
ሣልሳዊ ቴዎድሮስ ወይም “ቴዲ አፍሮ” በሰባ ደረጃ የተባለ(ች) ነጠላ ዘፈን ለቆልናል፡፡
“በሰባ ደረጃ”ን እኔ ስሰማው እልም ያለ የፍቅር ዘፈን ነው፡፡ ፍቅርን ልዩ በሆነ ቦታና ልዩ በሆነ ሥፍራ የሚያሳይ ዘፈን፡፡ በአማርኛ ዘፈን ባህል ውስጥ ቦታን ማስጎብኘት የተለመደ ነው፡፡ “የሐረር ልጅ ነች ወጣቷ/ጀጎል ነው ቤቷ” አይነት ዘፈን ሞልቶናል፡፡ አብዛኛው ያገራችን ዘፋኝ፣ ያስጎብኝነት ሚናም ደርቦ ሲጫወት ኖሯል፡፡ በዚህ ምክንያት ተፈቃሪዋ ሴት ሁሌም ከታሪካዊ ቦታ አጠገብ ለመወለድ ትገደዳለች፡፡
ቴዲ በዚህ ዜማው ባልተሄደበት መንገድ ሄዷል፡፡ ሲጀምር፣ እዚህ ግባ የማይባል፣ ለዓይን የማይሞላ ቦታ መረጠ፡፡ ብዙ ጊዜ፣ ታሪካዊ ቦታ ሲባል አክሱም፣ ላሊበላ፣ ፋሲል፣ ሶፍኡመር፣ ጀጎል እንላለን፡፡ ካሜራው በኒህ ቅርሶች ላይ አፍጥጦ ኖሯል፡፡ ታሪክ አክሱም ላይ ጀምሮ ጀጎል ላይ የተጠናቀቀ ይመስል፡፡
ብዙዎቻችን በሸገር ላይ አድልኦ ስንፈጽም ኖረናል፡፡ አዲስ አበባ ለአቅመ ቅርስ የምትበቃ ከተማ አትመስለንም፡፡ ሸገር ታሪክ ሲሠራባትና ሲሠራላት እንደኖረች አናውቅም፡፡ ወይም ለማወቅ አንፈልግም፡፡ ቴዲ ይህንን እይታ ቀየረው፡፡
ሁለተኛ፣
ከላይ የጠቀስኳቸው ቅርሶች የጌቶች መታሰቢያ ናቸው፡፡ የምድራዊና ሰማያዊ መሪዎችን የሚወክሉ ናቸው፡፡ የስም የለሹን፣ የተርታውን ሰው ኑሮ የሚያሳዩ ቅርሶች ግን ደምቀው አልወጡም፡፡ አይተን እንዳላየን፣ ቸል ብለናቸው ቆይተናል፡፡ ቴዲ ግን ማንም ሲወጣበትና ሲወርደበት ለኖረው አንድ መንገድ ዘፈነለት፡፡ መዝፈን ቢሉህ ዝም ብሎ መዝፈን ብቻ አይደለም፤ አንድ ውብ የሆነ የፍቅር ታሪክ ተረከበት፡፡ ነጠላ ዜማው ከተለቀቀበት ጊዜ አንስቶ ሰባ ደረጃን በድሮ ዓይናችን አናየውም፡፡ አሪፍ ጥበብ ዓይን ገላጭ ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
ሦስተናው ነጥብ፣
ዘፋኞች ልዩ ቦታን ሲያሳዩ ኖረዋል፡፡ ቴዲ ደግሞ አንድን ልዩ ዘመን ለማሳየት ሞክሯል፡፡ የቴዲን ዘፈን ስሰማ፣ በካሳሁን ግርማሞ ዘመን የኖረ አንድ ሮሚዎ ይታየኛል፡፡ ሸዋ ዳቦ ሳይቋቋም፣ ከአርመን ሱቅ ፉርኖ በሚሸመትበት ዘመን፣ ምኒባስ ሳይገባ፣ ሰዎች ሴቼንቶ የሚሳፈሩበት ዘመን፣ ከጄኔራሎች በላይ ሴቼንቶ ነጂዎች ስመጥር የነበሩበት ዘመን፣ ሴቶች የጥላቸውን ቁመት አይተው ሰአት ከመገመት ወጥተው፣ ክንዳቸው ላይ ሰአት ማሰር የጀመሩበት ዘመን – በዚያ ዘመን የኖረ አፍቃሪ ይታየኛል፡፡ አንድን ልዩ ዘመን በሲኒማና በልቦለድ ማሳየት የተለመድ ነው፡፡ በጣም አጭር ቆይታ ባለው ዘፈን ውስጥ ዘመንን ለማሳየት በመሞከር ግን ቴዲ ፋና -ወጊ ይመስለኛል፡፡
ዜመኛ ስላልሆንሁ ስለቴዲ ዜማ ምንም ማለት አልችልም፡፡ያም ሆኖ ፣ግጥሙ የተዋጣለት እንደሆነ መመስከር እችላለሁ፡፡ አንድ ቦታ ላይ “አንደ አርሚዴ ሜሪ” የሚል ሐረግ ሰምቻለሁ፡፡ ዜመኛው፣ ሜሪ አርምዴን፣ አርምዴ ሜሪ ብሎ መጥራት የገጣሚነት ነጻነቱ ይፈቅድለታል፡፡ ገጣሚ እንደ ህጻን ልጅ፣ እንደ እብድና እንደ ቅዱሳን ከቋንቋ ሕግ በላይ ነው፡፡ እንደ ጋዜጠኛ፣ በሰዋስው ህግ አይታሠርም፡፡ እንዲያውም ሳይራቀቁ መግጠም፣ ፈሳሽ ውስጥ ሳይገቡ መስጠም አይታሰብም፡፡
በነገራችን ላይ በድሮ ዘመን በኢትዮጵያ የአባት ስም ከልጅ ስም ቀድሞ ይጻፍ ነበር፡፡ ቴዲን ትውፊትም ያግዘዋል ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ፣ በሚቀጥለው ጽሁፌ እናወጋለን፣ እስከዛ ድረስ ያንን ክራር ወዲህ በል! ታንታራራም ታራራም ታራራም!
(ምንጭ: Bewketu Seyoum facebook. ፎቶዎቹን የወሰድነው ከቴዲ አፍሮ ፌስቡክ ገጽ ነው)
Teddy nice music I like it or so smart
/////ክራር ወዲህ በል! ታንታራራም ታራራም ታራራም! …አዎን የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ…በሁሉን አናጥፋው ዘመን “የማፍረስ አባዜ” ይህ ወጣት ከታሪክ…አስክታሪካዊ ቦታና የፍቅር ሠፈር ሸገርን አስጎበኘን…ክብረት ይስጥልን ብለናል!።መቼም በግጥምም (አማርኛን በአማርእኛ)በትርጓሜና በትችት የሚችለን የለም ግን ሁሉን ቻይ አምላክ ለሁሉ ማሰብ፣ ክህሎት፣ ድምፅን ሲለግስ አንዳንዶች ያልተወለዱበትን ያላደጉበትን ባሕላና ቋንቋ መስለው ለመገኘት ብዙ ይጥራሉ። ያም ቢሆን ከማን አንሼ ያ..ብሄርና ሰፈርና ህዝቡ የአኔም ነው እኔም ያገባኛል አዘምርለታለሁ እቀኝለታለሁ አውቄው እቀውቅና ይሰጠኛል ብለው ነው መልካም ነው በልዩነታችን ውበታችንን ማሳየት ሳይሆን አንድነታችን ኅብረታችን ጥንካሬአችን ነው ታፍረንም ተከብረን የኖርነው ለዚያም ነው!እንግዲህ ሣልሳዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ፸ ደረጃን ወረደበት ! እናንት የቀበና፣ የሽሮ ሜዳም፣ የውቤ በረሃ፣ካዛንችስ፣ለገሃር አራት ኪሎ፣ሽሮ ሜዳ፣ ጃልሜዳ፣አፍንጮ በር፣ እሪ በከንቱ እያላችሁ ውረዱበት ! /////>>>ክራር ወዲህ በል! ታንታራራም ታራራም ታራራም!ተቀበል በለው!