
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም አሸባሪው እና ተስፋፊው የትህነግ ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ በተካሄደው የሕግ ማስከበር እርምጃ የተረፈው የጠላት ጦር የሸሸው ምዕራብ ጎንደርን በሚያዋስነው የሱዳን ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ነበር፡፡ ከሕግ ማስከበር እርምጃው በኋላ ላለፉት 10 ወራት በአካባቢው ጥቃት ለመሰንዘር ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርጉም በስፍራው ባለው የወገን ጦር እየተመታ ተመልሷል፡፡
ዛሬ ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ የጠላት ጦር ሽንፋን በአራት አቅጣጫ በኩል በመክበብ ጦርነት ከፍቶ ነበር ያሉት የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በሁሉም ግንባሮች በአካባቢው የጥምር ጦር አባላት ተገቢው እርምጃ ተወስዶበታል ብለዋል፡፡
በጦርነቱ የጠላትን ጦር በማገዝ እና በመምራት የአሸባሪው እና ተስፋፊው የትህነግ ቡድን ሌላኛው ሴል (ህዋስ) የሆነው ጽንፈኛው የቅማንት ታጣቂ ቡድን አባላት እንዳሉበት የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖ እና የአካባቢው ወጣቶች በተደራጀ ሁኔታ ምላሽ እየሰጡ ነው ብለዋል፡፡
ውስን የሆኑት ጽንፈኛ የቅማንት ታጣቂ ቡድን አባላት በርካታውን እና ሰላማዊውን የቅማንት ሕዝብ እንደማይዎክሉ የገለጹት አቶ ደሳለኝ በጦርነቱ ውስጥ የወገን ጦር በመቀላቀል እየተዋጉ ላሉ እና መረጃ በመስጠት ለሚተባበሩ የቅማንት ማኅበረሰብ አባላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
“በቲሃ በኩል ሽንፋን እና ቱመትን” ተከትሎ በአራት አቅጣጫ ከመጣው የጠላት ኀይል በሦስቱ አቅጣጫ የመጣው ቡድን ተደምስሶ ምርኮኛ እና ምርኮ እየተሰበሰበ ነው ተብሏል፡፡ በአንድ አቅጣጫ ይህ ዘገባ በሚጠናቀርበት ጊዜም ውጊያ ላይ ሲሆን ጦርነቱ በቅርብ ስዓት ሙሉ በሙሉ በድል ይጠናቀቃል ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፡፡
ዋና አስተዳዳሪው በመልዕክታቸው በዚህ አውደ ውጊያ ወጣቶች እና የአካባቢው ማኅበረሰብ መንግሥት በዘረጋው የጸጥታ መዋቅር ውስጥ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወጣቶችና የአካባቢው ማኅበረሰብም በምርኮ የሚያገኙትን ማንኛውንም መሳሪያ ለአካባቢው የጸጥታ መዋቅር እያሳወቁ እንዲታጠቁ ተፈቅዷል ብለዋል፡፡
(አማራ ኮሚዩኒኬሽን ) አሚኮ
አመሰግናለሁ። ሼር አድርጌዋለሁ።