በአዲስ አበባ እምብርት ፒያሳ፤ የሚኒሊክ ሀውልት እና የአራዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚያዋስኑት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። በቅርቡ ከታደሰው እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ከሚገኝበት ማዘጋጃ ቤት ጋር ደግሞ በድልድይ ተገናኝቷል።
እስከ ዛሬ ድረስ የራሱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ሳይኖረው የቆየው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትም ቋሚ መሰብሰቢያ አዳራሽ የሚያገኘው በዚህ ፕሮጀክት ነው። እየተጠናቀቀ ያለው ይህ ፕሮጀክት ሁለት ሺህ ሰዎችን የሚይዝ የከተማ አዳራሽም በውስጡ ይዟል።
ከሁሉም በላይ ግን የዓድዋ ሙዚየም ፕሮጀክት ግዙፍነት የሚነሳው ሊዘክረው ካሰበው ታሪካዊ ሁነት ነው። ይህ ግዙፍ መንግሥታዊ ፕሮጀክት፤ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት በተለየ የኢትዮጵያን ነጻነት ያስጠበቀው እና በተለያዩ አገራት የፀረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴን ያነሳሳው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ካስገነባቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች ውስጥ የሚጠቀሰው የዓድዋ ሙዚየም፤ ግንባታው የተጀመረው ሐምሌ 2011 ዓ.ም. ነበር። ህንጻው የማጠናቀቂያ ሥራዎች በላፉት ጥቂት ሳምንታት የተከናወኑ ሲሆን፣ ነገ እሁድ የካቲት 3/2016 ዓ.ም. እንደሚመረቅ ይጠበቃል።
የፒያሳ አዲስ ምልክት ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የዚህ ሙዚየም ዋና አርክቴክት እስክንድር ውበቱ ነው።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአርክቴክቸር እና የከተማ ፕላን ምሩቁ እስክንድር፤ ህንጻዎችን ሲነድፍ 28 ዓመት ገደማ አሳልፏል። ከሥራዎቹ መካከል አዲስ አበባ ሰንጋ ተራ አካባቢ የሚገኘው ባለ 37 ወለሉን የሕብረት ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት “ሕብር ታወር” ተጠቃሽ ነው።
ከእስከ ዛሬ ሥራዎቹ መካከል ትልቁ ደግሞ ፒያሳ ላይ የተዘረጋው የዓድዋ ሙዚየም ነው።
እንደ እስክንድር አገላለጽ ይህ ፕሮጀክት፤ እንደ ሌሎች ሥራዎች የደንበኛን ፍላጎት በህንጻ ንድፍ የመተርጎም ሥራ ብቻ አይደለም። “ከ1.5 ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ የሚቀመጥ ነገር ህንጻ ብቻ አይደለም” የሚለው እስክንድር፤ በትምህርት፣ በሙያ እና በንባብ ያሰባሰበውን የ“ኧርባን ዲዛይን” ጽንሰ ሀሳብ በትልቅ ደረጃ ሙከራ (experiment) ያደረገበት መሆኑን ይገልጻል።
አርክቴክት እስክንድር እና የዓድዋ ሙዚየም መገጣጠም
የዓድዋ ሙዚየምን የሚገነባው ተቋራጭ “ቻይና ጂያንግሱ ኢንተርናሽናል” ከእስክንድር ጋር ሲሠራ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። እስክንድር የነደፈውን የሕብረት ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ህንጻን የገነባው ይህ ኩባንያ ነበር።
በ2011 ዓ.ም. የዓድዋ ሙዚየምን ለመገንባት ጨረታ የወጣው ከቤተ መንግሥት ፓርኪንግ እና ከአብርሆት ቤተ መጽሐፍት ፕሮጀክቶች ጋር በአንድ ላይ እንደነበር እስክንድር ያስታውሳል። እነዚህን ፕሮጀክቶች ለመገንባት የሚጫረቱ ተቋራጮች የህንጻውን ንድፍ የሚሠራ የአርክቴክት ድርጅት አብረው ማቅረብ ነበረባቸው።
በዚህ ጨረታ ላይ የሚወዳደረው ጂያንግሱ ኢንተርናሽናል ለኢትዮጵያዊው የአርክቴክቸር ድርጅት “እስክንድር አርክቴክትስ” የእንጣመር ጥያቄ አቀረበ።
“እነዚህን ፕሮጀክቶች ሲጫረቱ ከፕሮጀክቶቹ ውስጥ ‘የትኛው ውስጥ መሳተፍ ትፈልጋለህ?’ ተብሎ ነው [ጥያቄው] የመጣው። ከነበሩት ውስጥ ይበልጥ ሊፈትነኝ የሚችል እና ሀሳቡም በጣም ቅንጭብ ሆኖ የቀረበ ስለሆነ፤ ብዙ ዲዛይን የማድረግ ዕድል ስለሚኖረኝ ዓድዋን መርጬ ከቻይና ጂያንግሱ ግሩፕ ጋር ተጣማሪ ሆነን እዚህ ውስጥ ገባን” ይላል ሥራው የመጣበትን አጋጣሚ ሲያስታውስ።
ፕሮጀክቱን ያስጀመረው በቀድሞው የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ የሚመራው የከተማዋ አስተዳደር የሚገነባውን ህንጻ በተመለከተ ያስቀመጣቸው የመነሻ ሀሳቦች ነበሩ። ህንጻው የሚኒሊክ ሀውልት ከሚገኝበት መንገድ እኩል ሆኖ እንዲጀምር እና እጅጉን ከፍታ ያለው እንዳይሆን ማድረግ ከከተማ አስተዳደሩ መነሻዎች ውስጥ አንዱ ነው።
በሙዚየሙ ህንጻ ላይ የሰንሰለታማ ተራራ እና የነጋሪት ሀሳቦችን እንዲጸባረቁ ማድረግም የከተማ አስተዳደሩ መስፈርቶች ነበሩ። እነዚህ ሀሳቦች እንዴት ይካተቱ የሚለው ደግሞ የህንጻ ነዳፊው እስክንድር ፈጠራ ነው።
“የራሴን ሀሳቦች እንድጨምር ነጻነት ነበረኝ” የሚለው አርክቴክቱ፤ “ሁልጊዜ የሚጠየቀውን ኢትዮጵያዊ ኪነ ህንጻ” ለመሥራት ሙከራ ማድረጉን ይናገራል።
ከሚኒሊክ ሀውልት ጋር ፀሐይ የሚጋራው የምድር ቤት ነጋሪት
በ3.3 ሄክታር ላይ ያረፈው የዓድዋ ሙዚየም ቁመቱን ከፍ ያደረገ አንድ ወጥ ህንጻ አይደለም። በተለያዩ መንገዶች የተሳሰሩ እና የአጠቃላይ ህንጻው አካል የሆኑ የተለያዩ ስብስቦችን (ሰብ ሴቶችን) የያዘ ነው።
ወደ ዓድዋ ሙዚየም የሚያስገቡት አራት ዋነኛ መግቢያዎች፤ የሚያደርሱት የተለያየ ገጽታ እና አገልግሎት ወዳላቸው የህንጻው ክፍሎች ነው። መግቢያዎቹ ስያሜያቸው የደቡብ ጀግኖች፣ የሰሜን ጀግኖች፣ የምሥራቅ ጀግኖች እና የምዕራብ ጀግኖች የሚል ነው።
እስክንድር፤ “ታሪክ እንደሚያሳየው ከሁሉም የኢትዮጵያ አቅጣጫ [ጦርነቱ ላይ] ተሳትፎ ተደርጓል ነው። ስለዚህ ሁሉም በአቅጣጫ ተወክለዋል። የበሮቹ ስያሜ ሲሰጥ ስሜቱም፣ ተመሳሌትነቱም እርሱ ነው” ይላል ከስያሜው ጀርባ ያለውን ምክንያት ሲያስረዳ።
ከዓድዋ ጦርነት ጋር የተያያዙ ቅርሶች የሚቀመጡበት ሙዚየም የሚገኘው በሚኒሊክ ሀውልት በኩል ባለው የሰሜን ጀግኖች መግቢያ ነው። ይህ መግቢያ ሀውልቱ ከሚገኝበት መንገድ እኩል (flat) ሆኖ የሚጀምር ሲሆን ለዓድዋ ድል በዓል ማክበሪያ የሚውል ሰፊ ፕላዛን ይዟል።
ከዚህ ዓመት ጀምሮ የዓድዋ ድል በዓል በዚህ ስፍራ ላይ እንደሚከበር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።
በዓድዋ ድል በዓል ማክበሪያው ስፍራ መሀል ላይ በአንድ ጎኑ ከፍ ያለ ባለመስታወት ክብ ቅርጽ ተቀምጧል። ከመስታወቱ ስር የሚገኘው፤ ምድር ቤት (basement) ውስጥ የተሠራው ባለ ሁለት ወለል ሙዚየም ነው።
መስታወቱ፤ አስፓልቱን ተሻግሮ ባለው የሚኒሊክን ሀውልት ላይ የምታርፈውን ፀሐይ ወደ ታች አውርዶ ምድር ቤት በሚገኘው ሙዚየሙ ውስጥ ተፈጥሯዊ ብርሃን ይፈነጥቃል። በክብ መስታወት (circular skylight) በኩል 20 ሜትር ቁልቁል የሚወረወረው የፀሐይ ብርሃን ማረፊያው ደግሞ በሙዚየሙ መሀል፣ ከመስታወቱ ትይዩ የተቀመጠ ነጋሪት ነው።
እስክንድር የነጋሪቱን አቀማመጥ ሲገልጽ፤ “የሙዚየሙ መጀመሪያም፣ ማጠንጠኛም ነው” ይላል።
“ጦርነት ሲገባ፣ አዋጅ ሲነገር፣ ክተት ሲታወጅ የሚጎሰመው ነጋሪት ነው። ነጋሪቱ መሃል ላይ ሆኖ የሙዚየሙ የትኩረት ማዕከል (focal point) ነው፤ መነሻም ነው። ሙዚየም ውስጥ ስትገባ ጉብኝትህን ከአንድ ነገር ትጀምራለህ” ሲል ያብራራል።
“ሙዚየሙ ራሱ ሙሉ በሙሉ ከመሬት በታች ነው ያለውና ቀጥታ የሚመጣልህ ብርሃን ነው” የሚለው አርክቴክቱ፤ “ብርሃንን ቀርጾ ማስገባት እና በብርሃን መጫወትን” ሙከራ ያደረገበት የህንጻው ክፍል መሆኑን ያስረዳል።
እስንክድር፤ በህንጻው ንድፍ ላይ ደጋግሞ ያንጸባረቀው ሌላኛው ሀሳብ የዓድዋ ጦርነት የተካሄደበትን ምድረ ገጽ የሚወክለው ሰንሰለታማ ተራራ ነው። የህንጻው የውስጥ እና የውጭ ጎኖች፣ የደረጃ መደገፊያዎች ላይ በተቀመጡት ወጣ ገባ እያሉ አግድም በሚሄዱ መስመሮች እንዲሁም በደረጃ ፋንታ በተቀመጡት ተዳፋቶች (ramp) ላይ መንጸባረቁን እስክንድር ይናገራል።
ተራራ “በአርክቴክቸራል ቋንቋ” ከተገለጸባቸው የህንጻው ክፍሎች ውስጥ አንዱ በማዘጋጃ ቤት በኩል የሚገኘው መግቢያ ነው። በዚህ መግቢያ ላይ ከደረጃ ባሻገር የተቀመጠው ዚግ ዛግ የሚሄድ ተዳፋት (ramp) ከርቀት ሲታይ የተራራ ይመስላል።
በዚህ መግቢያ ወደ የሚዘልቁ ጎብኚዎች ደረጃውን እንደጨረሱ የሚያገኙት እቴጌ ጣይቱ በመቀለው ውጊያ የውሃ ምንጮችን በመያዝ የጣልያን ጦር እጅ እንዲሰጥ ለተጠቀሙት ስልት መታሰቢያነት የዋለ የውሃ ፋውንቴን ነው።
ተራራማ እና ድንጋያማ አካባቢን በዓድዋ ሙዚየም ላይ የማንጸባረቅ ሀሳብ፤ የህንጻው ቀለም ላይም ታይቷል። በተለይ በህንጻው የውጭ ክፍል ላይ ጎልቶ የሚታየው ቀለም “ሸክላ መሳይ” ነው።
ከህንጻው ትልቅነት አንጻር የተለያዩ ቀለማትን መጠቀም ይቻል እንደነበር የሚናገረው እስክንድር፤ ይበልጥ “ተፈጥሯዊ ነው” ብሎ ያሰበውን ይህንን ቀለም በብቸኝነት መጠቀሙን ይገልጻል። “ተራሮቹን የበለጠ የመግለጽ አቅም ያለው ቀለም ነው። ለህንጻውም የራሱ መገለጫ ሰጥቶታል” ይላል።
ድንጉዛ በፒያሳ
እስክንድር፤ አንድ ህንጻ ሲሠራ ለአካባቢው እና ለነዋሪዎች የሚያስተላልፈው “ጥበብ” ሊኖረው ይገባል የሚል እምነት አለው።
በዓድዋ ሙዚየም ላይ “ሞክሬዋለሁ” የሚለው ዋነኛው ጉዳይ ኢትዮጵያዊ ምልክቶች እና መገለጫዎችን በህንጻ ዲዛይን ውስጥ የማካተት ሀሳብን ነው።
“ሌሎች አገራት ላይ ብዙ ፓተርኖች ላይ ኤክስፐርመንት ያደርጋሉ። እኛ አሁን ማየት ያለብን ወደ ውጭ ሳይሆን ወደ ውስጥ ነው። እነዚህን ነገሮች መሞከር እፈልግ ነበር” ሲል የህንጻን ገጽታ ከአገርኛ አውድ ጋር (local context) ጋር የማስተሳሰር ሙከራው በዚህ ፕሮጀክት መጀመሩን ያስረዳል።
በኢትዮጵያ ባህል ውስጥ “ያልታዩ ጥበቦች” መኖራቸውን የሚያነሳው እስክንድር፤ “ዘመናዊ ነገር እንሥራ ማለት አይደለም። በብዙ መልኩ እኛን የሚመስል ነገር [ወደ ማስቀመጥ] ነው መሄድ ያለብን” ይላል።
በዓድዋ ሙዚየም ላይ ያካተተው አንዱ አገርኛ ምልክት በደቡባዊ ኢትዮጵያ በጋሞ እና በወላይታ አካባቢዎች የሚለበሰው “ድንጉዛ” ነው። በደማቅ ቀይ፣ ቢጫ እና ጥቁር ቀለሞች ዐይን የሚገባው ድንጉዛ፤ በጥለቱ ላይ የሚቀመጡት ወጣ ገባ ያሉ መስመሮችም መለያዎቹ ናቸው።
ይህን የድንጉዛ ጥለት የመስመር አካሄድ ከ100 ሜትር በላይ በሚሄድ የህንጻው ክፍል ላይ ተንጸባርቋል። በህንጻው የውጪ ክፍል ላይ የሚገኙት የጦር እና ጋሻ ምልክቶች የተቀረጹት በድንጉዛ የመስመር አካሄድ በተቀመጡ ቅርጾች ላይ ነው።
ከአክሱም ሀውልት እና ከላሊበላ ኪነ ህንጻ የተወሰዱ ምልክቶችም በህንጻው የደረጃ ድጋፎች እና የኮሪደር ስፍራዎች ላይ ማንጸባረቁንም አርክቴክቱ ይናገራል።
የድሮዋ ፒያሳ መልክ በአዲሱ የአራዳ ምልክት ላይ
የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት፤ አዲስ አበባ አሉኝ የምትላቸው ኪነ ህንጻዊ ውበትን የተጎናጸፉ ህንጻዎች የተገነቡበት ነው። ብሔራዊ ቲያትር፣ ማዘጋጃ ቤት እና የንግድ ባንክ የቀድሞ ዋና መሥሪያ ቤት ከእነዚህ ህንጻዎች መካከል ናቸው።
እነዚህን ህንጻዎች የተነደፉት እንደ ፈረንሳዊው ሄንሪ ሾሜት እና ጣልያናዊው አርትሮ ሜዜዲሚ ባሉ የውጭ አርክቴክቶች ነው። እስክንድር፤ “የአካባቢውን ሁኔታ አጥንተው አካባቢያዊ አውዱን (local context) ለማምጣት የሚሞክሩ አርክቴክቶች ነበሩ” ሲል ያሞካሻቸዋል።
