እጅግ የረቀቀው ፤ የሰው ልጅ ሠልጥኖ
እጅግ መራቀቅን ፤ ሀ ያለው ጀግኖ
ለመቸውም ቢሆን ፤ ሆኖ የታደለ
ለሥልጣኔው ግንብ ፤ መሠረት የጣለ
ረቂቅ ሥዕላትን ፤ ነው ያኔ እንደሣለ
ያለእነዚያ ሥዕሉ ፤ በአገልግሎታቸው
አይገቡበት ነገር ፤ ምንም ስለሌለው
እንኳን እዚህ ሊደርስ ፤ እረቆ ሊማማር
ምንም ምን ለማድረግ ፤ ከቶም አይችል ነበር
በዓይን የማይታዩን ፤ በመሣሪያም ቢሆን
የማይዳሰሱም ፤ ብቻ የሚሰሙን
የሣለ ዕለት ነው ፤ ድንቅ አድርጎ እነሱን
በጆሮዎቹ ብቻ ፤ የሚያዳምጣቸውን
ለተለያዩ ድምፆች ፤ መልክ ቅርጻቸውን
እነ አበገደን ፤ እነ አሌፍ ቤትን
የሣለ ጊዜ ነው ፤ ጥንት በድሮ ዘመን
የኛ አያቶች ደግሞ ፤ በዚህ ጥበባቸው
እጅግ በረቀቀው ፤ የሥዕል ሞያቸው
የሚያህላቸው የለም ፤ የሚስተካከላቸው
ይሄን በክሂላቸው ፤ አሳይተዋልና
ከማን ቋንቋ ይልቅ ፤ በዓለም ካለው ዝና
በቋንቋ ያሉትን ፤ ድምፀ አካል ቁመና
እያንዳንዳቸውን ፤ ነጥለው በማየት
ብዙ የድምፅ ሥዕላትን ፤ ሥለው በማሳየት
ፎነቲክ ይለዋል ፤ ሥነ ልሳን ትምህርት
ከዚህም በይበልጥ ፤ እጅግ የሚደንቀው
የእነዚህ ሥዕላት ፤ የዓሣሣል ዘያቸው
ሥውር ወይ አብስትራክት ፤ ተብሎ እንደሚጠራው
ኅብረ መልክ የያዙ ፤ ምሥጢራዊ ናቸው ፡፡
ሀ ናት ብለን ስንል ፤ አም አብሮ ይሰማል
ለ ናት ብለን ስንል ፤ ·ም አብሮ ተሥሏል
አናባቢውና ፤ ተነባቢው አብረው
በአንድ የሚታዩበት ፤ እንደ አንድ ተዋሕደው
ሲለበሪ ተብለዋል ፤ በዚህ ባሕሪያቸው ፡፡
በዚህ ልዩ ባሕሪው ፤ በመጢቅ ብቃቱ
ከሰው ልጅ ላሳናት ፤ በዓለም ካሉቱ
ብቸኛው መሆኑን ፤ የኛ የሆነው ሀብቱ
ተመስክሮለታል ፤ ገና ከበፊቱ
በዲልማን በቤንደር ፤ በየሊቃውንቱ
መች በዚህ ይበቃና ፤ የአያቶቻችን ፤ የድምፅ ሥዕላት ምሥጢር
የእኛ የድምፅ ሥዕላት ፤ ሰብአዊ አካል ናቸው ፤ ባለ ብዙ ዓይነት ግብር
ሌላም ሌላም ብዙ ፤ ባሕል ወግ ሃይማኖት ፤ ሰብአዊ መስተጋብር
የሚያሳዩ ናቸው ፤ትንቢት የሚነግሩ ፤ የሚያስተምሩ ምሥጢር
ተጽፈው ሲታዩም ፤ ስንኝና ሐረግ ፤ ቃላትን መሥርተው
የአካለ ሰለጥ ፤ ማለት የጅምናስቲክ ፤ ትርዒት ዓሳይተው ነው
አንደኛው አንድ እግሩን ፤ ቄንጥ ባለው ሁሌታ ፤ ከፍ አድርጎ አንሥቶ
አንዱም ወገብ ይዞ ፤ ሌላው እጅ ዘርግቶ
አንዱ አጎንብሶ ፤ ሌላውም ተጣጥፎ
አንዱ ተንበርክኮ ፤ ሌላው ተደግፎ
አንዱ በጭንቅላት ፤ ሌላው በጉልበቱ
አንዱ በትከሻው ፤ ሌላው በደረቱ
ጢባጢቧቸውን ፤ ሲያንኳሉ ሲመቱ ፡፡
የእናት አባቶቻችን ፤ ዕጹብ ሠዓልያን ፤ የሥዕል ችሎታ
ብዙ ነው ምሥጢሩ ፤ ብዙ ያመራምራል ፤ ብዙ አለው አንድምታ
ብዙ ሀገራትም ፤ በዚህ በመመሰጥ ፤ ተማርከው በሥዕሉ
ፊደሎቻቸውን ፤ ከእኛ እየቀዱ ፤ የወሰዱ አሉ
እንደ አርመን ያሉ ፤ ከእኛ እንደወሰዱ ፤ ይመሰክራሉ
ሌሎቹም ብዙዎች ፤ ከእኛ እንደወሰዱ ፤ ብዙ ማስረጃ አለ
የዘረኝነት ከል ፤ ለብሰው ቢዳፈኑም ፤ አይቀር እንደታበለ
የሚሆን ከሆነ ፤ የእውነት ቀን የሚመጣ ፤ እብለት የሚከዳ
ያኔ ይታወቃል ፤ የፊደል ዘር ሁሉ ፤ ከእኛ እንደተቀዳ
የእኛ እጅ የሌለበት ፤ የጥበብ መሠረት ፤ አንድም የለምና
ከሥነ-ፈለኩ ፤ የሕዋ ምርምር ፤ እስከ ፍልስፍና
ከአሥተዳደር ጥበብ ፤ ከቅኔ ድርሰቱ ፤ እስከ ሕክምና
ከዮቶር እስከ ኤዞፕ ፤ የተውኩት ዕውቀት ነው ፤ የዓለሙ ፋና
በየትኛውም መስክ ፤ እኛ ያልረገጥነው ፤ የለምና ዳና፡፡
የአውሮፓ ሀገራት ፤ ጥንታዊ ፈላስፎች ፤ ኢትዮጵያን ሲያገኑ
ሕዝቧንም ሲያደንቁ ፤ እንዲሁ ያለምክንያት ፤ ይመስላል በውኑ?
የሐበሻ ፊደላት ፤ ዕጹብ ድንቅ ሥዕላት ፤ ብዙ ውለታ አላቸው
የሥልጣኔን በር ፤ ወለል አርገው ከፍተው ፤ በማስገባታቸው
ለመላው ዓለም ሕዝብ ፤ ሥልጣኔን ይዘው ፤ በመቆየታቸው
ታሪክ ፍልስፍናን ፤ የባሕል ትውፊት ጥበብ ፤ ባለአደራ ሆነው
በትውልደ ትውልድ ፤ መረጃውን ይዘው ፤ በማሻገራቸው፡፡
የዕጹብ ድንቅ ሥዕላት ፤ ዕጹብ ሠዓልያን ፤ የሐበሻ አያቶች
ለጥበብ ባለቤት ፤ መሣሪያ ሆናቹህ ፤ የእግዚአብሔር እጆች
የሣላቹህት ሥዕል ፤ ለሰው ልጆች ሁሉ ፤ ሥልጣኔን ሰቷል
ምስጋና ይግባቹህ ፤ ዕጹብ ሠዓልያን ፤ ኩራት ሆናቹህናል፡፡
ምስጋና ይግባቹህ ፤ ዕጹብ ሠዓልያን ፤ ኩራት ሆናቹህናል፡፡
መጋቢት 2003 ዓ.ም.
ayalew says
Thank you Ato Amsalu.
I am still waiting your article related to Ethiopian Writing system.
Ayalew