ሲሉ ሰምታ ዶሮ ሞተች ከቋት ገብታ ይሉ ነበር ሳይማሩ የተማሩት ጠቢባን የሆኑ ቀደምት እናትና አባቶቻችን። ድህነት ዛዝላውን ጭኖባቸው የመከራ ኑሮ የነበሩ ወገኖቻችንን መንግስት የቆለለው የቆሻሻ ምርት ተጭኗቸው ሲያልቁ መንግስት የሶስት ቀን ሀዘን ተቀመጠ የሚል አስቂኝ ወሬ በሰማሁ ጊዜ ነበር የጠቀስኩት የዶሮዋ ምሳሌ ትዝ ያለኝ። ሀገር አለን ብለው እንደወግና ስርአታቸው አደባባይ ሊውሉ የወጡ ወገኖቻችንን ባልተደበቀ ሸር በቢሸፍቱ ከተማ እንደወጡ ያስቀረው መንግስት በወቅቱ የሶስት ቀን ሀዘን በማወጅ በሙታንም ህያዋንም ላይ ቀልዶ ነበር። እነሆ አሁን ደግሞ በከመረው ቆሻሻ ህፃናትና ስቶችን ጨፍልቆ ከፈጀ በኋላ ሳቂታውን ፓርላማ ሰብስቦ በሉ አሁን ደግሞ የሀዘን ሰአት ነው አለ አሉ። እንዴት ያለ ቀልደኛ መንግስት ነው ጃል? ለገደለው ህዝብ ሆዱ የሚባባ ሩሩህ መንግስት! የዚህ አይነቱ ቀልድስ የሚያበቃው የት ላይ ይሆን?
በመሰረቱ የአንድ ከተማ አስተዳደር ሀላፊነት ቆሻሻ መቆለል ሳይሆን ከተማውን ማፅዳትና ህዝብንም ከበሽታ መከላከል አልነበረም? ከዚህ ቀደም የአፍሪካ መዲና የሆነችውን ታላቅ ከተማ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በማቆሸሽ ህዝብ ባ ባጣዳፊ ተቅማጥና ሁከት ማለቅ ሲጀምር “እጃችሁን ታጠቡ” ሲል የአንደኛ ክፍል የሳይንስ መፅሃፍን በማጣቀስ ያላቅሙ የሚያስተዳድረውን ህዝብ ሲመክር ያልገረመው አልነበረም። ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ። በከተማ ንፅህና ጉድለት የመጣውን ችግር እጃችሁን ሳትታጠቡ እየበላችሁ በሽታ አመጣችሁብን ሲል እንደልማዱ ለህዝብ ያለውን ንቀት ደገመው። ምን ደገመው ብቻ ደጋገመው ልበል እንጂ።
ነገሩማ የተባለውን ቀርቶ መስማት የሚፈልገውን ብቻ የሚሰማ መንግስት የህዝብን ችግር በበትክክለኛ ስሙ እንዲጠራ እንዴት መጠበቅ ይቻላል? ነፃነት አጣን ሲባል ስራ አጣን ነው ያላችሁኝ ይልና ስራ እንደሚያመጣ ሁሉ ወደጓዳ ገብቶ ጠመንጃ ይዞ ይመጣል። ስኳር ጠፋ ሲባል እኔ ስልጣን ከያዝኩ ጀምሮ ገበሬው ስኳር መጠጣት ስለጀመረ ነው አለ። ኧረ መብራት ተቸገርን ሲባል ምንላድርግ ልማቱ እኮ ነው ሲል አስረዳ። ሰብዓዊ መብት ለምን ይረገጣል ሲባል በህግ የበላይነት የሚያምንና ሃላፊነት የሚሰማው መንግስት ስላለን እኮ ነው ሲል አስተማረን። እንዴት ያለ ጉድ እኮ ነው ጎበዝ!
ከተነሳሁበት ነጥብ ወጣሁ መሰለኝ፤ የክምር ቆሻሻው ጉዳይ። መከራ በተጫነው ህዝብ ላይ ቆሻሻ ጭኖ ከገደሉ በኋላ ባንዲራ ማውረድና ሀዘን ማወጅ የቀበሮ ባህታዊነት ይመስለኛል። ሃላፊነት የሚሰማው መንግስት ተግባር ሰው እንዳይሞት መጠበቅ እንጂ ገድሎ ማጠን አይደለም። በዚህ ክስተት መንግስት ማዘን ሳይሆን ማፈር አለበት። ያውስ ሃፍረት የባህሪው ከሆነ አይደል? ጎበዝ ማለት ለጥፋቱ ሀላፊነት ወስዶ ይቅርታ መጠየቅና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሙሰኛ ተሿሚዎቹን መቅጣት ነው። ብቻ ይኅስ ቢሆን ለመገዛት እንጂ ገዢዎቹን በህግ ለመጠየቅ የታደለ ህዝብ በሌለበት ሀገር እንዴት ይታሰባል። እና እባካችሁ እንደፈረደብን ዝም ብለን እንሙትበት፤ እየሳቃችሁ አትዘኑልን በሏቸው። ጥያቄም አለኝ፤ ሀገር መምራቱስ ቢቀር፣ ቤት ጠርጎ መኖር እንኳን እንዴት ተሳናችሁ የሚል። የወገኖቻችንን ነፍስ ይማር።
ህሩይ ደምሴ (zobar2006@gmail.com)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Tadesse says
ewnet gud new,asafari, new,hezbun cheresut tegrewm sayker.