• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

አስቸኳይ የንስሃ ጥሪ ለሁሉም!!!

July 5, 2013 12:46 am by Editor 2 Comments

ከዛሬ ሠላሣ ሁለት ዓመት በፊት በአንድ ገዳም ውስጥ ይኖሩ የነበሩና ለ40 ዓመት የዘጉ አንድ ባሕታዊ ከዘጉበት ቤተ ጸሎት ወጥተው ለሕዝቡ ታዩ፡፡ ታይተው የማያውቁ እኚህ አባት ዛሬ መውጣታቸው ሕዝቡን አስደንግጦታል፡፡ ለሰንበት ቅዳሴ ለተሰበሰበው  ሕዝብ እንዲህ በማለት ተናገሩ፡- “በሕልሜ ቤበ- መኩ- እፍ- ጸጉ የሚሉ ቃላትን ያሳየኛል፡፡ ተጨንቄአለሁና እባካችሁ ፍቱልኝ” አሉ፡፡ ሕዝቡም፡- “አባታችን እኛ ምኑን እናውቀዋለን? ለእርስዎ እንዳሳየ ይፍታልዎ እንጂ” አሏቸው፡፡ እርሳቸውም ሕልሙን ሲተረጕሙ፡-

ቤበ  – ማለት ቤተ ክርስቲያን በረት ሆነች ማለት ነው፡፡

መኩ – መሥዋዕት ኩበት ሆነ ማለት ነው

እፍ –  ዕጣን ፍግ ሆነ ማለት ነው፡፡

ጸጉ – ጸሎት ጉባዔ/ ታይታ/ ሆነ ማለት ነው በማለት ተረጎሙ፡፡

ሕልምም ሆነ ትንቢት በፍጻሜው ይታወቃል፡፡ እኝህ አባት ያሳያቸው እውነት እንደሆነ ዛሬ እያየነው ነው፡፡ በረት ቆሻሻ የበዛበት፣ ንጽሕና የጎደለው፣ ሥነ ሥርዓት የሌለበት፣ የሕያው ነፍስ ሳይሆን የደመ ነፍስ /የእንስሳት/ መከማቻ፣ ነጻነት የማይሰጥ፣ በውስጡ የሚኖሩት የሕሊና፣ የሰብአዊና የመንፈሳዊ ሕግ የማያዛቸው፣ ዙሪያው የሚበርድ ክፍት የሆነ ስፍራ ነው፡፡ እኝህ አባት ቤተ ክርስቲያን በረት ሆነች ይለኛል አሉ፡፡ ንስሐን የመሰለ የሕይወት ውኃ የሚነገርባት ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮቿ  ያልታጠቡባት፣ ንስሐን ተሸክመው ንስሐ የሚቀበሉባት፣ በዓለም የሌለ ነውር በእርስዋ የሚሰማባት፣ ቅድስና የራቃት፣ ሁሉም በፊቱ ደስ ያለውን የሚያደርግባት፣ የደፈረ የሚኖርባት፣ እንኳን መንፈሳዊነት ሰብአዊነት የማይሰማቸው አገልጋዮች የተሰበሰቡባት፣ ትሩፋት የሚሠራ አይደለም የታዘዘውን የሚፈጽም የታጣባት፣ ለሚያያቸው ዕረፍት የማይሰጡ ያልተገሩ ሠራተኞች የሞሉባት፣ ለእግዚአብሔርና ለአገር ሕግ የማይገዙ የተከማቹባት፣ ሲያስቧቸው ብርድ ብርድ የሚሉ ሥርዓት አልበኞች የነገሡባት ስፍራ ሆናለች፡፡

መንፈሳዊት ተቋም የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ከመንፈሳዊነት አቋም ወጥታ ድርጅታዊ ሥርዓትን እንኳ አለማግኘቷ ያሳዝናል፡፡ የሥርዓት መገኛ ሥርዓት ስታጣ፣ የፍርድ ሰባኪ ፍርድ የለሽ ስትሆን፣ የነፍሶች ሰብሳቢ በታኝ ስትሆን፣ የራእይ መውጫ ራእይ ሲጨልምባት፣ የነገሥታት መካሪ በነገሥታት ስትመከር፣ ለገዛ ሕገ መንግሥቷ ለመጽሐፍ ቅዱስ አልገዛ ስትል፣ የኃጥአን መጠጊያ ሳትሆን የኃጢአት መለማመጃ ስትሆን፣ መሪዋን ክርስቶስን ለመስማት እምቢ ስትል እያየን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በረት ሆነች ያሉት እኒያ አባት የታያቸው እውነት መሆኑን እያየን ነው፡፡

በጸጋ የተመሠረተች ቤተ ክርስቲያን በሕግ የምትከራከርና የምትካሰስ ስትሆን፣ ሁሉን ትተናል መስቀል ተሸክመናል የሚሉት አገልጋዮችዋ ሁሉን ይዘናል፣ መስቀል ጥለናል የሚሉ ቅምጥሎች ሲሆኑባት እያየን ነው፡፡ ዓለምን ሰልችተው የሚመጡ ምእመናን ዓለምን በቤተ ክርስቲያን ሲያገኙ፣ ቤተ ክርስቲያንም የዓለምን መመሪያ የምትፈልግ ስትሆን፣ እንደ ቃሉ ሳይሆን እንደ ዘመኑ ለመኖር ስታቅድ ማየት፣ የተጣሉትን የምታስታርቀው በገላጋይ ስትኖር፣ ዓለምን በቅድስና ውበቷ የምትማርከው በዓለም ስትማረክ ማየት ያሳዝናል፡፡ የትዕግሥት አምላክ በትዕግሥቱ ቤተ ክርስቲያንን እየጠበቃት ነው፡፡ ትዕግሥቱ ካልገባት በዓለም ፊት የምትቀጣበትና የውስጥ ልብስዋ ተገልጦ የምትገረፍበት ዘመን ቅርብ ነው፡፡ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በታላቅ ትዕግሥቱ እያያት ነው፡፡ እርሱ በፍርድ የተነሣ ቀን ግን በትሩ እስኪያልቅ ይቀጣታል፡፡uturn

“የወፍ ዘፈን አውራጁ አይታወቅም” እንደሚባለው መደማመጥ የሌለባት፣ ሁሉም በየአቅጣጫው የሚዘፍንባት፣ ሕዝቡን እንደ ቅርጫ ከፋፍሎ የሚበላባት የጠላት ቤት ሆናለች፡፡ እኒያ ጭምት ልጆችዋ ከአደባባይዋ ርቀው፣ አመንዝሮችና ቀማኞች አለሁ አለሁ የሚሉባት፣ አንድ ሐሰተኛ ሲነቀል ሁለት የሚበቅልባት፣ በእውነት ቃል ሳይሆን በአፈ ጮሌነት የሚኖርባት … የእውነትን ሚዛን የጣለች ቤት ሆናለች፡፡ ለዚህ ሁሉ የሚቆጭ የለም፡፡ በክፋት ከመወዳደር በቀር የእግዚአብሔር ቤት ንጹሕ ይሁን ብሎ የሚቆረቆር ቢጠፋም ቤቱን የማይተው ጌታ ግን ይነሣል፡፡ ያልገመትነውንና ጆሮአችን ያልጠበቀውን ቍጣ እናያለን፣ እንሰማለን፡፡ ይህ ጊዜ የእግዚአብሔር የትዕግሥቱ ጥላ የተዘረጋበት ነው፡፡ የታጠፈ ቀን ግን የመዓቱን እሳት፣ የቍጣውን በረዶ አንችለውም፡፡ እግዚአብሔር መቀጣጫ እንድንሆን አድርጎ ይቀጣናል፡፡ እርሱ ከታሪካችን ርዝመት ጋር ጉዳይ የለውም፡፡ የዛሬን መታዘዛችንን ያያል፡፡ የማያምኑትን ከቀጣ አውቀው የሚያጠፉትንማ በደንብ ይቀጣል፡፡ ዛሬ የኮራንበት ካባ አልሠራንበትም ነገ እናፍርበታለን፡፡ እግዚአብሔር ከጣለን የሚያነሣን የለምና ዛሬ የምናከማቸው ሀብት አይረባንም፡፡ እግዚአብሔር ምንም ቢሆን ጥሎ አይጥለንም ብለን በባዶ የኮራንበት ቃልም አይጠልለንም፡፡ እርሱ እግዚአብሔር የሚያከብሩትን የሚያከብር፣ የናቁትን የሚንቅ ነው /1ሳሙ. 2፡30/፡፡ እንኳን እኛን እስራኤልን የጣላቸው ባለመታዘዝ ነው፡፡ ኃጢአት ትንቢት የተነገረለትን፣ ሱባዔ የተቆጠረለትን የሰሎሞንን መቅደስ አፍርሷል፡፡

