ሶርያን ጊዜያዊ ማረፊያው አድርጎ አገሪቱን እያዳሸቀ፣ ህዝቡን እየበላ፣ ያለው የ“አረብ ጸደይ” ብዙዎች እንደሚሉትና የመፈክር ያህል እንደሚስተጋባው መነሻው የቱኒዚያ ምድር ሳይሆን ቆመች ስትባል መልሳ በምትናጠው ጎረቤታችን ሶማሊያ ነው። ይኸው የለውጥ “ቀይ” ነፋስ በሊቢያ ጋዳፊን እንደምናምንቴ በውሻ አይነት አሟሟት እስከወዲያኛው አሰናብቷል። ጋዳፊ ላይ ከተፈጸመው ጋር በንጽጽር ላስተዋለው አሁን በሶሪያ እየተከናወነ ያለው የዚያ ግልባጭ መሆኑን ለመረዳት የሚያዳግት አይደለም፡፡ በአገራችን አባባል “የቆላ ቁስል” እንደምንለው!
ዓለምአቀፍ የግንኙነት ቡድን
ተፈላጊ የሆነው አገር ስም እየተሰጠው በዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ (በምዕራባውያን ወኪልነት) የሚቋቋመው ዓለምአቀፍ የግንኙነት ቡድን (International Contact Group) እየተባለ የሚጠራው አካል ለሶማሊያ የተመሠረተው እኤአ በ2006ዓም ነበር – ዓለምአቀፍ የሶማሊያ ግንኙነት ቡድን (International Somalia Contact Group) በሚል፡፡ ሃሳቡን አመንጪና ጀማሪ በዘመነ ፕሬዚዳንት ቡሽ በኮንዲ ራይስ ይመራ የነበረው የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲሆን ዓላማው በሶማሊያ የሚደረገውን “ሰላምና ዕርቅ” ለመደገፍ የሚል ሽፋን ተሰጠው፡፡ አሜሪካ፣ ጣሊያን፣ ስዊድን፣ ታንዛኒያ፣ እንግሊዝና የአውሮጳ ኅብረት በአባልነት የተሳተፉበትን የመጀመሪያውን ስብሰባ ኖርዌይ በሊቀመንበርነት ስትመራ የአፍሪካ ኅብረትና የአረብ መንግሥታት በታዛቢነት ተገኙ፡፡ ኬኒያ በስብሰባው ባለመጋበዟ መከፋቷ ተዘገበ፡፡ አቶ መለስ በጉዳዩ ላይ አንዳችም ሳይተነፍሱ ጸጥ አሉ – የኢትዮጵያ ድግስ ምን እንደሆነ አስቀድሞ ተነግሯቸዋልና፡፡
ስብሰባው በዚህ ሁኔታ ሲካሄድ ከጥቂት ቀናት በፊት የሶማሊያን ገጽታ ፈጽሞ የለወጠ ድርጊት ተከስቶ ነበር፡፡ የቡድኑን መቋቋም ሆነ የስብሰባው መካሄድ አስፈላጊነት አጽዕኖት እንዲሰጠው ያስገደደው የእስላማዊ ፍርድቤቶች ኅብረት (Islamic Courts Union) ለዘመናት ሰላምና መረጋጋት አጥቶ የነበረውን በተለይ ደቡባዊውን የሶማሊያ ክፍል ማስተዳደር መጀመሩና ሞቃዲሾን መቆጣጠሩ ነበር፡፡ የምዕራባውያን ቀጥተኛ ድጋፍ የነበረው የሶማሊያ ሽግግር ም/ቤት ሞቃዲሾን መቆጣጠር አለመቻሉና በእስላማዊ ፍርድቤቶች ኅብረት ተባርሮ ከሞቃዲሾ 250ኪሜ አካባቢ ርቃ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በምትቀርበው ባይዶዋ ከተማ መቀመጫውን ማድረጉ ምንም አቅም እንደሌለው ያስመሰከረበት ነበር፡፡
እስላማዊው የፍርድቤቶች ኅብረት “በሶማሊያ የሸሪያን ሕግ ያውጃል፤ አክራሪ መንግሥት ይመሠርታል፤ …” እየተባለ በወቅቱ ቢወራበትም በከተማዋ ሰላምና መረጋጋትን ከዓመታት በኋላ በማስፈኑና የጦር አበጋዞችን ትጥቅ እያስጣለ መሄዱ በርካታ ሶማሊያውያንን ያስደሰተና ተስፋ የሰጠ ነበር፡፡ በኬኒያ የአሜሪካ ኤምባሲ በቦምብ ለመጋየት ቀጥተኛ ተጠያቂ ነው የሚባለው ኬንያዊው ፋዝዋል አብደላ መሐመድ (በሌላ ስሙ ሐሩን ፋዙል የሚባለው) “በሶማሊያ የአልቃይዳ ወኪል ስለሆነ ከእስላማዊ ፍርድቤቶች ኅብረት ጋር ግንኙነት አለው” ተብሎ በአሜሪካ ቢከሰስም በወቅቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ሰዎችም ሆኑ የሲአይኤ ባለሥልጣናት ጉዳዩ በማስረጃ ሊረጋገጥ ያልቻለ ግምታዊ አስተሳሰብ መሆኑን አስታውቀው ነበር፡፡ ይልቁንም በዚህ ሰበብ እስላማዊ ፍርድቤቶችን በእጅአዙር ለመምታ ሲባል ለሶማሊያ የጦር አበጋዞች የሚሰጠው ድጋፍ በጥብቅ ሊታሰብበት እንደሚገባ አስጠነቀቁ፡፡ አሜሪካ የጦር ነጋሪት ለመጎሰም በተዘጋጀችበት በዚያን ወቅት በሶማሊያውያን ዘንድ መጪው ዓመት (2007) አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ሊሰፍን ይችላል የሚል ተስፋ ፈነጠቀ፡፡ ግን አልዘለቀም፡፡
እስላማዊ ፍርድቤቶች ኅብረትና የአቶ መለስ ሚና
የአስራአንድ የተለያዩ ጎሣ ፍርድቤቶች ስብስብ የነበረው ኅብረት ገና ከጅምሩ በምዕራባውያን ዘንድ በአክራሪነት በመፈረጁ ሞቃዲሾን እንደተቆጣጠረ የተለያዩ የማስተባበያ መግለጫዎችን ማውጣት ጀመረ፡፡ “የአሸባሪዎች መከማቻ፤ ራሱ አሸባሪ የሆነ፤ …” የሚሉትን ክሶች በግልጽ በመኮነን “አሸባሪነትን እንደሚያወግዝ” ጠቅሶ ለዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ ደብዳቤ ጻፈ፡፡ ከተቀረው ዓለም ጋር “የወዳጅነት ግንኙነት ለመመሥረት” መዘጋጀቱን በመግለጽ “የዘንባባ ዝንጣፊ” አቀረበ – የሚቀበለው ቢኖር፡፡ በወቅቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ጸሐፊ የነበሩት ጄንዳይ ፍሬዠር ከአለቆቻቸው የተሰጣቸው ሌላ የቤት ሥራ ስለነበር የዘንባባ ዝንጣፊውን ለመቀበል ትርፍ ጊዜ አልነበራቸውም፡፡
ፍረጃው እየቀጠለ ሲሄድ ኅብረቱ ሁኔታውን ለማለሳለስ ተደጋጋሚ መግለጫ ማውጣቱን ቀጠለ፡፡ በተለይ በአክራሪነት የሚታወቁትን መሪውን ሼክ ሐሰን ዳሒር አዊስን ወደኋላ በማድረግ ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው የሚባሉትንና ለዘብተኛ አቋም ያላቸውን የሕግና የእስልምና ሸሪያ ምሩቁን ሻሪፍ ሼክ አህመድን ፊታውራሪው አደረገ፡፡ በመስከረም 2006ዓም ስርቲ ሊቢያ በተደረገው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ ሻሪፍ አህመድ የልዑካን ቡድናቸውን በመምራት እስላማዊው ኅብረት ከሽግግር መንግሥቱ ጋር ንግግር ለማድረግ መፈለጉንና ለዚህም የሊቢያንና የሌሎች አፍሪካ አገራትን ድጋፍ እንደሚፈልጉ አስታወቁ፡፡ ወዲያውም ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሰላም እንዲሰፍን የማትፈልግ አገር መሆኗን በመጥቀስ ወነጀሉ፤ ጦሯንም ባይዶዋ ማስፈሯንና ከሽግግር መንግሥቱ ጋር በመሆን ሞቃዲሾን ለማጥቃት ማቀዷን ጨምረው ተናገሩ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መካሰስ ከሁለቱ ወገኖች እየከረረ በመምጣቱ የታቀዱ የሰላም ስብሰባዎች ፍሬያማ እንዳይሆኑ አጀንዳ የነበራቸው ኃይሎች በጽኑ እንደተንቀሳቀሱ ይጠቀሳል፡፡
የዚያኑ ወቅትም የዑጋንዳው መሪ ሙሴቪኒ የኢጋድ ስብሰባ እንዲጠራ ሲያስታውቁ “የአዲሲቷ ሶማሊያ መሃንዲስ” የተባሉት አቶ መለስም “ስለ ሶማሊያ ለመወያየት አስቸኳይ ስብሰባ መጠራቱ ጠቃሚ ነው” በማለት ጥሪውን በጥሪ አስተጋቡ፡፡ “የሶማሊያን ጉዳይ ለኔ ተዉልኝ” በማለት ምዕራባውያንን በተለይም አሜሪካንን ሲያባብሉና በውጪ ምንዛሪ እንዲሁም በጦር መሣሪያና በወታደራዊ ሥልጠና ሲያልቧቸው የነበሩት መለስ የሶማሊያን ሽግግር መንግሥት ኬኒያ ላይ ከመሠረቱ በኋላ ለምዕራባውያን
ለማስረከብ ሲጣደፉ ያላሰቡት ነበር የተከሰተው፡፡ እስላማዊው ፍርድቤቶች ኅብረት “በብርሃን ፍጥነት” ሶማሊያን ተቆጣጠረ፡፡ ይህም በመለስ ላይ ከምዕራባውያን በተለይም ከአሜሪካ የሰላ ነቀፋና ውግዘት አስከተለባቸው፡፡ ዓለምአቀፉ የግንኙነት ቡድን (International Somalia Contact Group) ሲቋቋም አቶ መለስ ያልተጋበዙበትን ሁኔታ ከዚሁ ክስረት ጋር የሚያያይዙ ወገኖች ጉዳዩ መለስን “አሁን አታስፈልግም፤ በፊት እፈጽማለሁ ያልከውን በተገቢው ሁኔታ ያላጠናቀቅህ ነህ” ከሚል ንቀት የመነጨ ነው ይላሉ፡፡ ሁኔታው እኤአ በ2005 (1997) የተካሄደውን ምርጫ አቶ መለስና ድርጅታቸው ካጭበረበሩና ያንንም ተከትሎ የሰውን ሕይወት ከመቅጠፉ ጋር ተዳምሮ የምዕራባውያኑ ፊት መንሳት ሥልጣናቸውን አደጋ ላይ እንደሚጥለው የተገነዘቡት መለስ ማንኛውንም ሥራ ለመሥራትና የምዕራባውያንን “ፈገግታ” በድጋሚ ለማየት ወሰኑ፡፡ ምዕራባውያንም መለስ የእነርሱ “ቆሻሻ ሥራ” ለመሥራት የወሰኑ መሆናቸውን አረጋገጡ፡፡ ኢጋድም በሶማሊያ ላይ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ ድራማውም ቀጠለ፡፡
የአቶ መለስ ጦርነት
ከእስላማዊው ምክርቤት በተደጋጋሚ ለሚሰነዘረው ክስ ግን አቶ መለስ “አንዳችም የኢትዮጵያ ሠራዊት ሶማሊያ የለም” በማለት ካዱ፡፡ በተለያዩ የዜና ምንጮች የኢትዮጵያ ጦር ድንበር አልፎ ሶማሊያ መግባቱ እየተረጋገጠ የመለስ ዓይን ያወጣ ክህደት “ምናልባትም ባይዶዋን የኢትዮጵያ አካል አድርገው ወስደዋት ይሆን” የሚያስብልም ነበር፡፡ ብዙም አልቆዩ በምን ዓይነት ፍጥነት ያንን ሁሉ ሰው ወደ ሶማሊያ ማጓጓዝ እንደቻሉ ሳያብራሩ አቶ መለስ “አሁን በሶማሊያ ያሉን ወታደሮች ሳይሆኑ የሽግግር መንግሥቱ በጠየቀን መሠረት አሠልጣኞችን” ናቸው በማለት የራሳቸውን ቃል አስተባበሉ፡፡ ቀጥለውም በአማርኛ ቢሆን እንደሚሉት “‘በመርህ ደረጃ’ ከሶማሊያ ጋር ጦርነት ገጥመናል” አሉ፡፡ (እርሳቸው ያሉት “ቴክኒካሊ” ነበር)
በኢራቅና አፍጋኒስታን የተሰማራውን የአሜሪካ ጦር የሚያስባሩትና የአሜሪካ የማዕከላዊ ዕዝ ዋና ኃላፊ የሆኑት ጄኔራል ጆን አቢዜይድ የእስላማዊ ፍርድቤቶች ኅብረትን ከሞቃዲሾ ማስወጣቱ ከመጀመሩ ጥቂት ሳምንታት በፊት ከአቶ መለስ ጋር ምሥጢራዊ ስብሰባ አደረጉ፡፡ በጦርነቱ አሜሪካ የምታስፈጽመው አጀንዳና የምታገኘው ጥቅም ምን እንደሚሆን ከተወያዩ በኋላ የአቶ መለስ ጦር በሶማሊያ ጥቃቱን ጀመረ፡፡ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች፣ መርከቦች፣ ልዩ ጦር፣ የስለላ ወኪሎች፣ … በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሲሳተፉ የሰው ሕይወት የሚጠይቀውን የምድር ጦር ኢትዮጵያ ሸፈነች፡፡ የእስላማዊ ፍርድቤቶች ኃይላት ባጭር ቀናት ውስጥ ሞቃዲሾን ለቅቀው ወደ ኪሲማዮ ሲያፈገፍጉ የሽግግሩ ፕሬዚዳንት አብዱላሂ ዩሱፍ ከሦስት ዓመታት በኋላ ሞቃዲሾ ገቡ፡፡ በውጤቱ የልብ ልብ የተሰማቸው መለስም ሶማሊያን በመውረር ከአሜሪካ ጥቅም አግኝተዋል ተብሎ ለተሰነዘረባቸው ወቀሳ “አምስት ሳንቲም ያገኘነው ጥቅም የለም … የራሳችንን የድንበር ሉዓላዊነትና ጥቅም ነው ያስከበርነው” በማለት “ኢትዮጵያዊ” ሆኑ፡፡ በዚህም አላቆሙም “ከፈለጉ ስንዴአቸውን መከልከል ይችላሉ” በማለት በአማርኛ ተዛለፉ፡፡ ከመጋረጃው በስተጀርባ ግን ከቡሽ አስተዳደር “ጎበዝ ልጅ” መባላቸውና የተቃዋሚ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ በተመለከተ ምንም እንዳይፈሩ ዋስትና እንደተሰጣቸው በማስረጃነት የተናገሩት ንግግር በራሱ ዋቢ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
የወደፊቱ የኢትዮጵያ ያሳሰባቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን በወቅቱ ወረራውን የተቃወሙ ሲሆን በተለይ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ጦርነቱ የኢትዮጵያ እንዳልሆነ ከመጥቀስ አልፈው “የሰው አገርን በመውረር ምን ይገኛል?” በሚል ርዕስ በጻፉት ለአሜሪካና ለኢትዮጵያ ያለውን ጥቅም በሚከተለው መንገድ ነበር የገለጹት፤ “ለአሜሪካ የኢትዮጵያ ጥቅም ሦስት ብቻ ይመስለኛል። አንዱ አልገብርም ያለውን ኤርትራን ለማስፈራሪያ ነው፤ ሁለተኛው ኢትዮጵያን ከእስልምና ጋር በዘላቂ ቅራኔ ለማጣመድ ነው፤ ሦስተኛው በይፋ እንደሚባለው አክራሪ የእስልምና ሽብርተኞች በሶማሊያ ውስጥ እንዳይገቡ ለመከላከል ነው። ሁለተኛውና ሦስተኛው የተያያዙ ናቸው። ሦስቱም የአሜሪካ ዓላማዎች የኢትዮጵያን መሠረታዊና የዘለቄታ ዓላማዎች የሚቃረኑ ናቸው። ለአሜሪካ ጥቅም ስትል ሶማሊያን በመውረር ኢትዮጵያ የምታገኘው ጥቅምስ ምንድን ነው? መሣሪያና ስንዴ።”
ጦርነቱ ተጠናቀቀ ከተባለ በኋላ በጦርነቱ የሞቱትን ወታደሮች ብዛት ምን ያህል እንደሆነ በፓርላማቸው ፊት የተጠየቁት አቶ መለስ “አያገባችሁም” ከማለት ያልተናነሰ የእብሪት ምላሽ ሲሰጡ በሶማሊያ ግን የሽግግር መንግሥቱ በሥልጣን መቆየት እያቃተው የአልሻባብ ጥቃትም እየጠነከረ ሄደ፡፡
ዓለምአቀፍ የግንኙነት ቡድን ንድፈሃሳብ ማንሰራራት
በአሜሪካ የተወጠነው (International Contact Group) ጽንሰሃሳብና ሥልጣኑን በሽግግር መንግሥት መልክ በማዋቀር ሶማሊያን ሞዴል አድርጎ ወደ ሌሎች አገራት “ኤክስፖርት” ለማድረግ የታሰበው ዕቅድ ተግባራዊ መሆን አቃተው፡፡ ሆኖም ጊዜውን ጠብቆና ተሻሽሎ በአማጺያን ጥቃት ለውጥ ከተካሄደባቸው አገራት በሊቢያ በድጋሚ ተግባራዊ ተደረገ፡፡ የአማጺያኑ እንቅስቃሴ በጥንቃቄ እየተመራ ጋዳፊን ሊያሳጣ በሚችል መልኩ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ ምዕራባውያን (ኔቶ እና አሜሪካ) የቀጥታ ድጋፋቸውን መስጠት ጀመሩ፡፡ እጅግ በርካታ የጦር መሣሪያ በኒጀር በኩል ወደ ሊቢያ ገባ፡፡ ከሶማሊያ በተወሰደው ትምህርት ጋዳፊን ከሥልጣን ለማስወገድና የሊቢያን ሽግግር ካውንስል (ምክርቤት) ለመደገፍ ዓለምአቀፍ የግንኙነት ቡድን ለሊቢያ (International Contact Group for Libya) (“የሊቢያ ወዳጆች” (Friends of Libya) በተሰኘ ሌላ ስምም ይጠራል) ተቋቋመ፡፡ ወደ ሠላሳ የሚጠጉ የአረብና የምዕራብ አገራት አባል በሆኑበት ስብስብ አቶ መለስ የሚመሯት ኢትዮጵያ የታዛቢነት ሥፍራ ተሰጥቷት ነበር፡፡
በሊቢያና ሶርያ ላይ አጀንዳ ያላቸው ምዕራባውያን “የአረብ ጸደይ” ከቁጥጥራቸው በመውጣት በግብጽ ላይ እንደተከሰተው ሁሉ ወደሌሎች “ወዳጅ” አረብና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት እንዳይዛመት አስፈላጊው አፈና ተካሄደበት፡፡ በአምባገነን አገዛዝ የሚመሩት ባህሬይን፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ዮርዳኖስ፣ ኩዌይት፣ … የለውጥ ማዕበል ገረፍ አድርጎ እንዲያልፋቸውና በምትኩ የመንግሥት ለውጥና ማሻሻያ በማድረግ አስፈላጊም በሆነበት ቦታ ያለ ምዕራባውያን ውግዘት በለውጥ ፈላጊዎች ላይ የኃይል እርምጃ በመውሰድ “ጸደዩ” እንዲጨልም ተደረገ፡፡
የሊቢያ አጀንዳውን በድል ያጠናቀቀው የግንኙነት ቡድን በቀጣይ በተሻሻለ መልኩ ተጠናክሮ በቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ዋናጸሐፊ ኮፊ አናን አቅራቢነት ዓለምአቀፉ የግንኙነት ቡድን የሶርያን ብሔራዊ ምክርቤት ወይም የሶርያን ብሔራዊ የሽግግር ምክርቤትን አቋቋመ፡፡ የባሻር አልአሳድን መንግሥት የሚጻረሩ የሶርያ የተቃዋሚ ኃይላት ኅብረት በመፍጠር ምክርቤቱን ተቀላቀሉ፡፡ አማጺያኑም አሳድን በሚያሳጣ መልኩ ጥቃት ሲሰነዝሩ የአሳድ አገዛዝም አስከፊ ምላሽ ሲሰጥ ሁኔታው እየከፋ መጣ፡፡ የምዕራቡም ዓለም በሊቢያ እንዳደረገው በሶርያም እንዲሁ የአማጺያኑን ኃይል መርዳትና ማስታጠቁን ቀጥሏል፡፡ የዚህ ጽሁፍ ዋንኛ ዓላማ አይደለም እንጂ የምዕራቡ ዓለም በሶርያ ላይ ያለው ጥቅም እጅግ ከፍተኛ ነው – ከእስራኤል እስከ ኢራን እስከ “አሸባሪዎችን ማጥፋት/መኮትኮት” የዘለቀ ነው፤ ጂኦፖለቲካና ነዳጅንም ጨምሮ፡፡ ከዚህም ሌላ ፖለቲካ በራሱ ሳይንስ ተብሎ የሚጠራ የትምህርት ዘርፍ እንደመሆኑ የፖለቲካ ምርምር ማካሄጃ “ቤተሙከራዎች” አስፈላጊ መሆናቸውም የሚዘነጋ አይደለም፡፡
