ታታሪው ሰው ነገሮች ሁሉ ከተጠናቀቁ በኋላ መግለጫ ሰጠ። መግለጫ እንዲህ በረከሰበት ዘመን እሱ ገላለጠው!!
“የግድቡ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሙሌት ተጠናቅቋል። እንኳን ደስ ያለን” አለ።
እኔ ግን ከፋኝ!! ቅር አለኝ! ደነገጥኩ!! “ግድቡን የሸጠው ጠቅላይ ሚኒስትር” የሚለው ትንታኔ ተናነቀኝ። ተጽፎ፣ ተነብቦ፣ ተቀርጾ፣ ተቀናብሮ፣ ስምና ባለቤት ኖሮት ለአለም የቀረበው ትንተና ትዝ አለኝ። ዕውቀት ቀፈፈሽ።
ስዩም መስፍን ያለቀሰለት ግድብ ትዝ አለኝ። ጌታቸው ረዳ ሲሸጥ ያየው ግድብ ትዝ አለኝ። አሜሪካና አለም ባንክ፤ ግብጽና ጂዳ ተጠቃቅሰው የገዙት ግድብ ትዝ አለኝ። ተደራዳሪዎቹ እየቆራረሱ የቸበቸቡት ግድብ ትዝ አለኝ። ያለ ልምድ፣ ያለ እውቀት እና ያለሀገር ፍቅር የተመራው የድርድር ቡድን አይኔ ላይ ድቅን አለብኝ!!
ይሄ ሁሉ የክስ ናዳ፤ ይሄ ሁሉ የትንተና ካብ ስድስት ወር አልሞላውም። በጥናት ስምም አዳራሽ ሙሉ ሰው ሰብስበው መሸጡን ነገሩን። ፈጠራቸው ግቡን አልመታ ቢል፣ ይህንን አይቶ ዝም አለ የተባለው የኢትዮጵያ ህዝብም ተዘለፈ። በነሱ ዘንድ፣ ሀሜትን አለማስተጋባትም ያስወቅሳል።
ኧረ ከቀናት በፊትና በሰኔ ወር መጨረሻም ይህንኑ ደጋግመው ሲነግሩን ነበር። ግድቡን እየጨረሰው ነው ሳይሆን እያበላሸው ነው፤ እየገዛ ነው ሳይሆን እየሸጠ ነው አሉን። ህዝብን በሀሜት ለማነሳሳትም ሞከሩ።
አየህ ወገኔ!
የዘንድሮ ፖለቲካ ዋጋዋ ይህቺ ናት። የዘንድሮ ክስ እንዲህ ጋሽባለች። የዘንድሮ ተንታኝ ይህቺ ናት ምጥቀቷ። የሴራ ቁመት ከመሬትም አጥሯል። ውርደት ራሱ ተዋርዷል። ሀሜት ጥንቡን ጥሏል። አናሊሲስ ኦናሊሲስ ሆኗል። ፖለቲካ አርጅቶ የሕወሓት መጫዎቻ ሆነ።
ምንድን ጉድ ነን ግን?
መገንባቱ ባይሆንልን በትክክል ማፍረስ እንደምን ተሳነን? ምስጋናው ቢያጥረን እንደምን በወጉ መሳደብ አቃተን? መልሱ ሰውዬው ጋ ብቻ ነው ያለው።
“ዝም ብለህ ስራ” ይልሃል። ሰውዬው ሲሰራ ብቻ ሳይሆን፣ ከጨረሰ በኋላም አይፎክርም። ሌላ ብዙ የሚጨርሳቸውን ስራዎች እያማተረ ይጓዛል። መጨረስ እንጂ ማስጨፈር አይወዱም።
“እያዳሜ ድጥ ድጡን እየመረጠ ሲረግጥ እየተከተልክ አትፍረጥ” ይልሃል። እንዲህ ያለ ነበር የዛሬው መግለጫ። ከሳሾቹን መደበቂያ ነፈጋቸው። በያደፈጡበት ደመደማቸው። የትም ያልዋለ ገበያ አስተዋወቀን።
የሸጠው ገዥ ሆኖ መጣ። ሻጩ ገዝቶ መጣ። ከገዙስ አይቀር እንዲህ ነው። ድሮም በሽታቸው መግዛቱ ነበር። ድርብርብ ሞት ይሉሃል ይሄ ነው። ካተረፉስ አይቀር እንዲህ ነው።
አዲስ የግንባታ ጥበብ ታየ። ናደው ሲሉት ካበው። ‘የዐብይ አህመድ ተች’ በለው ይሄንን የግንባታ ጥበብ። አየህ! ባህሩ ሞልቷልና የሁለቱ መርከቦች መዳረሻ ታወቀ። ባለቀዳዳው ሰጥሟል፤ ሽንቁር የለሹ በኩራት እየቀዘፈ ነው።
ያቺ ሴራና ተንኮል፤ አላዋቂነትና ድርቅና የበሳሳት መርከብ ሰጠመች። ሸክሟ ይዟት ዘቀጠ። ደንዳናይቱ፤ ብረት ለበሱዋ አንጥራ መላሿ ግን በኩራት እየቀዘፈች ነው።
ሰላም፣ ትህትና እና ብልጽግናን የሸከፈችው መርከብ ግን በድል እየተንሳፈፈች ነው። ሁሉም የሸክሙ እኩያ ነው።
ዐቢይ አህመድ ዐሊ!
እንዳንተ የተዋጋ ማን ይሆን? ስንቱን ልፍስፍስ አለፍከው? ብርቱ ገጥሞ መውደቅ እኮ በስንት ጣእሙ! እንዲህ እየተጎተትክ፤ በዚህ ሁሉ የገልቱ ልፊያ ውስጥ እዚህ ጋ መድረስ ከጥንካሬ ያይላል!!
ስንቱ ሊያወርድህ ወረደ? አንተ ግን አልክ:- “የግድቡ የመጀመሪያው ምእራፍ ሙሌት ተጠናቅቆል” ብለህ እንደዋዛ አበሰርከን።
ራማፎሳ ሳቅ ካልገደለው ይገርመኛል! ሙሳ ፋቂ መገረም ካላፈነው ይደንቀኛል። አይኔን ይቅር በለው!! ተገድቦ ሳየው ባህር ያየው መሰለኝ። ወደብ ትዝ አለኝ! ናፍቆት ነው። መበደል አይጣልህ! ማጣት ክፉ ነው። ውቅያኖስ መሰለኝ! የብዙ ሚሊዮኖች እንባ መሰለኝ።
ሀቅ ያኮራኛል! እውነት ያፈካኛል!! ግድቡ መሙላት ጀምሮአል።
አንተ ግን ሞልተህ ተርፈሃል!!
ገስግስ አለቃ!
__________
እጅግ ደስ ያሰኛል!!
የዘመናዊ እርምጃችን ጉዞ እውን ሆኖ ሲጀመር ማየት፣ የከፍታ ዘመን ጅማሮ ከትርክት ወደ እውን ሲተረጎም በእውን ለማየት መታደል፣ የራስን ሀያል አድዋ ሰርቶ ማሳየት፣ … በብዙ ምክንያት ለዚህ ቀን መብቃት የእውነት ደስስስ ያሰኛል። ለኔና ለትውልዴ ይህ የሁልጊዜ ሰበር ድላችን ነው። በወገኔና ሀገሬ ላይ የደረሰው እጅግ አሳፋሪና አስደንጋጭ ክስተት የሰበረውን አንገት፣ እንዲህ ካለው ግዙፍ ድል ውጪ ምን ቀና ማድረግ ይቻለው ነበር?
ክብር ለእናንተ…
ሀሩሩና አረሩ፣ ሽብሩና ሁከቱ፣ ዲፕሎማሲውና ጫናው፣ ዛቻና ፉከራው፣ … ሳይገታችሁ የትውልዳችንን አድዋ እውን ላደረጋችሁ ሁሉ ይሁን!!
ያዝ! ቢቢሲ የማይሰራው ዜና ርእሱ አንዲህ ይላል፤
“ከሳምንታት በፊት ትፈርሳለች፤ ትበታተናለች የተባለችውን ሀገር የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የህዳሴ ግድባቸውን የመጀመሪያ ምዕራፍ ሙሌት መጠናቀቅ አብስረዋል!”
ሀምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም… ታላቅና ታሪካዊ፣ እንዲሁም ጨዋታና አሰላለፍ ቀያሪው ልዩ ቀን!!
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣበ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply