ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) የተመሠረተባቸው አዕማዶች ሁለት ናቸው። እነዚህም ከጎሣ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ እንስጥ! እና ሁላችንም አብረን ነጻ ካልወጣን ማንም ብቻውን ነጻ ሊሆን አይችልም! የሚሉት ናቸው። እነዚህን ግዙፍ መርሆዎች ተግባራዊ ለማድረግ የሚጠቀምባቸው ስልቶች ደግሞ ዓመጽ፣ ጥላቻ፣ ክፋት፣ ምቀኝነት፣ ዘረኝነት፣ ወገንተኝነት፣ ወዘተ ሳይሆን ሰብዓዊ ዘርን ከልዩነት በጸዳ ጽኑ ፍቅር በማክበር፣ በመውደድና ለሌላው ሰው ከልብ በመነጨ ቅንነት በሚያስብ አመለካከት ላይ በመመሥረት ነው። የእነዚህ ተግባራት መዳረሻ ደግሞ በአገራችን ላይ ፍቅር፣ ሰላም፣ ኅብረት፣ ዕርቅና ፍትሕ ማስፈን ነው።
ከላይ የጠቀስናቸው መርሆዎች በተባለው አካሄድ ተፈጻሚ ይሆኑ ዘንድ የጋራ ንቅናቄያችን ለበርካታ ዓመታት ያለመታከት ሲሠራ ቆይቷል። ለዚህም ነው ኢትዮጵያውያን በቡድንም ይሁን በግል በተቸገሩ ጊዜ ያሉበት ድረስ በመሄድ ለችግራቸው መፍትሄ ስንሰጥ የቆየነው። ይህ ሰብዓዊነትን ቅድሚያ ያደረገ አሠራራችን አገራችን ለተዘፈቀችበት ዘርፈብዙ ችግሮች በተለይም ጎሣ/ብሔር ነክ ለሆኑት ተገቢውን ምላሽ በመስጠት በአገር ውስጥና በውጭ በርካታ ደጋፊዎችንና አባላትን ለመማረክና ወደ ዕቅፉ ለማምጣት ችሏል።
ከዚህ አንጻር አዲስ የተሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ የጋራ ንቅናቄያችን በድርጅት ደረጃ ሲያራምዳቸው የቆያቸውን መሪ ሃሳቦች እርሳቸው በመንግሥት ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ መጀመራቸውን ስንመለከት ጊዜ ሳንወስድ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለንን አድናቆትና ድጋፍ ሰጥተናል፤ ሌሎችም ከእርሳቸው ጋር አብረው እንዲቆሙ ጥሪ አድርገናል፤ አስተባብረናል። ይህንን ያደረግነው ከእርሳቸው ንግግሮችና ተግባራት አዲስ ኢትዮጵያ ከአድማሱ ብቅ ስትል በመመልከታችን ነው። ይህም ለጋራ ንቅናቄያችን እንደ ድርጅት የአዲስ ኢትዮጵያን ትንሣኤ አብስሮልናል፤ ለሕዝባችንም ተመሳሳይ እንደምታ ያለው መልዕክት እንደሰጠ እናምናለን።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ያከናወኗቸውን አመርቂ ተግባራትን በጥሞና ሲከታተል የቆየው አስተዋዩ የአገራችን ሕዝብ ቅዳሜ ሰኔ 16፤ 2010ዓም የምስጋና ሰልፍ ለመውጣት ማቀዱን ሰምተናል። አኢጋን ይህንን በሕዝብ አነሳሽነት የተዘጋጀና ከማንኛውም መንግሥታዊም ሆነ ፓርቲ ተጽዕኖ ነጻ የሆነ ሰልፍ እንደተባለው በቅንነት በመቀበል በሙሉ ልቡ ይደግፋል። የጋራ ንቅናቄያችን ይህንን የምስጋና ትዕይንተ ሕዝብ የሚደግፈው በሁለት ምክንያቶች ነው፤ አንደኛው ከላይ እንደገለጽነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባጭር ጊዜ ውስጥ ላከናወኑት ፈጣንና ድፍረትን የተላበሰ የለውጥ ተግባራት ተገቢውን ምስጋና ለመስጠት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በጀመሩት ፍጥነት የበለጠ የተሃድሶ ሥራዎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ለማበረታታት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሃድሶ እርምጃ መሠረት፣ ዋልታና ማገር በመሆን የበኩላቸውን እየተወጡ ያሉትን የተሃድሶው ሞተር የአቶ ለማ መገርሳ ቡድን እንዲሁም አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና አጋሮቻቸው እያከናወኑ ለሚገኙት ቀልብ የሚስቡ ተግባራት ሊደነቁና ሊወደሱ ይገባቸዋል። የእነርሱንም ፈለግ በመከተል የደቡብና የትግራይ ሕዝብ ድርጅቶችና ሌሎችም አጋር ፓርቲዎች በተሃድሶው ባቡር ላይ በፍጥነት እንዲሳፈሩ ጥሪ እናደርጋለን።
ከዚህ ሌላ የቅዳሜው ትዕይንተ ሕዝብ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ወገኖች የተቻላቸውን እንዲያደርጉ፤ ህዝባችንም ከሰልፉ ጋር በተያያዘ ነቅቶ እንዲጠብቅ አደራ እንላለን። በዚህ ሰልፍ የሚከናወነው ተግባር፣ የሚሰማው መፈክር፣ የሚነገሩት ቃላት ወዘተ በቀጣይ ለሚደረጉ ሰልፎች ሁሉ አስተማሪና ፈርቀዳጅ መሆን አለበት።