ታዲያ ጥሎ አይጥለንም እንዴት ማለት እንችላለን?  የኮራንበት የጦር መሣሪያም አያድነንም፡፡ እንኳን የእኛ መሣሪያ ኒውክለር የታጠቁም ከቍጣ አያመልጡም፡፡ ታላቅ ሕዝብ ነህ እያልን አመንዝራውንና ነፍሰ ገዳዩን ተከታያችንን አድንቀናል፡፡ ያው ሕዝብ ግን ይበላናል፡፡ ያላስተማርነው ሕዝብ ጠላት መሆኑን የምናይበት ዘመን ቀርቦአል፡፡ የማይሞላው ከረጢታችን ዘላለማዊ እሳት ይበላዋል፡፡ የመበለቶችን ቤት የዘረፍንበት፣ ወጣቶችን ያስነወርንበት፣ የድሆች ልጆችን ጉሮሮ የዘጋንበት፣ በመማፀኛ ዘመን ወገናችንን አውጥተን የጣልንበት፣ በወገናችን ሞት የተሠረግንበት፣ በጭንቁ የሳቅንበት፣ ትዳርን ያፋታንበት፣ እስቲ ይህን ሕዝብ ልጩህበት ያልንበት፣ እንደ አማልክት ውዳሴና ስግደት የተቀበልንበት፣ እግዚአብሔር ካለ ይህን ያድርግ ያልንበት፣ ወገንና ወገን ሲተላለቅ እንደሌለ ሆነን የተቀመጥንበት፣ ንጹሐንን የገደልንበት፣ ወንጌልን የገፋንበት፣ እውነትን የቀበርንበት … ያ የእርም ጽዋችን ሞልቷልና እግዚአብሔር ይነቅለናል፡፡ ቍጥቋጦ ሳይቀረን ከሥራችን ይፈነቅለናል፡፡ ያን ቀን የቀድሞ ወዳጆቻችንን እንፈልጋለን፡፡ እነርሱ ግን ከጠላት ይልቅ ይከፉብናል፡፡ ያን ቀን ያጠራቀምነውን ገንዘብ እንፈልጋለን፡፡ ለአንድ ቀን መታከሚያም አይሆነንም፡፡ ያን ቀን ወንጌል የቱ ነው? አሁንም ሰብከን እንብላ እንላለን፣ ጆሮ ግን ይከዳናል፡፡ ያን ቀን መንግሥት እንኳ  ጥግ ይሁነን እንላለን፣ እንደ አጸያፊ ቆሻሻም እንጣላለን፡፡ ያን ቀን ሠርጋችንን አጅቡት እንላለን፣ የልቅሶ ያህል አይደምቅም፡፡ ያን ቀን ማዘዝ እንፈልጋለን ቃላችን ግን ይቀላል፡፡ ዛሬ ያለነው የመጨረሻው መጀመሪያ ላይ ነን፡፡ አስማት ጥንቆላችን፣ ብዙዎችን ያሳበድንበት መተታችን ያለ ያዢ አብደን በአደባባይ ያሽከረክረናል፡፡ የሚያዝንልን አጥተን ያለ ታዛቢ እንቀራለን፡፡ ይህ አገልጋዮች ነን ለሚሉ ሁሉ የተደገሰ ድግስ ነው፡፡ ንስሐ በማይገቡት ላይ እግዚአብሔር ይህን መዓት ያፈስሳል፡፡ ትዕግሥቱ ይህ ሁሉ እንዳይመጣ ነበር፡፡ የትዕግሥቱ ምሥጢር ካልገባን የመዓቱን ሰይፍ እንጎርሳለን፡፡ እፈራለሁ ከቀድሞ ይልቅ ዛሬ እፈራለሁ፡፡ እግዚአብሔር ትዕግሥቱን ሲያሰፋ ይበልጥ እፈራለሁ፡፡ ካልተመለስን ጥበብ፣ ጉልበትና ሀብት የማያልፋት ብርቱ ቀን መጥታብናለች፡፡

የጠፋው እረኛ ብቻ አይደለም በግም ጠፍቷል፡፡ የምንመራው በአብዛኛው በግ መሳይ ነው፡፡ ሲሰክር አድሮ ጠዋት ጠበል የሚጠጣ፣ ሲያመነዝር አንግቶ ማለዳ ቅዳሴ የሚገኝ፣ ለሃይማኖቴ እገድላለሁ የሚል ለሃይማኖቱ ግን የማይሞት፣ ለእምነቱ የማይኖርላት ግን ሲሳደብላት የሚወል፣ ቅበላና ፋሲካን   በኃጢአት የሚፈጽም ጾመኛ መሳይ፣ በመድረክ ሳይሆን በሕይወቱ ድራማ የሚሠራ፣ ከዘረፈው ላይ ዓሥራት የሚያወጣ፣ ቆርቦ የሚያብድ፣ አምኖ የማያምን፣ ሠራተኞቹን እያስጨነቀ ቀሳውስትን የሚቀልብ፣ ድንበር እየገፋ አቤት አቤት እያለ የሚጸልይ፣ ጋራ ጋራውን ጠንቋይ ፍለጋ ሲያስስ አድሮ ጠዋት ለኪዳን የሚደርስ፣ እጁ በደም ተጨማልቆ ቤተ ክርስቲያን የሚያንፅ፣ የንስሐ ስብከት የሚወድ ንስሐን ግን የማይወድ፣ ሰባኪ ቀላቢ ወንጌል ተቃዋሚ፣ ለስድብ አጨብጫቢ ለእውነት አጉረምራሚ፣ ሕይወት ሲነገር የሚያንቀላፋ የሰው ነውር ሲወራ የሚነቃ፣ በለው የሚል ድምፅ የሚፈልግ ጦረኛ፣ ማንበብ የማይወድ የነገሩትን ብቻ የሚሰማ፣ እስኪሞላለት የቤተ ክርስቲያን  ወዳጅ ከሞላለት በኋላ ኵሩ፣ ዛሬን ለመርካት ስበኩኝ የሚል ዘላቂ ሕይወትን የማይሻ፣ ከእግዚአብሔር ርቆ አገልጋይ በመወዳጀት እድናለሁ የሚል፣ የመንገዱን ካርታ ጥሎ የሚንከራተት፣ ተረኛ ብልጥ እንደ ዘረፈው የሚኖር፣ ታላቅ ሕዝብ እያሉ የሚያሳንሱትን አወዳሾች የሚሸልም፣ ተመለስ ያለውን የሚወግር፣ እውነተኞችን ጥላሸት የሚቀባ፣ የአሉ ተከታይ የወሬ አንጋሽ፣ ከነሕመሙ ቤተ ክርስቲያን መጥቶ ከነሕመሙ የሚመለስ፣ የዋህ ሳይሆን ሞኝ የሆነ አማኒ ይዘናል፡፡ ይህ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በየአብያተ ክርስቲያናቱ እየፈላ ያለ ሞገደኛ ወገን ነው፡፡ ንስሐ ካልገባ ይህ ወገን ብርቱ ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡ መከራን እንደተለማመደ የሚኖር፣ አሁን ያለው መከራ ሳይደንቀው የሚመጣውን መከራ የሚናፍቅ ደንዳና ሕዝብ ይዘናል፡፡ የትዕግሥት አምላክ ዝም ያለን ሥራችን ተስማምቶት አይደለም፡፡ ለንስሐ ጊዜ እየሰጠን ነው፡፡ ራሳችንን የምናይበት ቍርጥ ጊዜ ቢኖር አሁን ነው፡፡ ስለዚህ ንስሐ እንግባ፡፡

በዓመት ውስጥ ባሉት ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ቀናት ጸሎት፣ አገልግሎት እንፈጽማለን፡፡ ይህ በሌላው ዓለም የሌለ የታደልነው ሀብት ነው፡፡ ነገር ግን ፍቅር የሌለው ጸሎት፣ ቅድስና የሌለበት ቅዳሴ፣ መታዘዝ የሌለበት አገልግሎት ስለሆነ ይሄው አልተባረክንም፡፡ ተገልጋዩ ግዳጅን ለመፈጸም ያህል ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር የናፍቆት ፍቅር የለውም፡፡ አገልጋዩ ለእንጀራ ይጮኻል፡፡ ከሚሰማው አምላክ ጋር አይነጋገርም፡፡ ልማድ እንዳይቀር ስለምናደርገው ጸልየን ለምን መልስ አጣን? ጾመን ለምን አልተባረክንም? ቀድሰን ለምን ጸጋ አልፈሰሰልንም?  አገልግለን ለምን አላፈራንም? ብለን ራሳችንን ለመጠየቅ ጊዜ የለንም፡፡ ግን የተለመደው እንዳይቋረጥ ሕይወት የሌለውን ሥነ ሥርዓት፣ ቅዱስ ፍርሃት የሌለበትን ጸሎት፣ ተመስጦ የሌለበትን ዜማ፣ መገዛት የሌለበትን ቅኔ እናቀርባለን፡፡ ከሚሰማን አምላክ ጋር እየተነጋገርን መልስ አጥተን ዘመናት አልፈዋል፡፡

እግዚአብሔር ከመሥዋዕት በፊት መታዘዝን ይፈልጋል፡፡ የእኛ የሆነውን ከመስጠታችን በፊት ራሳችንን እንድንሰጠው፣ ከአገልግሎት በፊት እንድናውቀው ይሻል፡፡ እኛ ግን ኑሮአችን ይዞታ ማስከበር እንጂ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ መናኘት አይደለም፡፡ ሕዝቡን ባለማወቅ መጋረጃ ጋርደን መፍረድ የምንፈልግ ቃልቻዎች እንጂ ሰብከን የምንለውጥ አገልጋዮች አልሆንም፡፡ ሕዝቡም ጧፍና ዕጣኑን አምጥቷል እርሱ ግን አልመጣም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ደጃፍም ያዘነውንና የተከፋውን ለመቀበል ሳይሆን ብርና ወርቅ ለመቀበል ተከፍተዋል፡፡ ጴጥሮስ ብርና ወርቅ የለኝም ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ ብሎ ሽባውን ፈወሰ /የሐዋ. 3፡6/፡፡ ዛሬ ግን ቤተ ክርስቲያን ብርና ወርቅ የለኝም አትልም፡፡ ግን የሥጋና የነፍስ በሽተኞች አይፈወሱም፡፡

እየዘመርን እንሰዳደባለን፣ ተጣልተን እንቆርባለን፣ ለወንድማችን ጉድጓድ እየቆፈርን አቤት አቤት እንላለን፡፡ እግዚአብሔር አዝኖብናል፡፡ እርሱን የሰው ያህል እንኳ ስላላከበርነው፣ ቤቱንም የቤታችንን ያህል እንኳ ስላላከበርን እግዚአብሔር ተቀይሞናል፡፡ ዛሬ የመዓቱን ሰይፍ በቁጣው ሰገባ ስለተያዘልን እንዝናናለን፡፡ ሰይፉ የተመዘዘ ቀን ግን የደሙ ምልክት እንጂ ገንዘባችን አያድነንም፡፡ እያደረግን ያለነው እግዚአብሔር ከቻለ ይፍረድብን የሚል ድፍረት ነው፡፡ ግን መከራውን ባንጎትተውም ሊወርድ ነው፡፡

እምነታችንን የያዝነው ለፉክክር እንጂ ለሕይወት አይደለም፡፡ ሌሎች ሲሰብኩ እንሰብካለን፣ ካልነኩን በእንቅልፋችን ራሳችን እንሞታለን፡፡ ሲነኩን በወንድነት ሃይማኖትን ለማስከበር እንነሣለን፡፡ “የእንጦጦ መምህር ቢናገር ባመት፣ ያውም እሬት” እንዲሉ፡፡ በንጹሕ ልብ መጸለይ አልሆነልንም፡፡ አገር ለአገር በመዞር እግዚአብሔርን የምናገኘው ይመስለናል፡፡ እርሱ ግን በንጹሕ ልብ እንጂ በፈጣን እግሮች የሚገኝ አይደለም፡፡ ጸሎታችንም ጉባዔ ወይም ለታይታ እንጂ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት አይደለም፡፡ ድንጋይ ውርወራ ስንጀምር፡- “ኃይል የእግዚአብሔር ነው” በሚል ዝማሬ በመሆኑ ምን ያህል እንደማናስተውል ይታያል፡፡ በእውነት የምናምነው ኃይል የእግዚአብሔር ነው ብለን ነው? ታዲያ ዓመፁ ከየት መጣ? “የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል” /2ጢሞ. 3፡5/ የሚለው ቃል ደርሶብናል፡፡ ስብከቱ፣ ዝማሬው ቢበዛም የእኛ ደንዳናነት ግን አልተፈረካከሰም፡፡ እዩኝ እዩኝ የሚል ክርስትና እንጂ የሚታይ ክርስትና የለንም፡፡ በሕይወታችን ነውር የሸሹንን በስብከታችን ለመመለስ የምንጥር ሞኞች ነን፡፡ ስብከት ሲጠፋን እንሳደባለን፡፡ የተጨነቀውን ሕዝብ በማስፈራራት እንዘርፋለን፡፡  የጠላነውን ሰው ታርጋ ሰጥተን ቅንዓታችንን የሃይማኖት ካባ እናለብሰዋለን፡፡ ቁመናችንን እንጂ የክርስቶስን መልክ ልናሳይ አልቻልንም፡፡ የልብሳችን ሽቱ እንጂ የሕይወታችን መዓዛ ሊያውድ አልቻለም፡፡ አጥንተን እንጂ ኖረን መናገር አልሆነልንም፡፡ ለምንዝርናችን ድንበር ብናሳጣውም የእግዚአብሔር ቁጣ ግን ሊገድበው ነውና ፈጥነን ንስሐ እንግባ፡፡ በዘርፋፋው ቀሚሳችን ሳይሆን በተትረፈረፈው ክርስትናችን፣ በነጭ ነጠላችን ሳይሆን በነጭ ልባችን የትዕግሥትን አምላክ ደስ እናሰኘው፡፡ ቃሉ፡- “እግዚአብሔር የእውነት ዳኛ ነው  ኃይለኛም ታጋሽም ነው፤ ሁልጊዜም አይቆጣም፡፡ ባትመለሱ ግን ሰይፉን ይስላል” /መዝ. 7፡11-12/ ይለናል፡፡ ትዕግሥቱ ለንስሐ ነው፡፡ ንስሐ መግባት እስከ ዛሬ ለታገሠው ትዕግሥቱ ክብር መስጠት ነው፡፡

እግዚአብሔር የንስሐና የፍቅርን መንፈስ ያድለን!

Print Friendly, PDF & Email

60

SHARES
Share on Facebook
Tweet
Follow us
Share
Share
Share
Share
Share

Filed Under: Opinions Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Comments

  1. ሰላም says

    July 5, 2013 02:46 pm at 2:46 pm

    WOE! WOE! WOE! WOE! WOE! WOE! WOE!!!!!!!

    1) HE WHO HAS AN EAR, LET HIM HEAR WHAT THE SPIRIT SAYS TO THE CHURCHES!!!

    2) HE WHO HAS AN EAR, LET HIM HEAR WHAT THE SPIRIT SAYS TO THE CHURCHES!!!

    3) HE WHO HAS AN EAR, LET HIM HEAR WHAT THE SPIRIT SAYS TO THE CHURCHES!!!

    4) HE WHO HAS AN EAR, LET HIM HEAR WHAT THE SPIRIT SAYS TO THE CHURCHES!!!

    5) HE WHO HAS AN EAR, LET HIM HEAR WHAT THE SPIRIT SAYS TO THE CHURCHES!!!

    6) HE WHO HAS AN EAR, LET HIM HEAR WHAT THE SPIRIT SAYS TO THE CHURCHES!!!

    7) HE WHO HAS AN EAR, LET HIM HEAR WHAT THE SPIRIT SAYS TO THE CHURCHES!!!

    God bless you Deacon Ashenafe for your timely message particularly for our mother church
    (Orthodox).

    Reply
  2. mesfin says

    July 14, 2013 05:50 pm at 5:50 pm

    THANK YOU DEACON IT WAS A STRONG AND TIMELY MESSAGE!!!!

    Reply

Leave a Reply to mesfin Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን ለማቋቋም የሚውል የ15 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ድጋፍ የዓለም ባንክ May 16, 2022 10:22 am
  • በአዲስ አበባ 1 ሺህ 98 የብሬን እና 2 ሺህ 162 የክላሽ ጥይት ተያዘ May 16, 2022 10:10 am
  • በአዲስ አበባ ከተማ በግለሰብ መኖሪያ ቤት ከ5 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላርና የተለያዩ አገራት ገንዘቦች ተያዙ May 16, 2022 09:53 am
  • አገር አፍራሹ ትህነግ ለቀለብ፣ መድኃኒትና ሥራ ማስኬጃ 76 ቢሊዮን ብር ቀርጥፏል May 16, 2022 08:30 am
  • እየተባባሰ ከመጣው የማህበራዊ ሚዲያ አጭበርባሪዎች ዜጎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ተጠየቀ May 15, 2022 09:38 am
  • የትህነግና ሸኔ መሠልጠኛ የምትባለው ዩጋንዳ መከላከያ ሚ/ር ከኤታማዦር ሹሙ ጋር ተወያዩ May 13, 2022 09:55 am
  • በትግራይ የውጊያ ምልመላው ጉዳይ May 11, 2022 02:37 am
  • መከላከያ በተጨማሪ ድሮን፣ በሥልጠና፣ በዝግጅት ራሱን አብቅቷል May 11, 2022 01:35 am
  • ትህነግ ለሌላ ውጊያ እየተዘጋጀ ነው ተባለ May 10, 2022 01:04 pm
  • ኤርትራ 8 ሩስያ ሠራሽ ድሮኖችን ተረክባለች May 10, 2022 12:37 am
  • ሙስሊምና ክርስቲያን በአንድነት የሚያከብረው የአኾላሌ ባሕላዊ ጭፈራ May 9, 2022 01:46 pm
  • በወልዲያ ፋኖዎች ተመረቁ May 9, 2022 12:51 pm
  • “ሠራዊታችን ድልን በአስተማማኝ መልኩ ማምጣት በሚችል ቁመና ላይ” ጀኔራል ጌታቸው May 9, 2022 11:57 am
  • ዋጋው 64 ሚሊዮን ብር የሚሆን (16 ኪሎ) ሕገወጥ ወርቅ ተያዘ May 9, 2022 11:51 am
  • አብን ክርስቲያን ታደለን ለመጨረሻ ጊዜ አስጠነቀቀ፤ 10 አባላቱን አገደ May 9, 2022 08:58 am
  • ራሱ አቡክቶ፣ ራሱ አሟሽሾ፣ ራሱ ጋግሮ በሰዓት 460 እንጀራ የሚያወጣ ፈጠራ May 9, 2022 08:17 am
  • በህገ ወጥ መንገድ 19 ህጻናትን ሲያዘዋወሩ የነበሩ 6 ሴቶች ተያዙ May 8, 2022 12:39 am
  • በአርሲ ሙስሊሞች ለቤ/ክ ማሠሪያ 3 ሚሊዮን ብርና 20 የቀንድ ከብት ሰጡ May 6, 2022 09:35 am
  • በአዲስ አበባ የሚኖረው የትህነግ ደጋፊ ማንነት በማስረጃ May 4, 2022 11:04 pm
  • ሙስሊም ወንድማማች የቤ/ክ ዘራፊዎችን በቁጥጥር ሥር አዋሉ May 4, 2022 09:04 am
  • ከ6 ሺህ የዓሳ ጫጩት ወደ 80 ሺህ May 4, 2022 08:57 am
  • ተስፋቢሱ ቴድሮስ May 3, 2022 12:16 pm
  • ከሽፏል! April 6, 2022 11:58 am
  • “ሩሲያ ዩክሬይንን ወረረች” እየተባለ ስለሚነዛው ወሬ ጥቂት እውነታዎች March 8, 2022 11:30 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2022 · Goolgule