አጉል ዘመን ገጥሟት በረት ብትከሳ፤
ከብቶች በመዥገሮች አዩ ብዙ አበሳ፡፡
ጡቶቿን አቃጣይ የነበልባል ጥጃ ላም እሳት ወለደች፤
ብ’ተው በማይተዋ ዘልለው ባልጠገቡ ወይፈኖች ነደደች፡፡
የከበረው ባህል ባለጌ ረጋግጦት እንደጨው ቀለለ፤
ወፍ ዘራሾች ነግሠው ባጥለቀለቁት ደም ምድር ተበከለ፡፡
አዎ፣ ላም እሳት ወለደች!
እንደዮዲት ጉዲት እቶኑ የሚፋጅ፤
ዕረፍት በማያ’ቅ ሠይፍ እንደነደርቡሾች እንደግራኝ አህመድ፤
ጭንቅላትን ገምሶ አንገትን ቆራርጦ ዜጎችን የሚያነድ፡፡
“አጥንትና ደሜ ይሄው የናንተው ነው፤
እኔ ከሌለሁኝ እናተም እንዲያው ነው፤
እርቧችሁ ጠግቤ፣ ብድንም ሞታችሁ፤
ማንም ስለሌለ ከኔ ‘ሚለያችሁ፤
እስከመጨረሻው አጅቡኝ ባካችሁ፡፡ ”
እያለ እሳት ጥጃው ሕዝብን ይማጠናል፤
መስሎት የማናውቀው ቁርበት ዘርጉ ይላል፡፡
ክፋትና ተንኮል ተፈጥሮው የሆነ፤
ሕግና ሥርዓትን ባዋጅ ያወደመ፤
የሰው ገላ ችቦ አንድዶ የሞቀ፤
ቆላ ደጋ ሳይል ሰደድ የለቀቀ፤
በገጠር ከተማ ቋያ ያዘነመ፤
ሁሉንም በመዝረፍ ራቁት ያስቀረ፤
መላ ከብትን ሸጦ በረት ያራቆተ፤
በዝረፍ እንዝረፍ የደንቆሮ ስብከት ሞኝን ያጃጃለ፤
ያልበላውን ዕዳ ትውልድ እንዲከፍል ቢል ያስተላለፈ፤
የሶላቶ ውላጅ ምድረ የሹምባሽ ልጅ፤
የባንዳ ጥርቅም የናት አንጀት በጣሽ፤
ላም እሳት ወለደች ታቅፎ የማይሳም ሣጥናኤልን ወራሽ፡፡
አዎ፣ ባንዳ ነገሠና ብዙ ታምር ታዬ፤
ጥላቻ ተዘርቶ ትርምስ በረዬ፤
ፍትህ ዐይኗ ጠፍቶ ዜጋ ተሰቃዬ፡፡
የከርቸሌ በሮች ሌት ተቀን ተከፍተው፤
ፍርድ ተገልብጦ ከሌለው ወዳለው፤
ይሉኝታና ሀፍረት ካድማስ ማዶ ርቀው፤
የ’ውነቱ አንገት ጠፍቶ ማተብ ማስቀመጫው፤
ተኖሮ ተሙቶ “አለን” እንላለን ላለፍ ላገደመው፡፡
እንጂ፤ ተቸግረን እንጂ እውነት ጠፍታብነ፤
ተሳስረን እንጂ ነው ፍትህ ወድማብነ፡-
ስርቆት ባህል ሆኖ እያስመሰገነ፤
ውሸት ጽድቅ ሆኖ ሃቅ እያስኮነነ፤
ክብር ውርደት ሆኖ ውርደት ሲሆን ክብር፤
መች እናይ ነበረ ፍርድ እየተዛባ ስትፈራርስ ሀገር?
ከደጓ ላም ማኅጸን የተወለደው’ሳት፤
ኦሮሞን ካማራ ትግሬን ከኤርትራ አኙዋኩን ከኑዌር፤
ሊያናቁር ሊያናክስ ሊያደርጋቸው ጠላት፤
ነሰነሰ መርዙን ለሩብ ም’ት ዓመታት፡፡
ስለዚህ ወገኔ ትግራዩ ተነሣ፤
“በቃኝ!” በለውና ባንዴራህን አንሳ፤
ለመብትህ እምቢ በል ትግሉን ተቀላቀል፤
ዮሐንስ ይኩራብህ አሉላም አይፈር፤
የወንድሞችህ ደም ያንተም ደም ነውና፤
በምታውቀው ትግል የአርዮስን አረም ከሥሩ በመንቀል፤
የተሻመንከው ሕዝብ በሃሤት ይፈንድቅ፣ አብሮህ እልል ይበል፡፡
የጋራ ጠላትን በሚጠራርገው የማይቀር ጎርፍ ላይ፤
ምራቅህን ጨምር ታሪክ ተለውጦ እውናዊ ነፃነት በተግባር እንዲታይ፡፡
ትግርኛ ግጥም – አሰር ኣሉላ ዮሐንስ
ነፃ ትርጉም – ይነጋል በላቸው (yinegal3@gmail.com)
የግጥሙ ርዕስ – ላሕሚ እንታይ ወሊዳ ?
ምንጭ – ethiomedia.com
ማጠቃለያ
- የኦሮሞው ደም፣ የአማራው ደም፣ የኮንሶው ደም፣ የጋምቤላው ደም የትግራይ ሕዝብ ደም ነው !
- ህወሓት ለአሁኒቷ ኢትዮጵያ ችግሮች ተባብሶ መቀጠልና ለውድቀታችን ዋና ተጠያቂ ነው !
- ህወሓት ሳይውል ሳያድር ከሥልጣን ይወገድ!
- (ሁሉንም ወገን የሚያሣትፍ) ዴሞክራሲያዊ የሽግግር መንግሥት አሁኑኑ በሀገራችን ይመሥረት!
Leave a Reply