ከዛሬ ሠላሣ ሁለት ዓመት በፊት በአንድ ገዳም ውስጥ ይኖሩ የነበሩና ለ40 ዓመት የዘጉ አንድ ባሕታዊ ከዘጉበት ቤተ ጸሎት ወጥተው ለሕዝቡ ታዩ፡፡ ታይተው የማያውቁ እኚህ አባት ዛሬ መውጣታቸው ሕዝቡን አስደንግጦታል፡፡ ለሰንበት ቅዳሴ ለተሰበሰበው ሕዝብ እንዲህ በማለት ተናገሩ፡- “በሕልሜ ቤበ- መኩ- እፍ- ጸጉ የሚሉ ቃላትን ያሳየኛል፡፡ ተጨንቄአለሁና እባካችሁ ፍቱልኝ” አሉ፡፡ ሕዝቡም፡- “አባታችን እኛ ምኑን እናውቀዋለን? ለእርስዎ እንዳሳየ ይፍታልዎ እንጂ” አሏቸው፡፡ እርሳቸውም ሕልሙን ሲተረጕሙ፡-
ቤበ – ማለት ቤተ ክርስቲያን በረት ሆነች ማለት ነው፡፡
መኩ – መሥዋዕት ኩበት ሆነ ማለት ነው
እፍ – ዕጣን ፍግ ሆነ ማለት ነው፡፡
ጸጉ – ጸሎት ጉባዔ/ ታይታ/ ሆነ ማለት ነው በማለት ተረጎሙ፡፡
ሕልምም ሆነ ትንቢት በፍጻሜው ይታወቃል፡፡ እኝህ አባት ያሳያቸው እውነት እንደሆነ ዛሬ እያየነው ነው፡፡ በረት ቆሻሻ የበዛበት፣ ንጽሕና የጎደለው፣ ሥነ ሥርዓት የሌለበት፣ የሕያው ነፍስ ሳይሆን የደመ ነፍስ /የእንስሳት/ መከማቻ፣ ነጻነት የማይሰጥ፣ በውስጡ የሚኖሩት የሕሊና፣ የሰብአዊና የመንፈሳዊ ሕግ የማያዛቸው፣ ዙሪያው የሚበርድ ክፍት የሆነ ስፍራ ነው፡፡ እኝህ አባት ቤተ ክርስቲያን በረት ሆነች ይለኛል አሉ፡፡ ንስሐን የመሰለ የሕይወት ውኃ የሚነገርባት ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮቿ ያልታጠቡባት፣ ንስሐን ተሸክመው ንስሐ የሚቀበሉባት፣ በዓለም የሌለ ነውር በእርስዋ የሚሰማባት፣ ቅድስና የራቃት፣ ሁሉም በፊቱ ደስ ያለውን የሚያደርግባት፣ የደፈረ የሚኖርባት፣ እንኳን መንፈሳዊነት ሰብአዊነት የማይሰማቸው አገልጋዮች የተሰበሰቡባት፣ ትሩፋት የሚሠራ አይደለም የታዘዘውን የሚፈጽም የታጣባት፣ ለሚያያቸው ዕረፍት የማይሰጡ ያልተገሩ ሠራተኞች የሞሉባት፣ ለእግዚአብሔርና ለአገር ሕግ የማይገዙ የተከማቹባት፣ ሲያስቧቸው ብርድ ብርድ የሚሉ ሥርዓት አልበኞች የነገሡባት ስፍራ ሆናለች፡፡
መንፈሳዊት ተቋም የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ከመንፈሳዊነት አቋም ወጥታ ድርጅታዊ ሥርዓትን እንኳ አለማግኘቷ ያሳዝናል፡፡ የሥርዓት መገኛ ሥርዓት ስታጣ፣ የፍርድ ሰባኪ ፍርድ የለሽ ስትሆን፣ የነፍሶች ሰብሳቢ በታኝ ስትሆን፣ የራእይ መውጫ ራእይ ሲጨልምባት፣ የነገሥታት መካሪ በነገሥታት ስትመከር፣ ለገዛ ሕገ መንግሥቷ ለመጽሐፍ ቅዱስ አልገዛ ስትል፣ የኃጥአን መጠጊያ ሳትሆን የኃጢአት መለማመጃ ስትሆን፣ መሪዋን ክርስቶስን ለመስማት እምቢ ስትል እያየን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በረት ሆነች ያሉት እኒያ አባት የታያቸው እውነት መሆኑን እያየን ነው፡፡
