ማነው ተጠያቂው?
ለኅሊናችን፣ ለትወልድ፣ ለሀገር
ሰው – ስለ ሰው ብሎ፣ እስቲ ሰው ይናገር፤
በዚች ዓለምችን፣ መለኪያው ምንድን ነው
ከገዥና ተገዥ፣ ተጠያቂው ማነው?
ጥቂቶች በቡድን፣ ብዙሀኑን ገፍተው
የሰውን ስብዕና፣ ማንነቱን ገፈው፤
በጥይትም ይሁን፣ በታንክ ደፍጥጠው
እነሱ እንዲገዙ … ማነው የፈቀደው?
ሰለኅሊናችን፣ ስለ እውነት በሀቅ
ሰው – ለራሱ ብሎ፣ ‘ራሱን ይጠይቅ።
ብዙ በልተው – ብዙ ‘ለማበት’
ብዙ ተግተው – ብዙ ለመሽናት፤
…ለጮማ – ቅርናታቸው…
…ለውስኪ – ቅርሻታቸው…
…ለእኩይ – ምግባራቸው፤…
እንደ አንድ ሰው ሆነው፣ሲቆሙ በአንድነት
ለክቡር አላማ፣ ሌላው ሲሆን “ኩበት’’፤
እነሱ ምን ያ’ርጉት?… ምንስ ያቅርቡለት…?
ሰው ነኝ የሚል ዜጋ፣ ከተነዳ እንደ ከብት።
ሀገርን አፍርሰው፣ ትውልደን አጥፈተው
እንድ ቅርጫ ስጋ፣ ህዝብንም ከፋፍለው
እጃቸውን በደም፣ በህዝብ አምባ ታጥበው፤
“ታላቁ ፍጡር፣ የዘመኑ ጀግና፣ ክቡር …” ከተባሉ
ገዥዎች ምን ያርጉ…?፣ ለምን አይፏልሉ…?
“ለምን እድሜ በቃህ’’ እንገዛለን አይሉ…?
ሰለ እውነት – በእውነት ፣ ስለ እውነት በሀቅ
ሰው ለራሱ ብሎ፣ ‘ራሱን ይጠይቅ።
የኪነ – ጥበብ ሰው፣ ‘ልሂቅ’ የተባለ
ማንነቱን ከዶ፣ ሞያውን አርክሶ፣ በከርሱ እየማለ፤
“…ሳይጠሩት – አቤት…!’’
“…ሳይልኩት – ወዴት…!’’
ጭራውን ከቆላ፣ “ውሾ!” እየተባለ
ከግራቸው ስር ልሁን፣ ልነጠፍ እያለ
ለገዠዎች እድሜ፣ ሱባኤ ካደረ፣ ሰበካ ከዋለ፤
ማነው ተጠታቄው? … በማን ላይ ይፈረድ?
“ከሀዲን’’ አንግሶ፣ ፍትህ አይወለድ፡፡
ለኅሊናችን ፣ ለትወልድ፣ ለሀገር
ሰው – ስለ ሰው ብሎ፣ እስቲ ሰው ይናገር፤
በዚች ዓለምችን፣ መለኪያው ምንድን ነው
ከገዥና ተገዥ፣ ተጠያቂው ማነው?
እየተራብ – እያጠገባቸው
እየታረዘ – እያስጌጣቸው፤
እየደህየ – እያከበራቸው
እያዋረዱት – እየተዋረደላቸው፤
እየዘረፉት – እያሞካሻቸው
እየገደሉት – እያኖራቸው፤
በስሙ – በሀብቱ፣ ሲደለልበት
እንደ እቃ ሲቆጠር፣ ሲነገድበት፤
“ዜጋ’’ ነኝ ሲላቸው፣ እየሳቁበት
የ’ኔ እሚለው ሀገር – ቤቱን ሲያሳጡት፤
“እኔ ምን ቸገረኝ፣ አለልኝ ‘ስደት”
ህሊና ተርቦ፣ ‘ከርስ’ እሚሞላበት
“አደናቅፎኝ ነው፣ የእናቴ መቀነት”
“ሆድ ይፍጀው’’ እያለ፣ ከጠበቀ ምፅ’ት፤
ገዥዎች ምን ያርጉ?…. ምን ይፈይዱለት?
ለመምራት አይደለም፣ ወይም ለመመራት
ለመግዛት እኮ ነው፣ “ገዳይ” ነን ያሉት።
ለኅሊናችን ፣ ለትወልድ፣ ለሀገር
ሰው – ስለ ሰው ብሎ፣ እስቲ ሰው ይናገር፤
በዚች ዓለምችን፣ መለኪያው ምንድን ነው
ከገዥና ተገዥ፣ ተጠያቂው ማነው?
ፊልጶስ ፊልጶስ
philiposmw@gmail.com
Leave a Reply