እንዲህ ያለው የምዕራባውያን የፖለቲካ አቋም በአሁኑ ጊዜ በሶርያ ከፍተኛ ውድመት እያስከተለ ይገኛል፡፡ ከሁለት ሳምንታት በፊት የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ የአሜሪካንን የስለላ መ/ቤት ባለሥልጣናትን ዋቢ በማድረግ የአሳድን አገዛዝ ለመጣል ከአሜሪካና በአጠቃላይ ከምዕራቡ ዓለም ለአማጺያን የሚላከው የጦር መሣሪያ እንደ አልቃይዳ ዓይነት አሸባሪ ድርጅቶችና የእስላም ጂሃዲስቶችና ሚሊሺያዎች እጅ እየገባ መሆኑን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ “የባሻር አልአሳድን መንግሥት ለመጣል ለሚታገሉት የሶርያ አማጺያን በሳዑዲ አረቢያና ኳታር አስቸኳይ ትዕዛዝ የሚላከው የጦር መሣሪያ እጅግ አክራሪ በሆኑ የእስላም አክራሪዎችና ጂሃዲስቶች እጅ እየገባ ነው” በማለት ጋዜጣው የአሜሪካ ባለሥልጣናትና የመካከለኛው ምስራቅ ዲፕሎማቶች ማስጠንቀቃቸውን ጠቅሶ ጽፏል፡፡ በመቀጠልም ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ኃላፊ የተናገሩትን ሲጠቅስ “እጅግ አደገኛ የሆኑትን የጦር መሣሪያዎች እየተረከቡ ያሉት መሣሪያዎቹን በጭራሽ እንዳያገኙ የምንፈልጋቸው የተቃዋሚ ኃይላት ናቸው” ማለታቸውን ዘግቧል፡፡ ለሊቢያ አማጺያን ያለገደብ የተላከው የጦር መሣሪያ በአሸባሪዎች እጅ በመውደቁ በቅርቡ በሊቢያ የአሜሪካ አምባሳደር መገደል ምክንያት መሆኑን የሚከራከሩ ወገኖች የዚያኑ ዓይነት ፍንጭ አሁንም በሶርያ መታየቱን ይጠቁማሉ፡፡ ከሳምንት በፊት በአሸባሪዎች ታፍነው የነበሩ በሶርያ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቄስ እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ መገደላቸው የአሜሪካ የስለላ ሰዎች እንዳሉት “የጦር መሣሪያው አላስፈላጊ ወደሆኑ ኃይላት እጅ” ለመግባቱ አመላካች ነው፡፡
ቄስ ፋዲ ጃሚል ሃዳድ ባልታወቁ ታጣቂዎች ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ 50ሚሊዮን የሶርያ ገንዘብ (ከ700ሺህ ዶላር በላይ) የማስለቀቂያ ገንዘብ ተጠይቆባቸው ነበር፡፡ ገንዘቡን ለማግኘት ባለመቻሉ ታጣቂዎቹ ካህኑን አሰቃይተውና ደብድበው ሲያበቁ ዓይናቸውን አውጥተው ከገደሉ በኋላ እጅግ የተበላሸውን አካላቸውን ወርውረውት ተገኝቷል፡፡ በሶርያ ግድያውና መተላለቁ ቀጥሏል፤ ምዕራባውያንም በመሣሪያና በገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉትን የሙከራ ፖለቲካ ቀጥለውበታል፡፡
“የአረብ ጸደይ” ወይስ “የቆላ ቁስል”?
ዓለምአቀፍ እውቅና የተሰጠው የሶማሊያ ፌዴራላዊ የሽግግር መንግሥት በአሜሪካ የተሰጠው ኃላፊነት “የሶማሊያን ኢኮኖሚ ተቋማት መልሶ ማቋቋም” ሲሆን የሙስሊም ወንድማማቾች (Muslim Brotherhood) በከፍተኛ ቁጥር የተቆጣጠሩት የሶርያ ብሔራዊ ም/ቤትና የሊቢያ የሽግግር ም/ቤትም የተሰጣቸው ኃላፊነት ተመሳሳይ ፕሮግራም እንዲስፈጽሙ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሊቢያ ነዳጅ ሃብት በሊቢያ-አሜሪካዊው የፋይናንስ ሚ/ር አማካኝነት ወደ አሜሪካ ንብረትነት እየተዛወረ ነው፡፡ የሊቢያ ሕዝብም የነዳጅ ኃብቱን እያጣ ይገኛል፡፡ ጉዳዩን በውል ያላስተዋሉት ሊቢያውያን ደግሞ ጋዳፊን ለማስወገድ ከምዕራባውያንና ከኔቶ በተሰጣቸው መጠን የለሽ የጦር መሣሪያ እርስበርስ እየተገዳደሉ ራሳቸውን በ“ሥራ” ጠምደው ይገኛሉ፡፡ በምዕራቡ ዓለም የተመደቡትና በሶማሊያና በሊቢያ አገራቸውን በማሸጥ ተግባር ላይ የሚገኙት ባለሥልጣናት ራሳቸውን በዋሽንግተን፣ ብራስልስ፣ የዓለም ባንክ፣ … ጉዳይ አስፈጻሚነት ጠምደው ሳለ አልሻባብ ሶማሊያን የሊቢያ እስላማዊ ተዋጊ ቡድን (Libyan Islamic Fighting Group) ደግሞ ሊቢያን እያመሷት እንደሚገኙ ሁሉ በሶርያም የምዕራቡ ዓለም አጀንዳ ከተሳካ ተመሳሳይ እልቂትና ሕገወጥነት እንደሚከሰት ተንታኞች ይተነብያሉ፡፡
ሙሉ ስማቸውን ለመስጠት ያልፈለጉና “ዓለሙ” በሚል ስም መጠራት የመረጡ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት “ከአረብ ጸደይ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይላት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲወስዱ” መክረዋል፡፡ “ወያኔ/ኢህአዴግ ኢ-ዴሞክራሲያዊ የሆነ ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ እንደሆነ፤ መወገድም እንዳለበት ብዙዎቻችን እንስማማለን፡፡ ሆኖም ‘ከወያኔ/ኢህአዴግ የማይሻል የለም’ በሚል ፈሊጥ ብቻ ለውጥን በጭፍን በመፈለግ አገራችን ከማትወጣበት አዘቅት ውስጥ እንዳትገባ ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ ሁሉም ተቃዋሚ ኃይላት ሊከተሉ ይገባቸዋል” ይላሉ፡፡ “በየጊዜው የሚነሱ እንቅስቃሴዎችን ከአገሪቷ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ድጋፍ ሊሰጣቸውም ሆነ ሊነፈጋቸው ይገባል” የሚሉት እኚሁ ምሁር “ጠላትን የማስወገድም ይሁን ሥልጣን የመያዝ ፍላጎት ከዓለማችን ተጨባጭ ሁኔታ፣ ከአገራችን ታሪክ፣ መልከዓምድር፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ … እንዲሁም የወደፊት መጻዒ ዕድል አንጻር በጥንቃቄ ሊታይና ሊመረመር ይገባዋል” ይላሉ፡፡ “አለበለዚያ አሁን ወያኔ/ኢህአዴግን በመጥላት ብቻ የሚደረግ የፖለቲካም ሆነ ማናቸውም እንቅስቃሴም ሆነ ድጋፍ ወደፊት ባልተጠበቀ ሁኔታ መልኩን የቀየረ ጊዜ ማጣፊያው እጅግ ከባድ እንደሚሆን” አስጠንቅቀዋል፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
dawit says
useless explanation. I think you say that is not a terrist. Amazing!!!…and also you want to say don’t work or oppose againest EPRDF;unless your leder’s assined by USA.
ምኑን DAWIT ሆንከው says
ጋዜጠኛ አሻግሮ ማየት አለበት፣ አርቆ ማያውን ማመለካት አለበት፣ ፍርሃቱን በመሰለው ቋንቃና መንገድ ማስቀመጥ አለበት። ነጻ ሃሳብና ነጻ ሚዲያ ጥቅሙ እዚህ ላይ ነው።አንድ ሪፖርት ሲጻፍ ማሳያ መጥቀስ አግባብ ነው። በእውነታዎች ማጠናከር አንባቢን ለማሳሰብ ይረዳል።እናም ይህ ጽሁፍ በግሌ ካንድ ወደቀ፣ተሰበረ፣ደቀቀ፣ታመመ…. በላይ ትልቅ ጉዳይ የያዘ ሃሳብ ይመስለኛል።ኢህአዴግ ከግለሰብ አምልኮ ያልወጣ ምናምንቴ አስተሳሰብ ያለው አዋራጅ መንግስት ነው።መወገድ ይገባዋል።ግን እንዴት?በንፋስ፣ምንነቱ ያልታወቀ እሳት ላይ ቤኒዝን በማርከፍከፍ?ለዘመናት ሲሞከር ለነበረ ክፉ ሃሳብ በመገዛት?ወይስ እንዴት DAWIT የተባሉት ሰው የሰጡት አስተያየት ግራ የሚያጋባው እዚህ ላይ ነው።አሜሪካንን አቶ DAWIT አዳፍተውና ዘርረው ይጣሉልን ከዛ በሁዋላ እርስዎን፣የልጅል ልጅዎን እኛ ብቻ ሳንሆን ዓለም በተለይም ሲደቆሱ የኖሩትና እየተደቆሱ ያሉት ሁሉ ይገዙ ዘንድ ከስምምነት ላይ ይደርሳል ብዬ አስባለሁ።ለማንኛውም ለሪፖርቱ ክብር እንዳለኝ፣በልብ የሚነበብ እንደሆነ አምናለሁ።
አ.በ. says
ፅሁፉ ከኢትዮጲያ ጋር የሚያገናኘው ነገር ምንም አልታየኝም። ምዕራቡ ዓለም በኢትዮጲያ ላይ ላለው አጀንዳ ሕወሀት/ኢህአዴግን የመሰለ መንግስት የት ይገኝና። ገበሬዎችን እያፈነቀለ የሀገሪቱን መሬተ እንደ ጣቃ ጨርቅ እየሸነሸነ የሚቸበችብ፤ በኢንቨስትመንት ስም የሀገሪቱን ሀብት ለውጭ “ባለሀብቶች” በበመሸጥ ኢትዮጲያውያንን ጥሪት አልባ አድርጎ ለባርነት የየሚያመቻች “ስርዐት” ምን አጎደለብን ብለው ነው ዩ ኤስ አሜሪካ ና ዩ ኬ ሌላ መንግስት በኢትዮጲያ ላይ ለመትከል የሚነሳሱት? ኢትዮጲያ እኮ ዛሬ ባለቤት አልባ ሀገር ናት ማንም ባዕድ መጥቶ ያሻውን ዘርፎ የሚሄድባት።
satenaw says
“አዜብ ገባች አዜብ ወጣች – ሃይለማርያም ገባ ሃይለማርያም ወጣ” የመሳሰለውን ተራ “የሞላ ጎደለ” ዓይነት የወሬ ቁማር ለለመደ ይህ ሪፖርት ምኑም አይደለም:: ላስተዋለው ግን በርካታ ቁምነገሮችን ያካተተ ነው – የሚሰማ ጆሮ – የሚያነብ ዓይን ላለው::
Mesfin says
The world is in a whirlpool…and unless we think for but beyond Ethiopia we might get lost just like the Libyan’s did. I think that is the message and such messages are unfortunately a rarity in Ethiopian political commentators. Tread carefully Brother!!