በጸጋ የተመሠረተች ቤተ ክርስቲያን በሕግ የምትከራከርና የምትካሰስ ስትሆን፣ ሁሉን ትተናል መስቀል ተሸክመናል የሚሉት አገልጋዮችዋ ሁሉን ይዘናል፣ መስቀል ጥለናል የሚሉ ቅምጥሎች ሲሆኑባት እያየን ነው፡፡ ዓለምን ሰልችተው የሚመጡ ምእመናን ዓለምን በቤተ ክርስቲያን ሲያገኙ፣ ቤተ ክርስቲያንም የዓለምን መመሪያ የምትፈልግ ስትሆን፣ እንደ ቃሉ ሳይሆን እንደ ዘመኑ ለመኖር ስታቅድ ማየት፣ የተጣሉትን የምታስታርቀው በገላጋይ ስትኖር፣ ዓለምን በቅድስና ውበቷ የምትማርከው በዓለም ስትማረክ ማየት ያሳዝናል፡፡ የትዕግሥት አምላክ በትዕግሥቱ ቤተ ክርስቲያንን እየጠበቃት ነው፡፡ ትዕግሥቱ ካልገባት በዓለም ፊት የምትቀጣበትና የውስጥ ልብስዋ ተገልጦ የምትገረፍበት ዘመን ቅርብ ነው፡፡ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በታላቅ ትዕግሥቱ እያያት ነው፡፡ እርሱ በፍርድ የተነሣ ቀን ግን በትሩ እስኪያልቅ ይቀጣታል፡፡
“የወፍ ዘፈን አውራጁ አይታወቅም” እንደሚባለው መደማመጥ የሌለባት፣ ሁሉም በየአቅጣጫው የሚዘፍንባት፣ ሕዝቡን እንደ ቅርጫ ከፋፍሎ የሚበላባት የጠላት ቤት ሆናለች፡፡ እኒያ ጭምት ልጆችዋ ከአደባባይዋ ርቀው፣ አመንዝሮችና ቀማኞች አለሁ አለሁ የሚሉባት፣ አንድ ሐሰተኛ ሲነቀል ሁለት የሚበቅልባት፣ በእውነት ቃል ሳይሆን በአፈ ጮሌነት የሚኖርባት … የእውነትን ሚዛን የጣለች ቤት ሆናለች፡፡ ለዚህ ሁሉ የሚቆጭ የለም፡፡ በክፋት ከመወዳደር በቀር የእግዚአብሔር ቤት ንጹሕ ይሁን ብሎ የሚቆረቆር ቢጠፋም ቤቱን የማይተው ጌታ ግን ይነሣል፡፡ ያልገመትነውንና ጆሮአችን ያልጠበቀውን ቍጣ እናያለን፣ እንሰማለን፡፡ ይህ ጊዜ የእግዚአብሔር የትዕግሥቱ ጥላ የተዘረጋበት ነው፡፡ የታጠፈ ቀን ግን የመዓቱን እሳት፣ የቍጣውን በረዶ አንችለውም፡፡ እግዚአብሔር መቀጣጫ እንድንሆን አድርጎ ይቀጣናል፡፡ እርሱ ከታሪካችን ርዝመት ጋር ጉዳይ የለውም፡፡ የዛሬን መታዘዛችንን ያያል፡፡ የማያምኑትን ከቀጣ አውቀው የሚያጠፉትንማ በደንብ ይቀጣል፡፡ ዛሬ የኮራንበት ካባ አልሠራንበትም ነገ እናፍርበታለን፡፡ እግዚአብሔር ከጣለን የሚያነሣን የለምና ዛሬ የምናከማቸው ሀብት አይረባንም፡፡ እግዚአብሔር ምንም ቢሆን ጥሎ አይጥለንም ብለን በባዶ የኮራንበት ቃልም አይጠልለንም፡፡ እርሱ እግዚአብሔር የሚያከብሩትን የሚያከብር፣ የናቁትን የሚንቅ ነው /1ሳሙ. 2፡30/፡፡ እንኳን እኛን እስራኤልን የጣላቸው ባለመታዘዝ ነው፡፡ ኃጢአት ትንቢት የተነገረለትን፣ ሱባዔ የተቆጠረለትን የሰሎሞንን መቅደስ አፍርሷል፡፡
ታዲያ ጥሎ አይጥለንም እንዴት ማለት እንችላለን? የኮራንበት የጦር መሣሪያም አያድነንም፡፡ እንኳን የእኛ መሣሪያ ኒውክለር የታጠቁም ከቍጣ አያመልጡም፡፡ ታላቅ ሕዝብ ነህ እያልን አመንዝራውንና ነፍሰ ገዳዩን ተከታያችንን አድንቀናል፡፡ ያው ሕዝብ ግን ይበላናል፡፡ ያላስተማርነው ሕዝብ ጠላት መሆኑን የምናይበት ዘመን ቀርቦአል፡፡ የማይሞላው ከረጢታችን ዘላለማዊ እሳት ይበላዋል፡፡ የመበለቶችን ቤት የዘረፍንበት፣ ወጣቶችን ያስነወርንበት፣ የድሆች ልጆችን ጉሮሮ የዘጋንበት፣ በመማፀኛ ዘመን ወገናችንን አውጥተን የጣልንበት፣ በወገናችን ሞት የተሠረግንበት፣ በጭንቁ የሳቅንበት፣ ትዳርን ያፋታንበት፣ እስቲ ይህን ሕዝብ ልጩህበት ያልንበት፣ እንደ አማልክት ውዳሴና ስግደት የተቀበልንበት፣ እግዚአብሔር ካለ ይህን ያድርግ ያልንበት፣ ወገንና ወገን ሲተላለቅ እንደሌለ ሆነን የተቀመጥንበት፣ ንጹሐንን የገደልንበት፣ ወንጌልን የገፋንበት፣ እውነትን የቀበርንበት … ያ የእርም ጽዋችን ሞልቷልና እግዚአብሔር ይነቅለናል፡፡ ቍጥቋጦ ሳይቀረን ከሥራችን ይፈነቅለናል፡፡ ያን ቀን የቀድሞ ወዳጆቻችንን እንፈልጋለን፡፡ እነርሱ ግን ከጠላት ይልቅ ይከፉብናል፡፡ ያን ቀን ያጠራቀምነውን ገንዘብ እንፈልጋለን፡፡ ለአንድ ቀን መታከሚያም አይሆነንም፡፡ ያን ቀን ወንጌል የቱ ነው? አሁንም ሰብከን እንብላ እንላለን፣ ጆሮ ግን ይከዳናል፡፡ ያን ቀን መንግሥት እንኳ ጥግ ይሁነን እንላለን፣ እንደ አጸያፊ ቆሻሻም እንጣላለን፡፡ ያን ቀን ሠርጋችንን አጅቡት እንላለን፣ የልቅሶ ያህል አይደምቅም፡፡ ያን ቀን ማዘዝ እንፈልጋለን ቃላችን ግን ይቀላል፡፡ ዛሬ ያለነው የመጨረሻው መጀመሪያ ላይ ነን፡፡ አስማት ጥንቆላችን፣ ብዙዎችን ያሳበድንበት መተታችን ያለ ያዢ አብደን በአደባባይ ያሽከረክረናል፡፡ የሚያዝንልን አጥተን ያለ ታዛቢ እንቀራለን፡፡ ይህ አገልጋዮች ነን ለሚሉ ሁሉ የተደገሰ ድግስ ነው፡፡ ንስሐ በማይገቡት ላይ እግዚአብሔር ይህን መዓት ያፈስሳል፡፡ ትዕግሥቱ ይህ ሁሉ እንዳይመጣ ነበር፡፡ የትዕግሥቱ ምሥጢር ካልገባን የመዓቱን ሰይፍ እንጎርሳለን፡፡ እፈራለሁ ከቀድሞ ይልቅ ዛሬ እፈራለሁ፡፡ እግዚአብሔር ትዕግሥቱን ሲያሰፋ ይበልጥ እፈራለሁ፡፡ ካልተመለስን ጥበብ፣ ጉልበትና ሀብት የማያልፋት ብርቱ ቀን መጥታብናለች፡፡
የጠፋው እረኛ ብቻ አይደለም በግም ጠፍቷል፡፡ የምንመራው በአብዛኛው በግ መሳይ ነው፡፡ ሲሰክር አድሮ ጠዋት ጠበል የሚጠጣ፣ ሲያመነዝር አንግቶ ማለዳ ቅዳሴ የሚገኝ፣ ለሃይማኖቴ እገድላለሁ የሚል ለሃይማኖቱ ግን የማይሞት፣ ለእምነቱ የማይኖርላት ግን ሲሳደብላት የሚወል፣ ቅበላና ፋሲካን በኃጢአት የሚፈጽም ጾመኛ መሳይ፣ በመድረክ ሳይሆን በሕይወቱ ድራማ የሚሠራ፣ ከዘረፈው ላይ ዓሥራት የሚያወጣ፣ ቆርቦ የሚያብድ፣ አምኖ የማያምን፣ ሠራተኞቹን እያስጨነቀ ቀሳውስትን የሚቀልብ፣ ድንበር እየገፋ አቤት አቤት እያለ የሚጸልይ፣ ጋራ ጋራውን ጠንቋይ ፍለጋ ሲያስስ አድሮ ጠዋት ለኪዳን የሚደርስ፣ እጁ በደም ተጨማልቆ ቤተ ክርስቲያን የሚያንፅ፣ የንስሐ ስብከት የሚወድ ንስሐን ግን የማይወድ፣ ሰባኪ ቀላቢ ወንጌል ተቃዋሚ፣ ለስድብ አጨብጫቢ ለእውነት አጉረምራሚ፣ ሕይወት ሲነገር የሚያንቀላፋ የሰው ነውር ሲወራ የሚነቃ፣ በለው የሚል ድምፅ የሚፈልግ ጦረኛ፣ ማንበብ የማይወድ የነገሩትን ብቻ የሚሰማ፣ እስኪሞላለት የቤተ ክርስቲያን ወዳጅ ከሞላለት በኋላ ኵሩ፣ ዛሬን ለመርካት ስበኩኝ የሚል ዘላቂ ሕይወትን የማይሻ፣ ከእግዚአብሔር ርቆ አገልጋይ በመወዳጀት እድናለሁ የሚል፣ የመንገዱን ካርታ ጥሎ የሚንከራተት፣ ተረኛ ብልጥ እንደ ዘረፈው የሚኖር፣ ታላቅ ሕዝብ እያሉ የሚያሳንሱትን አወዳሾች የሚሸልም፣ ተመለስ ያለውን የሚወግር፣ እውነተኞችን ጥላሸት የሚቀባ፣ የአሉ ተከታይ የወሬ አንጋሽ፣ ከነሕመሙ ቤተ ክርስቲያን መጥቶ ከነሕመሙ የሚመለስ፣ የዋህ ሳይሆን ሞኝ የሆነ አማኒ ይዘናል፡፡ ይህ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በየአብያተ ክርስቲያናቱ እየፈላ ያለ ሞገደኛ ወገን ነው፡፡ ንስሐ ካልገባ ይህ ወገን ብርቱ ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡ መከራን እንደተለማመደ የሚኖር፣ አሁን ያለው መከራ ሳይደንቀው የሚመጣውን መከራ የሚናፍቅ ደንዳና ሕዝብ ይዘናል፡፡ የትዕግሥት አምላክ ዝም ያለን ሥራችን ተስማምቶት አይደለም፡፡ ለንስሐ ጊዜ እየሰጠን ነው፡፡ ራሳችንን የምናይበት ቍርጥ ጊዜ ቢኖር አሁን ነው፡፡ ስለዚህ ንስሐ እንግባ፡፡
በዓመት ውስጥ ባሉት ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ቀናት ጸሎት፣ አገልግሎት እንፈጽማለን፡፡ ይህ በሌላው ዓለም የሌለ የታደልነው ሀብት ነው፡፡ ነገር ግን ፍቅር የሌለው ጸሎት፣ ቅድስና የሌለበት ቅዳሴ፣ መታዘዝ የሌለበት አገልግሎት ስለሆነ ይሄው አልተባረክንም፡፡ ተገልጋዩ ግዳጅን ለመፈጸም ያህል ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር የናፍቆት ፍቅር የለውም፡፡ አገልጋዩ ለእንጀራ ይጮኻል፡፡ ከሚሰማው አምላክ ጋር አይነጋገርም፡፡ ልማድ እንዳይቀር ስለምናደርገው ጸልየን ለምን መልስ አጣን? ጾመን ለምን አልተባረክንም? ቀድሰን ለምን ጸጋ አልፈሰሰልንም? አገልግለን ለምን አላፈራንም? ብለን ራሳችንን ለመጠየቅ ጊዜ የለንም፡፡ ግን የተለመደው እንዳይቋረጥ ሕይወት የሌለውን ሥነ ሥርዓት፣ ቅዱስ ፍርሃት የሌለበትን ጸሎት፣ ተመስጦ የሌለበትን ዜማ፣ መገዛት የሌለበትን ቅኔ እናቀርባለን፡፡ ከሚሰማን አምላክ ጋር እየተነጋገርን መልስ አጥተን ዘመናት አልፈዋል፡፡
