የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስና ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በሕገ ወጥ የውጭ ሀገራት ገንዘብ ምንዛሪ በተሰማሩ ግለሰቦችና ድርጅቶቻቸው ላይ ጥናትን መሰረት ያደረገ እርምጃ መወሰዱን አስታውቋል፡፡
አገልግሎቱ ለሚዲያ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ባለፉት ሁለት ወራት በሕገ ወጥ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች ምንዛሪ ዙሪያ ሰፊና ጥልቀት ያለው ጥናት ሲካሄድ እንደነበር አመልክቷል፡፡
ችግሩ በጥናት ከተለየ በኋላም መረጃዎችንና ማስረጃዎችን መነሻ በማድረግ በተከናወነው ክትትል በሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ ላይ ተሳታፊ የነበሩ 48 ግለሰቦችና ከፍተኛ መጠን ያላቸው የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች እንዲሁም ከድርጊቱ ጋር የተያያዙ የባንክ ደብተሮችና ልዩ ልዩ ሰነዶች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል ነው የተባለው፡፡
በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች የውጭ ሀገር የምንዛሪ ዋጋን የሚተምኑ፣ የሚሰበስቡና ሰብሳቢዎችንም የሚያሰማሩ መሆናቸውን መግለጫው ጠቁሟል፡፡ ሕገወጥ ድርጊታቸውንም ሕጋዊ ፈቃድ ባላቸው የተለያዩ የንግድ ድርጅቶች፣ የችርቻሮ ሱቆች፣ ቡቲኮች፣ ግሮሰሪዎችና ሱፐርማርኬቶች ሽፋን እንደሚያከናውኑ፤ በተሽከርካሪዎች ላይም ጭምር ይፈጽሙ እንደነበር አመላክቷል፡፡
በሕገ ወጥ መንገድ የሚሰበሰበው የውጭ ምንዛሪ በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ከሀገር ለማሸሽ እንዲሁም የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አቅም በማሳጠት ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት በማስከተል ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመፍጠር ታቅዶ ሲከናወን እንደነበር በጥናት መለየቱን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መግለጫ ጠቁሟል፡፡
በወንጀል ድርጊቱ ተጠርጥረው ከተያዙት ውስጥም ለህወሓት ድጋፍ ከሚያደርጉ የሽብር ቡድኑ ደጋፊዎች ጋር በትስስር የሚሠሩና ቀደም ብሎም የውጭ ምንዛሪን በሕገወጥ መንገድ ወደ ትግራይ ሲያስገቡ የነበሩ ይገኙበታል፡፡ ይህም በተቀናጀ መልኩ በውጭም በሀገር ውስጥም ሀብት ለማሸሽና የውጭ ምንዛሪ አቅምን ለማዳከም ይሠራ እንደነበር ያሳያል ብሏል መግለጫው፡፡
እንደ አገልግሎቱ መግለጫ ሕገ ወጥ የውጭ ሀገራት ገንዘብ ዝውውሩ ወንጀል ከኢትዮጵያ እስከ ሶማሌ ላንድ ሀርጌሳ፤ ከዱባይና አሜሪካ እንዲሁም በሌሎች ሀገራትም ጭምር በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ቤተሰባዊ በሆነ ኔትዎርክ ጭምር የተደራጀና የሚታዘዝ ነበር፡፡ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ አስተላላፊዎቹ መካከል አንዳንዶቹ ከዚህ ቀደም በቁጥጥር ስር ውለው ፍርዳቸውን ጨርሰው የተለቀቁ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ከ100 ሺሕ ብር በላይ በማስከፈል ወደ ውጭ እንልካለን በማለት የዜጎችን ሀብትና ንብረት ሲዘርፉ የነበሩም በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልና በውጭ ምንዛሪ ዝውውሩ በነበራቸው ተሳትፎ እንዲያዙ ተደርጓል፡፡
መንግሥት ሕገወጥ ድርጊቱን ለመከላከል የውጭ ሀገራት ገንዘቦች ከኢትዮጵያ የሚወጡባቸውን መንገዶችና ስልቶች በመረጃ በመለየትና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ጥብቅ ቁጥጥር ማድረጉንና በወንጀለኞች ላይ እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጫው አስታውቋል፡፡ የሀገርን ሀብትና ንብረት ዘርፈው ገንዘቡን በውጭ ምንዛሪ በማሸሽ ከሚፈጠሩ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ሀገሪቷን ለመታደግ የሚደረጉ ጥረቶችንም በከፍተኛ ትኩረት እየተከታተለና አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
ኅብረተሰቡ ሕገወጦች በቁጥጥር ሰር እንዲውሉ ጥቆማ በመስጠት ያበረከተው አስተዋጽዖ ከፍተኛ በመሆኑ ምስጋናውን ያቀረበው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በቀጣይም ከደኅንነትና ከጸጥታ ተቋማት ጎን በመሆን ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርቧል፡፡
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply