- ፈላጊና ተፈላጊን የሚያገናኙ ደላሎች እስከ 60 ሺህ ብር ኮሚሽን ይከፈላቸዋል
- ባሎቻቸው ሳያውቁ በውጭ አገር ማህፀን አከራይተው የተመለሱ ሴቶች አሉ
- ማህፀን ማከራየትም ሆነ መደለል ህገወጥ ነው – የህግ ባለሙያ
ማህፀን ለመከራየት ከአሜሪካና ከአውሮፓ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ባለትዳሮች በመበራከታቸው ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ እንደተስፋፋ ደላሎች የተናገሩ ሲሆን፤ የማህፀን ኪራይና የማህፀን ኪራይ ድለላ ህገ-ወጥ እንደሆነ የህግ ባለሙያ ገለፁ፡፡
የዛሬ 3 ዓመት ወደ ህንድ ሄዳ የማህፀን ኪራይ አገልግሎት እንደሰጠች የተናገረች አንዲት ወጣት፤ የ11 ወር ወጪዋ ተችሎ 250ሺ ብር እንደተከፈላት ገልፃለች፡፡ አሁን ክፍያው በእጥፍ አድጐ 500ሺ ብር መድረሱን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የማህፀን አከራይዋንና ተከራዮቹን የሚያገናኙ ወኪሎች፤ክፍያው ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ፈላጊና ተፈላጊን በማገናኘት እስከ 60ሺ ብር የሚደርስ የአገልግሎት ክፍያ እንደሚከፈላቸው የጠቆሙት ደላሎች፤ ክፍያው ከሚሰጡት አገልግሎት አንፃር በቂ አለመሆኑን ይገልፃሉ፡፡
ከ98 ዓ.ም ጀምሮ በዚሁ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ስምንት ሴቶችን ከማህፀን ኪራይ ፈላጊዎች ጋር እንዳገናኘ የሚናገረው የኮሚሽን ሰራተኛ፤ ቀደም ሲል ሴቶች የማህፀን ኪራይ አገልግሎት እንዲሰጡ ማሳመን ፈታኝ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ አሁን ግን ነገሮች ተለውጠዋል ይላል – ወጣቱ የኮሚሽን ሰራተኛ፡፡
ማህጸን ለማከራየት ፍቃደኛ የሆኑ ሴቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ጠቅሶ፤ ቀድሞ የኮሚሽን ክፍያ የማገኘው ከአገልግሎት ፈላጊዎቹ ብቻ ነበር፤ አሁን ግን ከአገልግሎት ሰጪዎቹም ክፍያ ማግኘት ጀምሬያለሁ ብሏል፡፡ ማህፀን አከራይ ሴቶችን ፍለጋ ከካናዳ፣ ጣሊያን፣ አሜሪካና ስፔይን የሚመጡ ጥንዶች መበርከታቸውን የጠቆመው የኮሚሽን ሰራተኛ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች በሚጠይቁት አነስተኛ ክፍያና በታማኝነታቸው ተፈላጊነታቸው ጨምሯል ይላል፡፡
እንዲህ አይነት የኪራይ ስምምነት በአገራችን ህጋዊ ስላልሆነ አከራይዋና ተከራዮቹ ስምምነታቸውን የሚያደርጉት ለሥራው በሚሄዱበት አገር ህግ መሠረት መሆኑን የጠቀሰው ወኪሉ፤ አብዛኛውን ጊዜ ለዚህ አገልግሎት ውጭ የሚሄዱ ሴቶች ለምን ሥራ እንደሚሄዱ ቤተሰቦቻቸውን ስለሚደብቁ ስምምነታቸውን አፍርሰው፣ በማህፀናቸው አሳድገው የወለዱትን ልጅ ለመውሰድ ወይም ተጨማሪ ክፍያን ለመጠየቅ አይፈልጉም ብሏል፡፡ የሴቶቹ ትልቁ ጭንቀት ጉዳዩ በሚስጢር እንዲያዝላቸው ማድረግ ነው ሲልም ወኪሉ ገልጿል፡፡ አገልግሎቱን የሚፈልጉ ሰዎች ከመላው ዓለም ለማግኘት የሚረዱ ድረገፆችና የኢንተርኔት አድራሻዎች መኖራቸውን የሚናገረው የኮሚሽን ሰራተኛው፤ የማህፀን ኪራይ አገልግሎት ፈላጊዎች የሚጠይቁት የተለየ መስፈርት እንዳለ በማጣራትና ለአገልግሎቱ የሚከፍሉትን የገንዘብ መጠንና ሌሎች መረጃዎችን በመላክ ተፈላጊዋን የማህፀን አከራይ እንደሚያቀርቡ ተናግሯል፡፡
በአሁኑ ወቅት ለማህፀን ኪራይ ተፈላጊ ሴቶችን መመልመል እንደበፊቱ አድካሚ አለመሆኑን የሚናገረው ወኪሉ፤ ለብዙዎቹ ሴቶች ሥራው ከአገር ውጪ መሆኑና በምስጢር መያዙ እንደሚስማማቸው ጠቁሞ፤ የትዳር አጋራቸው ሳያውቅ ለሥራ በሚል ሰበብ ወደ ህንድና የተለያዩ አገራት በመሄድ፣ የማህፀን ኪራይ አገልግሎት ሰጥተው የሚመለሱ ሴቶች እንዳሉ ይናገራል፡፡ አብዛኛዎቹ ሴቶች ጉዳዩ በምስጢር እንዲያዝላቸው ከመፈለጋቸው የተነሳም ትክክለኛ አድራሻቸውንና ማንነታቸውን አይገልፁም ብሏል፡፡
ከዚህ ቀደም በአገራችን አንድ የግል ክሊኒክ ውስጥ የዘር ፍሬን በሌላ ሴት ማህፀን ውስጥ በመጨመር መውለድ ያልቻሉ ጥንዶች ልጅ እንዲያገኙ መደረጉን ያስታወሱ አንድ የህክምና ባለሙያ፤ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ተሰማርተውበታል ስለሚባለው የውጭ አገር የማህፀን ኪራይ ንግድ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
በአገራችን የማህፀን ኪራይ ከህግ አንፃር እንዴት እንደሚታይ የጠየቅናቸው የህግ ባለሙያው አቶ ገዛኸኝ ታደሰ፤ ድርጊቱ ህጋዊ መሠረት የሌለውና በሰው ልጆች ሰብአዊ መብትና ክብር ላይ የሚፈፀም ህገወጥ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ ሴቶችን እንደሸቀጥ ተምኖ የአገልግሎት ዋጋ ማስከፈል ህገወጥነት ነው ያሉት የህግ ባለሙያው፤ አከራይና ተከራዮችን በማገናኘት ተግባር ላይ የተሰማሩት ደላሎችም ህገወጥ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
ህፃናቱን ወልደው የሚሰጡት እናቶች ከወለዷቸው ህፃናት ጋር በሚኖራቸው ስሜታዊ ትስስሮች ሳቢያ በህፃናቱ ላይ የሚደርሰው የስሜት መጐዳትና እናቲቱም የሚሰማት የሰብአዊነት ክብር ማጣት የማያሳስባቸው ራስ ወዳዶች የሚያከናውኑትን ይህን አይነቱን ተግባር ህጋዊ ያደረጉ አገሮች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ገዛኸኝ፤ አገራችን ግን ድርጊቱን በህጋዊነት አለመቀበሏን ተናግረዋል፡፡(ምንጭ: አዲስ አድማስ፤ በመታሰቢያ ካሣዬ)
Leave a Reply