በማይካድራ ንጹሃንን ጨፍጭፎ የሸሸው የአሸባሪው የህወሓት ወንጀለኛ ታጣቂ ቡድን በሱዳን መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ሴቶችን መድፈሩን በመከላከያ ሰራዊት የተማረኩት የህክምና ባለሙያና ወታደራዊ አመራር የሆኑት ሻምበል ተክለወይኒ ታረቀ ማጋለጣቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።
በሱዳን የስደተኛ ጣቢያ ውስጥ ከሚገኙ ከ170 በላይ የሚሆኑት የጁንታው አባላት ሴቶች ላልተፈለገ እርግዝናና ለአባላዘር በሽታዎች መጋለጣቸውንም ምረኮኛው ገልጸዋል።
ወንጀል ፈፅመው ወደ ሱዳን የሸሹ የትህነግ ታጣቂዎች በስደተኞቹ ላይ ወሲባዊ ጥቃት እንደሚፈፀሙና በዚህም ያልተፈለገ እርግዝናና የአባላዘር በሽታዎች መስፋፋታቸውን ሲታዘቡ መቆየታቸውን ገልፀዋል።
ሻምበል ተክለወይኒ ታረቀ ትውልዳቸውና ዕድገታቸው በሰሜን ምስራቅ ትግራይ ታህታይ አዲያቦ በባድመ አካባቢ ሲሆን ከሰራዊቱ በጡረታ ከተገለሉ በኋላ በግል የህክምና ስራ ሲሰሩ ቆይተው በ2011 ዓ/ም ጁንታው ባደረገላቸው ጥሪ የልዩ ሀይሉን መቀላቀላቸውን ተናግረዋል።
በልዩ ሀይሉም የ6ኛ ሬጅመንት ሀኪም በኋላም የሬጅመንቱ ምክትል አዛዥ በመሆን በአዲጎሹና በአብድራፊ ቀጥሎም ወደ ደደቢት በመሄድ በአቃቤ ሰሀት ፣ በአድዋ ፣ በተንቤንና በህንፃፅ የጥፋት ተልዕኮ ሲፈፅሙ መቆየታቸውን ገልፀው፤ በውጊያው እንደማያሸንፉ ሲያውቁ የተወሰኑ ታጣቂዎችን ይዘው ወደ ሱዳን ቢሸሹም በቡድኑ አመራሮች አስገዳጅነት ሌላ ተልዕኮ በመስጠት ወደ ሀገር ቤት መላካቸውን ተናግረዋል።
በስደተኛ ጣቢያዎቹ ያለው ህይወት በጣም አስቸጋሪ መሆኑን የሚናገሩት ምርኮኛው ፣ ተገድባ በተባለው ካምፕ በአይን ተላላፊ በሽታ ብዙ ስደተኞች መጠቃታቸውንና በሱዳን በሚገኙት አራቱም የስደተኛ ጣቢያዎች ተቅማጥና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች በብዛት እንደሚታዩም ተናግረዋል።
ሻምበል ተክለወይኒ ከሱዳን በመነሳት ከጁንታው ተልዕኮ ተቀብለው ከሶስት መቶ በላይ ታጣቂዎችን በመምራት ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት ሲሞክሩ በመከላከያ ሰራዊቱ መማረካቸው ይታወሳል ሲል የመከላከያ ሰራዊት በማህበራዊ ገጹ ላይ አስታውቋል።
በሰሜን ምዕራብ ዞን ላዕላይ አዳቦ ወረዳ ዓዲ ዳዕሮ ከተማ 15 ሺህ ነዋሪዎች ሰልፍ በመውጣት ከ10 በላይ ባለትዳር ሴቶችን በመድፈር የተከሰሰን ፖሊስ በመቃወም ሰልፍ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በትግራይ ክልል ሴቶችን የመድፈር ወንጀል በመበራከቱ ወጣት ሴቶች ጥቁር ልብስ በመልበስ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በተመሳሳይም ይህ የሴት መድፈር ወንጀልን በመቃወም የአረና ፓርቲ አመራሩ አብረሃ ደስታ በማህበራዊ ገጹ ላይ ድርጊቱን በማውገዝ መልዕክት ማስተላለፉም አይዘነጋም ።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply