“…መሃል ፒያሳ ላይ መርከብ እንዲያንሳፍፍልዎ ነበር እንዴ የፈለጉት? ወይስ አይሮፕላን አኮብኩቦ እንዲያሳርፍልዎ?”
አልታዬ የተባሉ ጸሃፊ በቅርቡ “…ለረጅም አመታተ የጣሉትን ብዕር ድር ካደራበት ሰገባው…” መዝዘው “የተቆለፈበት ቁልፍ” በቃላት ቁልፍ ተቆላልፏል!” በሚል ርዕስ አስነብበውናል። ዶ/ር በፍቃዱ በቀለ በ“የተቆለፈበት ቁልፍ” መጽሃፍ ላይ በጻፉት ግምገማ ላይ ተነስተው ትችታቸውን ያስነበቡን አልታዬ፣ ከስነ-ጽሁፋዊ ትችታቸው በፊት ያስቀደሙት፣ ዶ/ር በፍቃዱ፣ በ‘የተቆለፈበት ቁልፍ’ መፅሐፍ ላይ ያቀረቡት ጽሁፍ “…የወዳጅነት ፍቅር፣ አክብሮትና ስሜታቸውን ነው … ወይስ በእውነት ምክንያታዊ ትችታቸውን?!…” በሚል፣ ምናልባትም “speculation” (ተጨባጭ ማስረጃ የሌለው “ቲዎሪ”) ነው። እንኳንስ አይደለም “ወዳጅ”፤ አባት እና ልጅ ቢሆኑስ አልታዬን ምን አገባዎት? ልጅ የአባቱን፣ አባት የልጁን ስነ-ጽሁፍ ስራ ቢተች ምን ችግር አለው? ትኩረትዎን ለምን ሃሳቡ እና ጽሁፉ ላይ አላደረጉም? ወዳጅነታቸውንስ መጥቀስ ለምን አስፈለገ? “speculation” ካልሆነ ደግሞ የዶ/ር በቀለን እና የደራሲውን ወዳጅነት አልታዬ ያውቃሉ? ምናልባትም ጽሁፉ ከእውነተኛ ስነ-ጽሁፋዊ ትችት ይልቅ “character assassination”/ሃሳብን ሳይሆን ግለሰብን ማጥቃት (ad hominem) አያስመስልብዎትም?
በመሰረቱ አልታዬ መጽሃፉን የተቹበት አንድ እና አንድ ጉዳይ ቢኖር ደራሲው ዶ/ር ምህረት ደበበ የተጠቀሙበትን ቋንቋ ነው። “….በ‘የተቆለፈበት ቁልፍ’ መፅሐፍ ውስጥ ተመሳሳይ ቃላት ከመጠን በላይ ተደራርበው ነው የምናገኘው…..” ሲሉን፣ ባጭሩ “ለምን ቃላት ተደጋጋሙ” ነው። በግምት 99% የሚሆነው የአልታዬ ትችት “ለምን ቃላት ተደጋጋሙ” የሚል የመሆኑን ያህል፣ ተደጋገሙ ላሏቸው ቃላት ምትክ የሚሆኑ ሌሎች የቃላት አማራጮችን አንዴም (እደግመዋለሁ፤ አንዴም፣ አንዲት ቃል እንኳን ተክተው) አላሳዩንም። ከመጽሃፉ ውስጥ የከበብቧቸውን ቃላት እና ሃረጋት እየጠቀሱ (“ይሄ”፣ “ያ” ወዘተ የሚሉ ቃላት ባይገቡ …እንዲህ…..ቃላት ያልተደጋገሙበት ዓ/ነገር ወይም አንቀጽ ይሆን ነበር…”) ብሎ መተቸትም ያባት ነው። በአንድ ሙሉ አንቀጽ (አንዳንድ እስከ 500 በሆኑ ቃላት በተገነባ) ውስጥ አንድ ቃል ለምን ሁለት ጊዜ ተጠቀሰ…” በሚል እና በመጽሃፉ የሰፈሩትን ተመሳሳይ ቃላቶች እየለቀሙ በማክበብ “ቃላት ተደጋገሙ” ማለት ሙያዊ ትችት አይደለም።
ከስነ-ጽሁፍ አላባዎች ውስጥ አንዱ የሆነው “ቋንቋ” አልታዬ ካዩበት ማዕዘን (የቃላት መደጋገም) በላይ ቢሆንም፣ ቃላት ካለቦታቸው እየተሰደሩ ሲደጋገሙ፣ የቋንቋን ውበት እንደሚያደበዝዙት እርግጥ ነው። አልታዬ ተደጋገሙ የሚሏቸውን ቃላት፣ በሌላ የተሻለ ቃል፣ ቃላት ወይም ሃረግ ሊገለጹ ይችሉ የነበሩ መሆናቸውን እና ባቀረቧቸው ምትኮች ሳቢያ ቋንቋው የተሻለ መሆኑን ቢያሳዩን ኖሮ፣ አላግባብ ተድጋግመው ቃላት የባከኑበት ጽሁፍ መሆኑ ይገለጽልን ይሆናል። አልታዬ የከበቧቸው ቃላት ሁሉ አንድም ቦታ አላግባብ የባከኑም፣ የቋንቋውን ውብት ያደበዘዙም አይደሉም። “… እኔ ነኝ” ያለ የአማርኛ ቋንቋ ሊቅ ቢመጣ፣ አልታዬ በቀኝ በኩል ከመጽሃፉ ቀድቶ በከበባቸው አብዛኛዎቹ ቃላት ምትክ ሌላ ቃላት ቢያስገባ፣ ከደራሲው ሃሳብ የተሻለ ቀርቶ፣ ያለውን ሃሳብ መግለጽ የሚችል ዓ/ነገር መስራት የሚችል አይመስለኝም (ይሄ የቤት ስራ ለአልታዬም ነው)።
“የተቆለፈበት ቁልፍ” በሚል ርዕስ በተጻፈ መጽሃፍ፣ “ቁልፍልፍ” በሚል ርዕስ በተጀመረ ምዕራፍ፣ በመጀመሪያው አንቀጽ ላይ “ቁልፉን” የሚል ቃል ለምን ተጠቀሰ የሚል ትችት ማቅረብ የስነ-ጽሁፍ እውቀት ድህነት መገለጫ ነው። በሁለተኛው አንቀጽ፣ መጀመሪያ መስመር ላይ “ተቆልፎአል” በሚለውስ ምትክ ምን አይነት ቃል/ሃረግ ሊገባ ይችል ነበር?–“ተዘግቷል?”፣ “ተከርችሟል?”፣ “ተጠርቅሟል”?
አልታዬ “ቋንቋ”፣ እንደ አንድ የስነ-ጽሁፍ አላባ፣ ምን ማለት እንደሆነ ያወቁ አይመስለኝም። ደራሲው ዶ/ር ምህረት ደበበ የተጠቀመበት የቃላት ድግግሞሽ፣ አንዱ የአጻጻፍ ስልት ነው፣ በእንግሊዝኛ “Repetition” ነው። የመጽሃፉ ርዕስ “የተቆለፈበት ቁልፍ” ራሱ “Repetition” አለው፣ ድግግሞሹ የፈጠረው (በግጥም ውስጥ እንደምናየው የመጨረሻው ድምጽ መመሳሰል አይነት) “ዜማ” አለው፤ በእንግሊዝኛው “Rhythm” እንዲሉ። ግርምታ የሚፈጥር ርዕስ ነው፣ የመጽሃፍ ርዕስ (Eye catchy) መሆን አለበት እንደሚሉት ነው። ርዕሱ ድንቅ ነው። በሁለተኛው አንቀጽ ላይ የተጠቀሱትም የ“ቁልፍ” እርባታዎች፣ ርዕሱን የሚገልጹ፣ ታሪኩንም በሚገባ ለማስተዋወቅ የገቡ ናቸው፣ ( ‘የተቆለፈበት ቁልፍ’ የሚለውን ርዕስ እያሰብን…“ወይ ጉድ! ገና ካሁኑ መኪናው ውስጥ መግቢያ የሆነውን የመኪናውን “ቁልፍ” ረስቶ “ቆልፎበት” ወርዶ፣ የቤቱም “ቁልፍ” እዚሁ መኪናው ውስጥ “ተቆልፎበታል”…. እና ‘ይሄን ሰውየ ምን ሊውጠው ነው?) የሚል የንባብ ጉጉት (suspense) ያጭራል አንቀጹ። ደራሲው በትክክለኛው መቼት (setting)፣ እጅግ ብቃት ባለው (efficiently) ሁኔታ ነው የቃላት ድግግሞሹን “Repetition” የተጠቀመበት።
“Repetition in literature” ወይም “Repetition as a literary device…” የሚለውን ቀድተህ ጎግል ላይ ብትለጥፈው ምናልባትም በሺዎች የሚቆጠሩ፣ “Repetition is a powerful force in fiction” አይነት ዓ/ነገሮች፣ ከተለያዩ ምንጮች ተኮልኩለው ይደረደሩልሃል። ድግግሞሽ የልብ ወለድ ድርሰት አጻጻፍ አንዱ “ጉልበታም” ስልት/ዘዬ ነው…።
በቀኝ በኩል አላታዬ በሶስተኛው መስመር ላይ ያከበቡት “ከሰው” የሚለው ቃል፣ በሚቀጥለው በ4ኛው መስመር ላይ ከተጠቀሰው “ሰው” ጋር መደጋገሙን ለማሳየት ሲሉ ያደረጉት ነው ብለን እንለፈው። ደህና። በ4ኛው መስመር ላይ የተጠቀሰው “ሰው”፣ በምን ሊተካ ይቻል ነበር? “ተሳፋሪ?” አያስኬድም። ምክንያቱም ሰው የሆኑትን ወያላውን፣ ሾፌሩንም ታናግራለች። ወይስ ደራሲው ለአልታዬ ሲል አንበሳ ያሳፍርለት እንዴ? አንቀጽ ሶስት ላይ በተጠቀሰው “ታክሲዎች” ምትክ ደራሲው መሃል ፒያሳ ላይ መርከብ እንዲያንሳፍፍልዎ ነበር እንዴ የፈለጉት? ወይስ አይሮፕላን አኮብኩቦ እንዲያሳርፍልዎ?”
አልታዬ ራሳቸው “…እንደተቆለፈበት ተመጋቢ ዘጋኝ – “የተቆለፈበት ቁልፍ” ሲሉን እና በአንድ ዐ/ነገር ውስጥ ሶስት ጊዜ “ቁልፍ” ሲሉን “Rhythmic Repetition” ነው። እሳቸው የተጠቀሙበትን ይህን ጥበብ ሌላው መጠቀም የለበትም የሚል ህግ ማን እንዳወጣላቸው የሚያውቁት አልታዬ እና የአልታዬ የስነ-ጽሁፍ እዚሃር ብቻ መሆን አለባቸው። እውነት ለመናገር አልታዬ “…ከላዩ ላይ ጸያፍ ነገር ዓይቶ ወስፋቱ “እንደተቆለፈበት” ተመጋቢ ዘጋኝ…” በሚል የተጠቀሙበት ቋንቋ ልቅ ነው፣ ቢያንስ ለዚህ መጽሃፍ ደራሲ አይገባውም። ደግሞስ ገንቢ የሆኑ ቃላትን በመጠቀም መተቸት አይቻልም እንዴ?
“ቋንቋ” ሃሳብ መግለጫ ነው፤ ሃሳብን በቀላሉ እና በአጭሩ፣ ግልጽ እና በሚገባ ቃላት እና ዓ/ነገሮች አንሰላስሎ ምሉዕ ሃሳብ ማቅረብ ከቻለ፣ የሚፈለገው እሱ ነው። ደራሲው በዚህ ተዋጥቶለታል፣ እንዲያውም አጫጭር ዓ/ነገሮች፣ ግልጽ እና ቀላል አማርኛ መጠቀሙ፣ ከበዓሉ ግርማ አጻጻፍ ስልት ጋር ይመሳሰላል። እኔ አንድም የባከነ ቃልም ሆነ ዓ/ነገር አላገኘሁም።
“…አንድን መፅሐፍ “ምሉዑ” ከሚያስኙት መስፈርቶች አንዱና ዋናው ደራሲው ሃሳቡን ለመግለፅ የሚጠቀመበት የቋንቋ ውበት ነው…” ከሚል እና ስለቋንቋ ውበት ከሚጨነቅ ሰው “…በዚህም ሳቢያ ሀረጋት ሳይወዱ በግድ መንትተው የቃላት ማጥ ፈጥረዋል…” የሚል የቋንቋ ድህነት ማንበብ ያለብን አይመስለኝም። “…ቃላት ከመጠን በላይ…ተደራርበው ነው የምናገኙው። በዚህም ሳቢያ ሀረጋት ሳይወዱ በግድ መንትተው የቃላት ማጥ ፈጥረዋል። ይህ ደግሞ አንባቢን በተገቢው ፍጥነት ከታሪኩ ፍሰት ጋር አብሮ እንዳይወርድ ያዳልጡታል…” በሚለው ውስጥ ያለው “ማጥ”፣ በእንግሊዝኛው “ሜታፎር” የሚሉት ምስል መከሰቻ ይመስለኛል። አልታዬ “…በጉጉት እና በፍጥነት እያነበቡኩት የነበረው ታሪክ ድንገት ቃላት ስለተደጋገሙብኝ፣ ንባቤን መቀጠል አልቻልኩም”፣ ምክንያት? “…በመነተቱት…” ቃላት ምክንያት “ማጥ” አዳልጦኝ ወደቅሁ..” እያሉን ነው። “መንትተው” እና “ማጥ” በዓ/ነገሩ ውስጥ የተፈለገውን ምስል አልከሰቱም።
“…የመፅሐፉ ጠርዝ ቀኝ እጄን እንደመዘነ አጠፍቁት። በጅምር።” የሚለውንም ለመረዳት ብዙ ጊዜ ፈጅቶብኛል፣ ለዚያውም ግብቶኝ ከሆነ እድለኛ ነኝ። ሲመስለኝ “ጣቶቼ ለንባብ ገጾቹን መግለጡን ስላልገፉበት (ቃላት በመደጋገማቸው ምክንያት?)፣ ገጾቹን የማልገልጥበት እጄ ሚዛኑን መጠበቅ ስላቃተው፣ መጽሃፉ አዘነበለብኝ…?” ማለት ይሆን? የመጽሃፉ ክብደት እጅዎ ላይ አረፈ? ወይስ የእጅዎ ክብደት መጽሃፍዎ ላይ? አልታዬ እባክዎ ይንገሩን፤ በግራ እጅዎ ነው ወይስ በቀኝ እጅዎ ገጹን እየገለጡት የነበረው? በአውራ ጣትዎ ነበር? ወይስ በቀለበት ጣትዎ?… ተሆነ አይቀር ይንገሩን እንጂ!… ይኼን ያህል “መራቀቅ” ያስፈልግ ነበር? እውነት ለመናገር ቋንቋ የሞተበት ዓ/ነገር ነው።
አልታዪ ደጋግመው በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ አስገብተው “ሃያሲው” እያሉ የሚገልጿቸው ዶ/ር ፍቃዱን፣ “ሃያሲ” የሚለው ስም አይገባህም (“ገ”ን ጠበቅ)፣ አንተ ብሎ ሃያሲ…” የሚል እንድምታ አለው። ዶ/ር ፍቃዱን በሚጽፋቸው ጽሁፎቹ አውቀዋለሁ። ደጋግሞ በሚለቃቸው ጽሁፎቹ–ስለ ስነ-ጽሁፍ፣ ኢኮኖሚ፣ ሳይንስ … ወዘተ ዘርፎች የመፈላሰፍን አስፈላጊነት ደጋግሞ ጽፎ የማነብበው ሰው ነው። ሳላነብብ ያለፍኩት የዶ/ር በፍቃዱ ጽሁፍ ያለ አይመስለኝም። ማንበብ ባህላችን ያለመሆኑ ችግር እንዳለ ሆኖ፣ ጽሁፎቹ ረጃጅም በመሆናቸው ምክንያት ብቻ ሊያነብለት የሚችለውን ሰው ብዛት የሚቀንስ የመሆኑ ጉዳይ እያሰብኩ ሁሌም የምቆጭለት ጸሃፊ ነው። ይሄ የኔ ጽሁፍ ሰሞነኛ ነው። አንዴ ካነበብህ የምትደግመው አይደለም። የዶ/ር በፍቃዱ ጽሁፎች ለብሄራዊ ልማት እና እድገት እንደ “ሪሶርስ” ሊያገለግሉ የሚችሉ የምርምር ስራዎችም ናቸው። ራዕዩ ለአገራችን ብሄራዊ ችግሮች፣ ለወደፊት እድገት እና ልማት ፈር ቀዳጆችም ጭምር ናቸው። ብዙ ጊዜ የሚያነሳቸው “ስለ ቆንጆ ቆንጆ የሆኑ ስእሎች፣ ስነ-ጽሁፎች (literary/artistic beauty” ማለቱ ነው)፣ በስነ-ጥበብ፣ ኢኮኖሚ፣ ወዘተ… ስለመፈላሰፍ… ወዘተ….” በሚሉ ስራዎቹ አውቀዋለሁ። ስለ ደራሲው “የዘመናችን ፈላስፋነት” በትችቱ ውስጥ ጠቅሶ የጻፈው ዶ/ር ፍቃዱ፣ ያን ለማለት ሙሉ ስልጣን (authority) ያለው ሰው እንደሆነ እመሰክራለሁ። እናም “የተቆለፈበት ቁልፍ”ን ገዝቼ አነባለሁ፣ ሌሎቹንም አበረታታለሁ። አልታዬ መቼም “…እንዴ! ባላነበብከው መጽሃፍ ላይ ነው እንዴ አስተያየት የምትሰጠው …?” የሚል የሞኝ ጥያቄ እንደማያቀርቡብኝ ተስፋ አደርጋለሁ።
እውነት ለመናገር እነ “አሸናፊ ዘ-ደቡብ አ.አበባ …”ን ካነበበ አንባቢ ብዙ እንጠብቃለን። በነገራችን ላይ አልታዬ “አሸናፊ ዘ-ደቡብ አ.አበባ”ን ጨርሶ አላነበቡትም። አሸናፊ የሚታወቅበት አንዱ እና አንዱ የአጻጻፍ ስልቱ ድግግሞሽ መጠቀሙ ነው። ይሄ የሱ፣ የራሱ ብቸኛው የአጻጻፍ ስልቱ ነው። ለምሳሌ እኔና እርስዎ “አበበ ሱቅ ውስጥ ገባና፣ በልኩ ልብስ ካስለካ በኋላ፣ ገንዘቡን ከፍሎ ወጣ…” ብለን የምንጽፈውን፣ አሸናፊ ዘ-ደቡብ አ.አ ቢያገኘው “… አበበ ሱቅ ግብቶ፣ በልኩ አስለክቶ፣ ገንዘቡን አስልቶ፣ ለካሼሪዋ ሰጥቶ፣ ከሱቅ ወጥቶ….” ብሎ ይጽፈው ይመስለኛል። የአሸናፊ ዘ-ደቡብ ዘዬ የቃል “Rhythmic Repetition” ሲሆን፣ የደራሲ ምህረት ደበበ ደግሞ በቃላት ድግግሞሽ “word Repetition” የሚገለጽ የአጻጻፍ ዘዬ መሆኑ ነው–“Repetition is a powerful force in fiction”
አልታዬ ሆይ! እነ “አሸናፊ ዘ-ደቡብ አ.አበባ፣ ዳግላስ፣ ወዘተ…”ን መጥቀስ ብቻውን አንባቢም ሃያሲም ቢያስመስልዎት እንጂ፣ አንባቢም ሃያሲም ሊያደርግዎት አልቻለም። ከቻሉ፣ አንብበው፣ ስለሚጽፉበት ጉዳይ አውቀው እና አስተውለው ቁብ ያለው ጽሁፍ ይጻፉልን፣ ካልሆነ ግን “…ድር ያደራበት ብዕርዎን…” እባክዎ ወደ ሰገባው ይመልሱት።
መዝገቡ ሊበን፣ ከሜነሶታ
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply