… በበረዶ፣ በዝናም፣ በሐሩር፣ በቁሩ . . . መፈክር አንግበን፣
ላንቃችን እስኪታይ – አምባገነኖችን በጩኸት አውግዘን፣
የድምጽ-አልባውን ሕዝብ – የጭቆና ብሶት፣
ላለም ስናሰማ – ለሩብ ምዕተ-ዓመት፤
ጆሮ ዳባ ብለው – የተሳለቁብን፣
ከጨቋኝ ወግነው፣ በዶላር አፋፍተው…
ነጻነታችንን በጅ-አዙር ያስቀሙን. . .፤
ቦ! ጊዜ ለኩሉ!…
የተፈጥሮ አዙሪት-ህግ – የወር-ተራው እዚያም ደርሶ፣
በታላቋ አሜሪካ – “አምባገነን” ትራምፕ ነግሶ፣
‘የባቢሎን ግምቡን‘ አጥሮ . . . ነጻነትን ፊጥኝ አስሮ፣
ህገ-መንግስት ተሰውቶ. . . ፍርድ ቤቱም ለርሱ አድልቶ…፣
የአሜሪካ ሃምሳ ስቴቶች – ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው፣
በመፈክር ተጥለቅልቀው – በራብ-አድማ ጠቁረው ከስተው፤
በላያችን የወረደ ፣ መብረቅ… ዝናም ወርዶባቸው፣
የነጻነት ረሃብ፣ ጥሙ – ዘልቆ ገብቶ ካንጀታቸው…፤
… እነ ካርተር፣ እነ ቡሽ፣ እነ ኦባማ፣ እነ ክሊንተን… ፣
እነ ኮኸን፣ እነ ራይስ፣ እነ ጌይል ፣ እነ ሱዛን…፣
ኋይት-ሃውስ ተኮልኩለው – ዩ ኤን ደጃፍ ኒውዮርክ ቆመው፣
“አምባገነን ይውደም!” ሲሉ – ማየት ነበር “እምመኘው”!
ለዘረኞች ድጋፍ ሰጥተው – በእብለት፣ በሳቅ… እያሾፉ፣
”በዴሞክራሲ ተመረጡ…” “መቶ ፐርሰንት አሸነፉ…”፣
ብለው በኛ ሲያላግጡ – ባደባባይ ሕዝብን ንቀው፣
ቢያስገርመኝ ድርጊታቸው – ቢያቃጥለኝ ተግባራቸው፣
እነሱም ዘንድ የኛ ዕጣ – በእውን ደርሶ በቤታቸው፣
ስቃያችን ቢታያቸው – ሕመማችን ቢሰማቸው፣
ብዬ አሰብኩኝ በመቆጨት – ተስፋ ብቆርጥ፣ አቅም ባጣ፣
እናት ሀገር መተብተቧ – ቢያሳዝነኝ ባለም ጣጣ!
ጌታቸው አበራ
ጥቅምት 2009 ዓ/ም
(ኦክቶበር 2016)
Leave a Reply