እግዚአብሔር ከመሥዋዕት በፊት መታዘዝን ይፈልጋል፡፡ የእኛ የሆነውን ከመስጠታችን በፊት ራሳችንን እንድንሰጠው፣ ከአገልግሎት በፊት እንድናውቀው ይሻል፡፡ እኛ ግን ኑሮአችን ይዞታ ማስከበር እንጂ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ መናኘት አይደለም፡፡ ሕዝቡን ባለማወቅ መጋረጃ ጋርደን መፍረድ የምንፈልግ ቃልቻዎች እንጂ ሰብከን የምንለውጥ አገልጋዮች አልሆንም፡፡ ሕዝቡም ጧፍና ዕጣኑን አምጥቷል እርሱ ግን አልመጣም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ደጃፍም ያዘነውንና የተከፋውን ለመቀበል ሳይሆን ብርና ወርቅ ለመቀበል ተከፍተዋል፡፡ ጴጥሮስ ብርና ወርቅ የለኝም ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ ብሎ ሽባውን ፈወሰ /የሐዋ. 3፡6/፡፡ ዛሬ ግን ቤተ ክርስቲያን ብርና ወርቅ የለኝም አትልም፡፡ ግን የሥጋና የነፍስ በሽተኞች አይፈወሱም፡፡
እየዘመርን እንሰዳደባለን፣ ተጣልተን እንቆርባለን፣ ለወንድማችን ጉድጓድ እየቆፈርን አቤት አቤት እንላለን፡፡ እግዚአብሔር አዝኖብናል፡፡ እርሱን የሰው ያህል እንኳ ስላላከበርነው፣ ቤቱንም የቤታችንን ያህል እንኳ ስላላከበርን እግዚአብሔር ተቀይሞናል፡፡ ዛሬ የመዓቱን ሰይፍ በቁጣው ሰገባ ስለተያዘልን እንዝናናለን፡፡ ሰይፉ የተመዘዘ ቀን ግን የደሙ ምልክት እንጂ ገንዘባችን አያድነንም፡፡ እያደረግን ያለነው እግዚአብሔር ከቻለ ይፍረድብን የሚል ድፍረት ነው፡፡ ግን መከራውን ባንጎትተውም ሊወርድ ነው፡፡
እምነታችንን የያዝነው ለፉክክር እንጂ ለሕይወት አይደለም፡፡ ሌሎች ሲሰብኩ እንሰብካለን፣ ካልነኩን በእንቅልፋችን ራሳችን እንሞታለን፡፡ ሲነኩን በወንድነት ሃይማኖትን ለማስከበር እንነሣለን፡፡ “የእንጦጦ መምህር ቢናገር ባመት፣ ያውም እሬት” እንዲሉ፡፡ በንጹሕ ልብ መጸለይ አልሆነልንም፡፡ አገር ለአገር በመዞር እግዚአብሔርን የምናገኘው ይመስለናል፡፡ እርሱ ግን በንጹሕ ልብ እንጂ በፈጣን እግሮች የሚገኝ አይደለም፡፡ ጸሎታችንም ጉባዔ ወይም ለታይታ እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት አይደለም፡፡ ድንጋይ ውርወራ ስንጀምር፡- “ኃይል የእግዚአብሔር ነው” በሚል ዝማሬ በመሆኑ ምን ያህል እንደማናስተውል ይታያል፡፡ በእውነት የምናምነው ኃይል የእግዚአብሔር ነው ብለን ነው? ታዲያ ዓመፁ ከየት