ስለዚህ ሰልፉ ፍቅር የሚገለጽበት እንጂ ጥላቻ የሚነግሥበት መሆን የለበትም፤ የተስፋ ራዕይ ይበልጥ ፈንጥቆ የሚታይበት እንጂ የክፋት ጽልመት ሥፍራ እንዲይዝ የሚፈቀድበት መሆን የለበትም። የጎሣ ፖለቲካ በሰብዓዊነት ተሸንፎ ኢትዮጵያዊነት ደምቆ የሚታበት ሊሆን ይገባል። የመበሻሽቅ፣ የመጠላለፍ፣ የመነታረክ፣ የመጣላት ፖለቲካ ይከፋፍለናል እንጂ አይደምረንም፤ ይቀንሰናል እንጂ አያበዛንም።
ስለዚህ ይህንን ታሪካዊ ቀን በእኩይ ተግባራችሁ ለማጠልሸት የምታስቡ ወገኖች ካላችሁ ትንሽ ቆም ብላችሁ ለራሳችሁ ብታስቡ ይበጃል እንላለን። የኢትዮጵያን ሕዝብ ተስፋና ራዕይ (ከተሳካላችሁ) ነጥቃችሁ ኅልውና ይኖረናል ብላችሁ ባታስቡ መልካም ነው። ሁላችንም እንጠፋፋለን እንጂ ከዚህ የሚጠቀም ማንም አይኖርም። ለፍቅርና ለሰብዓዊነት መሸነፍ ድክመት ሳይሆን ድፍረትና ጀግንነት መሆኑን አስባችሁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ እንደሚሉት ያምርብናልና “እንደመር”። በትንንሹ እዚህና እዚያ ሆነን ተሸራርፈን ኅብረት አለን ከምንል፤ በይቅርታ፣ በፍቅር እና ፍትህ ላይ በተመሠረተ ዕርቅ ሳንሸራረፍ ምልዑ እንሁን። በጥላቻ፣ በተንኮልና በክፋት ከምታተርፉት እጅግ የበለጠ ጥቅምና ትርፍ በመደመር፣ በአብሮነት ከሁሉ በላይ ደግሞ በሰብዓዊነት ታገኙታላችሁና ሰከን በሉ።
በዚህ ታሪካዊ ትዕይንተ ህዝብ ላይ ከወገናችን ጋር በመሆን ድጋፋችንን ለመስጠት ባንችልም መልካም ምኞታችንን ግን ለመግለጽ እንወዳለን። የጋራ ንቅናቄያችን መርሆዎች ከምንግዜውም ይልቅ በአሁኑ ሰዓት ለአገራችን ተፈላጊ በመሆናቸው በቀጣይ በሚደረጉ ሰልፎች በአካል ተገኝተን ከሕዝባችን ጋር የምንሳተፋቸው ይሆናሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ከዚህ በበለጠ ግን አሁን ያሉት ሁኔታዎች ምቹ በር እየከፈቱ ስለሆነ ለአገራችን እጅግ ጠቃሚ የሆነው የጋራ ንቅናቄያችን ከጎሣ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ እንስጥ መርህ ተፈጻሚነት በውጭ የምናደርገው ትግል መሆኑ ቀርቶ በቅርቡ በምድራችን ለሕዝባችን የምናካፍለው እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን።
አምላካችን የተሃድሶ መሪዎቻችን ይጠብቅ! ራዕያቸውን ያስፋ!
ፈጣሪያችን አገራችንን ኢትዮጵያ ይጠብቅልን!
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በአሜሪካ አገር በሕግ የተመዘገበ ድርጅት ሲሆን በትርፍ አልባ የሲቪክ ድርጅትነት በ501(c)(3) ምደባ ሥር የተካተተ ነው። ለተጨማሪ መረጃ የአኢጋን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ በስልክ ቁጥር፤ 202-725-1616 ወይም በኢሜል፤ obang@solidaritymovement.org ማግኘት ይቻላል።
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Alem says
ህዝባዊ ድጋፍ ሰልፉ ታሪካዊና የተሳካ ነበር፡፡ ይኸው ነው ጉዳዩ፡፡ ህወሓትና ግብረአበሮቹ በገሃድ የሞቱበት ቀን ነበር፡፡ የሞት ጣእር ሲይዝ ግን መንፈራገጥ አይቀርም፡፡ መንፈራገጥ ደግሞ ለመላላጥ ካልሆነ ከሞት አያድንም፡፡ ከእንግዲህ ሰኔ 16/2010 በግንቦት 20 ምትክ ሊከበር ይገባል፡፡
Mesfin Lemma says
I appreciate your motto. Every person must be able to love others in order to be loved. We must
not only be by talking but by deeds as well. How does everyone participate? your starting point as a human to give attention to everyone , treat all equally important and keep everyone dignity in all aspects are perfectly an excellent starting. I buy your idea and give full support as to my capacity.
Let’s giveaway everything we have for the dignity of all human being without any distinction.
Then and only then God loves us and every challenges will be overcome through.All of us are blessed if we deny ourself from to much egotistical character and
as a true man. Let’s Love others as we do love ourselves.