
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ በቁጥጥር ስር መዋሉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አብዱልአዚም መሀመድ እንደገለጹት፣ በክልሉ በሚገኙ 4 የተለያዩ ኬላዎች በተደረገ ፍተሻ 2,370,000 ብር በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡
በክልሉ ኩርሙክ ወረዳ ሱዳን ድንበር አካባቢ በግለሰብ ሲዘዋወር የነበረ 600 ሺህ ብር የሚሆን ገንዘብ በቁጥጥር ስር እንደዋለ ተናግረዋል፡፡ ግለሰቡ 600 ሺህ ብር በሞተር ብስክሌት ጭኖ ሲጓዝ የጸጥታ ኃይሎች ባደረጉት ፍተሻ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቀዋል።
በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪው ለፖሊስ በሰጠው ቃል ገንዘቡን ለወርቅ ግዥ እያንቀሳቀስኩ ነው ማለቱን ተናግረዋል።
በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ ማንኩሽ ኬላ 300 ሺህ ብር በቁጥጥር ስር መዋሉን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽነር አብዱልአዚም አክለውም፣ በክልሉ አሶሳ ከተማ አሶሳ ኬላ 700 ሺህ ብር በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ አሶሳ ዞን ቡልድግሉ ወረዳ ጎንቆሮ ኬላ ደግሞ 770 ሺህ ብር በቁጥጥር ስር መዋሉንም አመልክተዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት መሠል ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር ክትትሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ኮሚሽነር አብዱልአዚም፣ ኀብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር ማድረጉን አጠናክሮ እንዲቀጥለም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እጅግ በርካታ ግፍና ወንጀል በሚፈጸምበት የቤንሻንጉል ክልል ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ ዝውውር እንደሚደረግ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ ጉዳይ ውስጥ መቀሌ የመሸገው የወንበዴዎች ስብስብ እጁ እንዳለበት መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ትላንት በጅጅጋ ጉምሩክ ወደ ሀገር ሊገባ የነበረ 200,000 ብር የገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቋል።
በመንግሥት ይፋ በተደረገው የብር ኖት ቅያሪ ምክንያት ከሱማሌላንድ በቶጎ ውጫሌ በኩል በተለያየ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ የሸሸ የኢትዮጵያ ብር በአንድ ግለሰብ አማካኝነት ወደ ሀገር ሊገባ የነበረ 200,000 ብር በጉምሩክ ፈታሽ አማካኝነት ከነተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር መዋሉን የሚኒስቴር መ/ቤቱ አስታውቋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
thank you so much,for you are a reliable source of informations!