ግንቦት 20 ከመደዴ ቀንነት ተመንጥቆ፣ ቅድስና ተቀብቶ መዘከር ከጀመረ ይኽው ሀያ ስድስት አመት ሆነ፡፡ በየካቲት 1983 አ.ም. ጎንደር በኢህአዴግ ሲያዝ፣ እኔና ጓደኞቼ እናስተምርበት ከነበረው ከጎርጎራ መንደር፣ በውጫሌ በኩል በኢህአዴግ ተሸኝተን፣ ደሴ ላይ አንድ ኩንታል ስንዴ ተመጽውተን አዲስ አበባ ገባን፡፡
ውጫሌ ላይ የሸኙን የኢህአዴግ ታጋዮች ቀድመውን አዲስ አበባ እንደሚገቡ ነግረውን ነበር፤ እንዳሉት ቀድመውን ባይገቡም፣ ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ ከኢህአዴግ የመጨረሻ ግዛት ከውጫሌ የደርግ ግዛት እስከነበረው የሀይቅ ከተማ የነበረውን የፈሪ ምድር ያቋረጥነው በእግር ነበር፡፡
ያንን ረባዳ ለምለም ስፍራ በእግር ስጓዝ አስበው የነበረው (አሁን ምኞት ብለው ይሻላል) ልብን የሚያሞቅ፣ ብርታት የሚሰጥ ነገር እስካሁን ከህሊናዬ አልጠፋም፡፡ ” . . . . ከሁሉም በላይ የደርግ መንግስት ወድቆ፣ ሀገሪቱ ከነበረችበት ማጥ ስትወጣ ይታየኝ ነበር፤ የኢህአዴግ ታጋዮች እየከፈሉት ያለው መስዋእትነት ልቤን ያሞቀው ነበር፤ ድሆች በቀን ሶስት ጊዜ በልተው ሲያድሩ ይታየኝ ነበር፤ የግል ፕሬስ ሲያብብ. . .ሲያፈራ፣ ሰዎች ያለፍርሀት ሀሳባቸውን በነጻነት ሲገልጹ ይታየኝ ነበር፣ ዜጎች በመረጡት መንግስት ሲተዳደሩ ይታየኝ ነበር፡፡ . . . “
ይህ ሁሉ በደርግ የአገዛዝ ዘመን አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ በደርግ የአገዛዝ ዘመን ድንበርዋ የታፈረና የተከበረ እትዮጵያ ነበረች፤ ይህች ኢትዮጵያ ጠንካራ የፍትህ ስርአት ነበራት፤ ደርግ ወጣቱን ወደ እስር ቤት ያጋዘውና በየመንገዱ የረሸነው በመደበኛ ፍርድ ቤት ፍትህን መሳሪያው አድርጎ አይደለም – የራሱን የጦር ፍርድ ቤት መስርቶ ነው፡፡
ዛሬ ከ26 አመት በኋላ የደርግ አንባገነናዊ መንግስት የለም፡፡ በኢህአዴግ ያገኘሁት ብቸኛ በረከት እሱ ነው – የደርግ መገርሰስ፡፡ እነዚያ ሁሉ . . ከውጫሌ እስከ ሀይቅ በእግር ስጓዝ አስባቸው የነበሩት፣ በተስፋ አሙቀው ለመንገዴ ብርታት የነበሩት ሀሳቦቼ ሁሉ ሀሳብ ሆነው ቀርተዋል፡፡ ብዙዎች “ልማትን ከኢህአዴግ አግኝተሀል” ይሉኛል፡፡
እኔ ግን፣ “አንድ መንግስት መንገድ መስራትና ባቡር መዘርጋት፣ ውሀና መብራት ማስገባት ስራው – ግዴታው ነው፣ ያለዚያ ስለምን ይነግሳል? አባት ልጁን ማልበስና መመገብ ግዴታው ነው እንጂ እንደ ውለታ ተቆጥሮ ያስመሰግነዋልን?” እላቸዋለሁ፡፡
ይሁን እንጂ ድሆች በቀን ሶስቴ በልተው ሲያድሩ አላየሁም፤ ህዝቦች ሀሳባቸውን በነጻነት ሲገልጹ አላየሁም፣ ዲሞክራሲ ሰፍኖ አላየሁም፡፡ እነዚህ ግን በደርግም ዘመን አልነበሩምና ኢህአዴግ አልነጠቀኝም፤ ኢህአዴግ ያጎደለብኝ በደርግ ጊዜ የነበሩትን ድንበሯ የተከበረ ኢትዮጵያና ፍትህ የማይዛባበት ፍርድ ቤት ነው፡፡
(በድሉ ዋቅጅራ)
Leave a Reply