ሰሞኑን በሳውዲ አረቢያ በተለይ በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ እየተፈፀመ ያለው እንግልት፣ ድብደባ፣ ግድያና ለህይወት አስጊ በሆነ ሥፍራ ማጎር ከኢሰብአዊነትም በላይበኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው፡፡
ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ(አንድት) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ!
በአባቶቻችን ደም ታፍራና ተከብራ የኖረችው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በገዢው ፓርቲ ቸልታ፣ የፖሊሲ ችግርና የሀገር ፍቅር ማጣት የተነሳ ዜጎቿ በውርደት እንዲኖሩ ተፈርዶባቸዋል፡፡ ዛሬም መገለጫችን ስደት፣ ጦርነት፣ በዜግነታችን ክብር ማጣትና ሞት ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ሀገራዊ ውርደትና ሞት ከተበላሸ ሥርዓት የሚወለድ፣ ካልተስተካከለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚፈጠር ነው፡፡
ፓርቲያችን የተሻለ ኢኮኖሚ ፍለጋ፣ የተሻለ ማህበራዊ ፍትህ ለማግኘትና አሰቃቂ የሆነውን ፖለቲካ ሽሽት ኢትዮጵያውያን ዜጎች ሀገራቸውን ጥለው እንደሚሰደዱ ያምናል፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦትና ሥራ ፍለጋ የሚያንከራትታቸው ኢትዮጵያውያን ቁጥር የትየለሌም ነው፡፡ ጋሎፕ የተባለ አለማቀፍ ጥናት እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ጎልማሶች መካከል 46% የሚሆኑት ከሀገራቸው በመሰደድ ወደ ሌላ ሀገር ሄደው ለመኖር ይፈልጋሉ፡፡ ይህ የሆነው የተስተካከለ ስርዓት ባለመፈጠሩ ነው፡፡
ሰሞኑን በሳውዲ አረቢያ በተለይ በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ እየተፈፀመ ያለው እንግልት፣ ድብደባ፣ ግድያና ለህይወት አስጊ በሆነ ሥፍራ ማጎር ከኢሰብአዊነትም በላይ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው፡፡ ዜጎቻችን ዋስትናና ከለላ አጥተው በሳውዲ ፖሊስ በየጎዳናው ሲፈነከቱና ሲገደሉ ከማየት በላይ አሰቃቂ ነገር የት አለ? በሳውዲ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመው ወንጀል የሀገር ሉዓላዊነትም ጉዳይ ነው፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያን መንግሥት የዲፕሎማሲ ደካማነትና በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ባህላዊ ግንኙነቶች ላይ ተጽእኖ መፍጠር ያልቻለ መሆኑን ያስረዳናል፡፡ ደካማ መንግሥት፣ ደካማ አስተዳደርና የራሱን ስልጣን ብቻ የሚያዳምጥ ፓርቲ ዜጎቹን ያስደፍራል፣ ሉዓላዊነትን ያስነካል፣ ኢትዮጵያዊ ክብርን ያዋርዳል፡፡
አንድነት ፓርቲ የሰቆቃ ዘመናችን የሚያጥረው ለሀገር የሚያስብ የተስተካከለ ሥርዓት ሲፈጠር ብቻ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያውያንን ሰብአዊ ክብር ማስጠበቅ የተሳነው መንግሥት ላይ ጫና ማድረግና በሠላማዊ ትግል መቀየር ወሳኝ ነው፡፡ አንድነት የሳውዲ አረብያ መንግስት በዜጎቻችን ላይ የፈፀመውን ድርጊት ተከትሎ ያለውን አቋም እንደሚከተለው ያቀርባል፡፡
1. የሳውዲ መንግሥት በኢትዮጵያውያን ላይ እየፈፀመ ያለውን የሰብአዊ ክብር ገፈፋ፣ እስር፣ ግድያና ማዋከብ በአስቸኳይ እንዲያቆም፡፡
2. ለፈፀመው ሰብአዊ ጥፋት ተጠያቂ እንዲሆንና ለተጎጂዎች ካሳ እንዲከፍል፡፡
3. የኢትዮጵያ መንግስት ለተጎጂዎች አስቸኳይ ርዳታና ለችግራቸው መፍትሔ እንዲሰጥ፡፡
4. የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህንን በፈፀመው የሳውዲ መንግሥት ላይ ጠንካራ አቋም እንዲይዝና ለኢትዮጵያውያን በችግሩ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጥ እንጠይቃል፡፡
በተጨማሪም በዜጎች ላይ የተፈፀመውና እየተፈፀመ ያለው ግፍ የገዢው ፓርቲ የዲፕሎማሲ ድክመት ያመጣው መሆኑንና እንዲሁም የአምባሳደርነት ሥልጣን የሚሰጠው በችሎታ ሳይሆን በፓርቲ ታማኝነት እንደሆነ ያሳየን ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግሩን ከሥሩ ለማድረቅ የሚያስፈልገው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማሻሻያ መሆኑ ታውቆ ህዝቡ የተስተካከለ ሥርዓት የመፍጠር ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ እያቀረብን በተከታይ የምንውደውን ርምጃ ለህዝቡ የምናሳውቅ መሆኑን እንገልፃለን፡፡
ዘላለማዊ ክብር ለኢትያጵያና ኢትዮጵያዊነት!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ህዳር 2 ቀን 2ዐዐ6 ዓም
Leave a Reply