የእነዚህ ህንጻዎች አንድ መገለጫ ከፊታቸው አጭር ሆነው ለእግረኛ መረማመጃ ስፍራ መፍጠራቸው ነው። “የአራት ኪሎ መደዳው እና ዞሮ ወደ ፒያሳ ሲመጣ [ህንጻዎች] በደረጃዎች እተገናኙ አርኬድ (ታዛ) አላቸው። እግረኛ በምቾት፣ በጥላ እንዲሄድ ነው” የሚለው አርክቴክቱ፤ የፒያሳ ህንጻዎች ከመንገዱ ጋር “በጣም የተናበቡ” መሆናቸውን ያነሳል።
“ከፒያሳ የምወስደውን የበፊት (traditional) ፕላኒንግ ልበለው። አሁን ዘመናዊ ፕላኒንግ ደግሞ አለ። እኔ ወደዚያ [ወደበፊቱ] ነው መመለስ የምፈልገው። ያ ጥሩ ፕላኒንግ ነው” የሚለው አርክቴክቱ በዓድዋ ሙዚየም ላይ እግረኛ የሚራመድባቸው ታዛዎችን መፍጠሩን ያስረዳል።
በሙዚየሙ ህንጻ ውስጥ የሚገኙት መደብሮች ደጃፋቸው እንደ ፒያሳው መብራት ኃይል ህንጻ እግረኛን የሚያስተናግዱ ናቸው።
ከአራዳ ህንጻ ጋር አዋሳኝ በሆነው አቅጣጫ የሚገኘው የዓድዋ ሙዚየም ደግሞ ሌላኛው የፒያሳ ገጽታ ምሳሌ አድርጎ የተነደፈ ነው። በሙዚየሙ ሁለት ብሎኮች መካከል ረጅም ደረጃ የተዘረጋበት ይህ የደቡብ ጀግኖች መግቢያ፤ ከፒያሳው 70 ደረጃ ጋር ተመሳሳይነት አለው።
የዓድዋ ሙዚየም ሀውልቶች እና የሚነሱ አስተያቶች
የዓድዋ ሙዚየም የህንፃ ንድፍ ሲሠራ ከጦርነቱ ጋር የተያያዙ 40 ገደማ ቅርጾች እንደተካተቱበት እስክንድር ይናገራል። ከእነዚህ የሚቆሙ እና በግድግዳ ላይ የሚለጠፉ ቅርጾች ውስጥ ግማሾቹ መሠራታቸውን የሚገልጸው አርክቴክቱ፤ “የተወሰኑት ወደፊት ይሰራሉ” ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሷል።
በአሁኑ ጊዜ ተቀርጸው ከቆሙት ሀውልቶች መካከል የአጼ ሚኒሊክ እና የእቴጌ ጣይቱ እንዲሁም 12 የጦርነቱ አዝማቾች ይገኙበታል። የአጼ ሚኒሊክ እና እቴጌ ጣይቱ ሀውልት የውሃ ፋውንቴን በሚገኝበት ፕላዛ ላይ ጎን ለጎን ተቀምጠዋል። የጦር አዝማቾች ሀውልት ደግሞ በከተማ አዳራሽ የውጨኛ ክፍል ላይ በሚገኙት አምዶች ላይ ተቀምጠዋል።
እንደ እስክንድር ገለጻ የሀውልቶቹን አቀማመጥ በተመለከተ መጀመሪያ የሠራው ንድፍ ላይ ተጨማሪ ሀሳቦች ተካትተዋል። በንድፉ ላይ የ12ቱ የጦር አዛዦች ሀውልቶች በአንድ እልፍኝ ላይ እንዲቀመጥ ተደርጎ ነበር። የእቴጌ ጣይቱ ሀውልት ደግሞ በመቀለው ጦርነት ንግሥቲት ላመጡት የጦርነት ስልት መታሰቢያ በተሠራው የውሃ ፋውንቴን መሃል ላይ እንዲሰፍር ተነድፎ ነበር።
የእነዚህ ሀውልቶች ፎቶግራፍ በሶሻል ሚዲያ ገጾች ላይ ከተሰራጨ በኋላ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ተደምጠዋል። በቅሬታ መልክ ከተነሱት አስተያየቶች ውስጥ የሀውልቶቹን የቁመት መጠን እና ገጽታ እንዲሁም የተሰሩበት ቁስን የተመለከቱ ይገኙበታል። የሠዓሊያን እና የቀራፂያን ማኅበር በሙዚየሙ ቅርፃ ቅርፅ ሥራዎች ላይ “አልተሳተፍኩም” ማለቱም ሌላኛው አስተያየት ነበር።
የሀውልት እና ሌሎች የቅርፅ ሥራዎች የሚከናወኑት ከ20 እስከ 25 አባላት ባሉት የቀራፂያን ቡድን መሆኑን የሚናገረው እስክንድር፤ “በፎቶግራፍ የተደገፉ የታሪክ መጽሐፍትን ይዘው፤ ጊዜው በቂ እንኳን ባይሆን [የሀውልቶቹን] ገጽታ ከዚያ ላይ እያጠኑ ሠርተዋል። ይህንን አይቻለሁ” ይላል።
ይሁንና የቅርጽ ሥራዎቹ ቀድመው ተጀምረው ለጥናት ሰፊ ጊዜ መሰጠት እንደነበር ይገልጻል።
አርክቴክቱ እንደሚያስረዳው በዓድዋ ሙዚየም ውስጥ ከሚቀመጡት የቅርፃ ቅርፅ ሥራዎች መካከል “ወሳኝ” የሆኑት ከነሐስ እንዲሠሩ በህንጻው ንድፍ ላይ ሰፍሯል። ይሁንና በአሁኑ ሰዓት ለሀውልቶቹ ግንባታ ጥቅም ላይ የዋለው ቁስ ሌላ መሆኑን አመልክቷል።
“እኛ ስናስቀምጥ ወሳኝ ሥራዎች በነሐስ እንዲሠሩ ተቀምጧል። የተያዘላቸው የሥራ ዝርዝር እንደዚያ ነው። በዚህኛው ግን አሁን ለማስመረቂያ ስለማይደርሱ፤ በመቀጠል የነሐስ ሀውልቶች እንደሚሠሩ ነው የማውቀው” ሲል በህንጻው ንድፍ ላይ በተቀመጠው መሠረት ሀውልቶቹ በድጋሚ ይሠራሉ የሚል እምነቱን ገልጿል።
ሀውልቶቹ አሁን የተሠሩበት ቁስም ቢሆን ግን ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ቅርፆችን ለመሥራት ጥቅም ላይ የዋለ መሆኑን አስረድቷል።
ከቅርፅ ሥራዎች ጋር በተያያዘ የሚነሱትን አስተያየቶች እንደሚጋራ የሚናገረው እስክንድር፤ “የአርት ሥራን መልሶ አሻሽሎ መሥራት፣ መለወጥ ይቻላል” ይላል። በአሁኑ ሰዓት ያልተሠሩት የቅርፃ ቅርፅ ሥራዎች ሲከናወኑ “ከዚህ ልምድ ተወስዶ የሚቀጥለውን ሂደት በማሳተፍ፣ ጊዜ በመስጠት እና በጥናት ይበልጥ ቢኬድበት” የሚል ምክረ ሀሳቡን አስቀምጧል።
የሀውልቶቹን ሥራ ጨምሮ ከዋና ንድፍ ላይ ለውጥ የተደረገባቸው ነገሮች ቢኖሩም “90 በመቶ በሚባል ደረጃ” ያስቀመጠው አርክቴክቸር ወደ ተግባር መተርጎሙን እስክንድር ይናገራል። የዓድዋ ሙዚየም ግንባታ “በአስቸጋሪ” ሁኔታ ውስጥ የተከናወነ መሆኑን በመጥቀስም ጥሩ ሥራ መሠራቱን ያስረዳል።
ከሙዚየሙ ግንባታ ጋር የሜካኒካል፣ የኤሌክትሪካል እና የኦዲዮ ቪዥዋል ሥራዎችም “በጣም በከፍተኛ ሁኔታ” መከናወናቸውን በመግለጽ፣ በግንባታው ሂደት ጥቅም ላይ የዋሉት እቃዎችም ደረጃውን የጠበቁ እንደሆኑ አክሏል።
እስክንድር፤ “ለዓድዋ በሚመጥን መልኩ ያለንን ሁሉ ሰጥተን ሠርተነዋል። ለብዙ ጊዜ ሌሎች ሥራዎችን ሳንሠራ ሁልጊዜ እዚህ ጋር ነን። ማንኛውም እንደዚህ [ዓይነት] ኪነ ህንጻ ሲሠራ ፍጹም ሊሆን አይችልም፤ ብዙ ትችቶች እንደሚመጡ አውቃለሁ። ግን ባለን አቅም ሁሉ የምንችለውን ጥረት አድርገን [ሠርተነዋል]” ይላል።
እስክንድር ወደ ሦስት አስርት ዓመታት እየተጠጋ ባለው የሥራ ልምዱ ውስጥ ትልቁ ስለሆነው ፕሮጀክት ሲያነሳ፤ “በውጭም ዓለም ሙዚየምን የሚሠራ አርክቴክት ‘ዕድለኛ ነው’ ይባላል። በክፍለ ዘመን [አንዴ] የሚመጣ ዕድል ሊሆን ይችላል። እጅግ በጣም ዕድለኛ ነኝ” ሲል ስሜቱን ለቢቢሲ አጋርቷል። (ቢቢሲ አማርኛ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply