በዞን ዘጠኝ ዓለማቀፍ የማሰቃየት ተግባር ተጠቂዎችን የመደገፍ ቀን (International Day in Support of Victims of Torture) ከጎርጎሮሳዊያኑ 1998 ጀምሮ በየዓመቱ ጁን 26 ቀን ይከበራል፡፡ ቀኑ ጁን 26 ላይ የሚከበርበት ሁለት ምክንያቶች ሲኖሩ፤ አንደኛ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር በመስራች አባል አገራት ቻርተሩን የፈረሙበት ቀን ጁን 26፣ 1945 ሲሆን በሁለተኝነት የተባበሩት መንግስታት የፀረ ማሰቃየትና የጭካኔ የቅጣት ተግባር ኮንቬንሽን (Convention against Torture and Other Cruel, Inhuman or Degrading Treatment or Punishment) ወደ ስራ የገባው ጁን 26፣ 1987 በመሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የቻርተሩም መስራች ፈራሚ ስትሆን ኮንቬንሽኑን ደግሞ በፓርላማ አጽድቃ ተቀብላለች፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ የማሰቃየት ተግባር እንደሚፈፅም ለሚቀርብበት ትችት በጥቅሉ ‹‹ውሸት ነው›› ከማለት ውጭ ሁኔታዎቹን ለማሻሻል ምንም አይነት እርምጃ እየወሰደ ካለመሆኑም በላይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ነገሮች እየተባባሱና በተለይም የፖለቲካ እስረኞች ላይ ጠንክረው ቀጥለዋል፡፡ እኛም በኢትዮጵያ ያለውን የማሰቃየት ተግባር ስፋት ያሳያል ይሆናል በሚል መነሻ ቀኑ የሚከበርበት ጁን 26 ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ አማካኝነት ክስ ተመስርቶባቸው ታስረው የሚገኙና ታስረው የነበሩ ግለሰቦች የደረሰባቸውን የማሰቃየት ተግባራት ራሳቸው በተለያዩ ጊዜያት እንደተረኩት በማሰባበሰብ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡
የተራኪዎቹን ማንነት በጽሁፉ ግርጌ ላይ ያገኙታል፡፡
አሕመድ ሙስጠፋ[1]
[ገና] ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ [ተረኛው ፖሊስ] በሩን አንገጫግጮ ከፍቶ ‹‹አህመድ ሙስጠፋ ተነስ ውጣ!›› አለኝ። ተነሳሁና ወጣሁ። እጄን በሰንሰለት አስሮ ወስዶ የምርመራ ክፍል ውስጥ ገብቼ ተቀመጥኩ። አጠገቤ ባለው ወንበር ላይ ጥቁር ቡኒ እስካርቭ ተቀምጧል። ከትንሽ ቆይታ በኋላ ወጥቶ አይኔን በእስካርቩ ሸፈኖ እስኪያመኝ ግጥም አድርጎ አሰረኝ። አፍንጫዬ አየር ሲያንሰኝ ተጨናነኩ። ‹‹አፈነህ›› ብሎ ትንሽ ከፍ አደረገልኝ። እጄን ይዞ የትኛው ክፍል ውስጥ እንደገባሁ እንዳላውቅ በኮሪደሩ አሽከረከረኝ። በመጨረሻም አንድ ክፍለ ውስጥ አስገብቶ ለቀቀኝ። ሰው በቀኜ በኩል እንዳለ ተሰማኝ። ወዴት መሄድ እና ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግን አላወኩም። አንዱ እጄን ይዞ ካራመደኝ በኋላ ቁጭ በል አለኝ። ሁኔታው ሁሉ የሚያስጨንቅ ነበር። ቁጭ በል ሲለኝ ኤሌክትሪክ ወንበር መሰለኝ። ቀስ ብዬ ተቀመጥኩ። ደስ አለኝ። ትንሽ ተረጋጋሁ። ‹‹እሺ አህመድ ሙስጠፋ!›› ጎርናና ድምፅ ተሰማኝ። ‹‹አቤት›› አልኩት። ወዲያው ቁጣ ጩኸት ተከተለ። በዚያ ጎርናና ድምፅ ክፍሉን አስጨነቀው። ‹‹ከኔዘርላንድ ካለ ሰው ጋር ስትፃፃፍ የነበረውን በዝርዝር ተናገር›› አለኝ። ‹‹ኧረ እኔ ኔዘርላንድ የማውቀው ሰው የለኝም።›› አንባረቀ። ንዴት በተሞላበት መልክ ተስፈንጥሮ ተነስቶ ‹‹ተኛ!›› ብሎ ከወንበሬ አስነሳኝ። በፊት ለፊቴ ወለል ላይ ተደፋሁ። እግሬን ገልብጦ ያለርህራሄ ገረፈኝ። ተወራጨሁ። ጮህኩ። ግርፊያውን አቆመና ‹‹ቁም›› አለኝ። ቆምኩ። ‹‹ሱሪህን አውልቅ።›› አወለቅኩ። ብልቴን ገረፈኝ። ጮሄ ተጎነበስኩ። ‹‹እኔ እንዲህ እንደማለቅህ ምልክት እንዲሆንህ ነው! ቁጭ በል!›› አለኝ። ተቀመጥኩ። ኔዘርላንድ ከሚኖር ሰው ጋር ተፃፅፈሃል ያለውን እንግሊዘኛ መልእክት አነበበልኝ። ዲያስፖራው ሙስሊሙን በሙሉ ሀይሉ ሊያግዝ የሚገባው ጊዜ ላይ መሆኑን እና መልእክቱ ለተላከለት ሰው ምስጋና የሚያቀርብ ነው።
ፈፅሞ እንደማላውቀውና ኔዘርላንድ ከሚኖር ሰው ጋር የተላላኩት መልእክት እንደሌለ ገለፅኩለት። አጠገቤ ቆሞ አናቴን ያንጓጓው ጀመር። ቦርጫም፣ ወፍራም እና ረጅም ሰው መሆኑን ተረዳሁ። ርእሱን ቀየረና ስለኳታር ጉዞ ይጠይቀኝ ጀመር። ‹‹ኳታር የሄዳችሁት ለሌላ አላማ ነው›› አለኝ። ‹‹አይደለም›› አልኩት። ድጋሚ ገረፈኝ። ጭንቅላቴን በሁለት እጁ መታኝ። በቦክስ፣ በእርግጫ፣ በዱላ አጣዳፈኝ። ለተወሰኑ ደቂቃዎች የአባቱን ገዳይ እንዳገኘ ንዴት በተሞላበት ሁኔታ ተሳደበ፤ ጮኸ፤ ተማታ፤ ፍፁም ጤነኛ አይመስልም ነበር። ሰው እንዴት የማያውቀውን ሰው እንዲህ በጥላቻ እና በንዴት ተሞልቶ ያናግራል።
በመሃል ሲጋራውን ያቦናል። ከሌላ መርማሪ ጋር የስልክ ልውውጥ ያደርጋል። ምቱ ሲበዛብኝ ሌላ ዓላማ እንደሌለን፣ የሄድነው ግን ለሥልጠና እንደነበር ነገርኩት። ‹‹ማነው ሥልጠና ይሰጣችሁ የነበረው?›› አለኝ። ነገርኩት። ‹‹የተሰጣችሁ mission (ተልእኮ) ምንድን ነው?›› አለኝ። ‹‹የምን ተልእኮ?›› በድንጋጤ ጠየኩት። በእርግጫና በዱላ አጣደፈኝ። ‹‹እያንዳንዱ ሀገር ለራሱ ደኅንነት እና ሰላም ሲል ከሌላው ጋር የመረጃ ግንኙነት ያደርጋል። ስለዚህ ኢትዮጵያም ከኳታር መረጃ ታገኛለች›› አለኝ። ማእከሉ የሀይማኖት ትምህርት እና ሥልጠና ከመስጠት ውጪ ምንም ተልእኮም ሆነ ከዚያ በኋላ ግንኙነት ኖሮን እንደማያውቅ አስረዳሁት። እሱ ተልእኮ እንዳለ እንዳምን፣ እኔም ተልእኮም ሆነ ግንኙነት እንደሌለን አሳማኝ ነው ብዬ የማስበውን በመግለፅ እንዲያምነኝ ለማድረግ ስንጥር ምሳ ሰአት ደረሰ።
ማቆሚያ ከሌለው ጩኸት፣ ግርፋት፣ እርግጫ፣ ስድብ፣ ቦክስ ምሳ ሰዓት ገላገለን። ‹‹አልሃምዱሊላህ!›› አልኩኝ እረፍት ስላገኘሁ። ወደ ወንበሬ ጠጋ ብሎ ‹‹ደሞዝህ ስንት ነው?›› አለኝ። ነገርኩት። ‹‹ተው ባክህ። ተመልሼ እመጣለሁ። እረፍት የሌለው ምርመራ ነው የምናደርገው›› ብሎ ወጣ። ኮሪደሩን አሽከርክረው አይኔን ያሰሩኝ ክፍል ውስጥ መልሰው አስቀመጡኝ። ወንበሩ ላይ ቁጭ እንዳልኩ እስካርቩን ፈቱልኝ። ለተወሰነ ደቂቃ ዓይኔ ብዥ አለብኝ። በእጄ አሻሸሁት። ሰዓት ሲጠያየቁ ሰማሁ። ሰባት ሰዓት ሆኗል። ‹‹ሰላት ልስገድ›› አልኳቸው። ፈቀዱልኝ። እዚያው ቢሮ ውስጥ ቂብላውን ጠብቄ ሳይሆን ለሱጁድ የሚበቃውን አቅጣጫ መርጬ ሰገድኩ። ስጨርስ ወንበር ላይ ቁጭ አልኩ። ‹‹ቁም›› አሉኝና ምርመራው እስኪጀመር ቆምኩ። ከሰላት በኋላ የሚባል ዚክር አልጨረስኩም ነበርና ዚክሬን ቆሜ ማለት ቀጠልኩ። ‹‹ምን እያልክ ነው?›› ብሎ ተቆጣ። ‹‹ከሰላት በኋላ የሚባል ዚክር ነው›› አልኩት። ‹‹ታዲያ እዛው አትልም ነበር›› ብሎ ዝም አለኝ። መርማሪው ወይም ገራፊው ሲመጣ ድጋሚ አይኔ ታስሮ ወደ መጀመሪያው ክፍል አመራሁ። እስከ አስር ሰዓት ድብደባውና ምርመራው ቀጠለ። አስር ሰዓት አካባቢ ስልክ ተደወለና ቶሎ እንደሚመለስ ነግሯቸው ወጣ። ሌሎችም ተከትለውት ወጡ። አንድ ሰው እንዳለ ይሰማኛል። አፍንጫዬ አካባቢ እስካርቩ ወርዶ ስላፈነኝ ላስተካክለው ሞከርኩኝ። ‹‹አርፈህ ቁጭ በል›› አለኝ። ትንሽ ቆይቶ የማውቀው ድምፅ ሰማሁኝ። እንድቆም አዘዘኝ። ቆምኩ። ዝምታ ሰፈነ። ‹‹ሰላት ልስገድ›› አልኩት። እንደማቅማማት አለና ‹‹ስንት ደቂቃ ይወስድብሃል?›› አለኝ። ‹‹አምስት ደቂቃ ይበቃኛል›› አልኩት። ‹‹እሺ ቶሎ ስገድ›› አለኝ። ቆሜ በነበርኩበት አቅጣጫ በዚያው ሀርሜ ሰላቴን ጀመርኩ። ሁለት ረከአ እንደሰገድኩ ‹‹ቶሎ ብለህ ጨርስ›› አለኝ በቁጣ። ልክ ሱጁድ ስወርድ ሱጁድ በማደርግበት ቦታ አንዱ ቀጥ ብሎ ቆሞ እግሩን ወደ ግንባሬ አስጠጋ፤ ሱጁድ ሳደርግ ጫማው ላይ እንዳደርግ። ራሴን ወደኋላ ሳብ አድርጌ ወለሉ ላይ ሱጁድ አደረኩ። ሱጁዱን እስክጨርስ እግሩን ዞር አላደረገም። ጫማው ፀጉሬን ነክቶ ቆሟል። በጣም የሚረብሽ ስሜት ተሰማኝ። ሀይማኖታችንን መናቅ፣ ክብራችንን መንካት፣ ትእቢት፣ ጀብደኝነት፣ ምን ዓይነት ሰሜት ተሰምቶት እና ምን እንዲሰማኝ ፈልጎ ይህን እንዳደረገ ሳስብ ብዙ የተምታቱ ሀሳቦች ይመጡብኛል። አንድ ሰው እምነቱና ነፃነቱ ሲነካ የሚሰማው ሙሉ ስሜት ውስጤ ድረስ ሰርጾ ተሰማኝ። ኦ … በጣም ስሜት ይጎዳል! ስለ ሃይማኖት እኩልነት፣ የሌላውን ባህል እና እምነት ስለማክበር፣ ስለነፃነት የሚሰበኩ ወሬዎች ሁሉ ባዶ ገለባ ሆኑብኝ። ህግን አክብሮ ያስከብራል የሚባለው አካል ይህን ያህል ሃይማኖት ላይ ሲሳለቅ በፍትህ አካላት ላይ ሊኖረን የሚገባው እምነት እንደ ጉም በኖ እንዲጠፋ ያደርገዋል።
*ምንጭ ፡ ‹የተዘነበለ ፍትህ› መጽሐፍ፣ ሰኔ 2006፣ አዘጋጅ፡ ድምጻችን ይሰማ
አበበ ካሴ[2]
እኔ አበበ ካሴ እባላለሁ፡፡ የሰሜን ጎንደር ተወላጅ ነኝ፡፡ በማዕከላዊ እስር ቤት ከ5 ወር በላይ ታስሬለሁ፡፡ ከዚህ መካከል 4 ወር ከ25 ቀናት በጨለማ ቤት ተቆልፎብኝ ቆይቻለሁ፡፡ ማዕከላዊ በነበርኩበት ወቅት የሁሉም እግርና እጆቼ ጥፍሮች ተነቅለዋል፡፡ አንዳንድ ቀን እጄ ላይ የሆነ ነገር ስለሚወጉኝ ጥፍሮቼ ሲነቀሉ አላውቅም፡፡ ስነቃ ነው መነቀላቸውን የማውቀው፡፡ ከዛም ቁስሉን እየነካኩ ያሰቃዩኛል፡፡ ማደንዛዣ ለምን እንደሚወጉኝ አላውቅም፡፡ ጥፍሮቼን ሲነቅሉኝ ብቻ ሳይሆን ሌላ ጊዜም ራሴን እንድስት ያደርጉኛል፡፡ እጅና እግሬን አስረው እንደ ፍሪጅ ያለ እቃ ውስጥ ያለ በረዶ ውስጥ ያስቆሙኛል፡፡ ለብዙ ሰዓት በጣም ቀዝቃዛ የሆነ ቦታ ላይ እስክደነዝዝ ቆሜ እውላለሁ፡፡ እስኪበቃቸው ከደበደቡ በኋላ እጅና እግሬን አስረው ከምርመራ ክፍሉ በታች በሚገኝ ምድር ቤት ክፍል ውስጥ ያለ ጉድጓድ ላይ ጥለውኝ ይሄዳሉ፡፡ ጉድጓዱ ጉንዳንን ጨምሮ ተባዮች ያሉት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እግሬንና እጄን አስረው ዘቅዝቀውኝ ይሄዳሉ፡፡ የመጣው ሁሉ ዝዋዥዌ እንደሚጫወት ህፃን ወዲያና ወዲህ ያደርገኛል፡፡ ገልብጠው አስረው ሲዘቀዝቁኝ በአብዛኛው ራሴን እስታለሁ፡፡ እግርና እጄን ከወንበር ጋር ያስሩኛል፡፡
ከወንዶች በተጨማሪ ሴቶችም ይመረምሩኛል፡፡ ሴቶቹ የሚመረምሩኝ ራቁቴን አርገው ነው፡፡ እነሱም ራቁታቸውን ሆነው ነው የሚመረምሩኝ፡፡ አሁን ለመናገር የማልደፈርው አፀያፊ ነገርም ፈፅመውብኛል፡፡ ይህን አፀያፊ ነገር የሚፈፅሙት አደንዛዥ እፅ እየተጠቀሙ ነው፡፡ ይህን ሲያደርጉ በአይኔ አይቻቸዋለሁ፡፡ መርማሪዎቹ ሰውነቴን በኤሌክትሪክ አቃጥለውኛል፡፡ ኤሌክትሪኩን የሚሰኩት ደረቴና የውስጥ እግሬ ላይ ነው፡፡ በዚህም የውስጥ እግሬ ተገልብጦ ሌላ ሰውነት አምጥቶ ነበር፡፡ እጄን ወደ ላይ አስረው ብልቴ ላይ ሀይላንድ አንጠልጥለውበታል፡፡ ሴቶቹ ሀይላንዱን የሚበቃቸውን ያህል ያወዛውዙታል፡፡ በዚህም ምክንያት ከጥቅም ውጭ ሆኗል፡፡ የዘር ፍሬየን ከጥቅም ውጭ አድርገው ዘሬን እንዳልተካ አድርገውኛል፡፡ ሽንቴንም መቆጣጠር አልችልም፡፡ ይህን ያህል አሰቃይተው ከጥቅም ውጭ ስሆን ቂሊንጦ አምጥተው ጣሉኝ፡፡ 11 ወር ያህል አልጋ ላይ ነበርኩ፡፡ በኤሌክትሪክ ግርፊያው ምክንያት ግራ ሰውነቴ ሽባ ሆኖ ነበር፡፡ ግራ እግሬ መንቀሳቀስ አይችልም ነበር፡፡ በምርኩዝ ነበር የምሄደው፡፡ አሁን እያነከስኩ ነው የምሄደው፡፡
በተለይ ማዕከላዊ ውስጥ ይህን ያህል የሚሰቃዩኝ ‹‹አንደኛ የሚያግዛችሁ አገር ማን ነው?›› በሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹አማራ ክልል ውስጥ እንድትንቀሳቀሱ የሚተባበሯችሁን የብአዴን ባለስልጣናት ስም ተናገር›› እያሉ ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ የሚያሰቃዩኝ ‹‹የት የት ቦታ ነው የሰለጠንከው?›› እያሉ ነው፡፡
እዚህ ቂሊንጦ ከመጣሁ በኋላም ያሰቃዩኛል፡፡ ወጣቶች እንዳይቀርቡኝ ያስፈራሩዋቸዋል፡፡ ማንም ጠርቶ እንዳይጠይቀኝ እየተደረገ ነው፡፡ ጨለማ ክፍል ወስደውም አስረውኝ ያውቃሉ፡፡ እነሱ ደብድበው ከጥቅም ውጭ ካደረጉኝ በኋላ የምደገፍበትን ምርኩዝም ቀምተውኛል፡፡ ‹‹ይህኮ የጦር መሳሪያ አይደለም፡፡ እንጨት ነው፡፡ ለምን ትቀሙኛላችሁ? ደግሞም እናንተ ናችሁ እንዲህ ያደረጋችሁኝ፡፡›› ብያቸው ነበር፡፡ የሚሰሙ ሰዎች አይደሉም፡፡ የታሰርኩበት ክፍል ውስጥ እንድተኛበት የተሰጠኝ ቦታ ሽንት ቤቱ አጠገብ ነው፡፡ ሽንት እየሸተተኝ ነው የምተኝው፡፡ ‹‹ወደ ሌላ ቦታ ቀይሩኝ!›› ስላቸው ‹‹ደግሞ ለአንተ ይህ አንሶህ ነው?›› ይሉኛል፡፡ ያ ሁሉ ድብደባ ደርሶብኝ አልጋ ላይ በነበርኩበት ወቅት ወጣቶቹ ህክምና እንዳገኝ ወደ ሀኪም ቤቱ ወሰዱኝ፡፡ እነሱ ግን ‹‹ለአንተ ህክምና ሳይሆን ጥይት ነበር የሚገባህ›› ብለው መለሱኝ፡፡ እንዲህ እያሉ ለምን እንደማይገድሉኝ ይገርመኛል፡፡
*ምንጩን እዚህ ላይ ይመልከቱ
አቤል ዋበላ[3]
የተያዝኩበት ማግስት ‹ምንላድርግልህ› የተባለ የምርመራ ክፍሉ አባል ብሄሬን ጠይቆኝ ኢትዬጵያዊ መሆኔን እና በተለያዬ ብሄሮች ስር ራሴን አንደማልገልጽ እና በጥቅል ‹ኢትዬጵያዊ› መባል አንደምመርጥ ነገርኩት፡፡ ተነስቶ ድብደባ ጀመረ ፡፡ በጥፌና በእርግጫ በተደጋጋሚ መታኝ፡፡ ሌላው መርማሪ ንግግራችንን ያልሰማ ከውጪ መጥቶ ያለምንም ጥያቄ ድብዳባውን ተቀላቀለ ፡፡ ከዱላው በተጨማሪ በጣም አጸያፌ ስድቦችን ሰደቡኝ፡፡ ብሄርህን የካድክ በብሄርህ የምታፍር ይሉኝም ነበር፡፡ ከሚያዝያ 19-ሰኔ 26 2006 ባሉት ቀናት ለፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረብ አያድንህም በማለት አጸያፌ ቃላት በመሰንዘር ሰውነቴ ሊቋቋመው የማይችለው የአካል እንቅስቃሴ እንዳደርግ ተገድጃለሁ ፡፡ በተለይ ግንቦት 11 ላይ የዞን 9 አላማ ጠይቀውኝ ስናገር እውነቱን አውጣ በሚል በተደጋጋሚ ድብደባ የደረሰብኝ ሲሆን ደስታ እና ሃሰን የተባሉ ሽፋን ስሞች የሚጠቀመው መርማሪ በተደጋጋሚ ባደረሰብኝ ጥፌ ድብዳባ ጆሮዬ ተጎድቶ በህመም ላይ እገኛለሁ፡፡
ቤቴ የተገኘው ማስታወሻ ደብተሬ ላይ ያሉትን ቃላት ነጣጥለው የሰጠሁት ቃል ውስጥ ያስገቡትን፣ ማስታወሻ ደብተሬ ላይ ያለው ሙሉው ነው አንጂ ተነጣጥሎ ቃሌ ውስጥ ተካቶ አልፈርምም በማለቴ አቶ ፈይሳ፣ አቶ ዬሃንስ (ስማቸው የሽፋን አንደሆነ የምጠረጥረው) ታደሰ (ጥጋቡ በሚልም ይጠራል) ከፍተኛ ድብደባ አድርሰውብኛል፡፡
ድብደባውም ጨለማ ክፍል ውስጥ በማስገባት አፌ ውስጥ ካልሲ በመወተፍ እግሮቼን ከላይ፣ ውስጥ እግሬን እና ከውስጥ ባቴን ታፋዬን እንዲሁም ጀርባዬን በእንጨትና በኮምፒውተር ገመድ ገርፈውኛል፡፡ የምርመራ ክፍሉ ወለል ላይ በደረቴ አንዲሁም በጀርባዬ እያገላበጡ በማስተኛት መላ ሰውነቴን ረግጠው ተራምደውብኛል። አፌን ሳይቀር ረግጠውታል። ይህንን በሚያደርጉበት ሰአት ሞራል የሚነካ ስድብ ይሳደቡ ነበር፡፡ ሁሉም የአካል ሆነ የስነልቦና ጥቃት ሲደርስብኝ እጄ በካቴና ታስሮ ሲሆን በቀን 15 ደቂቃ በላይ የጸሃይ ብርሃን የማላይበት ቀዝቃዛ ክፍል ውስጥ ለ76 ቀናት ቆይቻለሁ፡፡
*ምንጭ፡ አቤል ዋበላ ለኢትዬጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ካስገባው አቤቱታ የተወሰደ
ዘመነ ምሕረት[4]
ጥር 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ማክሰኝት የጽዮን ማርያም ታቦትን ወደ ጥምቀተ ባሕር ስናወርድ በኋላየ የማላውቃቸው ሰዎች መጥተው ያዙኝ፡፡ ሲይዙኝ ምንድን ነው ብየ ገጠምኳቸው፡፡ ከያዙኝ ሰዎች ጋር ስንተናነቅ ፌደራል ፖሊስ ወረረኝ፡፡ የፌደራል ፖሊሶች ከስድስት መኪና በላይ ይሆናሉ፡፡ መጥተው ከዚያው ላይ በአፈ ሙዝ ደበደቡኝ፡፡ ዕውነት ለመናገር መጀመሪያ ሲይዙኝ የሆነ ከቤተሰብ ጋር እኔ ሳላውቀው በተፈጠረ ችግር ሊይዙኝ የመጡ ወንበዴዎች ናቸው የመሠሉኝ እንጅ በመንግሥት የተላኩ እንደሆኑ አላወቅኩም ነበር፡፡ የፖሊስ ዩኒፎርም አልለበሱም፤ ሲቪሎች ናቸው፡፡ ወታደሮቹ ከሕዝብ ፊት ደበደቡኝ፡፡ ልጄና ሚስቴ አብረውኝ ነበሩ፡፡ ልጄ ሕጻን ነው እኔን ሲደበድቡኝ እያለቀሰ መጣ፡፡ የሚገርምህ ልጄን በአፈሙዝ ደበደቡት፡፡
የቀበርከውን አምጣ፣ መሣሪያህን አምጣ አሉኝ፡፡ ቤቴን ሲፈትሹ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ የሰበሰብኩትን የአዲስ ራዕይ መጽሔት አገኙ፡፡ ምክንያቱም በየወሩ የሚሉትን ለማየት ስበስበው ነበር፡፡ በኋላ የደበቅኩት ቦንብ እርሱ ነው አልኳቸው፡፡ የተለያዩ የፖለቲካና የታሪክ መጽሐፍት እንዳገኙ አሁንም ከልጄም ከሚስቴም ፊት ደበደቡኝ፡፡ ሚስቴ ከፊት አትምቱት ብላ እየጮኸች ወጣች፡፡ ጫማዬን አስወልቀው ካሰሩኝ ወደ መኪና ሲወረውሩኝ ሦስት ዓመት የሚሆነው ልጄ መጥቶ ሲይዘኝ መጥቶ ሲይዘኝ በአፈሙዝ መቱት፡፡ ከዚያ ወደ ጉማራ ወንዝ ስንደርስ ዓይኔን ሸፈኑኝ፤ ከዚያ በኋላ የት እንዳስገቡኝ አላውቅም፡፡ አዘዞ ተክለ ሃይማኖት አካባቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ መጀመሪያ የያዘኝ ሰው አሸናፊ ተስፋው የሚባል ነው፤ ከዚያ በኋላ ግን አላውቃቸውም፤ ትግሬዎች ናቸው፡፡ ‹‹ትግርኛ ቋንቋ ተናገር፤ አንተ ትምክተኛ፣ ነፍጠኛ፣ የአማራን የበላይነት ለማምጣት የምትጥር፣…›› ብዙ ብዙ ነገር ነው የሚሰድቡኝ፡፡ የዱላው ነገር ቅጥ የለውም፡፡ ከአውሬም አይጠበቅ እንኳን ከሰው፡፡ እኔን በጣም ደብድበውኛል፤ የኔ ሳይሆን ልጄ ላይ የሠሩት ነው የሚያሳዝነኝ፡፡ እኔማ መቼም አንድ ጊዜ የፖለቲካ ተሳትፎ አድርጌያለሁ፡፡ ወንጀል ባይሆንም ተቃውሚያለሁ፤ አምኜበትም ነው የገባሁ፡፡ ልጄ ግን ምንም ሳይሠራ መደብደቡ ያሳዝነኛል፡፡
ወያኔዎቹ ከአማራው ላይ ያላቸው ጥላቻ በጣም ከፍተኛ ነው ብልህ አልገልጸውም፤ በጣም በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ሕወሓቶች በተቃዋሚ ላይ ሳይሆን በአማራ ላይ ጥላቻ እንዳላቸው ነው የተገነዘብኩት፡፡ ሲደበድቡኝም አንተ አማራ፣ አንተ ትምክተኛ… እያሉ ነው፡፡ ስታያቸው ጥላቻቸው ከፍተኛ በሽታ የሆነባቸው ይመስለኛል፡፡ በአማራነቴ ሲደበድቡኝና ሲሰድቡኝ እኔ ለእነርሱ አዝን ነበር፡፡ የሚናገሩት ቋንቋ ከሰው የማይጠበቅ የአውሬ ልትለው ትችላለህ፡፡ አማራ ሆኖ መወለድ ወንጀል ነው ለእነርሱ፤ አማራ ምን እንዳደረጋቸው አንተ ንገረኝ፣ ሌላም ሰው ካለ ቢያስረዳኝ ደስ ይለኛል፤ የታሪክ መረጃም ባገኝ ደስ ባለኝ፤ ያሳዝናል፡፡ ከሚደበድቡኝ ይልቅ አነጋገራቸው ነው የሚያመኝ ለእኔ፡፡ ዱላቸውማ ማንንም በተለይ አማራ ሁሉ እንደሚደበድቡት ነው የደበደቡኝ፡፡ አነጋገራቸው ከጤነኛ ሰው ሳይሆን አእምሮው ከታወከ ሰው እንኳ የማይጠበቅ ነው፡፡
ጉድጓድ ውስጥ ራቁቴን ከተው ይሸኑብኛል፤ ይተፉብኛል፤ ትግርኛ ቋንቋ ተናገር ይሉኝ ነበር፡፡ ሱሪየን ፓንቴን ሁሉ ጨምሮ አስወልቀውኛል፡፡ ከላየ ላይ ከሸሚዜ ውጭ አልነበረም፡፡ ዓይኔ ተሸፍኖ ስለነበር የሚደበድቡኝን ሰዎች አላውቃቸውም፡፡ የምሰማው ስድባቸውን ብቻ ነው፡፡ ከፈለጉ ደግሞ አንስተው ሰቅለው እያገላበጡ ይደበድቡኛል፡፡ ያሳዝናል፤ ሁሉንም ለመናገር ቃላት የለኝም፤ አልችልምም፡፡ በጠቅላላው ደስ የማይል ነገር ነው፡፡
ወደ አዲስ አበባ ሲያመጡኝ ወዴት እየወሰዱኝ እንደሆነ አላወቅኩም ነበር፡፡ ማርቆስ ስደርስ ዓይኔን ገለጡልኝ፡፡ የመኢአድ አባል የሆነው መለሰ መንገሻን ማሰራቸውን አላወቅኩም ነበር፡፡ በድብደባ ብዛት ሁለታችንም ራሳችን ስተን ነበር፡፡ ዓይናችን ማርቆስ ላይ የተሸፈነውን አንስተውልን ማርቆስ ካለፍን በኋላ ሽንት እንድንሸና ከመኪና ወረድን ወረድን፡፡ ከዚያ መለሰ መንገሻ መሆኑን በዓይኑ ለየሁት እንጅ የሁለታችንም ሰውነት በድብደባ ብዛት ተለዋውጠን ስለነበር ማን ማን መሆናችን ራሱ አይለይም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ስንገባ ጨለማ ቤት ውስጥ ቢሆንም ከሰው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተጨመርን፡፡ የተያዝንበት ምክንያት ከፓርቲው እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እነርሱ ሲጠይቁኝ የነበረው ለምን ከአቶ አበባው መሐሪ ጋር አብረህ አትሠራም? የመኢአድ አመራር ሆኖ ከአንተ ጋር አብረው የሚሠራውን ሰው ንገረን፡፡ ያደረጀውን ሰው ንገረን፡፡ ለምን አርፈህ አትቀመጥም? የአማራ የበላይነትን ልታመጣነው የምትታገለው የሚሉ ነገሮችን ነው የጠየቁኝ፡፡ ከግንቦት ሰባት ጋር ትገናኛለህ ምናም የሚሉትን ለስሙ ነው የሚጠይቁኝ፡፡
*ምንጭ፡ ‹የቀለም ቀንድ› ጋዜጣ፣ ግንቦት 02፣ 2008
መከተ ሙሔ[5]
ነሐሴ 5/2004 ለእኔ በሕይወቴ እጅግ የስቃይ ቀን ነበረች! ከጧቱ 3፡30 አካባቢ ተጠራሁ። እንደተለመደው የምርመራ ቢሮ ቁጥር 27 እንድገባ ታዘዝኩ። የእኔ ዋና መርማሪ አንዳርጋቸው ቀዶ ጠረንጴዛ ላይ ያስቀመጠውን የሻሽ መህረብ አነሳና አይኔን እንዳላይ አድርጎ ግጥም አድርጎ አሰረኝ። ሌላ ጓደኛው ጋር እጄን እየጎተቱ ‹‹ቀጥል ለበጎ ነው!›› በማለት መሳለቅ ጀመሩ። ነገሩ ገባኝ። የከፋ ሁኔታ እንደሚከሰት አረጋገጥኩኝ። ዱዓና ዚክሬን እያልኩ እየጎተቱኝ ወደ ላይ ወደታች በፎቅ ውስጥ አንከራተቱኝ። ከክፍል ክፍል በግንባሬ ከበር ጋር እየተጋጨሁ የፈለጉት ክፍል አስገቡኝ። በእጄና በእግሬ ስዳስስ ሶፋ ወንበርና ጠረጴዛ ያለበት ክፍል ነው። የተወሰኑ ሰዎች ቀድመው ገብተው ነበር። ‹‹አስገባውና ቁጭ ብድግ ፑሽ አፕ አሰራው›› አለው። እኔን ‹‹ሥራ›› ሲለኝ ‹‹አልችልም በሽተኛ ነኝ! ይህን ስፖርት ሰርቼ አላውቅም!›› አልኳቸው። ‹‹ቁጭ ብድግ አሰራው!›› አለ በድጋሚ። ‹‹2000 አሰራው›› ብሎም ትዕዛዙን አጠነከረ። እኔም ቁጭ ብድጉን ተያያዝኩት። መጨረሻ ላይ መነሳትና መቀመጥ ጭራሹኑ አቃተኝ። ይህን የሚያሰሩኝ ደግሞ ሙሉ ሰውነቴን ራቁቴን አድርገው ነው። በግምት ከሰባት በላይ የሚሆኑ መርማሪዎች ነበሩ። ጊዜውም ቀን በሥራ ሰዓት ነበር። በድምጻቸው ለመለየት የቻልኩት ኮማንደር ጸጋን፣ ኮማንደር ከተማን እና የመርማሪዎች ሐላፊ የሆኑትን ኮማንደር ተክላይን ነበር፤ ሌሎቹን መለየት አልቻልኩም። ልብሴን በሙሉ እንዳወልቅ አስገደዱኝ። ሱሪና ፓንቴን በእጃቸው ገፈፉኝ። ደክሞኝ ቁጭ ለማለት ስሞክር አንድ መርማሪ ከጫንቃዬ ላይ ተቀመጠብኝ። ‹‹የአከርካሪ ኦፕራሲዮን አለብኝ›› እያልኩ ስጮኸ ‹‹የተጠየቅከውን መልስ አትቀባጥር!›› እያለ መደብደቡን ቀጠለ። እንደምንም ብዬ ከስሩ ስወጣ በወለሉ ላይ ወደቅኩ። ከዚያ ደረቴ ላይ አንድ ሰው ቆመ። ሌላው እግሬ ላይ ረገጠኝ። ሶስተኛውም በኤሌክትሪክ ሽቦ መላውን ሰውነቴን መምታቱን ተያያዘው። በተለይ ብልቴን እጅግ አሳመመኝ። እስኪበቃቸው ከመቱኝ በኋላ የውስጥ እግሬን ገልብጠው መደብደብ ጀመሩ። ‹‹የእኛ እስላም! የእኛ ፆመኛ! ውሸታም! አስመሳይ! እርጉም! ስደተኛ! እንዳይወልድ አኮላሸው!›› እያሉ ይዝታሉ።
በድብደባው መሀል ከግል ማስታወሻዬ ውስጥ እንዳነበቡ በማስመሰል እንዳምን የሚፈልጓቸውን ንግግሮች ይጠይቁኝ ጀመር። ድብደባ ሲበዛብኝና ራሴን ስስት ቀዝቃዛ ውሃ በቅንጭላቴ ደፉብኝ። በድንጋጤ የተወሰነ ስሜቴን ለማወቅ ሞከርኩ። ከዋና መርማሪዬ አንዳርጋቸው በስተቀር ሌሎቹ ክፍሉን ለቀው ሔዱ። ራሴን እያወቅኩ ስሔድ በግምት ከ40 ደቂቃ በኋላ ተመልሰው መጡ። ‹‹እሺ! ለመናገር ፍቃደኛ አይደለህም?›› ሲሉ ጠየቁኝ። መርማሪዬ ጠጋ ብሎ ‹‹አንተ ሼኪ እኛ የምንልህን አምነህ ሕይወትህን ብታድን ይሻልሀል›› አለኝ።
ቀጥለው ውሃ ያለበትና የሚቀዘቅዝ ቦታ አስገቡኝ። የቻሉትን ያህል ገርፈው ትተውኝ ሔዱ። 11፡00 ሰዓት አካባቢ አንድ ሰው መጥቶ ልብሴን እንድለብስ አዘዘኝ። አይኔ ከጧት ጀምሮ በሻሽ ግጥም ብሎ እንደታሰረ ነው፤ ራሴን እጅግ አሞኛል፤ እንደማዞርም ያደርገኛል። ሰውየው ልብሶቼን አቀረበልኝና ለበስኩ። በባዶ እግሬ በወሰዱብኝ መንገድ ይመስለኛል ወደ ላይ ወደታች በተለያዩ ቢሮዎች ከበር ጋር እያጋጨ ወደ ፎቁ መውረጃ አደረሰኝና ትቶኝ ሔደ። ከአምስት ደቂቃ በኋላ ሌላ መርማሪ መጣና ልክ እንደአዲስ እንዳዬና እንደተገረመ በማስመሰል ‹‹ማነው አይንህን ያሰረህ? በጣም ይገርማል! አንተነህ ያሰርከው? ዓይንህን ፍታው›› አለኝ። ‹‹እንዴት ዓይኔን በራሴ ፍቃድ አሥራለሁ?›› አልኩት። ‹‹እሺ ልፍታልህ›› ብሎ ፈታልኝ። ለተወሰነ ጊዜ ለማየት ተቸገርኩ። እግሮቼ ይብረከረካሉ። ከፎቁ መውረጃ አጠገብ በረንዳው ላይ ወንበር ነበር፤ ‹‹ሂድ እዚያ ወንበር ላይ አረፍ በል›› አለኝ።
መጀመሪያ እየጎተተ ከምርመራ ቦታ ያመጣኝ ሰው ካልሲዬንና ነጠላ ጫማዬን ከአስቆመኝ ቦታ አስቀምጦት ነበርና ዓይኔን ሲፈታልኝ አየሁት። ‹‹ጫማህንም ልበስ›› አለኝ ዓይኔን የፈታልኝ መርማሪ። እንደምንም ብዬ ለበስኩት። ወንበር ላይ ካረፍኩ ከአምስት ደቂቃ በኋላ ሌላ መርማሪ መጣና ‹‹እዚህ ምን ታደርጋለህ? የሚመልስህ ፖሊስ የለም?›› አለኝ። ዝም አልኩት። ፖሊስ ጠራና ‹‹ወደ ክፍሉ መልሰው›› ሲል አዘዘ። መንገድ እንደጀመርን አብሮኝ የነበረውን ፖሊስ ጠራው። እኔን ‹‹ቁም ባለህበት›› አለኝና ወደጠራው መርማሪ ፖሊስ ተመለሶ አናገረው። ወደመጣሁበት ጣውላ ቤት ሊመልሰኝ ነው ብዬ ስጠብቅ ‹‹ቁም!›› አለኝ ፖሊሱ። እኔ መራመድም መቆምም አቅቶኛል። ከውስጥ ለነበሩት ጓደኞቼ ለእነ ኡስታዝ ሰዒድ አሊ ‹‹የሱን ዕቃ አውጡለት›› አለና ዕቃዬን አስወጣ። ፖሊሱ ራሱ ተሸከመውና ወደወትሮው ቦታዬ 84 ቁጥር (ጨለማ ክፍል) ተብሎ ወደሚታወቀው ቦታ ክፍል ቁጥር 10 አስገብቶ ዘጋብኝ። በዚህ ጊዜ ነበር በሕይወቴ አስቸጋሪው ሁኔታ የተፈጠረብኝ። የደበደቡኝን በቫዝሊን እንኳ የሚያሽልኝ ሰው በሌለበት፣ አይዞህ የሚልህ በሌለበት፣ እንዲህ አይነቱን የምርመራ ስቃይ በተደጋጋሚ ማሳለፉን ተያያዝኩት፤ ሐስቡነላህ!! ኦፕራሲዮን ያደረግኩት የጀርባ አጥንት ህክምና እንደገና ያመኝ ጀመር። ወገቤን ይዤ እያነከስኩ መሔድ ጀመርኩ። ለጓደኞቼ በ3 ቀን አንድ ቀን ለ10 ደቂቃ ፀሐይ እንድንሞቅ ሲፈቀድ ማናገር ባልችልም በምልክት የደረሰብኝን እገልፅላቸው ነበር።
*ምንጭ ፡ ‹የተዘነበለ ፍትህ› መጽሐፍ፣ ሰኔ 2006፣ አዘጋጅ፡ ድምጻችን ይሰማ
ቶፊቅ ረሽድ[6]
ቀኑ ግንቦት 06፣ 2006 ነበር፡፡ ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ አስረው እንዳመጡኝ ቀጥታ ያስገቡኝ የፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) በተለምዶ ጨለማ ቤት የሚባለው ቤት ውስጥ ስምንት ቁጥር የሚባለው ክፍል ውስጥ አራተኛው ቤት ውስጥ ነበር፡፡ ያመጡኝ እለት ሌሊቱን እጄን በካቴና አስረው አንድ ክፍል ውስት አስገቡኝና የኦነግ አባል መቼ እንደሆንክ ተናገር ብለው በገመድ ጀርባየን ይገርፉኝ ጀመር፡፡ እኔ በተደጋጋሚ እኔ ኦነግ አይደለውም ብልም፤ ነህ እኛ እናውቃለን እያሉ ሲቀጠቅጡኝ አደሩ፡፡ ሲደክማቸው ደግሞ ስፖርት ያሰሩኛል፡፡ በእግሬ መሃል እንጨት አስገብተው በማንጠልጠል ወፌ ይላል ይሰቅሉኝ ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ ከእኔ ምንም ማግኘት ባለመቻላቸው ስቃዩን ለመጨመር የወሰኑ ይመስለኛል፡፡ ነገሩን እያባባሱብኝ ሲሄዱ ግንቦት 14፣ 2006 ‹‹እኔ የሐረር ሰው ነኝ ጫት ካልቃምኩ አላስታውስም፡፡ ጫት አምጡልኝና አስታውሼ ልንገራችሁ›› ብያቸው እነሱም ጫት፣ ኮካ ኮላና ቡና ካመጡልኝ በኋላ መርቅኝ ‹‹ተናገር›› ሲሉኝ እኔም ‹‹የቃምኩት ዱላውና ድብደባው ስለበረታብኝ እንድችለው ነው እንጅ እኔ ምንም የምናገረው ነገር የለም›› አልኳቸው፡፡ እነሱም በብስጭት ‹‹ትኮላሻታለህ›› በማለት አንድ ሊትር ውሃ ልብሴን አስወልቀው ብልቴ ላይ አሰርው ካልዘለልክ አሉኝ፡፡ በዚህም ምክንያት ለረጅም ጊዜ ሽንቴን መሽናት እቸገር ነበር፡፡
*ምንጭ፡ ቶፊቅ ረሺድ ላቀረብንለት ጥያቄ የሰጠን ምላሽ
በፍቃዱ ኃይሉ[7]
ማዕከላዊ ምርመራ በቆየሁባቸው 85 ቀናት ከእሁድ በስተቀር ጠዋት ከሰአት ማታ እየተጠራሁ በዛቻ በአጸያፌ ስድብ ጭካኔ የተሞላበት ግርፊያ ጥፊና እርግጫ አንዲሁም ከአቅሜ በላይ የሆነ ስፓርት እየሰራሁ ቃሌን እንድሰጥ እገደድ ነበር፡፡ ‹‹የተያዝክበትን ድብቅ አጀንዳ ንገረን›› በማለት ራሴን እንድወነጅል ተገድጃለሁ፡፡
አንድ ቀን መርማሪው በመጀመሪያ ቀን ምርመራ በጥፊ መምታት የጀመረ ሲሆን እያንዳንዱን ጥያቄ ከጠየቀኝ በኋላ በጥፌ ይመታኝ ነበር፡፡ የዞን 9 አላማ ጠይቆኝ ስነግረው ‹‹ድብቁን አውጣ›› በማለት መሬት ላይ አንድቀመጥ እና ያደረኩትን ነጠላ ጫማ እነዳወልቅ አዞኝ በኮምፒውተር ገመድ እግሬን መግረፍ ጀመረ፡፡ በተጨማሪም በሆዴ አንድተኛ በማዘዝ እና እግሬን አጥፌ ከፍ አንዳደርገው በማድረግ ውስጥ እግሬን ገርፎኛል፡፡ ‹‹ድብቅ አጀንዳህን ካልተናገርክ ነገ እዘለዝልሃለሁ›› በማለት ይዝትብኝ ነበር፡፡ ግርፊያው ውስጥ እግሬን ሲለበልበኝ ነበር፡፡
ድምጽ እንዲያፍን ሆኖ ወደተሰራው የስብሰባ አዳራሽ ተወስጄ በጥፊ እየደበደቡኝ ‹‹የዞን 9ን አላማ ተናገር›› ተብዬ ተደብድቤያለሁ፡፡ ስቃዬ ሲበዛብኝም የፈጠራ ታሪክ አንዳወራ ተገድጃለሁ፡፡ በመጨረሻም ‹‹እኔ የምጽፈው ኢትዬጵያ ውስጥ አብዬት ለማስነሳት ነው ብዬ›› እንድፈርምም አስገድደውኛል::
በምርመራ ወቅት እጄ በካቴና እነደታሰረ ለሰአታት ቁጭ ብድግ አንድል እገደድ ነበር፡፡ በሌላ ቀን ደግሞ መርማሪው ‹‹በአንድ ወቅት አራት የዞን 9 አባላት ሆናችሁ ስለአላማው የተወያያችሁትን በቃል መስጫው ክስ ላይ ልጽፍ ነው›› ሲለኝ ‹‹እንደዛ አይነት ውይይት ማድረጋችንን አላስታውስም›› ስለው እንዴት ‹‹አታስታውስም›› ብሎ በጥፌ መማታት ጀመረ፡። በተደጋጋሚ ከመደብደብም በላይ ‹‹እስክስታስታውስ እዚሁ ታድራታለህ›› በማለት ድብደባው በመቀጠሉ ‹‹አስታውሳለሁ›› ብዬ ተገላገልኩ ፡፡ የሰጠሁት ቃል ላይም እንደፈለገው አድርጎ ጻፈው፡፡
እንዲሁም ‹‹ዞን 9 ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የሌለው ከሆነ ይህንን ህዝብ አንዴት ነው ነጻ የምታወጡት?›› በሚል ሲጠይቁኝ ‹‹የነጻ አውጪነት ሚና የለንም›› ስላቸው፤ ከወንበሬ አንድነሳ አዘዙኝ፡። ከዚያም በቆምኩበት ግራ ብብቴን እና እጄን በአንድ እጁ አንዳልወድቅ ወጥሮ ይዞ በእግሩ ጭኔን በሃይል ደበደበኝ ፡፡ ከድብደባው በማስከተል ደግሞ እግሬ መሃል እግሩን በማስገባት ወደግራ እና ወደቀኝ በመምታት ተዘርጥጬ እንድቆይ በማድረግ እጄን ወደላይ አድርጌ እግሬ ግራና ቀኝ ተዘርጥጦ (በተለምዶ ስፕሊት በሚባለው) በግራ እና ከቀኝ በመደብደብ እጄን ወደላይ አድርጌ እንድመረመር ተደርጌያለሁ፡፡ ከዚህ ምርመራ በኋላ ለሁለት ቀናት እያነከሰኩ ነበር፡፡
በጥቅሉ ምርመራው በተከናወነባቸው ቀናት ከእሁድ በስተቀር ሳልደበደብ ቢያንስ በጥፌ ሳልመታ የቀረሁበት ቀን የለም፡፡ ድበደባዎቹ አብዛኛው ‹‹ድብቅ አጀንዳችሁን ተናገር!›› የሚሉ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በጣም ጥቃቅን በመሆኑ ምክንያቶች ነው ፡፡ ‹‹መልስህ ንቀት አለበት››፤ ‹‹ለምን አላስታወስክም?›› በሚሉ ምክንያቶች ሳይቀር ስደበደብ ነበር፡፡
*ምንጭ፡ በፍቃዱ ኃይሉ ለኢትዬጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ካስገባው አቤቱታ የተወሰደ
ዩሱፍ ጌታቸው[8]
አንድ ቀን ወደ መፀዳጃ ቤት ልገባ ስል ከግድግዳ ላይ የተፃፈ መመሪያ አየሁ፤ ስለ ቅሬታ አቀራረብ ያስረዳል፡፡ ከለር ፕሪንት ነው፡፡ የዕለቱ ተረኛ ጠባቂ በስልጣን ትከሻው ላይ አንድ ኮከብ አለው፤ ጥላሁን ይባላል፡፡ ‹‹ሃላፊ ጋር ውሰደኝ፡፡ ቅሬታ ማቅረብ እፈልጋለሁ፤ መርማሪ እንዲለወጥልኝ›› አልኩት፡፡ ‹‹ያልተለመደ ጥያቄ ነው አይቻልም›› አለኝ፡፡ ‹‹ለምን? ይሄን አንብበው›› ብዬ መመሪያውን አሳየሁት፡፡ መርማሪ እንዴት መለወጥ መጠየቅ እንደሚገባኝ፣ ቅሬታ የትኛው ቢሮ ማቅረብ እንዳለብኝ መመሪያው ላይ የተጻፈውን አሳየሁት፡፡ አነበበው፡፡ ‹‹ይህ የቆየ ነው፡፡ አይቻልም›› ሲለኝ፤ ‹‹እንደዛ ከሆነ ቅደደው›› አልኩት፡፡ ‹‹ስራ እንስራበት፡፡ መፀዳጃ ተጠቅመህ ግባ›› ሲል ጮኸብኝ፡፡ ጉዳዩን ከነባር እስረኞችና አብረውኝ ካሉት ጋር ተነጋግረን የበለጠ መከራ ማብዛት ነው፡፡ ማንም ከጎንህ አይሆንም አሉኝ፡፡ ሐሳቤን ለወጥኩ፡፡ ለ15 ደቂቃ የዕለቱን ፀሓይ ለመሞቅ በወጣንበት ጊዜ የእስረኞች አስተዳደር ኢንስፔክተር ገብሩ ‹‹ዩሱፍ ማነው›› ብሎ ጠየቀ፡፡ እኔ መሆኔን ነገርኩት፡፡ ‹‹ምንድን ነው የምትበጠብጠው፡፡ መርማሪ ይለወጥልኝ፤ ሃላፊ ጋር ውሰደኝ እያልክ የምታስቸግረው?›› ብሎ አፈጠጠብኝ፡፡ እኔም ‹‹ጠባቂውን ጥላሁንን ጠየቅኩት አይቻልም አለኝ፡፡ ተውኩት፡፡ ሀሳቤን ለውጫለሁ›› አልኩት፡፡ ‹‹በመሰረቱ በመመሪያው መሰረት ከምርመራ ጋር በተያያዘ መልኩ የሚመለከተው ቢሮ ሌላ ነበር፡፡ ብቻ ትቼዋለሁ›› ስለው፤ እሱም ‹‹መርማሪ የሚልህን እሺ ማለት ብቻ ነው የሚያዋጣህ፡፡ አድማ አመፅ፣ እዚህ አይሰራም!›› ብሎኝ ሄደ፡፡ ወዲያው ከፀሃይ መሞቅ እንደገባሁ ቢሮ ቁጥር 49 ለምርመራ ተጠራሁ፤ በካቴና ታስሬ ነበር የመጣሁት፡፡ አለማየሁ የተባለው መርማሪ ‹‹መርማሪ ይለወጥልኝ ትላለህ አሉ? ምን አይነት መርማሪ ነው የመትፈልገው?›› አለኝ፡፡ ዝም አልኩት፡፡
‹‹ሱሪህን አውልቅ›› አለኝ፡፡
‹‹እኔ ወንድ ነኝ፡፡ ወንድ ፊት ሱሪዬን አላወልቅም፡፡ ወንድ የወንድን ገላ ለማየት አይጓጓም፡፡ ሱሪዬን አላወልቅም፡፡ ከፈለግክ አውልቀው›› ስለው አብሮት የነበረው ደህንነት ተናዶ ምራቁን ተፍቶብኝ በቦክስ ሆዴን አለው፡፡ የስነ ልቦና ጫና ስላደረኩበት ሱሪዬን ሳያወልቅ ቀረ፡፡ ኢንስፔክተር አለማየሁ ተቀብሎ ፂሜን ሲነጭ አስጮኸኝ፡፡ ‹‹ዝም በል!›› ብሎ ጉሮሮየን ሲያንቀኝ ትንፋሽ አጥሮኝ ዝም አልኩ፡፡ ፊት ለፊት ታስሮ ነበረውን ካቴና ፈትቶ ወደኋ አሰረኝ፡፡ ደህንነቱ ቀድሞ ፂሜን እየነጨ በስክሪብቶ ጫፍ ጠቀጠቀኝ፡፡ ‹‹ይህ ሆያለው ሕዝብ ነገ ዞር ብሎ አያይህም! አንተንም ሕዝብህንም እናስተነፍሳችኋለን፡፡ አሁን ራስህን ብታወጣ ይሻልሀል፡፡›› እጄ ወደላይ በመታሰሩ ፌቴ ላይ ተገትሮ እስክሪብቶውን የአይኔ ብሌን ላይ እያደረሰ አሳቀቀኝ፡፡ አፍንጫዬ ውስጥ ከትቶም ስቃየን አብዝቶታል፡፡
እሱ ስልክ ተደውሎለት ሲወጣ ኢንስፔክተር አለማየሁ ተቀበለኝ፡፡ መሬት ጣለኝ፡፡ ‹‹ተንበርክከህ፤ ሒድ›› አለኝ፡፡ በቅጣት ጫና ‹‹የበፊት ጉዳቴ እየተሰማኝ ነው፤ ዛሬ አሳርፈኝ›› አልኩት፡፡ አልተባበረኝም፡፡ አላዘነልኝም፡፡ መሬት አንከባሎ ረግጦኝ ትቶኝ ቁጭ ብሎ መጽሔት ያነብ ጀመር፡፡በመሐል ‹‹ተነስ ቁጭ በል›› አለኝ፡፡ ሁለት እጅ ወደኋላ ታሰሮ ራስን ችሎ ከመሬት መነሳት ከባድ ነው፡፡ በተለይ ለደከመ ጾመኛ፡፡ ግድግዳ ተደግፌ ተነሳሁ፡፡ ‹‹ወንበር ላይ ተቀመጥ›› አለኝ፤ ተቀመጥኩ፡፡ የሚያነበውን ‹የሙስሊሞች ጉዳይ› መፅሔት ጠረጼዛ ላይ አመቻችቶ አስቀምጦ፤ ‹‹አንብብ›› አለኝ ፡፡ ‹‹በሃገሪቱ የስራ ቋንቋ ነው የተፃፈው፤ ለምን አንተ አታነበውም?›› አልኩት፡፡ በጥፊ መታኝ፡፡ በራሱ ምልክት ሰጠኝ ‹‹አንብብ›› የሚል፡፡ ‹‹ነፃ ሀሳብ›› በሚል አምድ ስር የተፃፈ ነው፡፡ ጸሐፊው እኔ ራሴ ነኝ፡፡ ‹‹ሰላም ሲበዛ ራስ ያማል እንዴ?›› በሚል ርዕስ ስር የተፃፈ ነው፡፡ ፎቶግራፌም የኢሜይል አድራሻየም በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ለረጅም ደቂቃ ሳነበው ቆይቼ ‹‹ድምጽህን ከፍ አድርግ›› ብሎ እያነበብኩ እያለ ድንገት ከኋላየ ጆሮ ግንዴን የሚያላጋ ጥፊ ነፍሴን አሳተው፡፡ እነሆ ዛሬ ድረስ የግራ ጆሮየ ለበሽታ ተዳርጓል፡፡ በወቅቱ ማዕከላዊ በሚገኝው ክሊኒክ ባደረኩት ምርመራ ‹‹ጆሮህ ቁስለት አለው›› የሚል ምላሽ ተሰጥቶኛል፡፡ በአወዳደቄ ጎኔ ከፍተኛ መቀጥቀጥ ገጥሞኝ ስለነበር መታሻና መርፌ ተወግቻለሁ፡፡
*ምንጭ ፡ ከዩሱፍ ጌታቸው የክስ መከላከያ የተወሰደ
***********
[1] አሕመድ ሙስጠፋ በጥር 2004 የተቋቋመው እና ሶስቱን የህዝበ ሙስሊሙን ጥያቄዎች ይዞ ሲንቀሳቀስ በነበረው የመፍትኄ አፈላላጊ ኮሚቴ ውስጥ በሕዝብ ተመራጭና፣ የኮሚቴው ጸሐፊ የነበረ ሲሆን፤ በበፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) ለአራት ወራት ገደማ ከቆየ በኋላ የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶበት በአሁኑ ወቅት 15 ዓመት ፅኑ እስራት ፍርድ ተፈርዶበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ይገኛል፡፡
[2] አበበ ካሴ በፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) ለአምስት ወራት ገደማ ከቆየ በኋላ ‹‹የግንቦት ሰባት ወታደር ነህ›› በሚል የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶበት የሰባት ዓመት ፅኑ እስራት ፍርደኛ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በዝዋይ ማረሚያ ቤት ይገኛል፡፡
[3] አቤል ዋበላ የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ሲሆን በሚያዚያ 2006 ከሌሎች ስምንት ጓደኞቹ ጋር ተይዞ ለ85 ቀናት በፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) ከቆየ በኋላ የሽብርተኝነት ክስ የተመሰረተበት ሲሆን፤ በጥቅምት 2008 የተመሰረተበት ክስ ውድቅ ተደርጎ ከእሰር ተፈትቷል፡፡ ነገር ግን ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ግን በውሳኔው ባለመስማማት ይግባኝ ጠይቆ ክሱ አሁንም በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል፡፡
[4] ዘመነ ምህረት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መ.ኢ.አ.ድ.) አመራር የነበረና በጥር 2007 ተይዞ ለአራት ወራት በፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) ከቆየ በኋላ የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶበት ክሱን ለአንድ ዓመት ያህል ከተከታተለ በኋላ ፍርድ ቤቱ ክሱን ወደ አመፅ ማነሳሳት ቀይሮ በዋስትና የለቀቀው ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ክሱን በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡
[5] መከተ ሙሔ ከ1994-1998 የፌደራል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍ/ቤት ኘሬዝዳንት በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፣ በጥር 2004 የተቋቋመው እና ሶስቱን የህዝበ ሙስሊሙን ጥያቄዎች ይዞ ሲንቀሳቀስ ለነበረው የመፍትኄ አፈላላጊ ኮሚቴ አጋዥ የነበሩ ናቸው፡፡ ለአራት ወራት ገደማ በፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) ከቆዩ በኋላ የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው በአሁኑ ወቅት 15 ዓመታት ፅኑ እስራት ፍርድ ተፈርዶባቸው በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ይገኛሉ፡፡
[6] ቶፊቅ ረሽድ ‹‹በሚያዚያ 2006 በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ረብሻ አስተባብረሃል›› በሚል እና ‹‹የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር አባል ነህ›› ተብሎ ተይዞ ለአራት ወራት በፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) ከቆየ በኋላ የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶበት ክሱን ለአንድ ዓመት ሲከታተል ቆይቶ በሰኔ 2007 በፍርድ ቤት ነፃ የተባለ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በስደት በውጭ አገር እየኖረ ይገኛል፡፡
[7] በፍቃዱ ኃይሉ የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ሲሆን በሚያዚያ 2006 ከሌሎች ስምንት ጓደኞቹ ጋር ተይዞ ለ85 ቀናት በፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) ከቆየ በኋላ የሽብርተኝነት ክስ የተመሰረተበት ሲሆን፤ በጥቅምት 2008 የተመሰረተበት ክስ ውድቅ ተደርጎ በማሰቃየት የሰጠው ቃል ማስረጃ ሁኖበት እና ክሱ ወደ አመፅ ማነሳሳት ተቀይሮ በዋስ ተፈትቶ የሚገኝ ሲሆን፤ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ግን በውሳኔው ባለመስማማት ይግባኝ ጠይቆ ክሱ አሁንም በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል፡፡
[8] ዩሱፍ ጌታቸው በጥር 2004 የተቋቋመው እና ሶስቱን የህዝበ ሙስሊሙን ጥያቄዎች ይዞ ሲንቀሳቀስ ለነበረው የመፍትኄ አፈላላጊ ኮሚቴ አጋዥ እንዲሁም ከ2002-2004 ‹የሙስሊሞች ጉዳይ› መጽሄት ዋና አዘጋጅ የነበረ ሲሆን በሃምሌ 2004 ተይዞ በበፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) ለአራት ወራት ገደማ ከቆየ በኋላ የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶበት በአሁኑ ወቅት ሰባት ዓመት ፅኑ እስራት ፍርድ ተፈርዶበት በቃሊቲ እስር ቤት ይገኛል፡፡
(ምንጭ: ዞን ዘጠኝ)
(ፎቶዎቹን ከተለያዩ ድረገጾች ላይ ለማሳያ ይረዳ ዘንድ የተወሰዱ ናችው – ህወሃት ከሚፈጽማቸው ጋር ተመሳሳዪነት ባላቸው ምስራቃዊ ቲሞርና በቻይና የተካሄዱ ሰቆቃዎች ናቸው)
Leave a Reply