ህወሐት በትግል ፕሮግራሙ የአማራን ያክል የሚጠላው ሌላ ህዝብም ሆነ አካል እንደሌለ በግልጽ ያስቀመጠ ድርጅት ነው። የአማራ ህዝብ መሬት እያረሰ የሚኖር ደሀ ህዝብ ቢሆንም በህወሐት የምስረታ ሰነዶች እንደ ገዥ ብሄር ተፈርጆአል።
አስገራሚው ነገር አማራ ንጉሱንም ሆነ ደርግን በማስወገድ ትግል ከሌሎች ህዝቦች እኩል ድርሻ የነበረው ህዝብ ነው። እንደ ህዝብ በህወሐት የሚጠላው በተጨበጠ ምክንያት አይደለም። ህወሐት የአማራን በሌሎች እንዲጠላ ካደረገባቸው የተደራጁ ስብከቶች በተጨማሪ የብሄረሰቡን ማንነት የሚያዳክምባቸው ልዩ ልዩ እርምጃዎችንም ወስዶአል። አንዱ ሴቶች ፍላጎታቸው ሳይጠየቅ የረጅም ግዜ የወሊድ መከላከያ መርፌ እንዲወጉ ማድረጉ ነው። በዚህም እኤአ 2007 የህዝብ ቆጠራ የህዝብ ቁጥሩ ከሚጠበቀው በ3 ሚሊዮን የቀነሰ ብቸኛ ህዝብ ሆኖአል። ሌላው በትግራይ ክልል የልዩ ወረዳ አስተዳደር ክብር የሚገባቸው ልዩ ልዩ ብሄረሰቦች እያሉ ህወሐት አማራ ክልል መጥቶ የልዩ ዞን ፍላጎት ቀስቀሰሽና አስፈጻሚ መሆኑም ከዚሁ አማራን ለማዳከም ካለው ጽኑ ፍላጎት ጋር ይያያዛል።
የአማራን ክልል መሬት በጉልበት ወደራሱ የማካለል ስራም ሌላው ተግባሩ ነው። ራሳቸውን በአማራነት የሚገልጹ ሰዎችን በግፊት ወደ ትግሬነት የመቀየር ስራም ሰርቶአል። ህወሐት በፕሮግራሙ ውስጥ አማራን ግንባር ቀደም ጠላቴ ነው ብሎ ከመጻፍ ጀምሮ በተከታታይ በዚህ ህዝብ ላይ እየፈጸማቸው ያሉ ግፎች መነሻቸው ምንድን ነው?
የመጀመሪያው መሰረታዊ ምክንያት ህወሐት ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ፈጽሞ ማየት አለመፈለጉ ነው። ይህ ጥላቻ ምንጩ የወራሪው ኢጣልያ አገልጋይ ከነበሩ ጥቂት ባንዳ የትግራይ ልጆች ነው። እነዚህ በቀድሞው የህወሐት አባል በአቶ ገብረመድን አጠራር ሻምቡሽ እየተባሉ የሚጠሩት የትግራይ ባንዳዎች በልጆቻቸው በኩል ስብከቱን በማጉላት በአሁኑ ወቅት ብዙ ተከታይ አግኝተዋል። የአማራ ህዝብ ደግሞ ፖለቲከኛ ሆነ ደሀ ገበሬ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሀገሪቷን ከወራሪ ሲከላከል የቆየ ህዝብ ነበር። በዚህም ቂም ተይዞበታል።
ብዙዎች የዋሆች ህወሐት ኢትዮጵያዊ መባል ካልፈለገ ለምን ታዲያ ሁሉን አድራጊ በሆነበት በአሁን ወቅት መገንጠልን አይፈጽመውም የሚል ጥያቄ ይጠይቃሉ። መልሱ የትግራይ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የስነልቦና የበላይነቱ እስካልተነካበት የመገንጠል ፍላጎቱን ገሀድ አያወጣም የሚል ይሆናል። አዎ እንደ ነብር ደምህን እየመጠጠ ይቆያል። ደምህ ካለቀ ወይም አሻፈረኝ ካልክ ግን ያኔ ይተገብረዋል።
ሁለተኛው ምክንያት የተለመደው የከፋፍለህ ግዛ ባህሪው ነው። ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦችን ኣስፈራርቶ ለመግዛት የሚፈሩት ጠላት ሊፈጥርላቸው ይገባል። ለዚህም አማራን አስቀምጦላቸዋል። በሁለተኛነትም ከአማራ ህዝብ ጋር ህብረት እንዳይፈጥሩ ማድረጊያ ስልቱም ነው። ይህ ስልቱም ከጠበቀው በላይ ሰርቶለታል። በዚህም የአማራ ህዝብ ለትውልዶች ከኖረባቸው አካባቢዎች ተደጋጋሚ ጥቃቶች ተፈጽሞበታል። በኦሮሚያ፣ ደቡብ ብ/ብ/ህ ክልል እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የተፈጸሙትን ግድያዎችና ማፈናቀል መጥቀስ ይቻላል።
የአለም ህዝቦች መልቲ ካልራሊዝምን እንደ ሀብት በሚቆጥሩበት በዚህ የስልጣኔ ዘመን አባቶቹ የጣልያን ሻምቡሽ ሆነው የተነገራቸው ስብከት ላይ ተቸንክሮ የቆመውን ህወሐት በተግባር በቃ ልንለው ይገባል። አለበለዚያ ግን የሰሞኑ የአለም ባንክ ይፋ ያወጣው የኢትዮጵያ ክልሎች የመንገድ ግንባታ ግስጋሴ የ 10 ዓመት ሪፖርት በግልጽ እንዳስቀመጠው (ትግራይ ክልል አንደኛ እንዲሁም አማራ መጨረሻ) ህወሀት የአማራንም ሆነ ሌሎች ህዝቦችን ደም መምጠጡን ይቀጥላል።
ያሬድ አውግቸው (yaredawgichew@gmail.com)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply