
ትግራይን ማቃናት ያቃተው ካድሬ – አቅቶሃል ተባለ
“ሰላሳ ሰባት ሚሊዮን ብር ለትግራይ አስተዳደር መሰጠቱን ስንሰማ ደንገጠናል። ዜናውን የሰሙ ሁሉ ብሩ የት ገባ? የሚል ጉምጉምታ እያሰሙ ነው። አካል ጉዳተኞች ጸጉራቸውን እየነጩ ነው። ጉዳዩን ትግራይ ያሉ ፖለቲከኞችም እየመከሩበት ነው። ሕዝብ ተናድዷል” ስትል ተቀማጭነቷ አዲስ አበባ የሆነ የትግራይ ተወላጅ ለጎልጉል የአዲስ አበባ ተባባሪ ነግራዋለች።
ወጣቷ በጦርነቱ አንድ ወንድሟን አጥታለች። ኮምቦልቻ እስከሚደርስ በሕይወት ስለመኖሩ መረጃ እንደነበራት፣ ከዚያ በኋላ ደብዛው ጠፍቶባት መጨረሻ ላይ እናቷ መርዶ እንደተነገራቸው የምትናገረዋ ወጣት፣ ስለ ትሕነግ (የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር) ስትናገር ያንዘዘርታል። ኃላፊዎቹን ስታያቸው ያማታል። ኃፍረትና ጸጸት የሚባል ነገር ያልፈጠረባቸው መሆናቸውን ስታስብ… “ትግራይን ለግል ሥልጣናቸው ብለው ደሴት አድርገው ብቻዋን አስቀሯት” ስትል የማኅበራዊ ጠባሳውን ግዝፈት ትናገራለች።

የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተደረገ በኋላ ለድህረ ግጭት መልሶ ግንባታ ከፌዴራል መንግሥት ለትግራይ በትንሹ ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉ ይፋ ከሆነ በኋላ “ብሩ የት ገባ?” የሚሉ ወገኖች በርካታ ናቸው። ጎልጉል ያነጋገራት ወጣት “እነሱ ስለ መንግሥት የሚያወሩትና ለሕዝብ የሚነግሩት ምንም ድጋፍ እንደሌለ ነው። 64 ቀናት ተሰብስበው ምላሽም ይሰጣሉ ሲባሉ ስለገንዘቡ ያሉት ነገር የለም። ይህ ጉዳይ ውሎ አድሮ ከፍተኛ ረብሻና ክልላዊ ቀውስ እንደሚያስነሳ ጥርጥር የለውም” ትላለች።
የፌዴራል መንግሥቱን በተደጋጋሚ ሲነቅፍ አልፎም ሲሳደብ የነበረው የትግራይ አመራር ይህንን ብር የት እንዳደረሰውና በፕሪቶሪያ ስምምነት አተገባበር ላይ “ጥብቅ ግምገማ” ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባዘዙት መሠረት ቡድኑ አዲስ አበባ መግባቱን በምስል የተደገፉ መረጃዎች ዜና አድርገውታል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የነበሩትን ሥራዎች እና መሻሻሎች በጥልቀት መገምገም መጀመሩን፣ የሚደረገው ግምገማ በድኅረ ግጭት መልሶ ግንባታ እና በሰላም ስምምነት አፈጻጸም ላይ ያተኮረ መሆኑን በደፈናው ከማስታወቅ በዘለለ ዝርዝር ጉዳይ አላነሳም።
ከቀናት በፊት ስለ 37 ቢሊዮን ብሩ ምንም ትንፍሽ ሳይል “ወልቃይትን ዳግም ካልወሰድኩ በትግራይም ሆነ በመላው አገሪቱ ሰላም ለማስፈን በሚደረግ ጥረት ውስጥ ተሳታፊ አልሆንም” ብሎ ያስፈራራው ትህነግ፣ ይህን ባለ ማግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ለግምገማ መሰየሙ ከዜናው በላይ ገንኖ መነጋገሪያ ሆኗል።

“ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ምድር ላይ ያሉ የስድብና የማቆሸሺያ ቃላትን በሙሉ አሟጠው በመጠቀም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ ዘመቻ ሲያካሂዱ የነበሩት የትህነግ አመራሮችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ተኮልኩለው ሳያቸው ሰው ሆኖ መፈጠርን ጠላሁ። የትግራይን ወጣት ሙት፣ ቁስለኛና ለማኝ አድርገው፣ ሕዝቡን በዓለም ሁሉ የማይረሳ መዘባበቻ አድርገው ዛሬም …” ከአይኗ በድንገት የወረደው እምባ ንግግሯን አስቆማት።
“ … እ.. ትግራይ ወጣቱ ሁሉ አካሉ ጎድሏል። በትግራይ አካላቸው የጎደለ ወጣቶች፣ ጧሪ አልባ አዛውንቶች፣ ተስፋቸው የተሟጠጠ …” አሁንም መቀጠል አልቻለችም አነባች።
እሷ እንደምትለው ሰብከው አካሉን እንዲያጣ ላደረጉት ወጣት አንዳችም ሳያደርጉ፣ ልጆቻቸውን ላጡ ምንም ዓይነት መቋቋሚያ ሳያስቡ … ይህን ያህል ብር ወስደው “ምንም እገዛ አላገኘንም” ማለታቸው “እነዚህ ሰዎች ምን ሲሆን ወደ ልባቸው ሊመለሱ እንደሚችሉ አስቦ መረዳት እንደማይቻል ማሳያ ነው” ብላለች።

በዚህ የሠለጠነ ዘመን ትሕነግ እና የትግራይ አመራር ሁለት ወር ከአራት ቀናት ስብሰባ አድርጎ ከድርጊት መርሃግብር ይልቅ ተራ እና ለትግራይ ሕዝብ ፈጽሞ በማይጠቅም አጀንዳ ሲነታረክ እንደነበር አቶ ጌታቸው መናገራቸው ይታወሳል። ትህነግ የለመደውን ዓይነት የሤራ ፖለቲካ ትንተና በማድረግ ከፌዴራል መንግሥት ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ቢገባም በስተመጨረሻ አዲስ አበባ መታየቱ ሌላም ስሜት ፈጥሯል።
በዓለም አቅፍ የአሸባሪዎች ቋት እስካሁን በአሸባሪነት ተመዝግቦ የሚገኘው ትህነግ በተደጋጋሚ ባወጣው መግለጫ በድኅረ ግጭት ለትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ የተላከለትን በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ምን እንዳደረገው አንድም ሪፖርት አውጥቶ የማያውቅ በመሆኑ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትሩና በካቢኔ አባሎቻቸው ፊት ቃሉን መስጠት ጀምሯል፤ ለጉዳይ ቅርብ የሆኑ እንዳሉት ገንዘቡን የት እንዳገባው ይገመገማል። ሚኒስትሮች በየዘርፉ የትህነግ ሰዎች የሚያቀርቡትን ምላሽ ተከትሎ ቅጥፈትን በመከላከል በመረጃ እውነታውን ይመሰክራሉ።

የጎልጉል ዜና አቀባዮች እንዳሉት የምርጫ ጉዳይና በርካታ ታጣቂዎችን ካምፕ አስቀምጦ የመቀለቡ ጉዳይ ዕልባት እንዲያገኝ መንግሥት አቋም ይዟል።
ጌታቸው ረዳ፣ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ ጻድቃን ወልደትንሳኤ፣ ታደሰ ወረደ እና ሌሎች ወያኔዎች ለዚሁ ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ከተገኙት የትህነግ ሰዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
የዜናው ሰዎች እንዳሉት ጌታቸው በችሎታ ማነስ፣ በአቅም ማጣትና ሠርቶ በማሠራት ትጋት ክልሉን በጊዜያዊነት መርቶ ወደ ምርጫ እንዲሄድ አያስችልም ተብሏል። ከሥራ ይልቅ የሥልጣን ዕርከኑን እየጣሰ ለባሕር ማዶ አካላት የሚያሰማው ድምጽና አሉባልታ በተሰብሳቢዎች እንዲነቀፍና አድርጎታል። ጌታቸው ብቻ ሳይሆን በዋናነት ባይሳካም ጦርነት ለመስበቅ ደፋ ቀና የሚለው የትሕነግ ሊቀመንበር ደብረጽዮንም ክፉኛ ተገምግሟል፣ ተገስጾዋል።

በሌላ ዜና እንግዳ የሆነባቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሲረግጡ ያዩትን ሥርዓትና ንጽሕና ማመን እንዳቃታቸው ከዜናው ሰዎች ትዝብት ለማረጋግጥ ተችሏል። በቀጣይ ቀናት በአዲስ አበባ እየተዘዋወሩ አዳዲስና ውብ ፕሮጄክቶችን እንዲጎበኙ እንደሚደረግ፣ እሁድ በሚደረገው የዓድዋ ሙዚየም ምረቃ ላይ በአካል እንደሚገኙ ተሰምቷል።
ሰሞኑን ምርጫ ቦርድ በትግራይ የሚንቀሳቀሰውን ባይቶናን ጨምሮ ለሌሎች ሁለት ፓርቲዎች የምዝገባና የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ሠርቲፊኬት ሲሰጥ ለትሕነግ ግን የሰጠነው ምንም አዲስ ዕውቅና የለም ማለቱ ይታወቃል።

ለፕሪቶሪያው ስምምነት ሲባል በፓርላማ ከአሸባሪነት ፍረጃ ነጻ የተደረገው ትሕነግ ሰሞኑን በሳይበር ሚሊሻዎቹ አማካኝነት በድጋሚ ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና እንደተሰጠው መረጃ ቢያሰራጭም ከሁለት ዓመት በፊት በሕገወጥነት ተፈርጆ ዕውቅናው እንደተሠረዘበት ቦርዱ በድጋሚ ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም።
ከድህረ ግጭት እና መልሶ ማቋቋም ተግባራት መካከል አንዱ ምርጫ ሲሆን ይህም በትግራይ ሁሉም ቦታዎች እንዲካሄድ እየተሠራ እንደሆነ ይታወቃል።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
ምድሪቱ ተረግማለች አለኝ አንድ ወዳጄ። አይ እንዲያ ብሎ ነገር የለም። ሰው ማሰብ ሲያቅተውና አብሮ መኖርን ሲጠላ ግኡዟ መሬትን መኮነን አለማወቅ ነው። ሲጀመር ረጋሚም ተረጋሚም የለም። ችግሩ እኛው ነን። የሶስት ሺህ ዘመን ነጻነት አለን እያልን ከምሲን ነገር ያልቀረልን። ቀበሮን የደሮ እንቁላል ጠባቂ አድርገን ከተበላ በህዋላ የት ገባ የምንል ጉዶች። የምድሪቱን ገመና ከአጼው አፈናና ግድያ እስከ ደርግ የመደዳ ጭፍጨፋና አረመኔዊ ተግባር ገባ ብሎ ለተመለከተ የችግራችን ምንጭ እኛው እንጂ ከሰማይ የወረደ ድብ እዳ አይደለም። ችግሩ ከፈጣሪ ጋር ሊያገናኙት የሚፈልጉ ሁሉ ማሳበቢያ ፈላጊዎችና ራሳቸው ግፍ ፈጻሚዎቹ ናቸው።
ሁለቱ መንግስታት ንጉሱና ደርግ ከተሸኙ በህዋላ በምድሪቱ ላይ የተፈጸመው በደል ጣሊያን በሁለት ጊዜ ወረራው ካደረገው ግፍ በላይ ነው። ይህ የሆነውና የሚሆነው በሃገሪቱ ተወልደው፤ በገበሬው አንጡራ ሃብት ተምረው በዘርና በቋንቋቸው በሰከሩ ስመ የብሄር ነጻነት ተፋላሚዎች ተግባር ነው። የ21ኛው ከፍለ ዘመን አፍሪቃዊ የክፋት ቁንጮዎች ሻቢያና ወያኔ ናቸው። የዛሬውን አያድርገውና አብረው ተፋልመውና አፋልመው የብዙሃን ደም ረግጠው ዛሬ ላሉበት የባለህበት ሂድ ሰቆቃ ህዝባቸውን አብቅተዋል። ይህ ነጻነት ነው፤ ለውጥ ነው የሚሉ ካሉ ተጨፈኑና ላሞኛችሁ እንደማለት ይቆጠራል። ድሮ ድሮ ገና በታህሳሱ ግር ግር ተጠርጥሮ ግዞት የተላከው የአልወለድም መጽሃፍ ደራሲ አቶ አቤ ጉበኛ … በደርግ ጊዜ አቤ ሰፈው ህዝብ ማለት ምን ማለት ነው ተብሎ ሲጠየቅ “ሞቶ የማያልቅ” ማለት ነው ያለው እውነትነት አለው። አሁን እንሆ በደም የተነከረ እጃቸውን ታጥበው በጠረጴዛ ዙሪያ የሚታዪት የወያኔ መሪዎች እውነት ራሷ ስትመሰክርባቸው አሻፈረኝ በማለት ነገንም እንደ ዛሬው ለማድረግ ያለምንም ማስተካከያ ደፋ ቀና የሚሉ እጅግ ተንኮለኞች ናቸው። አሁን ጠ/ሚሩ በይፋም ሆነ በድብቅ ከእነርሱ ጋር የመከረውና አሜሪካም አብራ የሸረከችበት ጉዳይ (ወያኔ ከተሸነፈ በህዋላ፟ ማለት ነው)። የአማራና የትግራይን ድንበር ማካለል የሚቻለው አማራ ትጥቁን ሲፈታ ነው በማለት ተስማምተው ወያኔ ለ 50 ዓመት ያደረሰበት በደል አልበቃ ብሎ እንሆ አሁንም አማራው በዚህም በዚያም በመጨፍጨፍ ላይ ይገኛል። ታላቋ ትግራይ ህልም ሆና ስትቀር፤ ከአማራ ህዝብ ይልቅ የሱዳን ህዝብ ይቀለናል ያሉት የወያኔ መሪዎች ሱዳን አሁን የጦር አውድማ ስትሆን የት ይግቡ? ፓለቲካ አመላካች የሌለው ሸፍጠኛ ነፋስ ነው። ከእነዚህ ጉዶች ጋር ስለ ኢትዮጵያም ሆነ ስለ ትግራይ ህዝብ የወደፊት እጣ ፈንታ መምከር ሂትለንርና አይሁዶችን ለማስታረቅ እንደመሞከር ይቆጠራል። የማይሆን ነገር ለሚስትህ አትንገር! ጠ/ሚሩ ምን አይነት አማካሪ ምን አይነት እይታ እንዳለው እኔ ይገርመኛል። እንዴት የራሱን ሰራዊት የበላ ወያኔ እሱን አንድ ቀን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንደሚያስወግድት ይጠፋዋል? የእውቁ የኪነት ሰው የሃጫሉ ገዳዪች ተይዘዋል ተብለናል። ግን ማን እንዴትና ለምን ግድያው እንዲፈጸም እንዳገዘ ይታወቃል? ወይስ እንደ ሌሎቹ ሟቾች ነገርየው ተሸፋፍኖ ቀረ? ለዚህ ነው የሃበሻ ፓለቲካ የውስልትና ፓለቲካ ነው የምንለው።
በቅርቡ ከአንድ ጦርነቱን ሸሽቶ ከወጣ ዪክሬናዊ ጋር ስንጫወት ” አይ ስህተት የሰራችሁት እናንተ ናችሁ። ከቅርብ ጉርብትና የአውሮፓ አካልና የኔቶ አባል ለመሆን የወሰዳችሁት ምርጫ ሃገራቹን እያወደማት ነው አልኩት” ኦ ልክ አይደለህም አለኝ። የቱ ላይ ስለው? ለትንሽ ጊዜ ጭጭ ብሎ ከቆየ በህዋላ ” ስማ የዪክሬን ህዝብ እኮ ምርጫ አልነበረውም። የመረጡልን አሜሪካኖች ናቸው” በማለት እንባ አይኑ ላይ አቀረረ.. በዚህ ዙሪያ ብዙ ማለት ይቻላል። ግን የሮም መንግስትም ወድቋል፤ ጊዜ ሁሉን ይለውጣል። የግፍ መቆሚያ አለው። ያን ቀን ግን የሚያውቅ የለም።
ወያኔ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት፤ የኦሮሞ ታጣቂ ሃይሎች ሽርከኛ። የአማራ ህዝብ ቀንደኛ ጠላት ለመሆኑ በሥራው አስመስክሯል። ዛሬ በመቃዲሾ ቱርኮች ሽር ጉድ የሚሉት ለሱማሊያ ህዝብ አስበው ሳይሆን እነርሱም ልክ እንደ ጅቡቲ ላይ እንደሰፈሩት መርከቦቻቸውን እነርሱም በሱማሊያ በማድረግ እሳት እያቀበሉና እየተቀበሉ ሃገር ለማተራመስ ነው። ለዚህ ነው የሱማሊያው መሪ ያለምንም ሃፍረት ለኢትዮጵያ ውጊያ ተዘጋጅተናል የሚለው። አይ አፍሪቃ። የወስላታ መሪዎች ስብስብ! የምትለብሰው የሌላት የምትከናነበው አማራት ማለት ይህ ነው። ሁሌ ግጭትና ጦርነትን መምረጥ!
ባጭሩ የወያኔን ባህሪና ያለፈና የአሁን አሰራር ለማወቅ የፈለገ ከራሳቸው አብራክ የወጡ ሰዎች የጻፏቸውን፤ በይፋ የተናገሯቸውን፤ እንዲሁም ነጩ አለም ለወሬ ማሟያ የእኛን ሰቆቃ አጋኖ ያወራበትንና የጻፍበትን እያመሳከሩ መመልከቱ ተገቢ ይሆናል። ከወያኔ መሪዎች ምንም መልካም ነገር አይጠበቅም!
በመጨረሻም ስለ አለፈው የሃገራችን ሁኔታ ማለትም በንጉሱ፤ በደርግና በወያኔ ስለነበረው የፓለቲካ ፍትጊያ የበለጠ ለመረዳት በኮ/ሌ አስናቀ እንግዳ የተጻፈውን – “ሸክም የማይከብደው ህዝብ” የሚለውን መመልከት ተገቢ ይሆናል። ሃገሪቱ ዘራፊዎችን ባልጠገቡ ዘራፊዎች የምትተካ፤ ለሃገሬ ለህዝቤ የሚሉትን በግዞትና በስደት እንዲሁም በሞትና በእስራት የምታስወግድ “የሞተላት ቀርቶ የገደላት የሚበላባት” ምድር ናት። ወያኔ ሰማይ ጠቀስ በደሎችን ፈጽሞ አሁን እነርሱ በከተማና በገጠር እንደልባቸው ሲሆኑ ማየት በእነዚህ የፓለቲካ ሙታን ተንኳሽነት እልፍ የትግራይ ልጆች፤ የአማራና የአፋር ወገኖቻችን አፈር ከበላቸው ሰነበቱ። ግን የሞተን ማን ያስባል? ምርጫ በትግራይ፤ ትጥቅ መፍታት፤ ለህዝቡ ሰላምና ደስታን ማምጣት ሁሉ የጊዜ መግዣ ብልሃቶች እንጂ ወያኔ ያኔም አሁንም ለትግራይ ህዝብ ደንታ የለውም። የሚፈጸም ተግባርም አይደለም። ጠ/ሚሩም ከእነዚህ ጉዶች ጋር ገበጣ ጫወታውን በመተው ከቃላት ድርደራ ባሻገር የትግራህ ህዝብን መከራ ለመለወጥ መስራት አለበት። ለነገሩ መከራው መቼ በትግራይ ብቻ ሆነ፤ ጠበንጃ አንጋች በሚንጋጋባት ምድር እንዴት ነው ዘላቂ ሰላም የሚኖረው? መቼ ነው የወለጋ እናቶች እንባ የሚቆመው? መቼ ነው የአማራው መፈናቀልና እስራት የሚያበቃው? አይ ጊዜ… ከክፋት ወደ ላቀ ክፋት መሸጋገር! በሃበሻ ምድር የለውጥ ትርጉሙ ይህ ነው። ትሻልን ትቼ ትብስን እንዲሉ!