መጣ? “የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል” /2ጢሞ. 3፡5/ የሚለው ቃል ደርሶብናል፡፡ ስብከቱ፣ ዝማሬው ቢበዛም የእኛ ደንዳናነት ግን አልተፈረካከሰም፡፡ እዩኝ እዩኝ የሚል ክርስትና እንጂ የሚታይ ክርስትና የለንም፡፡ በሕይወታችን ነውር የሸሹንን በስብከታችን ለመመለስ የምንጥር ሞኞች ነን፡፡ ስብከት ሲጠፋን እንሳደባለን፡፡ የተጨነቀውን ሕዝብ በማስፈራራት እንዘርፋለን፡፡ የጠላነውን ሰው ታርጋ ሰጥተን ቅንዓታችንን የሃይማኖት ካባ እናለብሰዋለን፡፡ ቁመናችንን እንጂ የክርስቶስን መልክ ልናሳይ አልቻልንም፡፡ የልብሳችን ሽቱ እንጂ የሕይወታችን መዓዛ ሊያውድ አልቻለም፡፡ አጥንተን እንጂ ኖረን መናገር አልሆነልንም፡፡ ለምንዝርናችን ድንበር ብናሳጣውም የእግዚአብሔር ቁጣ ግን ሊገድበው ነውና ፈጥነን ንስሐ እንግባ፡፡ በዘርፋፋው ቀሚሳችን ሳይሆን በተትረፈረፈው ክርስትናችን፣ በነጭ ነጠላችን ሳይሆን በነጭ ልባችን የትዕግሥትን አምላክ ደስ እናሰኘው፡፡ ቃሉ፡- “እግዚአብሔር የእውነት ዳኛ ነው ኃይለኛም ታጋሽም ነው፤ ሁልጊዜም አይቆጣም፡፡ ባትመለሱ ግን ሰይፉን ይስላል” /መዝ. 7፡11-12/ ይለናል፡፡ ትዕግሥቱ ለንስሐ ነው፡፡ ንስሐ መግባት እስከ ዛሬ ለታገሠው ትዕግሥቱ ክብር መስጠት ነው፡፡
እግዚአብሔር የንስሐና የፍቅርን መንፈስ ያድለን!
ሰላም says
WOE! WOE! WOE! WOE! WOE! WOE! WOE!!!!!!!
1) HE WHO HAS AN EAR, LET HIM HEAR WHAT THE SPIRIT SAYS TO THE CHURCHES!!!
2) HE WHO HAS AN EAR, LET HIM HEAR WHAT THE SPIRIT SAYS TO THE CHURCHES!!!
3) HE WHO HAS AN EAR, LET HIM HEAR WHAT THE SPIRIT SAYS TO THE CHURCHES!!!
4) HE WHO HAS AN EAR, LET HIM HEAR WHAT THE SPIRIT SAYS TO THE CHURCHES!!!
5) HE WHO HAS AN EAR, LET HIM HEAR WHAT THE SPIRIT SAYS TO THE CHURCHES!!!
6) HE WHO HAS AN EAR, LET HIM HEAR WHAT THE SPIRIT SAYS TO THE CHURCHES!!!
7) HE WHO HAS AN EAR, LET HIM HEAR WHAT THE SPIRIT SAYS TO THE CHURCHES!!!
God bless you Deacon Ashenafe for your timely message particularly for our mother church
(Orthodox).
mesfin says
THANK YOU DEACON IT WAS A STRONG AND TIMELY MESSAGE!!!!