
ከ180 ሺህ ብር በላይ ሀሰተኛ ገንዘብ ኖቶችን ወደ ንብ ባንክ ወስደው ሊቀይሩ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች ዛሬ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ሁለቱ ግለሰቦች በሕጋዊ ባንክ ስም ተመሳስሎ በተሰራ እና ወደፊት በሚጣራ ቲተር በመጠቀም ከ180 ሺህ ብር በላይ ሃሰተኛ ገንዘብ ወደ ንብ ባንክ ወስደው ሊቀይሩ ሲሉ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።
ግለሰቦቹ የያዙትን ሃሰተኛ ብር ንብ ባንክ ካዛንቺስ ቅርጫፍ ካሉ ሰራተኞች ጋር 40 ከመቶ ለባንክ 60 ከመቶ ለራሳቸው ለማዋል ስምምነት አድርገው ከመኪናቸው አወጥተው ብሩን ሊመነዝሩ ሲሉ በባንኩ ጥቆማ በተደረገ ክትትል በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የፋይንስና ንግድ ነክ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ብርሃኑ አበበ ለፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ ጋር በተደረገ ክትትል ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።
ከዚያም ባለፈ በቱሉ ዲምቱ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በተደረገ ፍተሻ ተመሳሳይ መጠን ያለው ሃሰተኛ ብር መያዙን ረዳት ኮሚሸነር ብርሃኑ ተናገረዋል።
በአሁኑ ወቅት ግለሰቦቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ይገኛልም ነው ያሉት።
ረዳት ኮሚሽነር ብርሃኑ አያይዘውም ባንኮችም ሆኑ ህብረተሰቡ ከአዲሱ ብር ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ማንኛውንም ህገወጥ እንቅስቃሴ ለጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጡ አሳሰበዋል። (ታሪክ አዱኛ፤ ፋና – ኤፍ.ቢ.ሲ)
ከሌላ ሦስተኛ ወገን ለማረጋገጥ ባይቻልም ሁለቱ ግለሰቦች ይዘውት የነበረው ብር በቡና ኢንተርናሽናል ባንክ መቀሌ ሞሚና ቅርጫፍ በታተመ እና እናት ባንክ አዲሃቂ ቅርጫፍ በታተመ ማሸጊያ የተጠቀለለ እንደነበር በማኅበራዊ ሚዲያ ዜና ከሚያሰራጩ የተገኘው ዘገባ ያመለክታል። (ፎቶው ለማሳያነት የቀረበ እንጂ የተያዘው አይደለም)
ተጨማሪ፥ ይህንን ዜና ካተምን በኋላ የፌዴራል ፖሊስ በርግጥ ገንዘቡ የመጣው ከትግራይ ክልል መሆኑን ይኸውም ከቡና ኢንተርናሽናል ባንክ መቀሌ ሞሚና ቅርጫፍ በታተመ እና እናት ባንክ አዲሃቂ ቅርጫፍ በታተመ ማሸጊያ የተጠቀለለ እንደነበር በፌስቡክ ገጹ መዘገቡን አረጋግጠናል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply