በቦሌ ክፍለ ከተማ 2 ሚሊዮን 3 ሺህ 407 የሀሰተኛ ብር ኖት ሲያዘጋጁ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
ለአቤቱታ ወደ ፖሊስ በመጡ ሰዎች ጥቆማ ሰጪነት ነው ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ያስታወቀው።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀልን ትራፊክ አደጋ ምርመራ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ያሬድ ታረቀኝ መስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም ሁለት ተጠርጣሪዎች በአጠቃላይ 2 ሚሊዮን 3 ሺህ 407 ሀሰተኛ የብር ኖት፤ የአሜሪካ ዶላር እና የተለያዩ ሐገራትን ገንዘቦችን በመኖሪያ ቤታቸው ሲያዘጋጁ መያዛቸውን ገልጸዋል።
ከሚጠቀሙበት የተለያዩ ቁሳቁሶች ጋርም እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ተጠርጣሪዎቹ የኮትዲዩቫር ተወላጆች ሲሆኑ ጉብኝት ለመድረግ በሚል ሰበብ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ምንም አይንት ንብረት ለጉምሩክ አለማስመዝገባቸውን የገለጹት ሃላፊው ዋነኛ አላማቸው የሀሰተኛ የብር ኖቶችን ለማባዛትና ለማሰራጨት መሆኑን ገልጸዋል።
ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመቆጣጠር የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሥርዓት ለማረጋጋት የተጀመረውን አሮጌ የገንዘብ ኖቶችን ቅያሪ ተከትሎ የሚከሰቱ የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን ለመቆጣጠር ፖሊስ ጥብቅ የወንጀል መከላከል ተግባሩን እያከናወነ ይገኛል።
ወቅትን ጠብቀው የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላል ፖሊስ የሚያደርገውን ጥረት በማገዝ በኩል ህብረተሰቡ ተባባሪነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል። (©የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply