
ባለፉት 5 ዓመታት ከተወለዱ 10 ሚሊዮን ህጻናት ውስጥ 84 በመቶዎቹ ያልተመዘገቡ ናቸው ተባለ።
የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ባለፉት 5 ዓመታት የመዘገበው የውልደት ኩነት 16 በመቶ ብቻ መሆኑንና ይህም 84 በመቶ የሚሆኑት ተወላጆች በመንግስት ሰንድ ላይ ያልተመዘገቡ እና የማይታወቁ ናቸው ብሏል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጀብ ጀማል ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት ከአውሮፓውያኑ 2012 ጀምሮ 10 ሚሊየን ህፃናት ይወለዳሉ የሚል ግምት የነበረ ቢሆንም በወሳኝ ኩነት የተመዘገቡት ግን 2 ሚሊየን ያህሉ ብቻ ናቸው።
በዚህ መሀል ያልተመዘገቡትን 8 ሚሊየን ህፃናት ስለመወለዳቸው እና ስለመኖራቸው መንግስት እንደማያውቅ ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
በህገ መንግስቱ መሠረት ህፃናት እንደተወለዱ በ90 ቀናት ውስጥ መመዝገብ፣ ስም ማግኘት እና መታወቂያ አግኝተው ዜግነታቸው መታወቅ አለበት።
ይህ የውልደት ምዝገባ አልተከናወነም ማለት ደግሞ የህፃናቱን መብት አለማክበር ሲሆን ቤተሰብ ይህን የማድረግ ግዴታ አለበት ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
አሁን ላይ ባለው የአመዘጋገብ ስርዓት ህፃናት 5 ዓመት ሞልቷቸው ትምህርት ቤት በሚገቡ ወቅት በዘገየ የምዝገባ ሂደት የሚከናወንላቸው ቢሆንም 5 ዓመት እስኪሞላቸው ግን በመንግሥት አይታወቁም።
ህፃናት 5 ዓመት እስኪሞላቸው በመንግስት አይታወቁም ማለት ስለ ትምህርታቸው፣ ስለ ጤናቸው ሁኔታና በሌሎች ጉዳዮው ላይ መንግስት የሚያወጣው ፖሊስ በመላምት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል።
በመሆኑም ወላጆች ይህን ሀላፊነት ወስደው በ90 ቀናት ውስጥ ህጻናትን ማስመዝገብ እንደሚኖርባቸው ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
የዓለም ባንክ በአንድ ወቅት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያላክተው በአፍሪካ ከ500 ሚሊየን በላይ ሰዎች በመንግሥት ሪከርድ ላይ አልተመዘገቡም።
በኢትዮጵያም አብዛኛዎቹ ከ18 ዓመት በታች ያሉ ህፃናት በመንግስት ዶክመንት ላይ አልተመዘገቡም ወይም አይታወቁም ተብሏል።(ትግስት ዘላለም፤ ኢትዮ ኤፍ ኤም)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply