!!!! መቼም ዘመኑ ለሚያምታቱም ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።